የኢንዱስትሪው ልማት ቀጣይነት ማሳያ!

 ኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብቷን ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር ራዕይ ሰንቃ መስራት ከጀመረች ዓመታት ተቆጥረዋል፤ ለእዚህም ለኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚያስፈልጉ መደላድሎችን በማዘጋጀት እየሰራች ትገኛለች። በኢንዱስትሪው ዘርፍ የተያዘውን ራእይ ለማሳካት ደንቃራ ሆኖ የቆየውን የመሬት፣ የመሰረተ ልማትና የመሳሰሉት ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል ተግባር ሲከናወን ቆይቷል።

በእዚህም የውጭም ሆኑ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ መሰማራት ሲፈልጉ ማሽነሪዎቻቸውን ብቻ አምጥተውና ገጣጥመው፣ ሰራተኞችን አሰልጥነው በማሰማራት ወደ ስራ መግባት የሚያስችሏቸው 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮች ተገንብተዋል። ፓርኮቹ የመንገድ፣ የኤሌክትሪክ፣ የውሃ፣ የቴሌኮምና የመሳሰሉት መሰረተ ልማቶች የተሟሉላቸው ግዙፍ ሼዶችን ያካተቱ በመሆናቸውም በእርግጥም የባለሀብቶችን የዘመናት ጥያቄ የሚመልሱ፣ የሀገሪቱንም የኢንዱስትሪ ልማት ጉዞ የሚያሳልጡ ናቸው። እንደ ሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ባሉት ፓርኮች እየታየ ያለውም ይሄው ነው።

መንግስት የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ብቻውን መገንባት አንደሌለበትም ያምናል፤ የግሉ ዘርፍም የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ገንብቶ ለባለሀብቶች ምቹ ሁኔታዎችን እንዲፈጥር ሠርቷል፤ በዱከም ተገንብቶ በርካታ አምራቾችን እያገለገለ የሚገኘው የቻይናው ኢስተርን ኢንዱስትሪ ፓርክም ከዚህ አኳያ የሚጠቀስ ነው።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘት ታልመው የተገነቡ እንደመሆናቸው ምርቶቻቸው ለውጭ ገበያ እየቀረበ ይገኛል። በርካታ ዓለም-አቀፍ ብራንድ ያላቸው ኩባንያዎች በእነዚህ ፓርኮች ገብተው እየሰሩ ምርቶቻቸውን ለውጭ ገበያ እያቀረቡ ይገኛሉ። ፓርኮቹ ለብዙ ሺህ ኢትዮጵያውያንም የሥራ ዕድል መፍጠር ችለዋል።

የቴክኖሎጂ እና የእውቀት ማሸጋገሪያ ድልድይ በመሆን እያገለገሉም ናቸው። የነገ የተዘጋጁ አልባሳት አምራቾች በፓርኮቹ እየተፈጠሩ ናቸው። ሀገሪቱ በውጭ ምንዛሬ ግኝት፣ በሼዶች ኪራይና በሚሰጡ የተለያዩ አገልግሎቶች ተጠቃሚ እየሆነችም ትገኛለች። በቴክኖሎጂና የዕውቀት ሽግግር፣ በግብአት አቅርቦት ትስስር፣ የገቢ ምርቶችን በመተካት በኩልም ተጠቃሚ እየሆነች ትገኛለች።

የሀገሪቱ የኢንዱስትሪ ራዕይ በ13 የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት በሚከናወን እንዲሁም እስከ አሁን ባለው የግሉ ዘርፍ ጥረት ብቻ ከግቡ የሚደርስ አይደለም። እነዚህ ፓርኮች በቀጣይ ሀገሪቱ ለሚያስፈልጓት አያሌ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ማሳያዎችና እርሾዎች ናቸው። ሌሎች በርካታ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ያስፈልጋሉ።

ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረግ ጉዞ በየጊዜው የኢንዱስትሪ መሰረተ ልማቶችን መገንባትን ይጠይቃል። የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በመጪዎቹ ዓመታት ከ100 በላይ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለመገንባት ማቀዱ ከዚህ አኳያ ሲታይ የኢንዱስትሪ ፓርክ የማልማቱ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ያመለክታል።

ሀገሪቱ ሥራ ላይ ባሉት ፓርኮች ብዙ ተሞክሮ የቀሰመች እንደመሆኑ እነዚህን ፓርኮች የመገንባቱ ስራ እንደ ውጭ ምንዛሬ እጥረት ያሉ ፈተናዎች ካልገጠሙ በስተቀር ብዙም ፈታኝ ይሆናል ተብሎ አይታሰብም። ዋናው ነገር ቀጣዩን የኢንዱስትሪ ዘመን ታሳቢ በማድረግ ለኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ትኩረት መሰጠቱ ነው።

ሀገሪቱ በሰሜን ኢትዮጵያ ከገጠማት ጦርነት፣ ከኮቪድ ወረርሽኝ፣ ከዓለም አቀፍ ጫና ጋር በተያያዘ ስራ ላይ ያሉት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ፈተና እንደገጠማቸው ይታወቃል። ይህ ፈተና ግን የኢንዱስትሪ ልማቱን አንገጫግጮታል እንጂ፣ ቀጣይነቱን አላቆመውም። መንግስትና ባለሀብቶች እያደረጉ ያሉትን ጥረት ተከትሎ ከዚህ ፈተና እየተወጣ ነው፤ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በስምምነት መቋጨቱ፣ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄና በመሳሰሉት የኢንዱስትሪው ዘርፍ እንዲነቃቃ እየተደረገ ያለው ርብርብና እየታየ ያለው ለውጥ የኢንዱስትሪው ዘርፍ በጥሩ መሰረት ላይ መቆሙን ያመለክታል። በፈተና ውስጥ በዘርፉ እየታየ ያለው ለውጥ ዘርፉ በቀጣይም ተጠናክሮ አንደሚቀጥል ያስገነዝባል።

ለኢንዱስትሪው በተጣለው መሰረት ላይ የሚደረገው የኢንዱስትሪ መሰረተ ልማት ግንባታ መጠናከር ይኖርበታል። ይህ እንዲሆን የሚያስገድዱ ሁኔታዎች በርካታ ናቸው።

በሀገሪቱ ባለሀብቶች ትኩረት ሳይሰጠው የቆየው የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ አሁን ትኩረት እያገኘ ነው፤ አንዱ አንዱን እያየ ወደ ዘርፉ እየተሳበ ይገኛል። አዳዲስ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ሊሰማሩ የሚችሉ ባለሀብቶች እየተፈጠሩ ናቸው። በቀጣይም ይሄ በሰፊው ይፈጸማል።

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላት ስፍራ እየጨመረ መምጣት፣ በተለይ ሰሞኑን በብሪክስ የተሰጣት ትልቅ ስፍራ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰቱ እንዲጨምር ሊያደርግ እንደሚችል ከወዲሁ እየተተነበየ ነው። ይህ ሁሉ በኢንዱስትሪ መሰረተ ልማት ግንባታ ላይ ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግና መሥራትን ይጠይቃል።

ሀገሪቱ ምጣኔ ሀብቷን ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር የምትሰራ እንደመሆኗ አቅም ካልፈተነ በቀር ሁሉም መሰረተ ልማት የተሟላላቸው፣ ባለሀብቶች ማሽነሪዎቻቸውን አስመጥተው በመገጣጠም ሰራተኞችን አሰልጥነው በማሰማራት በቀጥታ ወደ ማምረት የሚገቡበትን ሁኔታ አሟልተው የያዙ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ገንብቶ መጠበቅ ያስፈልጋል። የኮርፖሬሽኑ ዕቅድ ከዚህ አኳያ ሲታይ ተገቢና አስቀድሞ የታየ ሊባል የሚችል የኢንዱስትሪው ልማት ቀጣይነት ማሳያ ነው!

 አዲስ ዘመን ነሐሴ 29 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You