ለሠላም ተገቢውን ዋጋ በመስጠት ከግጭት እንውጣ!

ሠላም ለአንድ ማኅበረሰብም ሆነ ሀገር ከሚኖረው ሁለንተናዊ አስተዋጽኦ አንጻር ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ ማኅበራዊ እሴት ነው። ስለ ሠላም የሚዘረጉ እጆችንም ሆነ፣ ለሠላም የተገዙ አስተሳሰቦችን ለመቀበልና ለመተግበር ፈቃደኝነት ማጣትም ሊያስከፍል የሚችለው ዋጋ ከፍያለ ነው። ከዚህም የተነሳም ለሠላም ተገዥ መሆን ራስን ሊመጣ ካለ ጥፋት መታደግ ነው ። ይህ እውነት ለእኛ ለኢትዮጵያውያን እንደ አዲስ የሚነገር አይደለም። በየዘመኑ ብዙ ዋጋ ላስከፈሉን ግጭቶችና ጦርነቶች ተዳርገን ብዙ ዋጋ ከፍለናልና።

ሠላም በትውልዶች መካከል ዘመን ላስቆጠረው ትልቅ ሀገርና ታላቅ ሕዝብ የመሆን መሻታችን መሠረት መሆኑን መረዳት ተስኖን፣ ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶቻችን መሠረት ያደረጉትን መከባበርና ይቅር መባባልን ዋጋ ሳንሰጥ በደነደነ ልብ ሀገርን አኬልዳማ ከማድረግ መታደግ ሳንችልም ቀርተናል።

ከዚህ የተነሳም የታሪካችን ሰፊው ትርክት የግጭት እና የጦርነት ሆኗል። መዘዙም በዓለም በድህነታቸውና በኋላቀርነታቸው ከሚጠቀሱ ሀገራት መካከል ተጠቃሽ እንድንሆን አድርጎናል። ለብዙዎች የሚተርፍ ጸጋ ተሸክመን በሠላም እጦት ወደሚጨበጥ ሀብት መለወጥ ባለመቻላችን ተመጽዋች ሆነን ኖረናል። እንደ ትውልድም በራሳችን ታሪክ ቀና ብለን ለመሄድ የምንችልባቸው ብዙ ዕድሎችና ድሎች እያሉን በእዚህ ለመጠቀም እንዳንችል አድርጎናል።

ይህ ለሠላም ግንባታ የሚሆኑ ብዙ መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊ እና ባህላዊ እሴቶች ባለቤት ሆነን፣ እንደ ትውልድ ለእነዚህ እሴቶቻችን ተገቢውን ከበሬታ በማጣታችን እያጋጠመን ያለው የሠላም እጦት፣ ዛሬም ብዙ ዋጋ እያስከፈለን ስለመሆኑ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን እያጋጠመን ያለው ፈተና፣ ፈተናው እየፈጠረብን ያለው ቁዘማ ተጨባጭ ማሳያ ነው።

ከትናንት ያልተገቡ ማኅበራዊ ትርክቶቻችን እየተቀዱ፣ ዛሬን እያበላሹብን ያሉት ልብ አደንዳኝ አስተሳሰቦችን አሁን ላይ ቆመን ማረም ካልቻልን፣ እንደ ሀገር አሁን ላይ ካለንበት ድህነትና ኋላ ቀርነት ሊያወጡን የሚችሉትን ዕድሎች በአግባቡ ተጠቅመን ወደ ምናስበው ዕድገትና ብልጽግና ልናመራ አንችልም።

የትኛውም አስተሳሰብ (ሀሳብ) በተቃርኖ የተሞላ፣ ይህም ተፈጥሯዊ መገለጫ መሆኑን በመገንዘብ የአስተሳሰብ ልዩነቶችን እንደ ጸጋ መቀበል የሚችል የአእምሮ ውቅር መፍጠር፣ ይህም የትውልዶች የአስተሳሰብ መሠረት የሚሆንበትን መንገድ መፍጠርና በመንገዱ በመጓዝ በተጨባጭ ተሞክሮ የታጀበ የአዲስ የወንድማማችነትና እህትማማችነት ትርክት ልንፈጥር ይገባል።

በተለይም አሁን እንደ ሀገር ድህነትን ታሪክ ለማድረግ ካለን ሀገራዊ መሻት፣ መሻቱ ከፈጠረው ሕዝባዊ ንቅናቄ አንጻር፣ ስለ ሠላም ያለንን ግንዛቤ ከፍ በማድረግ እንደ ሕዝብ ለሠላም መክፈል ያለብንን መስዋዕትነት በቁርጠኝነት በመክፈል ከመጣንበት የግጭት አዙሪት ልንወጣ የሚያስችለንን ሀገራዊ እውነታ ፣ ለዚህ የሚሆን ዝግጁነትና ቁርጠኝነት መፍጠር ይጠበቅብናል!፡፡

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 27/2015

Recommended For You