ድርድሩ በሕዳሴው ያስመለስነውን ጂኦፖለቲካዊ ከፍታ የሚያዘልቅ ይሁን፤

 (ክፍል አንድ)

ምስጋና ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ይግባና ግድቡ ከለየለት ክሽፈት ድኖ ዛሬ ላይ አፈጻጸሙ 90 በመቶ ደርሷል። 540 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይልም ማመንጨት ችሏል። ለአራተኛው ዙር ውሃ ሙሊትም እየተዘጋጀ ነው። ከሁሉም ከሁሉም በላይ ግን እንደ ቬኒዞላ ገንዘብ «ቦሊቫር» ጋሽቦ የነበረውን የሀገራችንን ስትራቴጂካዊ ይዞታ በሕዳሴው ደንደስ መመለስ ተችሏል። ከምንም ነገር በላይ ከግብጽ ጋር የሚደረግ ድርድር ይሄን የጂኦፖለቲካ ከፍታ የሚያስጠብቅ ፣ የሚያጸናና የሚያዘልቅ ሊሆን ይገባል የሚል ጽኑ እምነት አለኝ። ወደ ሰሞነኛው የካይሮ ድርድር ከመመለሴ በፊት ስለ ጂኦፖለቲክስ ትንሽ ልበል።

ቀለል ባለ አገላለጽ ጂኦፖለቲክስ ማለት ከዓለምአቀፍ ግንኙነት አንጻር ወይም አኳይ የጂኦግራፊንና የፖለቲካን ግንኙነት ማጥናት ነው። የሀገራችን ድንበር፣ የተፈጥሮ ሀብት፣ የሕዝብ አሰፋፈር፣ የእድገት ደረጃ፣ የምታራምደው የፖለቲካ ሥርዓትና ወታደራዊ አቅም የሀገራችንን የጂኦፖለቲክስ ይወስናል። የሀገራችን የሕዝብ ብዛትና የተፈጥሮ ሀብት ጂኦፖለቲክሷን ከፍ ሲያደርጉት በአንጻሩ የሀገሪቷ ውስጣዊ አንድነት ደካማ መሆን ጂኦፖለቲካዊ ስፍራዋን ወይም ዋጋውን ያሳንሰዋል። የሕዳሴው ግድብ መጠናቀቅ ደግሞ ጂኦፖለቲካዊ ቦታዋን ከፍ ያደርገዋል።

የዐረቡ ዓለም የነዳጅ ባለቤት መሆኑ ከተረጋገጠ፣ እኤአ በ1948 ዓ.ም እሥራኤል የአይሁዶች መንግሥት ሆና ከቆመች፣ ከ1993 ዓ.ም የመስከረም 1 ቀን የሽብር ጥቃት በኋላ የአሜሪካ፣ የምዕራባውያንና የዓለምአቀፉ ተቋማት የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ማጠንጠኛ ነዳጅ፣ የእሥራኤል ደህንነት እና የጸረ ሽብር ዘመቻ ሆነ። ዛሬ እንዲህ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ ወደ ቻይናና ራሽያ ሊወሰድ።

ሆኖም ለቆየው የአሜሪካ የውጭ ግንኙነት ፖሊስ እና ስትራቴጂ ተግባራዊነት ከዐረቡ ዓለም ግብፅ ቀዳሚዋ ስትራቴጂካዊ አጋር ሆና ተመርጣለች። ግብፅን ተመራጭ ያደረጋት ለምዕራባውያን የጡት ልጅ እሥራኤል ጎረቤት መሆኗ፤ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጧ በተለይ የስዊዝ ቦይ ባለቤት መሆኗ፤ የእስላማዊ ትምህርት ማዕከል እና የዐረብ ብሔርተኝነት አቀንቃኝ መሆኗ፤ ዜጎቿ ከሌላው የዐረብ ዓለም ጋር ሲነጻጸር በዓለማዊም ሆነ በእስላማዊ ትምህርት የገፉ በመሆናቸው በአጠቃላይ በነበራት ጂኦፖለቲካዊ በምዕራባውያንም ሆነ በእስላማዊው ዓለም ዘንድ ሞገስ አግኝታለች።

ይህን ሞገሷን የዐረቡን ዓለም ጨምሮ የዐረብ ሊግን እንዳሻት ለማሽከርከር ትጠቀምበታለች። በልዩነትና በክፍፍል ከሚንጠራወዘው የዐረቡ ዓለም ግብፅ እንደ ሰንደቅ ከፍ ብላ እንድትታይ ረድቷታል። ይህን መከፋፈል እሥራኤልን ጨምሮ አሜሪካውያን ሆኑ ምዕራባውያን ይፋ ባያወጡትም የሚደግፉት ስለሆነ ግብፅ ሽብልቅ ሆና እንድታገለግል (ብድርና እርዳታ እየሰጡ በአናቱ የጦር መሣሪያ እስካፍንጫዋ እያስታጠቁና ወታደራዊ ሥልጠና እየሰጡ ይንከባከቧታል። አሜሪካ ብቻ በየአመቱ ወደ 4 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የጦር መሣሪያ፣ የወታደራዊ እርዳታና የልማት ድጋፍ ታደርጋለች።

ግብፅ በአጠፋው ይህን ውለታ ከግምት ያስገባ እና እኤአ በ1979 በአንዋር ሳዳትና በእሥራኤል መካከል የተፈረመውን የሰላም ስምምነት መሠረት ያደረገ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ቀርጻለች። የሀገሪቱን ኢኮኖሚ፣ ደህንነትና ፖለቲካ በመዳፉ የጠቀለለው የግብፅ ጦርና ደህንነት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲን ተግባራዊነት ያረጋግጣል በዓይነ ቁራኛ ይከታተላል። ዘብ ሆኖ ሌት ተቀን ከዐረቡ አብዮት በኋላ በምርጫ የፈርኦኖችን በትረ ሥልጣን ጨብጠው የነበሩ የመጀመሪያው የእስላም ወንድማማቾቹ አባል ፕሬዚዳንት ሞሐመድ ሙርሲ እንኳ የድርጅታቸውንም ሆነ አክራሪ እስላሞች ግፊት ተቋቁመው የግብፅና እሥራኤልን የሰላም ስምምነት ማክበር ችለዋል ።

መጀመሪያ በመፈንቅለ መንግሥት በኋላ በምርጫ ወደ መንበሩ የመጡት ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲም ከሳዳት፣ ከሙባረክና ከሙርሲ በላይ የሰላም ስምምነቱን እያስፈጸሙ ነው። የእሥራኤል ጉዳይ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸው ቀኖና ነው ማለት ይቻላል። ከእሥራኤል ጀርባ ደግሞ አሜሪካ አለች። ግብፅ ናይል የህልውናዬ ጉዳይ ነው ብላ በሕገ መንግሥቷ ብታካትተውም፤ በውስጠ ታዋቂ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ የማዕዘን ራስ ቢሆንም በግላጭ ትኩረቱ እሥራኤል፣ ፍልስጤምና አሜሪካ ላይ ነው።

ግብፅ ዓባይን ከምንጩ ለመቆጣጠር፣ ሀገራችንን ቅኝ ለመግዛት እና ጠንካራ ሉዓላዊ ሀገር ሆና እንዳትወጣና ይህ ቀን ( ዓባይ የሚገደብበት ቀን ) እውን እንዳይሆን ከ11 ጊዜ በላይ ወራናለች። በስውር ደግሞ ምን አልባት ለሺህ ወይም ለሚሊዮን አመታት አሲራለች። በተለይ ከ20ኛው መክዘ ወዲህ ደግሞ የተለያዩ ኃይሎችን በመጠቀም የውክልና ( proxy ) ጦርነት በማካሄድ ሀገራችንን ስታዳክም ኖራለች። ይህ እኩይ ዓላማዋ ከሞላ ጎደል በመሳካቱ የቤት ሥራዋን በማጠናቀቋ ዝቅ አድርጋ ስታየን ኖራለች።

ከታሪካዊዋ ሐምሌ 15 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ግን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሁኔታዎች ተቀይረዋል። በሴራና በደባ በቀጣናውም ሆነ በዓለምአቀፍ መድረክ ያሳጣችን ጂኦ ፖለቲካዊ እና ስትራቴጂካዊ ስፍራ ከ30 አመታት በኋላ መልሰን ተረክበናል። ምርኳችን ተመልሷል። የቀጣናው ጂኦ ፖለቲካዊ አሰላለፍ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ እንደ አዲስ ተበይኗል። ተፐውዟል። የምለው ለዚህ ነው ። ከዚህ በኋላ የሀገራችን ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታና ጂኦ ፖለቲካዊ ስፍራ ከ1983 ዓ.ም በፊት ወደነበረው ከመመለሱ ባሻገር ከግብፅ የሚተናነስ አይደለም። ገና ዛሬ ታዋቂው የግሪክ የታሪክ ሰው ሔሮዶተስ እንዳለው ግብፅ የዓባይ (የኢትዮጵያ) ስጦታ ሆነች ። ስለ ጂኦፖለቲክስ አንድምታ ይህን ያህል ካልሁ ወደ ሰሞነኛው ድርድር ልመለስ።

የኢትዮጵያ የአሁኑም ሆነ የወደፊት ትውልዷን በዓባይ ውኃ የመጠቀም መብት አሳልፋ እንደማትሰጥ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች በድጋሚ ማረጋገጣቸውን፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን የመጀመሪያ ሙሌትና ውኃ አለቃቀቅ በተመለከተ በኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን መካከል በግብፅ ካይሮ ከተማ ከነሐሴ 21 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ቀናት የተካሄደው አዲስ ድርድር የመጀመሪያ ምዕራፍ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ የሦስቱ ሀገሮች ተደራዳሪዎች ቀጣዩን ዙር ውይይት በአዲስ አበባ ለማድረግ ቀጠሮ መያዛቸውንና የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድንም ባለፈው ማክሰኞ ነሐሴ 23 ቀን 2015 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ መመለሱን የአማርኛው ሪፖርተር ዘገባ ያስረዳል።

የሦስቱ ሀገሮች አዲስ ድርድር ባለፈው እሑድ ነሐሴ 21 ቀን 2015 ዓ.ም በግብፅ ካይሮ ከተማ ሲጀመር የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን መሪና በአሜሪካ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር የሆኑት ስለሺ በቀለ (ዶ/ር)፣ የሦስትዮሽ ድርድሩ በሦስቱ ሀገሮች መካከል ትብብርን ለማጠናከር እንደሚረዳ መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ድርድሩ በተጀመረበት ዕለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

አምባሳደር ስለሺ(ዶ/ር) ፣ «የኢትዮጵያ የአሁንና የወደፊት ትውልድ በዓባይ ውኃ የመጠቀም መብትና ጥቅም» መሠረታዊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው መናገራቸውን፤ በተጨማሪም ግድቡ ለሦስቱ ሀገሮች የሚሰጠው ጥቅም ከፍተኛ መሆኑንና ኢትዮጵያ በፍትሐዊና ምክንያታዊ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሠረተ አቋሟን አጠናክራ ድርድሩ ሁሉንም በሚያግባባ መልኩ እንዲጠናቀቅ እንደምትሠራ ገልጸዋል።

አምባሳደር ስለሺ በካይሮ የተካሄደው ድርድር ከተጠናቀቀ በኋላ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክትም ይህንኑ የጠቆሙ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን መካከል ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የነበረው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ሙሌት (ግድቡ በጥቂት ዓመታት ሙሉ ደረጃ እስኪደርስ ያለውን) እና የግድቡ የውኃ አለቃቀቅን የተመለከተው ድርድር ነሐሴ 22 ቀን መጠናቀቁን፣ ካይሮ ላይ በተካሄደው ድርድር ያልተሸፈኑና ስምምነት ባልተደረሰባቸው በርካታ የስምምነት አንቀጾች ላይ ሁለተኛ ዙር ድርድር በመጪው መስከረም ወር 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሁለተኛ ዙር በማድረግ ወደ ስምምነት ለመድረስ ቀጠሮ መያዙን ጠቁመዋል።

«የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ወገን፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን ጥቅምና በቀጣይ የዓባይ ውኃ ፍትሐዊና ምክንያታዊ አጠቃቀምን በሚያረጋግጥ መልኩ እንዲሁም በቀጣናው ሀገሮች መካከል ትብብርን በሚያጎለብት መልኩ እየሠራ ነው ።» በግድቡ ዙሪያ የተካሄደው የሁለት ቀናት ድርድር መጠናቀቁን አስመልክቶ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባወጣው መግለጫም፣ ኢትዮጵያ በፍትሐዊና ምክንያታዊ መርህ መሠረት የራሷን ድርሻና ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ ድርድሩ በስምምነት እንዲቋጭ ጥረቷን እንደምትቀጥል አስታውቋል።

በአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ የውኃ ምሕንድስና መምህርና የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን አማካሪ የሆኑት ይልማ ስለሺ (ፕሮፌሰር) ማክሰኞ ነሐሴ 22 ቀን በአልጀዚራ የቴሌቪዥን ጣቢያ በተደረገ የሦስቱ ሀገሮች ባለሙያዎች ክርክር ተሳትፈው፣ ስለአጠቃላይ የድርድሩ ሒደት ባደረጉት ገለጻ፣ ሦስቱ ሀገሮች ቀደም ሲል ባደረጓቸው ድርድሮች የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌትን በተመለከተ ያለ ልዩነት ስምምነት ላይ መድረሳቸውንና አሁን በተጀመረው አዲስ ድርድር የግድቡ የውኃ ሙሌት ሊያከራክር እንደማይችል አመልክተዋል፣ ሦስቱ ሀገሮች ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው ድርድሮች የሕዳሴ ግድቡ የውኃ ሙሌት ከአምስት እስከ ሰባት ዓመታት ባለው ጊዜ ውስጥ እንዲከናወንና በውኃ ሙሌቱ ወቅት የድርቅ ሁኔታ ያጋጠመ እንደሆነ ኢትዮጵያ ውኃ እንደማትይዝ ተነጋግረው ያለ ልዩነት መስማማታቸውን አስታውሰዋል።

ነገር ግን በሦስት ሀገሮች ድርድር ላይ አስቸጋሪ የሆነው የግድቡ ዓመታዊ ኦፕሬሽን ማለትም የግድቡ የውኃ አለቃቀን የተመለከተው ጉዳይ ነው። ይህንን አከራካሪ ጉዳይ በተመለከተ በግብፅ በኩል የሚቀርበው ጥያቄ ለሚቀጥሉት ሁለት አሠርት ዓመታት ከሕዳሴ ግድቡ በየዓመቱ የሚለቀቀው የውኃ መጠን ምን ያህል እንደሚሆን በቁጥር እንዲገለጽና ለዚህም ኢትዮጵያ በውል የታሰረ ዋስትና እንድትሰጥ በግብፅ በኩል አቋም መያዙን ይልማ ስለሺ (ፕሮፌሰር) ተናግረዋል። ይህ የግብፅ ጥያቄ በሌላ አገላለጽ ኢትዮጵያ ከሕዳሴ ግድቡ በላይ ባሉ አካባቢዎች ወይም በዓባይ ገባር ወንዞች ላይ ሌላ ተጨማሪ ልማት ማካሄድ የምትችለው ግብፅና ሱዳንን አሳውቃና ሁለቱ ሀገሮች የሚያገኙት የውኃ መጠን እንደማይቀንስ መረጋገጥ አለበት ማለት ነው ብለዋል።

ምክንያታቸውን ሲያስረዱም፣ ግብፅ የምትጠይቀው የዓባይ ውኃ ድርሻ እ.ኤ.አ. በ1959 ከሱዳን ጋር የተደረገውን የቅኝ ግዛት ውል በመጥቀስ ሲሆን፣ ይህ በሁለቱ ሀገሮች መካከል ብቻ የተደረገው ውል የዓባይ ውኃ ምንጭና ተፈጥሯዊ ባለቤት የሆነችውን ኢትዮጵያን ከማግለሉ በተጨማሪ ለኢትዮጵያ ምንም ዓይነት የውኃ ድርሻ የማይሰጥ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ይህንን ፈጽሞ ልትቀበል አትችልም ያሉት የተደራዳሪ ቡድኑ አማካሪ ስለሺ ይልማ (ፕሮፌሰር)፣ ምክንያታቸውን ሲያስረዱም ‹‹በአንድ በኩል የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚጋፋ በመሆኑ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ጥያቄው በቋንቋ አጠቃቀም ተሸፍኖ የቀረበ የውኃ ክፍፍል ጥያቄ በመሆኑ ነው ብለዋል። ይህ የሦስትዮሽ ድርድር እንደ አዲስ እንዲጀመር የተወሰነው ከአንድ ወር በፊት የሱዳንን ፖለቲካዊ ችግር ለመፍታት በግብፅ በተካሄደው ጉባዔ ለመሳተፍ ወደ ሥፍራው ያቀኑት ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከጉባኤው ጎን ለጎን ከግብጹ አቻቸው ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ ጋር ከተወያዩ በኋላ ነው። ሁለቱ መሪዎች ባደረጉት በዚህ ውይይት የሕዳሴ ግድቡን ድርድር ዳግም ለማስጀመርና በአራት ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ መስማማታቸውን በጋራ ባወጡት መግለጫ ማስታወቃቸው ይታወሳል።

ሁለቱ መሪዎች የሕዳሴ ግድቡን ድርድር በአራት ወራት ለማጠናቀቅ መስማማታቸውን በይፋ መግለጻቸውን ተከትሎ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ተደራዳሪና የባለሙያዎች ቡድን ሰብሳቢ የሆኑት ጌድዮን አስፋው (ኢንጂነር)፣ ነገሩ ድንገተኛና እርሳቸው የማያውቁት ቢሆንም እስካሁን ስምምነት እንዳይደረስ ያደረገውን ክርክር ግብጾች ይዘው የማይቀርቡ ከሆነ በአራት ወር ባይሆንም በአጭር ጊዜ ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚቻል ገልጸው ነበር።

በግብፅ በኩል የሚነሳውና ስምምነት እንዳይደረስ ምክንያት የሆነው የክርክር ነጥብ በ1959 በተደረገውን የዓባይ ውኃ ክፍፍል ያገኘችውን ድርሻ እንዲጠበቅ፣ በሌላ አነጋገር ኢትዮጵያ ከሕዳሴው ግድብ በኋላ በዓባይ ውኃ ላይ ምንም ዓይነት ልማት እንዳታካሂድ መቅረባቸው እንደሆነ የጠቀሱት ጌድዮን አስፋው (ኢንጂነር)፣ ግብፅ ይህንን ክርክር ከተወች በአጭር ጊዜ ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚቻል አስረድተዋል።

ሻሎም ! አሜን ።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)

አዲስ ዘመን ነሐሴ 28 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You