አዲስ ዓመት ከዓመቱ አዲስነት በላይ ይዞት ይመጣል ተብሎ የሚጠበቅው አዲስ ነገር በብዙዎች ዘንድ ትልቅ ትኩረት ይሰጠዋል። ከዚህ የተነሳም አንዳንዶች የሕይወታቸው መታጠፊያ መንገድ አድርገው በመውሰድ እራሳቸውን በሁለንተናዊ መልኩ የሚያዘጋጁበት ሁኔታ ይስተዋላል። በዚህም ስኬታማ መሆን የቻሉ ጥቂት አይደሉም።
ይህ ትናንቶቻችን ከራስ የመሆን መፈለግ ጋር በአግባቡ ከመገምገም የሚነሳው የነዚህ ሰዎች የአዲስ ዓመት አቀባበል ፣ አዲሱን ዓመት በተቻለው ሁሉ መሆን ለሚፈልጉት መሻታቸው ስኬት የሚሆንበትን አቅም በመፍጠር እና አሱን በአግባቡ ከራሳቸው ጋር በማስተሳሰር ተስፋቸውን የሚያድሱበት ነው።
ይህ በአዲስ ዓመት ዋዜማ ላይ የሚከናወን እራስን በተስፋ ውስጥ የማደስ ፤ ለዚህ የሚሆን መንፈሳዊ ፣ አእምሯዊና አካላዊ ዝግጁነት መፍጠር ከቀደሙት ትውልዶች ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ፤ ወደፊትም ቀጣይ የሆነ ትልቅ ሰብዓዊ እሴት እንደሆነም ይታመናል።
እንደ ማህበረሰብም ፤ አንድ ማህበረሰብ በተመሳሳይ መልኩ ፤ በአዲስ ዓመት ዋዜማ ላይ አዲሱን ዓመት በተስፋ መቀበል የሚያስችል መንፈሳዊ ፣ አእምዊና አካላዊ ዝግጁነት የሚያላብሱ ተግባራትን ይከውናል። ለዚህ የሚሆኑም መንፈሳዊ ፣ ማህበራዊ እና ባህላዊ እሴቶች ይኖሩታል።
እነዚህ እሴቶች ትናንቶችን ከማህበረሰቡ የመሆን መሻት አንጻር በተጨባጭ የሚገመግሙ ፤ ጠንካራና ደካማ ጎኖችን ለይተው ፤ ጠንካሮቹ የሚጎለብቱበትን ፤ ደካሞቹ የሚስተካከሉበትን የሚጠቁሙ ናቸው። ከዚህ ባለፈ ነውሮችን ፣ ከነውሮች በስተጀርባ ያሉ የአመለካከት መዛነፎች የሚያወግዙ ናቸው።
ይህ እውነታ እንደሀገር በእኛም ማህበረሰብ (ህዝብ) ውስጥ ዘመናት ያስቆጠረ፣ ዛሬም በስፋት የሚስተዋል ነው። አዲሱ ዓመት በአደይ አበባ ተሞሽሮ ሲመጣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለትናንት መሻቱ አዲስ ተስፋ ሰንቆ ለመንቀሳቀስ ከራሱ ጋር የሚመክርበት ፣ በምክሩም ራሱን አሳምኖ የሚቆምበት ነው።
ለዚህም በመንፈሳዊ ፣ ባህላዊና ማህበራዊ እሴቶቹ ውስጥ ያሉ ተስፋ አቆጥቋጭ እሴቶች ያላቸው ሚና ከፍ ያለ ነው። እነዚህ አሴቶች ከትናንት ስህተት ተምሮ መቆም ፣ መራመድ ፣ ከራስ ጋር በሚደረግ እርቅ (በአዲስ የማንነት ግንባታ) ነገዎችን የተስፋ መስሪያና ማረፊያ ማድረግ እንደሚቻል አበክረው የሚመክሩ ናቸው።
ይህ አዲስ ዓመት በራሱ የሚጭረው አዲስ የማንነት ግንባታ መነቃቃት ከግለሰብ አልፎ እንደሀገር ለጀመርነው ድህነትን አሸንፎ የመሻገር አዲስ የታሪክ ጉዞ ዋነኛ አቅም ሊሆን እንደሚችልም ይታመናል።
በተለይም በዚህ የአዲስ ዓመት ዋዜማ ትናንቶቻችንን በአግባቡ እና በታማኝነት መገምገም ከቻልን ፣ አዲሱ ዓመት ይዟቸው የሚመጣቸው ነገዎች የተስፋዎቻችን መሥሪያና ማብሰሪያዎች መሆን ስለመቻላቸው ብዙም የሚያከራክር አይሆንም።
ይህን በተጨባጭ እውን ለማድረግ ፤ በነዚህ ቀናቶች ውስጥ በጥድፊያ ከተሞላው የጥፋት መንገዶቻችን ቆም ብለን ስለተስፋችን እየተጓዝንበት ስላለው መንገድ ጠንካራና ደካማ ጎኖች ምንነት በአግባቡ መገምገም ይጠበቅብናል።
በመንገዳችን ላይ አሜኬላ የሆኑብን ነውሮቻችን ምን ያህል ያልተገባ ዋጋ እያስከፈሉን ስለመሆኑ በሰከነ መንፈስ ልንመረምራቸው ፣ ነውርነታቸው እስከምን ድረስ መንፈሳዊ፣ ማህበራዊ እና ባህላዊ አሴቶቻችንን እየተፈታተኑት እንደሆነም ልናጤነው ይገባል።
በተለይም ስለ ሕዝብ እና ስለ ሀገር ፣ ድህነትና ኋላቀርነትን አሸንፎ የበለጸገች ሀገር ስለመመስረት እያዜምን ፣ በተጨባጭ እየተጓዝን ስላለው የጥፋት መንገድና መንገዱ እንደግለሰብ ሆነ እንደሀገር እያስከፈለን ስላለው ያልተገባ ዋጋ በሃላፊነት መንፈስ ልናስብ ይገባል።
የዛሬው በግጭትና በሁከት የተሟሟቀው የታሪክ ጉዟችን ከኛም አልፎ ለመጭዎች ትውልዶች ጥሎት ሊሄድ ስለሚችለው ጠባሳ ፤ ጠባሳው በመጭዎቹ ትውልዶች ዘላቂ ሰላም ላይ ሊፈጥር ስለሚችለው አሉታዊ ተጽእኖ ፤ ልጅ ወልዶ ለልጆቹ ነገዎች በብዙ እንደሚቃትት ወላጅ አስበን ልንቀሳቀስ ይገባል። በዚህም አዲሱ ዓመት ከአዲስ ቀናቶች ስብስብነቱ ባለፈ የተስፋችን መስሪያና ማብሰሪያ ማድረግ እንችላለን።
አዲስ ዘመን ነሐሴ 28 ቀን 2015 ዓ.ም