
የበጋው ወቅት አልፎ ክረምት ሲመጣ ተማሪና መደበኛ ትምህርት ይለያያሉ፡፡ በዚህ ወቅት ታዲያ ጊዜአቸውን በተለያዩ አልባሌ ስፍራ የሚያሳልፉ ተማሪዎች የመኖራቸውን ያህል ብልጦች ለመጪው ጊዜ ይዘጋጁበታል፤ ነገን ዛሬ ላይ ይሠሩበታል፡፡ አንዳንዶች የመጪውን የትምህርት ዘመን ከወዲሁ በማጥናት ሲያሳልፉ በልዩ ልዩ የመዝናኛ እና የበጎ ሥራ ተግባራት ላይ የሚያሳልፉ ተማሪዎችም በርካታ ናቸው።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የ4ኛ ዓመት የኤሌክትሪካል ምህንድስናና የኮምፒውተር ሳይንስ ተማሪ ሄርሞን ጌታቸው የክረምት ጊዜአቸውን ለበጎ ሥራ ከሰጡ ተማሪዎች አንዱ ነው፡፡ ተማሪ ሄርሞን፣ የክረምት ጊዜውን ያሳለፈው በዳግማዊ ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በቀጣዩ ዓመት የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎችን በማስጠናት እና የፈተና ጥያቄዎችን በማሠራት ነው ያሳለፈው፡፡
ከማስተማር ውጪ ያለውን ሰዓት የተለያዩ ምስክር ወረቀቶችን ለማግኘት በበይነ መረብ አማካኝነት የሚሰጡ
ትምህርቶችን በመከታተልም ያሳልፋል፡፡
ሌሎች ተማሪዎችም የክረምት ወቅቱን በእንደዚህ ዓይነት በጎ ተግባራት ላይ ቢያውሉ ተማሪዎችን ከመደገፍ በተጨማሪ ለራሳቸውም የአዕምሮ እርካታ እንዲያገኙ እና ከሰዎች ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት እንዲሰፋ ይረዳል ሲል ምክሩን ይለግሳል፡፡
በካራአሎ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12 ክፍል ተማሪው አርሴማ ንብረቱ በበኩሏ፤ የክረምት ወቅቱን በ2016 ዓ.ም የብሔራዊ ፈተና ተፈታኝ እንደመሆኔ ትምህርቶችን በመከታተል፣ የፈተና ጥያቄዎችን በመሥራት እና ቤተሰብ በመርዳት አሳልፋለሁ ስትል ገልጻለች፡፡
ተማሪ አርሴማ እንደምትለው፤ተማሪዎች በክረምት ወቅት ከትምህርት ስለሚርቁ የመዘናጋት ነገር ይኖራል፤ ስለዚህ በክረምት ጊዜ ቢያጠኑ እና የክረምት ትምህርቶችን ቢከታተሉ ለቀጣይ የትምህርት ዘመናቸው ይረዳቸዋል፡፡
በተጨማሪም ተማሪ አርሴማ እና ወደ 30 የሚጠጉ ጓደኞቿ በማህበር በመሆን የክረምት ወቅቱን በሁለት ሳምንት አንዴ መቂዶኒያ ሄደው አረጋውያንን በመንከባከብ ግዜያቸውን በበጎ ተግባር ያሳልፋሉ፡፡
የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ናትናኤል ነብዩ፤ የክረምት ወቅቱን በፕሮጀክት በመታቀፍ እግር ኳስ በመጫወት እንደሚያሳልፍ ጠቅሶ፤ የቋንቋ ክህሎቱን ለማሳደግ የቋንቋ ትምህርት እንደሚከታተልም አስረድቷል፡፡ በተጨማሪም የኮምፒውተር ሥልጠና በመውሰድ፤ ቤተሰብ በመርዳት እንደሚያሳልፍ አስረድቷል፡፡
በመካነ ኢየሱስ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ሳይኚ ረሙዲን በበኩሉ፤ የክረምቱን ወቅት ስፖርት በመሥራት እና ቤተሰብ በመርዳት አሳልፋለሁ ሲል ገልጿል፡፡
የሰባተኛ ክፍል ተማሪ እዮስያስ ነብዩ ፤ የክረምት ጊዜውን እግር ኳስ በመጫወት እና የቋንቋ ትምህርት በመማር እያሳለፍኩ ነው ሲል ተናግሯል፡፡
ሌሎች ተማሪዎች የክረምቱን ወቅት ጤናቸውን ከመጠበቅ በተጨማሪ፤ ወደፊት ትልቅ ቦታ እንዲደርሱ ስለሚረዳቸው ስፖርት በመሥራት እና ትምህርታቸው ላይ ትኩረት በማድረግ ቢያሳልፉ የተሻለ ነው ሲል መልእክቱን አስተላልፏል፡፡
የተማሪ ወላጅ የሆኑት ወይዘሮ ፀሐይ ዘርጋው ልጆች በክረምት ወቅት እቤት ሲሆኑ ጊዜያቸውን ባልባሌ ቦታ እንዳያጠፉ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎችን እንዲሠሩ እና የተለያዩ ትምህርቶችን እንዲከታተሉ ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርጉላቸው ገልጸዋል፡፡
በክረምት ወቅት ልጆች ያለምንም ሥራ እና ትምህርት ሲቀመጡ ወዳልተገባ ነገር ስለሚሄዱ የቋንቋ ትምህርቶችን እንዲወስዱ፣ ከወላጆቻቸው ጋር ጊዜ እንዲያሳልፉ እና ለቀጣይ ትምህርታቸው የሚያግዟቸውን መጽሐፍት በመግዛት ክረምቱን በንባብ እንዲያሳልፉ እና መንፈሳዊ ትምህርቶችን እንዲከታተሉ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡
ወላጆች ተማሪዎች በክረምት ወቅት እቤት ሲሆኑ እንዳይቦዝኑ የተለያዩ ትምህርቶችን እንዲማሩ ሥራም እንዲለምዱ ሥራ በማዘዝ አብረው ቢያሳልፉ፣ ቢመክሯቸው ልጆች ትልቅ ደረጃ እንዲደርሱ ይረዳቸዋል ሲሉ ከተሞክሯቸው ተነስተው ይናገራሉ፡፡
ልጆች በክረምት ወቅት እንዲያጠኑ አስፈላጊውን መጽሐፍት በመግዛት ከጓደኞቻቸው ጋር ያላቸው ወዳጅነት ጥሩ እንዲሆን እንደሚመክሯቸው እና ሌሎች ድጋፎችን እንደሚያደርጉላቸው የተማሪ ወላጅ ወይዘሮ ደስታ ፀሐይ ተናግረዋል፡፡
ልጆች ከወላጆች ጋር በተቀራረቡ ቁጥር የወላጆችን ምክር ስለሚሰሙ ወላጆች ከልጆች ጋር ጊዜ ቢያሳልፉ የተሻለ ነው፡፡ በተጨማሪም ከማብላትና ከማጠጣት ባለፈ ጥሩ ሥነምግባር እንዲኖራቸው ለማድረግ ጤናማ በሆነ መልኩ መከታተል ያስፈልጋል ይላሉ፡፡
አመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 27/2015