‹‹ሴቶችን ማስተማር ማህበረሰብን ማስተማር ነው›› የሚባለው ያለምክንያት አይደለም፡፡ ከራሳቸው አልፈውም ቤተሰባቸውን፣ የአካባቢያቸውን ማህበ ረሰብና የሀገሪቱን ዜጎች ህይወት የመቀየር ትልቅ አቅም ስለአላቸው ነው፡፡ እርግጥ ነው ሴቶች ከተማሩ ቱሩፋቱ ብዙ ነው፡፡ የመማሩን ዕድል ካገኙ ከወንዶች ባልተናነሰ መልኩ በሚሰማሩባቸው የሥራ ዘርፎች ሁሉ ውጤታማ ይሆናሉ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ መሥራት የሚችሉበት ዕድል ከተዘጋ ይህ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አበርክቷቸው ይቀጭጫል፡፡
የሴቶችን በተለያዩ መስኮች ተሳታፊነት ማሳደግ የግድ እንደሆነ አብዝቶ የሚነገረውም በዚህ ሁሉ ምክንያት ነው፡፡ በአፍሪካ ያለውን እውነታ ብቻ ብንመለከት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በአሁኑ ወቅት ሴቶች አዳዲስ በተባሉ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ተሳታፊ እንደሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በኢትዮጵያም ያለው ሁኔታ ይህንኑ ይጠቁማል፡፡
ሴቶችን ወደፊት ለማምጣት በሚደረገው ጥረት በተለይም በአፍሪካ በርካታ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሴቶች ምሳሌ ሆነው ታይተዋል፡፡ በኢትዮጵያም እንዲሁ ከተለመደው ውጭ ሴቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሰማሩ ብቻ ሳይሆኑ፣ በተሰማሩባቸው መስኮች ትርጉም ያለው ሥራ ሲሰሩ ይስተዋላል፡፡
ኢትዮጵያዊ ሴት መሆን አያሌ መሰናክሎችን መጋፈጥ ቢሆንም፣ ይህን ፈተና ተቋቁመው በተለያዩ የሥራ ዘርፎች በመሰማራት ትርጉም ያለው ሥራ የሠሩ፤ እየሠሩ ያሉ በርካቶች ናቸው፡፡ የዕለቱ የስኬት እንግዳችንም በርካታ ሥራ ከሠሩና ምሳሌ መሆን ከቻሉ ኢትዮጵያዊ ሴቶች ተርታ ትመደባለች፡፡
እንግዳችን በአረብ አገር ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ ቆይታለች፡፡ በቆይታዋ የአገሯ ስም ከረሃብተኝነት ጋር ተያይዞ ሲነሳ ትሰማለች፡፡ ይህን አምኖ ለመቀበል በብዙ ተቸግራለች፡፡ የአርብቶ አደር ልጅ የሆነችው ይህች ኢትዮጵያዊት፣ ሌላው ቢቀር ወተትና ቅቤ እንዲሁም ማር በልታና ጠጥታ ማደጓን ታውቃለችና ኢትዮጵያ በረሃብተኝነት መፈረጇ ቁጭት አሳደረባት፡፡
ቁጭቷን ለመወጣትም ጥርሷን ነክሳ ጥሪት ቋጥራ ወደ አገሯ መመለስ እንዳለባት በማመን የአረብ አገር ቆይታዋ ትርጉም ያለው እንዲሆን የበለጠ መውተርተር ውስጥ ገባች፡፡ የአረብ ሀገር ቆይታዋን ገታ አድርጋ ወደ እናት አገሯ ትመለሳለች፡፡
በአሁኑ ወቅት በትውልድ አካባቢዋ ባቢሌ ወረዳ በግብርናው ዘርፍ ተሰማርታ አትክልትና ፍራፍሬዎችን በማልማት ሥራ ላይ ተሰማርታለች፡፡ በዚህም ከቤተሰቦቿም ባለፈ የአካባቢው ማህበረሰብ የሥራ ባህልን ይበልጥ እንዲገነዘብ በግብርና ስራዋ አስተምራለች፡፡
ባቢሌ ወረዳ ተወልዳ፤ ድሬዳዋና ሀረር ያደገችው የዛሬ እንግዳችን ወይዘሮ ፈትያ ሙሐመድ ትባላለች። ወይዘሮ ፈትያ፤ ቤተሰቦቿ ከከብቶቻቸው ጋር ከቦታ ቦታ ኑሯቸውን ይመሩ እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ውስጥ የአርሶና አርብቶ አደር ኑሮ ከእጅ ወደ አፍ ቢሆንም፣ ወይዘሮ ፈትያ ወተት፣ ቅቤና ማር ያጣችበትን የልጅነት ጊዜ አታስታውስም፡፡ ለዚህም ከአያቶቿ ጋር ማደጓ ሳይጠቅማት እንዳልቀረ ትናገራለች።
ወይዘሮ ፈትያ፤ ገና የአሥራ ሦስት ዓመት ታዳጊ እያለች ነው ወደ አረብ አገር የሄደችው፡፡ በአብዛኛው ሴት እህቶቻችን ወደ አረብ አገር በሚሄዱበት አግባብ በቤት ሠራተኝነት ሳይሆን በትዳር ነበር የሄደችው። በአሥራ ሦስት ዓመቷ በአካባቢው ባህልና ወግ መሰረት ባል ይመጣላታል፡፡ ቤተሰብ ያመጣውን ባል ልጅ መቀበል የግዱ ነውና በወቅቱ ማን ይሁን ማን ለማታውቀው የሳውዲ ዜግነት ላለው አረብ ተድራ ነው ወደ አረብ አገር ያቀናችው፡፡
ማስተዋል በማትችልበት በልጅነት ዕድሜዋ ትዳር ይዛ ወደ አረብ አገር የተጓዘችው ወይዘሮ ፈትያ፤ በአረብ አገር ቆይታዋ ከህይወት ብዙ ትምህርት መቅሰም ችላለች። ይህም ስለ አገሯ ሁኔታ የበለጠ ማወቅና መረዳት አስቻላት፡፡ ሀገሯ ረሃብተኛ መባሏን በወቅቱ ልጅ በመሆኗ አልተረዳችውም ነበር፡፡ እንዲያውም ‹‹ረሃብተኛ ማለት ምን ማለት ነው፤ ወተት ጠጥተን በቅቤና በማር አድገን ለምን ረሃብተኛ ተባልን›› የሚል ጥያቄም በልጅነት አዕምሮዋ ተፈጥሮባት እንደነበር ታስታውሳለች፤ ይህም አብዝቶ ይቆጫት፣ ያንገበግባት ጀመር፡፡
ወይዘሮ ፈትያ፤ እያደገች፣ እየበሰለች እና እያስተዋለች ስትመጣ አገሯ ኢትዮጵያን ከሌሎች አገራት ጋር በማነጻጸር አገሬ ምን አጣች፤ ምንስ ጎደላት የሚሉ ጥያቄዎችን እያነሳች ቀስ በቀስ በራሷ መመለስ ጀመረች፡፡ ገና በለጋነት ዕድሜዋ በቤተሰብ የመጣላትን ትዳር አሜን ብላ በመቀበል ወደ ሳውዲ ማቅናቷም ለበጎ እንደሆነ በማመን ቁጭቷን የምትወጣበትን መንገድ በማሰላሰል ሁኔታዎችን ማመቻቸት ጀመረች፡፡
‹‹አብዛኛው የሙስሊም እምነት ተከታይ ቤተሰብ ለሴት ልጁ ትዳር በማምጣት ይታወቃል›› የምትለው ወይዘሮ ፈትያ፤ በወቅቱ በአካባቢው ከነበሩ ታዳጊ ሴቶች እርሷ በቁንጅናዋ ሳቢያ ተመርጣ እንደተዳረች ታስታውሳለች፡፡ አረብ አገር አማቾቿን በተቀላቀለች ጊዜም አማቾቿ ቁንጅናዋን አድንቀው ሲያበቁ፤ ‹‹ይችን ቆንጆ ከየት ነው ያመጣት፤ ከየት አገኛት›› የሚል ጥያቄያቸውን ያነሱ ነበር፡፡ የጥያቄያቸው መልስ ደግሞ ‹‹አረብ አይደለችም ሀበሻ ናት›› የሚል ብቻ አልነበረም ‹‹ከዛ ከረሃብተኛ አገር ከኢትዮጵያ ነው የመጣችው›› የሚል ቅጥያም ነበረው፡፡ ይሄኔ በቁንጅናዋ መደነቋ ያስደሰታት ወይዘሮ ፈትያ፤ ‹‹ከኢትዮጵያ ከረሃብተኛ አገር መጣች››መባሏ ግን በእጅጉ ይቆጫት እንደነበርና ዛሬም ድረስ ስታስበው እንደሚሰማት አጫውታናለች።
በወቅቱ መልስ መስጠት ባትችልም ያደገችበትን ወተትና ቅቤ እያስታወሰች ‹‹ግን ለምን፤ ይህን ያህል ረሃብተኛ ነን እንዴ?›› በማለት እራሷን ትጠይቃለች። ይሁንና በቆይታዋ ሀገሯን ከእነሱ አገር ስታነጻጽር አገራቸው አሸዋ እንደሆነና አፈር እንኳን የሌላቸው መሆኑን ትረዳለች፤ ለከተማቸው ማስዋቢያ ከሌሎች አገራት አፈር ገዝተው እንደሚያመጡም ታውቃለች። ሶስትና አራት ሺ ሜትር ርቀት ያለው ጉድጓድ ቆፍረው የፈላ ውሃ እንደሚያወጡ፣ እሱኑ በታንከር አጠራቅመውና አቀዝቅዘው እንደሚጠቀሙ፡፡ ያስተዋለችው ወይዘሮ ፈትያ፤ የኢትዮጵያ ረሃብተኝነት አልታይሽ አላት፡፡
በዚህ ወቅት ታዲያ ‹‹እኔኮ አገሬ ዝናቡ የማያቋርጥበት፣ አረንጓዴ ለምለም የበዛበት፣ ምቹ አየር ያለበት፣ መሬቱ ጫር ጫር ቢደረግ ሁሉን የሚያበቅልበት፣ ለምለም አገር ናት ›› በማለት ኢትዮጵያ አገሯን አስባ ታዲያ ለምን ረሃብተኛ ተባልን ስትል ራሷን ሞገተች፡፡ ችግር ነው ያለችውን አንድ ሁለት ብላ መለየት ጀመረች። በወቅቱም በእሷ አቅም ለይታ ላስቀመጠችው ችግር የምትችለውን ለማድረግና መፍትሔ ለመሆን ስትዘጋጅ በአረብ አገር የሚኖራትን ቆይታ ማራዘም አንዱ መንገድ ሆኖ ታያት፡፡
ወይዘሮ ፈትያ፤ አረብ አገር በነበራት ቆይታ ብልጭልጭ ነገር ሳያታልላት ገንዘብ ማጠራቀም እንደጀመረች ትናገራለች፡፡ ከትዳር አጋሯ እንዲሁም ከዘመዶቹ የምታገኘውን ገንዘብ በሙሉ በመጠኑ ተጠቅማ ቀሪውን ማጠራቀም ጀመረች፡፡ በአብዛኛው ለወርቅ፣ ለአልባሳት፣ ለቤት ዕቃ መቀየሪያ፣ ለልጆች አልባሳትና መዝናኛ ጭምር የሚሰጣትን ገንዘብ በመጠኑ በመጠቀም ብዙ ነገር ሳያምራት፤ ብዙ ገንዘብ ማጠራቀም ቻለች፡፡
ከአገር አገር ተጓጉዞ መዝናናት በአረቦቹ የተለመደ ቢሆንም ወይዘሮ ፈትያ፤ ግን ጉዞውን ቀነስ በማድረግ ገንዘቧን ማጠራቀም ቀጠለች፡፡ ከዕለታት በአንዱ ቀን ከቤተሰቧ ጋር ለጉብኝት ሱዳን ባቀናችበት ወቅት ሱዳኖቹ ከ30 እስከ 40 ሜትር ከሚደርስ ጉድጓድ ውስጥ ውሃ ሲያወጡ ተመለከተች፡፡ ውሃ ማውጣት ብቻም አይደለም፤ የወጣውን ውሃ የውሃ መሳቢያ ሞተር ገጥመው ወደ እርሻቸው ሲለቁ አስተዋለች፡፡ በዚህ ወቅት በአገሯ በየሰው ደጅ አቋርጦ የሚሄደውን ወራጅ ውሃ እንዲሁም ወንዞችን አስታወሰች፡፡
‹‹ሱዳኖቹ እንዳደረጉት ሁሉ የአገሬ ህዝብም ወንዞቹንና ወራጅ ውሃውን ቢጠቀም የት ይደርስ ይሆን?›› ስትል እራሷን ጠየቀች፡፡ ቀጠል አድርጋም ‹‹እንዲህ መሥራት ከቻልን ከድህነት መውጣት እንችላለን›› የሚል መልስ ለጥያቄዋ ሰጠች፡፡ ስለዚህ አለች ወይዘሮ ፈትያ፤ ‹‹ስለዚህ ይህን ቴክኖሎጂ ወደ ኢትዮጵያ መውሰድ አለብኝ›› በማለት ለራሷ ቃል ገባች፡፡ ቃሏን ወደ ተግባር ለመለወጥ ጊዜ አላጠፋችም፤ ከመቅጽበት ወደ አገሯ ኤምባሲ በማቅናት አገሯ ላይ የግብርና ሥራ መሥራት እንደምትፈልግና ቴክኖሎጂውንም ወደ አገሯ የማስገባት ፍላጎት እንዳላት አስረዳች፡፡ ኤምባሲውም ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መራት፡፡
ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የት ቦታ ላይ መሥራት እንደምትፈልግ በጠየቃት ጊዜም በኦሮሚያ ክልል ባቢሌ ወረዳ ላይ መሥራት ፍላጎቷ እንደሆነ ትገልጻለች። ባቢሌ ጠረፍ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሽፍታ ያለበት አካባቢ እንደሆነና ሴት ሆና እንደማትችል ይነገራታል፡፡ ይሁንና ወይዘሮ ፈትያ፤ ባቢሌ የትውልድ ቦታዋ እንደሆነና አካባቢውን እንዲሁም የአካባቢውን ማህበረሰብ ጠንቅቃ የምታውቅ በመሆኑ ባቢሌ ካልሆነ አሻፈረኝ ትላለች፡፡ ‹‹የአገሬንና የአካባቢዬን ሰዎች በተለይም ሴቶችን የማስተምራቸው ነገር አለኝኛ በዚሁ አካባቢ መሬት ይሰጠኝ›› ብላ የሙጥኝ በማለቷ ሃምሳ ስድስት ሄክታር መሬት ተሰጥቷታል፡፡
የእርሻ መሬቱን ባገኘችበት ቅጽበት ጊዜ ሳታጠፋ ወደ ሱዳን በማቅናት ውሃ ከጉድጓድ አውጥተው በሞተር ወደ እርሻቸው ሲለቁ የተመለከተቻቸውን ባለሙያዎች ከነቴክኖሎጂያቸው በዶላር ቀጥራ ወደ ኢትዮጵያ ባቢሌ አመጣቻቸው፡፡ በእርሻ ቦታዋ መኖሪያ ቤት ሰርታላቸው ቆይታቸውን እዛው አድርገው አሥር የውሃ ጉድጓዶች እንዲያወጡላት አድርጋለች። ሱዳኖቹ ውሃውን በሚያወጡበት ጊዜ የአካባቢውን ወጣት አሰባስባ እየከፈለች ውሃ አወጣጡን እንዲማሩና ቴክኖሎጂውን እንዲያስቀሩ በማድረግ ትልቅ ሚና ነበራት፡፡
ከጉድጓዱ የወጣው ውሃም ሞተር ተገጥሞለት እስከ አንድ ሺ ሜትር ድረስ ተለቅቆ የእርሻ ቦታን ሲያጠጣ የተመለከተው የአካባቢው ማህበረሰብ ቴክኖሎጂውን እየተጠቀመ የግብርና ሥራውን በትጋት ማቀላጠፍ ችሏል፡፡ እርሷ ወደዚህ ሥራ ከመግባቷ አስቀድሞ ማንም የአካባቢው ሰው የግብርና ሥራን እንደማይሠራ ያስታወሰችው ወይዘሮ ፈትያ፤ በአሁኑ ወቅት ግን አካባቢው ላይ የእርሻ ሥራ በስፋት ተለምዶ ወጣቱ፣ አዛውንቱና ሴቱ የግብርና ሥራን በየጓሮው እያቀላጠፈው መሆኑን አጫውታናለች፡፡
‹‹ባቢሌ አካባቢ ያለው ማህበረሰብ በስፋት የሚታወቀው በአርብቶ አደርነት ቢሆንም ለምግብነት የሚሆን ማሽላን በመጠኑ ያመርታል፡፡ ያም ቢሆን ግን አጥጋቢ ምርት አያገኝም›› የምትለው ወይዘሮ ፈትያ፤ ከሚያገኙት የማሽላ ምርት ይልቅ አገዳውን ለከብቶቻቸው ይመግቡ እንደነበረ ታስታውሳለች፡፡ በአሁኑ ወቅትም በአርብቶ አደርነት ይታወቅ የነበረውን አካባቢ ማህበረሰቡ ወደ ግብርና ሥራ እንዲገባ ፈርቀዳጅ በመሆን ትልቅ አበርክቶ አድርጋለች፡፡ በዚህም ፍጹም ደስተኛ እንደሆነችና ኢትዮጵያውያን ጠንክረን ከሠራን ከድህነት መውጣት እንደምንችል ትናገራለች፡፡
ወይዘሮ ፈትያ፤ ለሃያ ስምንት ዓመታት በሳውዲ በነበራት ቆይታ ገንዘብ አጠራቅማ ዛሬ ከራሷ አልፋ የአካባቢውን ማህበረሰብ መቀየር የሚያስችላትን የግብርና ሥራ ብትሠራም ‹‹ከረሃብተኛ አገር ከኢትዮጵያ ነው የመጣችው›› የመባሏ ነገር ግን ዛሬም ድረስ ይቆጫታል፡፡ ያም ቢሆን ታዲያ ቁጭቷን በሥራ ለመወጣት እየታተረች ሲሆን፤ የዛሬ 16 ዓመት ወደ አገሯ መጥታ የጀመረችው የግብርና ሥራም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ነው ያጫወተችን፡፡
ወይዘሮ ፈትያ በሃምሳ ስድስት ሄክታር መሬት ላይ አትክልትና ፍራፍሬ አምርታ ለገበያ የምታቀርብ ሲሆን፤ ከፍራፍሬ ምርት በዋናነት አፕል ማንጎ፣ ቫላንሺያ የተባለው አንደኛ ደረጃ ብርቱካን፣ ፓፓዬና ዘይቱን ታመርታለች፡፡ ከአትክልትም እንዲሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ያልተለመደ ባሚያ ወይም የሰውነት ግራሶ የተባለውን ምርት ጨምሮ ቲማቲምና ሽንኩርት በስፋት አምርታ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማህበረሰቡ ታቀርባለች፡፡
አምርታ ከመሸጥ ባለፈ የአካባቢው ማህበረሰብ ቴክኖሎጂውን ተጠቅሞ ውሃ ከጉድጓድ በሞተር በማውጣት በየጓሮው አትክልትና ፍራፍሬ ማምረት እንዲችልና ከብቶቹንም ውሃ ማጠጣት የሚችሉበትን ዕድል በመፍጠር ማህበራዊ ኃላፊነቷን መወጣት የቻለች ታታሪ ናት፡፡
የሥራ ዕድልን አስመልክቶ በቋሚነት 70 ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለች ሲሆን፤ በጊዜያዊነት ደግሞ 150 የሚደርሱ ዜጎች በልተው ለማደራቸው ምክንያት ሆናለች፡፡ በቁጥር ከተቀመጠው የሥራ ዕድል በላይ በአካባቢው ለሚገኙ ሰዎች የግብርና ሥራን ማስተማር የቻለቸው ወይዘሮ ፈትያ፤ ከግብርናው ባሻገር ሴቶች ምርቱን ተረክበው ወደ ገበያ እንዲያወጡ በማድረግ በርካታ ሴቶችን ወደ ንግድ ማስገባት ችላለች።
ከግብርና ሥራ በተጨማሪ ምርትን ወደ ገበያ አውጥቶ በመሸጥ መጠቀም እንደሚቻል ለባቢሌ ወረዳ ያስተማረችው ወይዘሮ ፈትያ፤ በቀጣይም ግብርናውን አጠናክራ በመቀጠል ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ምርቶቿን እሴት ጨምራ በፋብሪካ የማቀነባበር ዕቅድ አላት፡፡ እኛም ዕቅዷ እንዲሳካ እየተመኘን የነበረንን ቆይታ አበቃን፡፡
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 27/2015