«ፍርሃት የእኛ ጌታ!»

 ፈራን! «ለምን ፈራችሁ አትበሉን»፤

የምናከብረው የሥነ ጽሑፍ አርአያችንና የመምህራችን የሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን «እሳት ወይ አበባ» የግጥም መድበል (1966 ዓ.ም) ለእኔና ለዘመነ አቻዎቼ ብቻ ሳይሆን በተከታዮቻችንም ዘንድ ቢሆን በርካታ የእኛነታችንን ጉዳዮች ለመፈተሽ ሲፈለግ ተደጋግሞ ይጠቀሳል፡፡ እኔውም ብሆን በዚህ አንጋፋ ጋዜጣ ላይ በተወዳጀሁበት በሦስት ዐሠርት ተኩል ዓመታት ውስጥ ባስነበብኳቸው በሺህ በሚቆጠሩ አርቲክሎቼ ውስጥ ከዚህቺው ዕድሜ ጠገብ ተጠቃሽ መድበል ላይ ምን ያህል ጊዜያት ለበጎነት የሚጠቀሱ የሃሳብ ፍሞችን እንደ ጫርኩና አእምሮ የሚያነቁና በአበባ የሚመሰሉ አዳዲስ «እምቡጥ» ምልከታዎችን እንዳጋራሁ በርግጡ የቁጥሩን ልክ አላውቀውም፡፡

በተለይም ሎሬቱ ታትሞ ባላገኘነው አንድ ሥራው ውስጥ ረቂቅ የፍርሃት ባህርይን የገለጸበት ቋንቋውም ሆነ ምልከታው ለወቅታዊ እህህታችን መገለጫነት ብቻ ሳይሆን ዘመንንና የጊዜን ውቂያኖስ እያቆራረጠ በትውልዶች ቅብብሎሽ ውስጥም ሳይቀር ስሜትን እየበረበረ «ፍርሃትን» ገሃድ የመግለጥ አቅሙ ከፍ ያለ አንድ ግጥም እናስታውሳለን፡፡ ግጥሙ ትናንት የተነበበ፣ ዛሬ የተጠቀሰ ብቻ ሳይሆን ለነገውም ቢሆን ሰዋዊ ስንቃችን እንደሆነ የሚቀጥል ዓይነት ስለሆነ ዕድሜው እንደ ማቱሳላ የረዘመ ነው፡፡ ይህ «ፈራን» የሚለው ግጥሙ እየሞቅናት ባለነው የዛሬዋ ጀንበር የወረሰንን ወቅታዊ የፍርሃት ስሜት በገሃድ የሚገልጽ ስለመሰለን እነሆ ሙሉውን የግጥሙን ይዘት ከእነ ወዙና ላህይው እንዲህ እናስታውሳለን፡፡

«ፈራን» – ፍቅርን ፈራን፣መቀራረብ ፈራን፣

እንዳልተላመድን እንዳልተዋለድን፣

ፈርተን መዋደድን፤ ጉርብትናን ናድን፣

እኛነትን ትተን እኔነትን ለመድን፡፡

«ፈራን» – ፍቅርን ፈራን፤ ጥላቻን ሠራን፣ ብቸኝነትን ጠራን፣

በጋራ ቤታችን አጥር ድንበር ሠራን፡፡

«ናቅን» – በልዩነት ደምቀን ይበጅን ይመስል በእልህ ተናነቅን፡፡

«ናቅን» – መቻቻልን ናቅን ለፀብ ተሟሟቅን፣

ለአመጽ በርትተን ለሰላም ወደቅን፣

ሀገር ስትቃጠል ከዳር ሆነን ሞቅን፡፡

«ጠላን» – መወያየት ጠላን፤ መነጋገር ጠላን፣

መደማመጥ ጠፍቶ፤ መነቋቆር ሰፍቶ፣ መናናቅ በርክቶ፤

መመካከርን ስንረሳ፤ መከባበርን ስንረሳ፣

እጃችን በወንድማችን ላይ ዱላ አነሳ፤

የቃየል ምቀኝነት በልባችን ነግሳ፡፡

«ራቅን» – የተስፋችን ሻማ ተለኩሶ፣

ወጋገኑ መታየት ሲጀምር፤ አድማሱን ጥሶ፣

እኛ ግን ራቅን ብሩህ ነገን ናቅን፣

ከዛሬ ተጣብቀን ትናንትን ናፈቅን፡፡

ሎሬቱ ይህን የግጥም አዝመራ በምን ስሜት ውስጥ ሆኖ እንዳዘመረውና መቼ እንደጻፈው እቅጩን ለመንገር ይህ አምደኛ መረጃ የለውም፡፡ ጥቅል አስተያየት ለመስጠት ካስፈለገ ግን ደራሲው በቃላት አሳክቶ ያደረስን ይህ «ውብ ግጥም» ትናንትን ብቻ ሳይሆን በዓመታት ላይ እየተረማመደ ነገንና ተነገወዲያንም የመግለጽ አቅሙ እጅግ ከፍ ያለ መሆኑን ቀደም ሲል ስለገለጽን የዓመት ዕድሜ ተገድቦለትና ተወስኖለት በዚህ ዓመት ተጻፈ ባይባል ይመረጣል፡፡ ለምን ቢሉ ይህ ከነፍስ የመነጨ «እሪታና ጩኸት» ሰዎች በምድር ላይ እስከኖሩ ድረስ አብሮ የሚከርም ስለሆነ ነው፡፡ «በዚህ ዘመን ለዚህ ጉዳይ ተጻፈ» ብሎ መደምደሙ እጅግም ተመራጭ የማይሆነውም ስለዚሁ ምክንያት ነው፡፡

ስለዚህ «ብዙ ወጀቦች ስለከበቡን» ለምን ፈራችሁ ተብለን ከቶውንም ልንጠየቅ ተገቢም አግባብም አይደለም፡፡ በሀገሬ ምድር የማያስፈራው «ፍርሃትን ራሱን እንዳንፈራ ሆነን መፈጠራችን» ሳይሆን አይቀርም፡፡ «ፍርሃት እንደምን የእኛ ጌታ ሊሆን ቻለ?» ተብዬ ብሞገት ደግሜ የምከራከረው ከዚያው ከሎሬቱ «የእሳት ወይ አበባ» የግጥም መድበል ኩልል ያለና «ማነው…‹ምንትስ› » በሚል ርእስ ከተለየው የጥበብ ምንጭ በመጥቀስ ይሆናል፡፡

«ያው መቼም እኔም እንደ ሰው፣

አንዳንዴ፣ አንዳንዴ ብቻ ሕሊናዬን እውነት ሲያምረው፣

ሰብሰብ ብዬ የማስበው፣

ተጨብጬ የማብላላው፣

ያው መቼም እኔም እንደ ሰው፣

የሐቅ ርሃብ ነፍሴን ሲያከው፣

ልቤ ልቤን ሲሞግተው፣

እውነትስ ምንትስ ማነው? እያልኩ እጠይቃለሁ።

እስቲ እንጠያየቅ እላለሁ፡፡

ዳኝነት የእግዜር ነውና እስቲ እንፋረድ እላለሁ።»

ቀጥለን የምንዘልቀው ወደ መሟገቱ ይሆናል። መሟገቻ አንድ፡- «ሀገራዊ ችግሮቻችንን በውይይት፣ በመመካከርና በስክነት ስለምን መፍታት ተሳነን?» ክርክሩ በአደባባይና በይፋ እንዲካሄድ ሳይሆን እያንዳንዱ ዜጋ በመከራከሪያ ጭብጡ ላይ

 በሩን ዘግቶ ከልቦናው ጋር «ቢሟገትበት» የጸሐፊው ምርጫ ነው፡፡

መሟገቻውን እናብራራው፡- መቼም የግጭትና የጦርነት ትርፉ ማሸነፍና መሸነፍ ሳይሆን «መሸናነፍ» መሆኑን የራሳችንም ሆኑ የዓለም የታሪክ መዛግብት እውነታውን ፍንትው አድርገው ያሳዩናል፡፡ በትምህርት ሥርዓታችን ውስጥ የዓለም ታሪክ፣ የአፍሪካ ታሪክና የኢትዮጵያ ታሪክ እያልን «የኮርስ ስም ሰጥተን» የምንሸመድዳቸው የታላቋ ምድራችን የትናንት ዜና መዋዕሎች በሙሉ የሚያረጋግጡልን በጀግንነት የሚያስጨበጭበው የሰላም ሰው ሆኖ መከራን መሻገር እንጂ «የደም መስዋዕትነት አስከፍሎ»ማሸነፍ ትርፉ ማቅ ለብሶ በጸጸት መቀጣት እንደሆነ ነው፡፡

እንኳንስ በደካማ የሰው ልጆች ብኩን ዓለም ቀርቶ በሰማይ ሠራዊት መካከል እንኳን ጠብና ግጭት እንደሚካሄድ የክርስቲያኖች ቅዱስ መጽሐፍ በሚገባ ይተርክልናል፡፡ በሰው ልጆች መካከልም ጠብና ክርክር መነሳቱ ከቶውንም የሚቀር አይደለም። በትናንቷም ሆነ በዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ምን ያህል ጊዜ እርስ በርስ ግጭትና መጠፋፋት እንደተደረገ ብንተርከው ስለሚሰለች አስታውሶ ብቻ ማለፉ ይሻላል፡፡ የዛሬው ሀገራዊ ችግራችን በርዶ ስለምን ሰላምን መምረጥ ተሳነን? ገድሎ ባለድል ከመሆን ለሰላም ተሸንፎ መዘመሩስ አይሻልም? አንዱ የፍርሃታችን ምንጭ ከሰላም ጋር መፈራራታችን ነው፡፡ ስለዚህ «ፈራን!» ብለን «በፍርሃታችን ብንርድ ይፈረድብናል?»

መሟገቻ ሁለት፡- ሙስና ይሉት ክፉ የሕዝብና የሀገር ደዌ በአደባባይ ነግሶ ዱታ ነኝ እያለ ሕዝብ ሲያስለቅስ ስለምን ይህንን ክፉ ነቀርሳ የሚነቅል «ዋግምት» ሊጠፋ ቻለ? እየተፈራራንና «ካብ ለካብ እየተያየን» እስከ መቼ እንዘልቀዋለን? ሀገራችንን ማዲያት ያለበሰው ይህ ክፉ ሥራይ እስከ መቼ እንደ መዥገር ተጣብቆብን እየመጠጠን ይኖራል፡፡ ስለዚህም «ሀገር እንደ ሀገር፤ እኛም ዜጎች እንደ ዜጋ» የመኖር ዋስትናችን ስለሚያጠራጥረን ፈርተናል፡፡ ስለምን ፈራችሁ የሚለን ራሱ ፈሪ ነው፡፡

መሟገቻ ሦስት፡- ላባችንን ጠብ አድርገን እንዳቅማችን የዕለት ጉሮሯችንን የምንደፍንበት «የደም ወዛችን – ደሞዛችን» እንኳን ኑሯችንን አሸንፎ በልተን ልናድር ቀርቶ እስከነአካቴው ጭንቀት ላይ ወድቀን «ወየው ለነገ!» እያልን በመቃተት ብቻ ደማችን ቀጥኖ እስትንፋሳችን ልትወጣ ጫፍ ላይ ደርሳለች፡፡ በጡንቻችን የምንፋለምበትን ወላንሶ እርግፍ አድርገን በመተው የግብርና ማሳችን ላይ ጉልበታችንን በማዋል ለማዕዳችን ሙላት መጨነቅ ሲገባን ስለምን መጨካከንን መርጠን ጦር እንደምንወራወር አልገባንም፡፡

የገባቸው ካሉ ያስረዱን፤ ወይንም የነገውን ተስፋችንን በእጃቸው ላይ ያኖርነው «እንደራሴዎቻችን» እንደራሳቸው ሳይሆን እንደራሳችን ሆነው እውነቱን ይግለጹልን፡፡ ዛሬ ያላረሰ ገበሬ ነገ ምኑን አቅርቦልን ነፍሳችንንና ነፍሱን ይታደጋል? ስለዚህም ነገን ስናስብ ፈርተናል፤ ለምን ፈራችሁ ተብለን ብንጠየቅ መልስ የለንም። መልስ የማንሰጠው መልሱ ጠፍቶን ሳይሆን «ጌታው ፍርሃት» እያንዘፈዘፈን ቃላት እንዳናወጣ ስለሚያንዘረዝረን ብቻ ነው፡፡

መሟገቻ አራት፡- ሳንወድ የተገኘንበትን፣ ሳንመርጥ የተወለድንበት ምንጫችንን ብቻ «ለእኔ ብቻ» በሚል አጥር ከልለን የሌሎችን «ምንጭ» እያንቦጫረቅን ማደፍረሱ ጦሱ የት አድርሶ የት እንደሚጥለን ስናስብ እንደነግጣለን፣ «ወዬው ለነጋችን!» እያልንም እንጨነቃለን፡፡ እስከ ዛሬ የተጓዝንበትን ኮረኮንች ጎዳና ምርጫን አድርገን ወዳሰብነው መዳረሻ ስለመቃረባችንም ጥርጥር ገብቶናል፡፡ ስለዚህም «ፈርተናል፤ ምን ያስፈራችኋል!» ብንባልም ተብለን ብንገሰጽም የመስሚያ ጆሯችን ስለተደፈነ ማንንም አንሰማም፡፡

መሟገቻ አምስት፡- እንደ ፈረሰኛ ጎርፍ ድንገት ደርሶብን ላጥለቀለቀን ዘመነ ሉላዊነት ቀድመን የሥነ ልቦና ዝግጅት በማድረግ «ታጥቀን ስላልቆየነው» እነሆ እንደ ሌባ ከተፍ ብሎ እጅ በማሰጠት ምርኮኛ አድርጎናል፡፡ «እህል ውሃችን፣ የጠብና የመነታረኪያ አጀንዳችን፣ የመፋዘዣ ማደንዘዣ፣ የልጆቻችን ማኮላሻ፣ የግንኙነታችን ፀር፣ የንጽህናችን ማርከሻ ወዘተ.» እየሆነ ያለውን ማኅበራዊ ሚዲያ ያለመፍራት እንደምን ይቻላል?» እንድንካድመው ከማረከን እኮ ቆይቷል፡፡ ስለዚህም ነጋችንን ስናልም ከፊታችን ያለው ጨለማ ስለሚያስደነግጠን ፈርተናል – ለምን ፈራችሁ ተብለን ልንወቀስም ሆነ ልንከሰስ አይገባም።

መሟገቻ ስድስት፡- የሃይማኖት ክብር ሚዛኑ ተዛብቶ፣ የአባቶች ምክር ሰሚ ጆሮ አጥቶ፣ የአረጋዊነት ሽበት አቅሙ ዝሎ ስንመለከት «ሽማግሌ ይገላግላል፤ የተጠቃ አቤት ይላል» የሚለው ጥንታዊ ብሂል ዋጋ እንዳጣ ገብቶን ፈርተናል፡፡ ስለምን ፈራችሁ ባንባል ደስ ይለናል፡፡

«ሽምግልናን ከኡኡታ በፊት» ባለማስቀደማችን «ነገራችን ሁሉ የእምቧይ ካብ፣ የእምቧይ ካብ» ሲሆን እያስተዋልን እንኳን ወደ ቀልባችን ለመመለስ ያለመጨከናችን ለተጠናወተን አዚም ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ ስለዚህም አስገባሪያችን «ፍርሃት የእኛ ጌታ» እጅ ተወርች ጠፍሮ ወህኒው ውስጥ ስለከተተን ኡኡታችንም ሆነ ተማጽኗችንን ሰምቶ የሚታደገን የክፉ ቀን አለሁ ባይ አላገኘንም፡፡ ስለዚህ ፈራን፤ ፈርተንም ተሸነፍን፡፡

መሟገቻ ሰባት፡- የከበቡን ጠላቶቻችን እርስ በእርሳችን «ጥለን ስንወድቅ» እያዩ ደስ በመሰኘት አታሞ በመደለቅ ይፍነከነካሉ፡፡ ሰይፍ በመሞሻለቅ ተሳዳጅና አሳዳጅ ሆነን አንዳችን አንዳችንን ስናባርር እነዚያው ወደረኞቻችን እየተሳለቁ ያሾፉብናል፡፡ ክብራችን ወድቆ፣ አንድነታችን ላልቶ ሲያስተውሉም ገፍትረው ሊጥሉን ቀን ከሌት ያደባሉ፡፡ ስለዚህ ፈርተናል – «ለምን ፈራችሁ» ተብለን ባንገሰጽ መልካም ነው፡፡ እንደውም ቁስላችን ላይ ጨው የመነስነስ ያህል ስለሚቆጠቁጠን ይከፋናል፡፡

እህህታችን ስለማያልቅ ለማጠቃለያ እንዲረዳን ከሎሬታችን የግጥም ማዕድ የመጨረሻውን የስንኞች ጉርሻ እንዋስ፡፡

«ይቅር ብቻ አንናገርም፤ ለውይይት አልታደልንም፣

እንዲያው ዝም፣ እንዲያው ዝም…ዝም፡፡

አበባ አንሆን ወይ እሳት፣ ተጠምደን በቅዠት ቅጣት፣

ሰመመን ባጫረው መዓት፤ እድሜያችንን እንዳማጥናት፣

አሳት አንሆን ወይ አበባ፤ በሐቅ እንቅ ስንባባ፣

ባከነች እኛነታችን እየቃተትን ስናነባ፡፡

ሳንፈጠር በሞትንባት፤ ሳናብብ በረገፍንባት፣

ሳንጠና ባረጀንባት፤

አበባ ወይንም እሳት መሆኑን ብቻ አጣንባት፡፡»

አይ ኢትዮጵያ! ሰላም ለሕዝባችን ለዜጎችም በጎ ፈቃድ፡፡

 (በጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)

gechoseni@gmail.com

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 27/2015

Recommended For You