አትሌቲክሱ«አንዱን ጥሎ፣ አንዱን አንጠልጥሎ» እንዳይሆን

ኢትዮጵያ ከስያሜዋ በስተጀርባ በወርቅ የደመቀ የአኩሪ ታሪክ ባለቤት ናት፡፡ ይህች ድንቅ ሀገር ዘመናትን የተሻገረው የጀግንነት ገድሏ ከበርካታ ጎራ ያሰልፋታል፡፡ በቅኝ ያለመገዛቷ እውነት ከራሷ የማንነት አውድ አሻግሮ ለመላው አፍሪካ የማይፈዝ የነፃነት ዐሻራውን አሳርፏል፡፡

ሀገራችን ከዚህ የማይፋቅ ታሪኳ ባሻገር ስሟን በክብር ከፍ የሚያደርግ ሌላም ታሪክ አላት፡፡ ዓመታትን ያለድካም የዘለቀው የአትሌቲክሳችን ስፖርት፡፡ ይህን የኢትየጵያውያንን ታሪክ ደጋግመን ስናወሳ አይረሴው እውነት ዓመታትን የኋሊት ይመልሰናል፡፡ ወደ ፈረንጆቹ ወርሀ መስከረም 1960፡፡

በዚህ ዘመን አፍሪካ ከቅኝ ግዛት ዕንቅልፏ በወጉ አልነቃችም፡፡ ጥቂት የሚባሉት ሀገራትም ካረፈባቸው የምዕራባውያን የጡጫ ሕመም ያላገገሙበት ጊዜ ነበር፡፡ ይህ ስሜት ግን በመላ ኢትዮጵያውያን ውስጠት ፈጽሞ አይታወቅም፡፡ እንዲህ ይሆን ዘንድ ታላቅ መስዋዕትነት ተከፍሏልና በነፃዪቱ ሀገር የነፃነት አየር በነፃነት እየነፈሰ ነው፡፡

በሌላው ገጽ ደግሞ በኢትዮጵያውያኑ ዘንድ ሌላው አዲስ ምዕራፍ ሊከወን መንገድ ይዟል፡፡ ነፃነትን በመንጠቅ ድንበር ጥሰው፣ ባህር ተሻግረው በመጡት ባዕዳን ምድር፡፡ ቅኝ ሊያስገዙ፣ አቅም ሊነፍጉ በሞከሩት ጣሊያኖች መሬት ሮም ከተማ ፡፡

በዚህ ቀን ፀሐይ ከመጥለቋ አስቀድሞ አንድ ታላቅ ፍልሚያ ሊካሄድ ጊዜው ደርሷል፡፡ ከመላው ዓለም የተውጣጡ ዝነኛ የማራቶን ሯጮች ውድድሩን ሊጀምሩ በመሟሟቅ ላይ ናቸው፡፡ በሁሉም ገጽታ የአሸናፊነት ስሜት እየተነበበ ነው፡፡ ከሰዓታት በኋላ ምን እንደሚፈጠር ማንም የሚያውቅ የለም፡፡

በወቅቱ በነበሩት ውድድሮች ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፎች ሜዳሊያ ይሉትን አልወሰደችም፡፡ መላው አፍሪካም እንደዚያው፡፡ ነገሩ ተስፋ የሚያስቆርጥ ቢመስልም ውድድሩ ገና አልተቋጨም፡፡ በዕለቱ ለተወዳዳሪዎች የሚሆኑ ምቹ ጫማዎች ታድለው አልቀዋል፡፡ ሁሉም ለእግሩ የሚመቸውን መጫሚያ አጥልቆ እየተቁነጠነጠ ነው፡፡

ከሁሉም ተወዳዳሪዎች መሀል ይህ ያልተሟላለት ኢትዮጵያዊው አትሌት አበበ ቢቂላ ነገሩ ያስገረመው አይመስልም፡፡ የአዲዳስ ኩባንያው ተወካይ ለእሱ እግር የሚገጥም ጫማ አለመኖሩን በግልፅ አርድቶታል፡፡ ይህ ቃል ግን ለአበበ ትርጉም እየሰጠው አይደለም፡፡ ፈጽሞ ተስፋ አልቆረጠም፡፡ ወሳኙን ፍልሚያ በባዶ እግሩ ሊያካሂድ ከራሱ ጋር መክሮ፣ ዘክሮ ከውሳኔ ደርሷል፡፡

ይህን እውነት ለሚሰሙት ሁሉ የማይዋጥ ሀቅ ሊሆን ይችላል፡፡ ኢትዮጵያዊው ግን ከራሱ ተማምሎ ጨርሷል፡፡ ምናልባትም ለእሱ በባዶ እግር መፋለም አዲስ አይደለም።ይህ ታሪክ የአያት ቅድመ አያቶቹ ነው፡፡ ጠላትን ድል የነሱት የወታደር ጫማ አጥልቀው አልነበረም። ለሀገራቸው ክብር በዱር በገደሉ እሾህ ጋሬጣው አድምቷቸዋል፡፡

እነሆ! አሁንም ጊዜው ራሱን ደግሟል፡፡ በወራሪዎቹ ምድር የባዶ እግር ታሪክ ዕውን ሊሆን ደቂቃዎች እየተቆጠሩ ነው፡፡ አሁን አበበ እግሮቻቸው በምቹ ጫማዎች ከረገጡ ተወዳዳሪዎች ጎን በቁርጠኝነት ተሰልፏል፡፡ በመወደሪያ ትራኩ ጫማ አልባ እግሮች ለሩጫ እንደተዘጋጁ ናቸው። ሁሉም ይህን እያስተዋለ በንቀት ፈገግታ ተውጧል። በድንገት ታላቁ የማራቶን ውድድር መጀመሩን የሚያበስረው ሽጉጥ ተተኮሰ፡፡

በርካታ ጥንድ እግሮች በፍጥነት ተፈተለኩ፡፡ በእኩል የሚራመዱ ቅልጥሞች፣ ጥቁርና ነጭ ታፋዎች፣ መንትያ መሳይ ጫማዎች ጎልተው ተስተዋሉ፡፡ ከሁሉም ተነጥለው የሚታዩት የአበበ ቢቂላ ባዶ እግሮች ፈጽሞ አልሰነፉም፡፡ ፈጥኖ እንደሚሰግር ፈረስ ወደፊት ነጎዱ፣ ገሰገሱ፡፡

አበበ የሚፋለመው ከራሱ ጋር ሆኗል፡፡ ስለ ባለጫማዎቹ ሯጮች ፈጽሞ የሚያስብ አይመስልም፡፡ አሁንም ትንፋሹን ሰብስቦ፣ ፊቱን አቀጭሞ እየጋለበ ነው፡፡ ከበስተጀርባው በርካታ ትከሻዎች አጅበውታል፡፡ ሁሉም አረንጓዴ ቢጫ ቀይ የለበሰውን ጥቁር አንበሳ በፍርሀት እየከተሉት ነው። የዓለም ዓይና ጆሮ በእሱ ላይ አተኩሯል፡፡

አበበ በማይታመን ፍጥነት በርካቶችን ከኋላው አስከትሎ የአርባ ሁለት ኪሎሜትሩን ውድድር ሊያጠናቅቅ ተቃርቧል፡፡ ሽንፈት፣ ተስፋ መቁረጥና ድካም በአይታመኔ አሸናፊነት እንደታጀቡ የባዶ እግር ዐሻራ ከመጨረሻው ትራክ ደርሷል፡፡ ጭብጨባው እንደጋለ ነው፡፡ ተመልካቹና ጋዜጠኞች አብዝተው ይጮሀሉ፡፡

የኋላ ኋላ ምሽቱ በድል ብርሃን ታጀበ፡፡ ባለ ባዶ እግሩ ኢትዮጵያዊ ጀግና አበበ ቢቂላ ዓለምን ጉድ አሰብሎ እጅን በአፍ አስጫነ፡፡ የመጨረሻዋ ክር በፈርጣማ እጆች ስትበጠስ ኢትዮጵያ በሮም አደባባይ ዳግም አሸነፈች። አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ ከፍ ብሎ ተውለበለበ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር በጣሊያኖች አጀብ ጎልቶ ተሰማ፣ ደማቁ የድል ብስራት በመላው ዓለም አስተጋባ፡፡

እነሆ በዚህ የተጀመረው አስደናቂ ገድል እርምጃውን አልገታም፡፡ ከዓመታት በኋላ በሀገረ -ቶኪዮና ሜክሲኮ አበበ ዳግም ድልና በማሞ ወልዴ የማራቶኑ ድል ተደጋግሟል፡፡ ጥንካሬና ድል የኢትዮጵያውያን ስያሜ እስኪመስል ማራቶን ዘመናትን ተሻግሮ በእነ ገዛኸኝ አበራም ኦሊምፒክ ላይ ከፍ ብሎ ነገሰ፡፡

ይህ የአትሌቲክስ ድል በማራቶን ብቻ አልተገታም። የኢትዮጵያውያን ብቃት የሚታወቁበት የረጅም ርቀት 5ሺ እና 10 ሺህ ሜትር ውድድር ተጠናክሮ ቀጠለ፡፡ በዚህ ዘርፍ ኢትዮጵያ ገናና ሆና መታየት ያዘች፡፡ በአንጻሩ ኬንያ ደግሞ በመካከለኛና ረጅም ርቀት ውድድር እውቅናውን አገኘች፡፡ የሁለቱ ሀገራት የአንገት ለአንገት ትንቅንቅ በመላው ዓለም ትኩረትን ሳበ፡፡

የኬንያና ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተለይተው በሚታወቁባቸው ውድድሮች አሸናፊነትን መነጣጠቅ ልምዳቸው ሆነ፡፡ በ2019 የዶሀ የዓለም ሻምፒዮና የ3ሺ ሜትር መሰናክል ኬንያዊው ኪፕሮቶ ለሜቻ ግርማን በሽርፍራፊ ማይክሮ ሰከንዶች በልጦ አሸናፊነትን ያዘ፡፡

ለሜቻ በ3ሺ መሰናክል ለኢትዮጵያ የብር ሜዳሊያ ያስገኘ የመጀመሪያው አትሌት ነው፡፡ በተመሳሳይ በኬንያዊቷ ፌይዝ ኪፕየጎን እና በጉዳፍ ጸጋዬ የ1ሺ 500 ሜትር ውድድር አሁንም ኬንያ ብቸኛውን ወርቅ ያገኘችበትና ኢትዮጵያ የብር ሜዳሊያ የወደሰችበት አጋጣሚ ሆኖ ተመዘገበ፡፡

በ2019 በኳታር ዶሀ በነበረው የዓለም ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ሁለት ወርቅ፣ አምስት ብርና አንድ ነሐስ ማግኘት ችላለች፡፡ በ1992 ዓ.ም በባርሴሎና በተካሄደው የ10ሺ ሜትር ውድድር ደራርቱ ቱሉ ለሀገሯ ወርቅ አስገኝታለች፡፡

ኢትዮጵያ ባለፉት 18 የዓለም ሻምፒዮናዎች በማራቶን 12 ሜዳሊያዎችን ወስዳለች፡፡ በዘንድሮው ዓመት በሀንጋሪ ቡዳፔስት በተካሄደው 19ኛው የዓለም ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በሴቶች ማራቶን የወርቅና ብር ሜዳሊያን ነጥቃለች፡፡ በተመሳሳይ በወንዶች ማራቶን ውጤታማ እንደምትሆን ቢጠበቅም በልዑል ገብረሥላሴ አንድ የነሐስ ሜዳሊያ ብቻ ማግኘት ተችሏል፡፡

ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ሻምፒዮናዎች በእያንዳንዱ ውድድር የወርቅና ብር ሜዳሊያዎችን ያጠለቁት አትሌቶች ዘንድሮ ከአሸናፊነት ጥግ መድረስ አልተቻላቸውም። ምንም እንኳን ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ማሸነፍ ማለት ወርቅ ማጥለቅ ብቻ ቢመስለንም የዘንድሮው ውጤት ድሉን ስለማፍዘዙ ግን መሸፋፈን አይቻልም፡፡

ኢትዮጵያውያን ገነው በሚታወቁበት የ5 ሺህ ሜትር ፍጻሜ በሁለቱም ፆታ አሸናፊነት ሳይቀናቸው ቀርቷል፡፡ ዮሚፍ ቀጀልቻን ጨምሮ፣ ሀጎስ ገብረሕይወትና በሪሁ አረጋዊ ውድድሩን እንደተጠበቀው በድል አልፈጸሙም። ይህ ቀደምት ታሪክ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ የመካከለኛ ርቀት አትሌቶች ድል መሆ ን ጀምሯል፡፡

ይህ ክፍተት በሴቶቹም ተመሳሳይ ርቀት እየተስተዋለ መምጣቱን ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ በ3 ሺህ መሰናክል የሴቶች ፍጻሜ ዘርፌ ወንድማገኝ አራተኛ ስትሆን በትውልደ ኬንያዊቷ የባህሬን አትሌት ያቪ ዊንፍሬድ ወርቁ ሲወሰድ ኬንያውያኑ ብርና ነሐሱን ተጋርተውታል፡፡

በዘንድሮው የሀንጋሪ ውድድር የታየውን የአትሌቲክስ ክፍተት ከወዲሁ መደፈን ይገባል፡፡ እንዲህ መሆን ካልቻለ ሀገርን ከወጣችበት የክብር ከፍታ ዝቅ ሊያደርግ የሚችል መንገራገጭ እንደሚኖር ምልክቱ እየታየ ነው፡፡ የአትሌቲክሱ መንደር ራሱን ይፈትሽ፡፡ አሁንም ትኩረት፣ አስተውሎትና የጋራ ምክር ሊኖር ይገባል፡፡

እነሆ! አትሌቶቻችን ውድድሩን አጠናቀው ወደሀገር ቤት ተመልሰዋል፡፡ ዛሬም ኢትዮጵያ ስለጀግኖቿ ታላቅ ክብር ትሰጣለች፡፡ እነሱ ውስጥ ጥንካሬ ብርታትና ጀግንነቱ እንደሚቀጥል ተስፋ አለ፡፡ እንደ ኬንያ ያሉ የቅርብ ተፎካካሪዎቻችን በአዳዲስ የአጭር ርቀት ውድድሮች ጭምር ተፎካካሪ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያም በተለይም እንደ 3ሺ ሜትር መሰናክል ባሉ ርቀቶች አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ከፍታለች፡፡ ይህ ብቻውን ግን ስኬት አይደለም፡፡ የቀደመው ውጤታማነት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንጂ ቦታውን መልቀቅ የለበትም፣ የውጤት ደረጃውም ሊዥጎረጎር አይገባም፡፡ አንዱን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ የስኬት ጉዞ ጎዶሎ ይሆናልና፡፡

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 27/2015

Recommended For You