የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ትሩፋቶች ይጎልብቱ!

 ኢትዮጵያውያን ባለፉት አራት ዓመታት፤ በመጀመሪያው ምዕራፍ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር 25 ቢሊዮን ችግኞችን መትከል ችለዋል። በመርሃ ግብሩ መጀመሪያ ወቅት በአንድ ጀንበር ከ350 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል አዲስ ታሪክም ጽፈዋል፡፡ በዚህም ዓለም አቀፍ ክብረወሰንን በእጃቸው አስገብተውም ነበር።

ሃያ ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ታስቦ ሃያ አምስት ቢሊዮን ችግኞች ተተክለው ዓምና በስኬት ከተጠናቀቀው የመጀመሪያው ምዕራፍ የአራት ዓመታት የዐረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ማግስት፤ በሌላ አራት ዓመት ውስጥ የሚከናወን 25 ቢሊዮን ችግኞችን የመትከል ግብ የተቀመጠለት ሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ዘንድሮ አንድ ብሎ ተጀም ሯል፡፡

በቀጣይም ለአራት ዓመታት በሚቆየው በዚህ የሁለተኛው ዙር መርሀ ግብር በሚተከሉ 25 ቢሊዮን ችግኞች በመታገዝ፤ በመርሃ ግብሩ ማጠቃለያ አራተኛው ዓመት ላይ ኢትዮጵያ ቢያንስ 50 ቢሊዮን ችግኞችን እንድትለብስ ይደረጋል፡፡ ይህ ግብ እንዲሳካም በዚህ ዓመት ብቻ ስድስት ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ውጥን ተይዞ በስፋት ተሰርቷል፡፡

እየተገባደደ ባለው በዚህ የክረምት ወቅት እንዲተከል የታቀደውን ከስድስት ቢሊዮን ችግኝ በላይ ለማሳካትም በተሰራው ስራም ዕቅዱ በስኬት መንገድ ላይ መሆኑ ታይቷል፡፡ ከዚህም በላይ በመጀመሪያው ምዕራፍ በአንድ ጀንበር ከ350 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል በራሳችን የያዝነውን ክብረ ወሰን በማሻሻል በአንድ ጀንበር ከ500 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን መትከል ተችሏል።

በዚህ መልኩ የሚገለጸው የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ታዲያ ዓለምን ስጋት ውስጥ የከተተውን የአየር ንብረት ለውጥ ከመከላከል አኳያ ከሚኖረው ሚና ባለፈ፤ እንደ ሀገር ለተያዘው የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለግብርና እና ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ስኬታማነት ትልቅ አቅም የሚፈጥር ነው። ይህንንም መላው ሕዝባችን ባለፉት አራት ዓመታት በመርሀ ግብሩ ከነበረው ተጨባጭ ተሳትፎ መገንዘብ ችሏል።

ሀገራችን ላለፉት አምስት ዓመታት ተግባራዊ እየሆነ ባለው የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር ሀገር እንደ ሀገር ዘርፈ ብዙ ተጠቃሚ ሆናለች። በዘመናት ሂደት የተራቆተውን የሀገሪቱን የደን ሀብት ከሦስት ከመቶ ወደ 17 ከመቶ ከማሳደግ ጀምሮ ለዜጎች የተለያዩ ትሩፋቶችን እያስገኘም ይገኛል።

በመርሃ ግብሩ እስካሁን ሀገር በቀል ችግኞች፤ የደን ተክሎች፣ ፍራሬዎች እና ሌሎች ተክሎች እንዲለሙ ተደርገዋል፡፡ በዚህም ሂደት በችግኝ ማፍላት፣ ጉድጓድ ቁፋሮና በእንክብካቤ ስራ እንዲሁም በተያያዥ ሥራዎች ላይ ዜጎች እንዲሳተፉ ተደርጓል።

እስካሁን ወደ 700 ሺህ የሚጠጉ ዜጎች ለአረንጓዴ ዐሻራ የሚውል የእጽዋት ዘሮችን በማቅረብ፤ በችግኝ ጣቢያዎች ተቀጥረው በመስራት ችግኞችን በመሸጥና የተለያዩ የአፈርና የውሃ ጥበቃ ሥራዎች ላይ በመሳተፍ የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል፡፡ በዚህም ኑሯቸውን በተሻለ መንገድ መምራት የሚያስችላቸውን አቅም ፈጥረዋል።

በአገሪቱ በርካታ ሥራ አጥ ወጣቶች እንደመኖራቸው፤ በቀጣይም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብሩን በስፋት እና በጥራት በማስቀጠል፤ ለዜጎች የስራ እድል በመፍጠር፤ አሁን ላይ ለሀገር ፈተና የሆነውን የሥራ አጥነት ችግር ትርጉም ባለው መንገድ መፍታት ይቻላል።

በመርሀ ግብሩ የፍራፍሬ ችግኞች መካተታቸው፤ በመርሀ ግብሩ የሚታቀፉ ዜጎች ተጨማሪ ገቢ የሚያገኙበትን የተመቻቸ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑ፣ እንደ ሀገር ለጀመርነው በምግብ ራስን መቻልም ሆነ ድህነትን ታሪክ የማድረግ ጉዞ ስኬት ትልቅ ጉልበት ከመሆኑም በላይ በተመጣጠነ የምግብ እጥረት አደጋ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ሕይወት በመታደግ ረገድም የጎላ ድርሻ ይኖረዋል።

የፖለቲካ አመራሩ ከፍ ያለ መነሳሳት እና የኅብረተሰቡ ፈቃደኛነት የታየበትን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር በማስቀጠል ሀገርን ሁለንተናዊ ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻል ያለፉት አራት ዓመታት ተጨባጭ ተሞክሮዎች ማሳያ ናቸው።

ከነዚህ ተጨባጭ ተሞክሮዎች በመነሳትም በቀጣይ መርሀ ግብሩን በተጠናከረ መልኩ ማስቀጠል፣ ችግኝ ለመትከል የተሰጠውን ትኩረት በመንከባከብም ተጠናክሮ እንዲቀጥል በማድረግ ሀገራዊ ትሩፋቶቹን ማጎልበት ያስፈልጋል !

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 26/2015

Recommended For You