እንዴት ነጻ እንውጣ?

ልማድ ተንቆ ሊተው የሚችል ተራ ጉዳይ አይደለም። ክፉም ሆነ ደግ ልማድ የሚቆሙት በብዙ ድካም ነው። ምክንያቱም ልማዶች ሱሰኛ የመሆን ውጤትን ያስከትላሉ። አልኮል የመጠጣት ልማድ፣ ጫት የመቃም ልማድ ወይም ሲጋራ የማጨስ ልማድ ሕክምና ተወስዶ በብዙ ድካም መወገድ የሚችሉ ናቸው። ክፉ ልማዶችን በተለይም ብዙዎችን ሊጎዱ የሚችሉ ልማዶችን በጊዜ ማቆም ያስፈልጋል።

ልክ እንደክፉ ሁሉ በተቃራኒው በበጎ ሊገለፁ የሚችሉ ሰው የማክበር፣ የማንበብ፣ ወደ ማምለኪያ ስፍራ ወይም ወደ ገበያ የመሔድ፣ የታመመ እና የታሠረ ሰውን የመጠየቅ ልማዶችም አሉ። እነዚህ ልማዶች መጥፎ ናቸው ማለት ባይቻልም፤ እንዲቆሙ ከተፈለገ እነኚዎቹም በቀላሉ የሚቆሙ አይደሉም። ምክንያቱም ልማዶች ሁሉ በውል ሳይታወቁ በፍጥነት ወደ ሱስነት ያመራሉ።

በሌላ በኩል በግለሰብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በቡድን ወይም በማህበረሰብ ደረጃ የሚፀናወቱ ልማዶች አሉ። ለምሳሌ የሰዎች ሞትን ያለመቀበል ልማድ፣ ሃዘንን የማብዛት ልማድ፣ የጦርነት ልማድ፣ ጊዜን የማባከን ልማድ፣ ሰዎች ያለማዳመጥ ልማድ፣ የስግብግብነት ልማድ … ወዘተ እያልን ብዙ ልማዶችን መግለፅ እንችላለን።

በእርግጥ የማህበረሰብም ሆኑ የግለሰብ ልማዶች ጠቃሚ ከሆኑ ቢቀጥሉ እና ቢያብቡ መልካም ነው። በተቃራኒው ግን የግለሰብ ብቻ ሳይሆን የማህበረሰብ ልማድ መስለው የሚታዩ ብዙዎችን በመጉዳት ላይ ያሉ ልማዶች ደግሞ በጊዜ መክሰም አለባቸው። ለምሳሌ ሙት አንጋሽ እና ሙት ወቃሽ የመሆን ልማድ በፍጥነት መቆም ያለባቸው ልማዶቻችን ናቸው።

ከተራ የግለሰብ ሞት የቀብር ሥነሥርዓት ላይ ከሚነበብ የሕይወት ታሪክ ጀምሮ የሞተን ማወደስ የተለመደ ነው። የሞተ ተወደሰ አልተወደሰ ምን ልዩነት አለው? ቢያንስ ሲኖር የተወቀሰ ሲሞት ይወደስ ሊባል ይችላል። ነገር ግን ይህ ልማድ በሕይወት እያለ ሰዎችን ሲያሰቃይ እና ሲገድል የነበረ ሰው ታዝኖለት ብቻ ሳይሆን ልማድ ሆኖ ውዳሴ መፃፉ ፍፁም ተገቢነት የጎደለው ነው። ይህ እየዳበረ ሲቀጥል፤ ውሸትን መፃፍ እንደትክክለኛ ተግባር ይወሰዳል። አሁንም ይህንኑ እየታዘብን ነው።

በተቃራኒው በጎ ነገር ሲሰራ የነበረ ሰው ወይም መጥፎ ነገር ሲሰራ የነበረ ሰው ይሞታል። ‹‹የሞተ አንበሳ ሣር ይበቅልበታል›› እንደሚባለው አንዳንድ ግለሰቦች ልማድ ሆኖባቸው ዘላለማቸውን፤ ገንዘባቸውን ጊዜያቸውን ሙሉ ሕይወታቸውን የሚሳልፉት የሞተውን ሰው በመውቀስ እና የአሁኑ ሕይወታቸው በዛ ሰው ምክንያት የተበላሸ መሆኑን በመግለፅ ነው። ዛሬ ላይ ቆመው ዛሬን እና ነገን የተሻለ የሚያደርጉ ሃሳቦችን ከማመንጨት እና ያንንም ከማስተላለፍ ይልቅ ጥላቻን በመዝራት ጊዜያቸውን ያባክናሉ።

አንዳንዶች ደግሞ በሁሉም ነገር ላይ እነርሱ ብቻ አዋቂ እንደሆኑ የሚያስቡ ነገር ግን አላዋቂነት የፀናባቸው ሰዎች አሉ። በሁሉም ነገር ላይ እኔ አዋቂ ነኝ ብለው ይከራከራሉ። ለዚህ ሁለት በግንባታ ሥራ ላይ ተሠማርተው ሥራቸውን ሲያከናውኑ የነበሩ ሰዎች ጥሩ ማሳያ ይሆናሉ። ሰዎቹ ሥራቸውን ሲሰሩ በአብዛኛው መከራከር ልማዳቸው ነው። ክርክራቸው ከስራቸው ያለፈ ሊሆን ይችላል። የዕለቱ ክርክራቸው ለገሃር የሚባለው ሰፈር አሰያየም ላይ ያተኮረ ነበር። በጣም የሚያስገርመው ጉዳዩ ለጭቅጭቅ የሚያደርሳቸው መሆን ባይኖርበትም መጨቃጨቅ ላይ ደረሱ።

አንደኛው የመከራከር ልማድ ተጠቂ፤ አንዱን የኢትዮጵያ ብሔር ቋንቋ ጠቅሶ ለገሃር የሚለው ቃል የመጣው ከዚህ ነው አለ። ሌላኛው ተከራካሪ ለገሃር አካባቢ ተወልዶ ያደገ ሲሆን፤ ቃሉ መነሻው ፈረንሳይኛ መሆኑን አስታውሶ ከነትርጉሙ አስረዳ። ነገር ግን ተከራካሪው ለማዳመጥ ዝግጁ አልነበረም። ቢያንስ ተደማምጠው መረዳዳት ባይችሉ እንኳን፤ የአካባቢውን ስያሜ አመጣጥ ለታሪክ ትተው በዕለቱ ሥራቸው ላይ ሃሳብ ከመለዋወጥ ይልቅ በማያዋጣ እና ጥቅም በሌለው ጉዳይ ላይ ሲጨቃጨቁ፤ ቀናቸውን ብቻ ሳይሆን ግንኙነታቸው ላይ ጠባሳ የሚጥል ተግባር ፈፀሙ። ዱላ እስከመማዘዝ ደርሰው ለገላጋይ አስቸገሩ።

ከላይ የተጠቀሱ ሁሉን እናውቃለን ባይ ተከራካሪዎች በልማዳቸው ምክንያት ለዱላ ሲጋበዙ፤ እርስ በእርስ ቢጎዳዱም ጉዳታቸው ጎልቶ ሌሎች ላይ አልታየም። ነገር ግን የአንዳንዶች ልማድ ግን ጉዳቱ ከአንድ ግለሰብ አልፎ ብዙዎች ላይ ያርፋል። ጎሳን፣ ሃይማኖትን፣ ፆታን ወይም አንድ ቡድንን (መደብን) መነሻ በማድረግ መሳብ እና የመሳሳብ ልማድ ከሆነ አደገኛ ነው። እንደዚህ ዓይነት አደገኛ አዝማሚያዎች ደግሞ በጊዜ ካልቆሙ መጨረሻ ላይ የሚያስከትሉት ጉዳት ከባድ እና ብዙ ዋጋ የሚያስከፍሉ ይሆናሉ። ጉዳታቸውም ከአንድ ግለሰብ አልፈው ብዙዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራሉ።

በዚህ ጊዜ ዓለም አቀፍ ዕውነታን ካለመ ለማመድ የተነሳ ዓለም እንዲህ ወደ አንድ መንደርነት እየተቀየረችበት ባለ ዘመን በተራ አንድ ቡድን ውስጥ ታጥሮ መባከን ክፉ ልምድ ነው። አሁን አሁን ደግሞ ይህ ክፉ ልማድ እንደ ዕውቀት እየተወሰደ መጓተቱ፤ የኋልዮሽ ለመሳሳብ መሞከሩ ያሳፍራል። በእርግጥ መስራት መልካም ነው። መማርም በጎ ነው። መስራት እና መማር ተዳምሮ ሥልጣን ሲያዝ አስተማማኝ እኩልነት እንዲሰፍን ማድረግ ሲገባ፤ በተቃራኒው ወደ ኋላ መመለስ ጊዜ ሲያልፍ ትውልድን ብዙ ዋጋ ያስከፍላል።

በእርግጥ ማንም ሊክደው በማይችል መልኩ በዓለም ላይ ሙሉ ለሙሉ እኩልነት ሰፍኗል ማለት አይቻልም። እያንዳንዱ አገር፣ እያንዳንዱ ከተማ፣ እያንዳንዱ ወረዳ፣ እያንዳንዱ ሆስፒታል፣ እያንዳንዱ ዩኒቨርሲቲ፣ እያንዳንዱ ተቋም በዓለም ላይ ከመምራት ጋር የተያያዙ ቦታዎች በሙሉ በጣት ከሚቆጠሩ ሴቶች በስተቀር ከ99 በመቶ በላይ የሚመሩት በወንዶች ነው። ምክንያቱም ተወደደም ተጠላ፤ በግልፅም ሆነ በስውር ዓለም ላይ ትልቅ ክፉ ልማድ አለ። ይኸውም መምራት የሚችለው እና መምራት ያለበት ወንድ ብቻ ነው የሚል ልማድ አለ። ይህንን ተከትሎ ከሴቶች ይልቅ ብዙ ገንዘብ፣ ብዙ የዓለም ሃብት በወንዶች እጅ ነው።

በሌላ በኩል ዓለምን መምራት ያለባት አሜሪካን ብቻ እንደሆነች የማሰብ ብቻ ሳይሆን የማመን ዝንባሌዎች አሉ። ቻይናም ሆነች ሩሲያ ወይም የትኛውም አገር በቴክኖሎጂም ሆነ በተለየ የሃብት መጠን በፍፁም ዓለምን መቆጣጠር አይችልም የሚል ልማድ ይስተዋላል። ይህ ብቻ አይደለም በሃይማኖት በኩልም በተመሳሳይ መልኩ የማይገቡ ልማዶች አሉ።

በዓለም ላይ ያሉ ልማዶች ተለይተው ሲስተዋሉ ፆታ፣ ሃይማኖት ወይም የቆዳ ቀለም ላይ የተመረኮዙትን እንደመነሻ ስንጠቅስ፤ ጉዳታቸው ከፍተኛ በመሆኑ መወገድ አለባቸው።

በዚህ ላይ ዓለምን ከእነዚህ ልማዶች ለማላቀቅ ቢከብድም፤ ቢያንስ ከራስ ቤተሰብ፣ ከራስ ተቋም፣ ከራስ አገር በመጀመር ክፉ ልማዶችን ለማስቆም የሚጠበቅብንን ሚና በመጫወት እራሳችንን ነጻ እናውጣ። ሰላም!

ምሕረት ሞገስ

 አዲስ ዘመን  ነሐሴ 29 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You