በሕገወጦች የተፈተነው የክልሉ የወርቅ ማዕድን

በማዕድን ሀብታቸው ከሚታወቁት ክልሎች መካከል የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ይጠቀሳል። ክልሉ በትኩረት ከሚሠራባቸው ማዕድናት መካከል የመጀመሪያዎቹ እንደ ወርቅ ያሉት የኤክስፖርት ማዕድናት ናቸው፤ እንደ ድንጋይ ከሰል ባሉት የኢንዱስትሪ ግብአት ማዕድናት ላይም በትኩረት እየሠራ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በመቶ ሺዎች ቶን የሚገመት ለኢንዱስትሪ ግብአት የሚውል የድንጋይ ከሰል በክልሉ እየተመረተ ይገኛል፡፡ የኮንስትራክሽን ግብአት ማዕድናት ልማትም ሌላው ክልሉ በስፋት የሚንቀሳቀስበት የማዕድን ልማት ዘርፍ ነው፡፡

ከክልሉ በተለይ በወርቅና የድንጋይ ከሰል ልማቱ በእጅጉ ይታወቃል፡፡ በዚህም ከክልሉ አልፎ ለሀገር ምጣኔ ሀብት አስተዋጽኦ እያደረገም ይገኛል፡፡ ክልሉ በማዕድን ሀብት በሚገባ የሚታወቅባቸውን እነዚህን የወርቅና የድንጋይ ከሰል ማዕድናትን በማልማት በኩል በስፋት እየሠራ መሆኑን የክልሉ ማዕድንና ኢነርጂ ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ገብረማርያም ሰጠኝ ይገልጻሉ፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ በክልሉ በማዕድኑ ዘርፉ ትኩረት ተደርጎ የተሠራባቸውን ዋና ዋና ተግባራትና የ2015 በጀት አመት የክልሉን የማዕድን ዘርፍ አጠቃላይ አፈጻጸምን በሚመለከት በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በገለጹበት ወቅት፤ «በማዕድን ዘርፉ የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አኳያም ለውጦች ተመዝግበዋል» የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ከሥራ ዕድል ፈጠራ እስከ መሠረተ ልማት መሟላት ድረስ በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውንም ይገልፃሉ። በተለይ በወርቅ ማዕድን ልማት ዙሪያ ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ በማድረግ በኩል የተገኘው ስኬት ተጠቃሽ ስለመሆኑም በምሳሌነት ይጠቅሳሉ፡፡

«ወርቅ እንደ ሀገር ትልቅ አቅም እየፈጠረ የሚገኝ ነው» ሲባል ወርቅ አምራች ክልሎች ለብሔራዊ ባንክ ምን ያህል ወርቅ አስገብተው የውጭ ምንዛሬ እያስገኙ ነው የሚለው ይታያል የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ ከዚህ ሀገራዊ ፋይዳው አኳያም የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልልም በዘርፉ የራሱን ዐሻራ እያኖረ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

የማዕድን ዘርፉ /የወርቅ ልማቱ/ በሕገወጦችና በሰላም እጦት እየተፈተነ ስለመሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ዋና ዳይሬክተሩም በክልሉ በወርቅ ልማት ላይ ሕገወጥነት መንሰራፋቱን ይጠቅሳሉ፡፡ ችግሩ በአመታዊ የወርቅ ምርት አቅርቦት እቅድ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳረፈ መሆኑን ይገልጸሉ፡፡

ክልሉ እስከዛሬ ለብሔራዊ ባንክ ከሚያቀርበው የወርቅ ምርት አኳያ የዘንድሮው አፈጻጸም በተለያዩ ምክንያቶች እጅግ ያነሰ መሆኑን ጠቅሰው፣ ቀደም ባሉት ጊዜያት ግን ከአካባቢው በተለይ በ2003 እና 2004 ዓ.ም/ ክልሉ ባልተመሠረተበት ወቅት/ የታየው አፈጻጸም እስከ 800 ኪሎግራም የሚደርስ እንደነበርና ይህም የተሻለ አፈጻጸም መሆኑን ያስታወሳሉ፡፡ በወርቅ ላይ በተፈጠሩ ሕገወጥ ድርጊቶችና በሌሎች ችግሮች ሳቢያ ዘንድሮ የሚፈለገውን የወርቅ መጠን ለብሔራዊ ባንክ ማቅረብ እንዳልተቻለ ይገልፃሉ። ከእቅድ አፈፃፀም አንፃር ሲመዘንም የእቅድ ግማሽ ያህሉ እንኳን መፈፀም እንዳልተቻለም ጠቁመዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ የክልሉ እቅድ፣ በ2015 በጀት አመት ለብሔራዊ ባንክ 450 ኪሎ ግራም ወርቅ ማቅረብ ነበር፤ የቀረበው ግን 67 ኪሎ ግራም ብቻ ነው፡፡ ይህ ማለት በመቶኛ ሲሰላ 14ነጥብ 8 በመቶ ብቻ ነው። ለጉድለቱ ምክንያቶቹ በርካታ ሲሆኑ፤ ከእነዚህም ውስጥ የጸጥታ ችግር፤ የሕገወጥነት መስፋፋትና የመሠረተ ልማት ችግሮች ይጠቀሳሉ፡፡

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፤ በክልሉ ካሉት ስድስት ዞኖች ወርቅ የሚመረተው በምዕራብ ኦሞ ዞን እና ቤሮ ወረዳ ብቻ ነው፡፡ በእነዚህ ወረዳዎችና ዞኖች አካባቢ ደግሞ ተደጋጋሚ የጸጥታ ችግሮች ያጋጥማሉ። አካባቢዎቹ ከደቡብ ሱዳንና ከጋምቤላ ጋር የሚዋሰኑ በመሆናቸው ችግሩ ሰፋ ይላል፡፡ በአርብቶ አደሩ መካከል ግጭት መከሰቱም ሌላው ፈተና ነው፡፡

የወርቅ ምርቱ ለብሔራዊ ባንክ እንዳይደርስ ያደረገው በማኅበር ተደራጅተው በማምረትና በግብይት ላይ የሚሠሩ አካላት በትክክል ወደ ብሔራዊ ባንክ አለማምጣቸው መሆኑን ጠቅሰው፣ እነዚህ አካላት ከብሔራዊ ባንክ ይልቅ ምርጫቸው በሕገ ወጥ መንገድ ዝውውር ማድረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይህ ችግር የወርቅ እቅድ የሚፈለገውን ውጤት እንዳይመጣ እንቅፋት መሆኑን ይጠቁማሉ። ችግሩን ለመፍታትም የመፍትሔ እርምጃዎች ተወስደዋል። በዋናነትም በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የሚመራ ግብረኃይል ተቋቁሞ እየተሠራ ነው፡፡

የተወሰዱ እርምጃዎች

ሕገወጦችን መከላከል እንደ ሀገር በአቅጣጫ የወረደ መሆኑን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ትግበራው የሚከናወነው በክልሎች እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ በመቀናጀት መሆኑን ያነሳሉ፡፡ በመሆኑም ክልሉ ይህንን አቅጣጫ ተከትሎ በግብረኃይሉ በኩል እቅድ ነድፎ ካለፈው መጋቢት ወር ጀምሮ ወደ ተግባር መግባቱን ይናገራሉ፡፡ በሂደቱም የተለያዩ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ይገልፃሉ፡፡ የመጀመሪያው በማዕድን ልማት በተሰማሩ ማኅበራት እና በአዟሪዎች ላይ የተወሰደው እርምጃ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡

በወርቅ ፍለጋና የግብይት ሥርዓት ሰንሰለት ውስጥ የተሰማሩት ማኅበራት ከ20 በላይ መሆናቸውን የሚገልጹት ዳይሬክተሩ፤ ከእነዚህ ማኅበራት ውስጥ ሁለቱ ብቻ በሥራቸው እንዲቀጥሉ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ ከ18 በላይ የሚሆኑት ግን እገዳ እንደተጣለባቸው አስታውቀዋል፡፡

«በግብረ ኃይሉ ውሳኔ መሠረት በወርቅ ማዕድን ፍለጋና ልማት የተሰማሩ ማኅበራት ለብሔራዊ ባንክ ከአንድ ኪሎግራም በታች ወርቅ ማቅረብ አይችሉም» የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ በዚህ ድንጋጌ መሠረት አፈፃፀማቸው ዝቅተኛ በሆነ ማኅበራት ላይ እርምጃ እንደተወሰደባቸው አስታውቀዋል፡፡ በተመሳሳይ የቁፋሮ ቦታ ተሰጥቷቸው ወደ ልማት ሳይገቡ የቀሩና የማይሆን ቦታ ተሰጥቷቸው ቅያሬ ወስደው ሥራ ያልጀመሩ ማኅበራትም መኖራቸውን ጠቅሰው፣ እነዚህም የእገዳው አካል እንዲሆኑ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡ በዚህ ውሳኔ ላይ ቅሬታዎች እየቀረቡ መሆኑን አንስተውም፣ ግብረኃይሉ ያቀረቡትን ቅሬታ መርምሮ ውሳኔ እንደሚሰጥ ገልፀዋል፡፡

እርምጃ ከተወሰደባቸው የዘርፉ አንቀሳቃሾች መካከል ‹‹ፒኤል ሲ›› ተብለው በፌዴራል ደረጃ ፈቃድ የሚሰጣቸው አሁን ደግሞ በአዟሪነት የተመዘገቡ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ከተመዘገቡት 44 አዟሪዎች ውስጥ 21 የሚሆኑት የንግድ ፈቃዳቸው ተሰርዟል፤ በ16ቱ ላይ ደግሞ የማስጠንቀቂያ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል፡፡ የማቅረብ አቅማቸው ተፈትሾ አፈፃፀማቸው ካልተሻሻለ ሙሉ እገዳ እንደሚጣልባቸው አመልክተው፣ መስፈርቱን ሲያሟሉ ግን ማስጠንቀቂያው የሚነሳ ይሆናል ይላሉ፡፡ ችግሩን ከመሠረቱ ለመፍታትም በዘርፉ የተሰማሩትን አካላት የማብቃትና ግንዛቤ የማስጨበጥ ተግባር እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ከእርምጃ በኋላ የመጡ ለውጦች

ሕገ ወጥነትን መከላከል መሠረት በማድረግ በክልሉ የማዕድን ልማት ዙሪያ ለውጦች መምጣታቸውን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል፤ ከጥር እስከ መጋቢት ባሉት 3 ወራት ወደ ብሔራዊ ባንክ የገባው የወርቅ መጠን ሦስት ኪሎ ግራም ብቻ እንደነበር አስታውሰው፤ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባ በኋላ ግን ነገሮች መቀየራቸውን ነው የገለጹት፡፡ በጥቂት የወርቅ አቅራቢዎችም ከሚያዝያ እስከ ሰኔ መጨረሻ ድረስ 21 ኪሎ ግራም ወርቅ ወደ ብሔራው ባንክ ማስገባት መቻሉን ይናገራሉ፡፡

ሌሎች የማዕድን ሀብቶች

ክልሉ ከወርቅ ሀብት ውጪ በማዕድኑ ዘርፍ የበለጸገ እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ አሁን ላይ ከኢንዱስትሪ ማዕድናት አንጻር ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው የድንጋይ ከሰል ሲሆን፤ በእዚህም አምራቾች በዳዎሮና ኮንታ ዞኖች በስፋት እያመረቱ ይገኛሉ። የተወሰኑት ደግሞ የቅኝትና ጥናት ፈቃድ ወስደው ለመሥራት እየተጉ ናቸው፡፡ በ2015 በጀት አመት 250 ሺህ ቶን ለማቅረብ ታቅዶ፣ 209 ሺህ 398 ቶን ማቅረብ ተችሏል፡፡ በዚህም የእቅዱን 83 ነጥብ 7 በመቶ ማቅረብ የተቻለበት ሁኔታም ተፈጥሯል፡፡

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከተከናወኑ የማዕድን ልማት ሥራዎች መካከል በድንጋይ ከሰል ንዑስ ዘርፍ የተከናወነው ቀዳሚው እንደሆነ የተናገሩት ዳይሬክተሩ፤ በክልሉ እስካሁን ባለው መረጃ በድንጋይ ከሰል ማምረትና ግብይት ላይ ለመሰማራት ፍላጎት ያቀረቡት 184 መሆናቸውን ገልፀዋል። ወደ ሥራው እንዲገቡ የተፈቀደላቸው ግን 72ቱ ብቻ መሆናቸውን ይናገራሉ። በድንጋይ ከሰል ልማቱ ላይ የተሰማሩት በሙሉ አቅማቸው ወደ ምርት ባይገቡም አንዱ ድርጅት ብቻ በሰዓት እስከ 150 ቶን እንደሚያመርት ይጠቅሳሉ።

በተመሳሳይ ከኮንስትራክሽን ማዕድናት አቅርቦት አንጻር 420 ሺህ ሜትር ኩብ ማዕድን ለማቅረብ ታቅዶ 332ሺህ 898ነጥብ 2 ሜትር ኩብ ማቅረብ መቻሉን የሚናገሩት አቶ ገብረማርያም፣ ይህም ከእቅዱ 79 ነጥብ 2 በመቶ መፈጸም የተቻለበት እንደሆነ ይናገራሉ። ከዚህም መረዳት የሚቻለው ከወርቅ ውጪ ባሉት ማዕድናት ላይ የተከናወነው ተግባር የተሻለ የአፈፃፀም አቅም የታየበት መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ያጋጠሙ ችግሮች

እሳቸው እንዳሉት፤ በክልሉ የወርቅ ምርትንም ሆነ ሌሎች ማዕድናትን አምርቶ ተገቢውን ጥቅም ለማግኘት ፈተና የሆኑ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ክልሉን በእጅጉ የፈተኑት የሕገወጥነት መንሰራፋት፣ የጸጥታና የመሠረተ ልማት ችግሮች ናቸው፡፡

ይህንንም በዋናነት ወርቅ በብዛት የሚቀርብባቸውን አራት ቀበሌዎችን ብቻ ለአብነት በመጥቀስ ሲያብራሩም፤ የመሠረተ ልማት ችግር በእጅጉ ፈተና መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ አካባቢዎቹ ምንም ዓይነት የመሠረተ ልማት እንደሌለባቸውም ገልፀዋል። በ2007 ዓ.ም በፌዴራል መንግሥት አስፋልት እንዲሆን ታምኖበት ቤቶች ፈርሰው ጭምር መሠረተ ልማት የሚገነባበት ስፍራ ለግንባታ ዝግጁ ቢደረግም፣ ግንባታዎቹ እስካሁን ድረስ እንዳልተጀመሩም ገልጸዋል፡፡ ለችግሩ እልባት ለመስጠት ከፌዴራል ማዕድን ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር መፍትሔዎችን ለማምጣት ሙከራ እንደሚደረግ ጠቅሰው፣ ይህ ካልሆነ ሀብቱ በአግባቡ ለምቶ ለሀገር ኢኮኖሚ መዋል እንደማይችል ይናገራሉ፡፡

«ሕገወጦችም ሀገርን በተለያየ መልኩ እየፈተኑ ይገኛሉ» ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ ያስገነዝባሉ፤ ይህን ሕገወጥነት ለመቆጣጠር እንደ ሀገር እየተወሰደ ባለው እርምጃ ለውጦች እየታዩ ቢሆኑም አሁንም ጠንካራ መፍትሔ እንደሚሻ ይገልፃሉ። ሌላው የጸጥታ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም ብዙ ሥራ ይጠይቃል ይላሉ፡፡ እንደ መንግሥት፤ እንደ ማኅበረሰብና ዘርፉን እንደሚመለከተው አካል ብዙ መሥራት ይጠበቃል ሲሉም አስተያየታቸውን ይሰጣሉ፡፡ ሁሉም ለሀገሩ ብሎ የበኩሉን አስተዋፅኦ ማድረግ ካልቻለ በስተቀር ፈተናው በቀላሉ እንደማይታልፍም አስገንዝበዋል፡፡

የቀጣይ እቅድ

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ እነዚህ የማዕድን ልማቱ ተግዳሮቶች በቀጣይም ፈተና ሊሆኑ ይችላሉ፤ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ብዙ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ አሁን እንደ ክልል በርካታ አምራችና አዟሪዎች የታገዱበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በአሁኑ ወቅት ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ የሚያቀርቡት ጥቂት ናቸው፡፡ እቅድን ከመጠን በላይ መለጠጡ ተገቢነት እንደሌለው ይታመናል። ጥሩ መደላደሎች እስኪፈጠሩ ድረስ ከእቅድ በላይ ይሠራል በሚል በዚህ ዓመት እንደ ክልል የተያዘው ከአምናው በቀነሰ መልኩ ነው፡፡ ይህም 400 ኪሎግራም ለብሔራዊ ባንክ ማቅረብ ይቻላል የሚል ሲሆን፤ አፈጻጸሙ ታይቶ ክለሳ እየተደረገበት የሚሠራ ይሆናል፡፡

«እንደ ክልል ወርቅ የሚመረተው በባህላዊ ደረጃ ነው» የሚሉት ዳይሬክተሩ፣ በክልሉ በኢንዱስትሪ ደረጃ የገቡ ወርቅ አምራቾች እንደሌሉም ይናገራሉ። የተሻለ አቅርቦት እንዲኖር ለማድረግ በመንግሥት በኩል እየተሠሩ ያሉ ተግባራት መኖራቸውንም ጠቁመዋል፡፡ አንዱ ጥናት እንዲያደርጉ ዕድሉ የተሰጣቸው ድርጅቶች መኖራቸውን ጠቅሰው፣ ለአዚህም ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ይላሉ፡፡ ማጂ አካባቢ የገቡ በወርቅ ማምረትና ግብይት ላይ የሚሠሩ ድርጅቶችን ለእዚህ በአብነት ጠቅሰዋል፡፡ ይህ ሲሆን፤ በዘመናዊ መሣሪያና በካፒታል የታገዘ ሥራ ለመሥራት ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 26/2015

Recommended For You