ዲፕሎማሲያዊ ባህሎቻችንን አሻሽለን ከብሪክስ ብሄራዊ ጥቅሞቻችንን እናስጠብቅ

በዓለም ታሪክ ኢትዮጵያ ከየትኛውም ሀገር ቀድማ ያልጀመረችው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሁነቶች የሉም ቢባል ማጋነን አይደለም። በርካታ ሥልጣኔዎችን ከየተኛውም ዓለም በፊት እንደጀመረች እና እነኚህን ሥልጣኔዎቿን ለዓለም ሕዝብ ያበረከተች ስለመሆኗ በተለያዩ መጽሐፍት እና ጥናታዊ ጽሁፎች ተመላክቷል።

ነግር ግን በቀደመው ጊዜ ከዓለም ሀገራት ቀዳሚ መሆን እና ለዓለም ሕዝብም የተለያዩ ሥልጣኔዎችን አበርክተን ነበር ማለት በአሁኑ ጊዜ በሥልጣኔ ማማ ላይ ነን ማለት አይደለም። በቀደሙት ዘመናት ከፊት መሆን በዚህ ወቅት ለሚኖረው የዓለም የሥልጣኔ አርሾ ሊሆን ይችላል እንጂ አሁን ላይ ላለን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚ አቅም ሊሆን አይችልም ።

አሁን ላይ ቀዳሚ መሆን ከተፈለገ በቀደመው ጊዜ ጠንካራ እንድንሆን ያስቻሉ ሀገር በቀል እውቀቶች እና አሰራሮች መመርመር ፤ ዛሬን መዋጀት በሚችሉበት አቅም ተግባራዊ ማድረግ ፣ለዚህ የሚሆን አዲስ ሀገር አሻጋሪ ትርክት መፍጠር ያስፈልጋል።

ዓለም ሁልጊዜም በተቃርኖ ውስጥ ናት። ተቃርኖዎች በራሳቸው አሉታዊ እና አወንታዊ ተጽዕኖ ማሳደራቸው የማይቀር ነው። እነኚህ ተቃርኖዎች ሜታፊዚክሳዊ ወይም ዳያሌክታዊ ምክንያት እና ውጤት ይኖራቸዋል። እነኚህን ተቃርኖዎች በቅጡ በመረዳት አወንታዊ ውጤት እንዲኖራቸው በማድረግ ለሥልጣኔ አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር ያስፈልጋል።

አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር ከሚቻልባቸው መንገዶች አንዱ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ነው ። ከዓለም አቀፍ ግንኙነቶች ተጠቃሚ መሆን የሚቻለው ግንኙነታችንን ተገማች እና ኢተጋማች በሆነ መልኩ ማደራጀት እና ማዘመን ስንችል ነው።

በዘመናዊ ዓለም ኢትዮጵያ በበርካታ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ ከአፍሪካ ብሎም ከዓለም ሀገራት ግንባር ቀደም ሆና አይተናታል። ነገር ግን ለዓለም ፖለቲካል ኢኮኖሚ ከምታበረክተው አብርክቶ አንጻር ምን ያህል ተጠቃሚ ናት? የሚለውን መገምገም ያስፈልጋል።

ኢትዮጵያ በዓለም ፖለቲካል ኢኮኖሚ ካላት ተሳትፎ አንጻር ተጠቃሚ አይደለችም። ለዚህም በርካታ ማሳያዎችን ማቅረብ ይቻላል። አንደኛ ኢትዮጵያ የዓለም ማህበር ( League of Nation) ሲመሠረት መስራች ሀገር ባትሆንም ከአፍሪካ ብቸኛዋ ከቅኝ ግዛት ነጻ አባል ሀገር ነበረች።

በአባልነት ጊዜዋም ለማህበሩ ሁለንተናዊ እድገት በርካታ ሥራዎችን ሰርታለች። ይሁን እንጂ ሌላኛዋ የዓለም ማህበር አባል ሀገር የነበረችው ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረራ ለመያዝ ስትመጣ አንድም ሀገር ለኢትዮጵያ አለሁልሽ ያላት አልነበረም።

ይባስ ብለው ጣሊያን በሶማሊያ ወልወል በኩል ወረራዋን ስታስፋፋ ኢትዮጵያ ያደረገችው መከላከል እንደ ወንጀል ተቆጥሮ “በድሎ ካሱኝ ፤ እሾህ ይዞ እጄን ዳብሱኝ” እንዲሉ በግፍ የወረረችን ጣሊያን በወልወል በኩል ኢትዮጵያ ጥቃት ስለፈጸመችብኝ ካሳ ትክፈለኝ አለች። አብዛኛው የዓለም ማህበር አባል ሀገራትም «ለጣሊያን ካሳ ያስፈልጋታል» ሲሉ ፍትህን አርቀው ቆፍረው ቀበሯት። ኢትዮጵያም ብዙ በደከምችበት ማህበር ክህደት ተፈጽሞባታል።

ሁለተኛ ኢትዮጵያ በመስራችነት ከምትታወቅባቸው ማህበራት አንዱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (United Nation) በዋነኝነት ይጠቀሳል። ኢትዮጵያ ድርጅቱን ከመመስርትም አልፋ አንድ ሉዓላዊ ሀገር በሌላ ሉዓላዊ ሀገር ብትወረር ማህበሩ መውሰድ የሚገባቸው ርምጃዎች ምን መምሰል አለባቸው የሚለውን ሕግ እንደ አንድ የማህበሩ ሕግ እንዲሆን አድርጋለች ። ከዚህ አኳያ ልጅ አክሊሉ ኃብተወልድ የፈጸሙት ገድል ሁሌም በታሪክ ሲዘከር የሚኖር ነው።

ከዚህ ባሻገር ኢትዮትጵያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተደረገላትን ጥሪ ተቀብላ በዓለማችን ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ በበርካታ ሀገራት በሰላም አስከባሪነት ተሳትፋለች፤ አሁንም እየተሳተፈች ነው። ለምሳሌ በኮሪያ፣ በኮንጎ፣ በላይቤሪያ፣ በሶማሊያ ፣ ባደርፉር፣ በደቡብ ሱዳን ወዘተ።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ለተባበሩት መንግሥታት ካበረከተቻቸው አበርክቶዎች አንጻር የሚገባትን ጥቅም አግኝታለች ለማለት ፈጽሞ የሚያስደፍር አይደለም። ይልቁንም ማህበሩ በተለያዩ ጊዜያት ከሕግ ውጪ በሆነ አግባብ ኢትዮጵያን ሲጨቁን ተመልክተናል። ለዚህም እንደማሳያ ከህዳሴው ግብድብ እና ከሰሜኑ ጦርነት ጋር ተያይዞ ለውሳኔ ይሰበሰብባቸው የነበሩ ስብስባዎች የቅርብ ጊዜ ትውስታዎች ናቸው። በእነኚህ መድረኮች አምባሳደር ታየ አጽቀስላሴ ያደርጓቸውን ተጋድሎዎች ማንም ኢትዮጵያዊ የሚረሳው አይደለም።

በእርግጥ ኢትዮጵያ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተለያዩ ርዳታዎችን ታገኛለች። ነገር ግን ተደረጉ የተባሉ ርዳታዎች የእውነት የኢትዮጵያን ችግሮች የሚፈቱ ሳይሆኑ ኢትዮጵያ የምዕራባውያንን ርዳታ አንጋጣ እየጠበቀች ምዕራባውያን ከሚዘውሩት የኢፔሪያሊዝም ባቡር ላይ ብቻ እንድትሳፈር የሚያደርግ በአሳሪ ትብታቦች እና ችንካሮች የተሞሉ ናቸው።

የተባበሩት መንግሥታት የእውነት ኢትዮጵያ ከችግር እንድትወጣ የሚፈልግ ድርጅት ቢሆን ኖሮ የገንዘብ ርዳታ ከማድረግ ይልቅ እንዴት ገንዘብ ማግኘት ይቻላል? የሚለውን ባስተማረ ነበር ። ስንዴ ከመርዳት ይልቅ እንዴት ዘመናዊ እርሻን ማረስ እንደሚቻል ቢያሳየን ፣ የእርሻ መሣሪያዎችን ከመርዳት ይልቅ በቀላል ወጪ እንዴት የእርሻ መሣሪያዎች ሊሰሩ ይችላሉ የሚለውን ቴክኖሎጂ ማሳየት ይሻል ነበር።

ይህ አልሆነም ፣ሊሆን ይችላል ብሎ ማሰብም በብዙ መልመኩ የዋህነት እንደሚሆን ለማመን አይከብድም። ምክንያቱም ሁሌም በእነሱ ርዳታ ተንጠልጥለን እነሱ በዘረጉት ሃዲድ ብቻ እየሸመጠጥን እንድንኖር ስለሚፈልጉ ነው። የማርሻል ፕላን የዚህ ሁነኛ ማሳያ ነው።

ሶስተኛ ኢትዮጵያ በመሥራችነት ከምትታወቅባቸው ማህበር መካከል የአፍሪካ እግር ኳስ ማህበር አንዱ ነው። ለዚህ ማህበር መመሥረት ኢትዮጵያ ከማንም ሀገር የበለጠ አስተዋጽኦ ብታደርግም አሁን ላይ በዘርፉ ያለችበት ደረጃ የሚታወቅ ነው ። በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ከኋላዋ ተነስተው ዛሬ ላይ የት እንደደረሱ ይታወቃል።

ሌላው ኢትዮጵያ ከመሠረተቻቸው ድርጅቶች መካከል የአፍሪካ ህብረት በግንባር ቀድምትነት ተጠቃሽ ነው። ይህ ድርጅት በኢትዮጵያ ፊትውራሪነት ተመስርቶ በርካታ የአፍሪካ ሀገራትን ከቅኝ ግዛት ነጻ ማውጣ ያስቻለ ድርጅት ነው። ነገር ግን ኢትዮጵያ ለዚህ ድርጅት ምስረታ እና ህልውና ካበረከተችው አብርክቶ አኳያ ምን ያህል ተጠቃሚ ናት ሲባል? መልሱ አጥጋቢ አይሆንም።

ኢትዮጵያ ካልጠቀስኳቸው አጅግ በርካታ ድርጅቶች ውስጥ በመሥራችነት እና በአባልነት ተሳትፋለች እየተሳተፈችም ትገኛለች። ነገር ግን በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት ኢትዮጵያ ለድርጅቶቹ ከምታበረክተው አብርክቶ አኳያ በቅጡ ተጠቅማለች ለማለት አያስደፍርም።

ከሰሞኑ የብሪክስ አባል ሀገር የሚያደርጋት አጋጣሚ ተፈጥሯል። ብሪክስ መግባቱ ብቻውን ትልቅ ነገር ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ኢትዮጵያ ካለፉት ስህተቶቿ ተምራ ከህብረቱ ማግኘት የሚገባትን ጥቅሞች ለይታ በዝርዝር በማስቀመጥ ጥቅሟን ማስከበር አለባት። ካልሆነ ግን ኢትዮጵያ ለሌሎች ፖለቲካል ኢኮኖሚ ኩነቶች የምታወጣቸውን የገንዘብ እና የጉለበት ወጪ ከመጨመር በቀር ምንም ጥቅም አይኖረውም።

እንደ ሀገር ካለፉ ችግሮቻችን በመማር በብሪክስ ብሔራዊ ጥቅሞቿን ለማስጠበቅ አንደኛ ተገማች እና ኢተገማች የሆኑ ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎችን መፈጸም ይገባታል። ሁለተኛ ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የነበሩ ዲፕሎማሲዊ ባህሎቿን ወይም አሠራሮች መቀየር ይጠበቅባታል ባይ ነኝ ። ሰላም!!

 አሸብር ኃይሉ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 28 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You