የብሪክስ አባልነት ታሪካዊ እድሉን በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል

 የአንዳንድ ታሪካዊ አጋጣሚዎች ትውልድ አካል መሆን ያኮራል፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ የመንግሥታቱ ማህበር (ሊግ ኦፍ ኔሽን) አባል የሆነችበትን ዘመን ኖረው ያዩ ሰዎች ታሪክ ጽፈዋል፡፡ በወቅቱ የዚህ የዓለም ኃያላን አገራት ማህበር ሲመሰረት ከአፍሪካ ብቸኛዋ አባል የነበረች መሆንዋ የታሪኳ አንድ ትልቅ ምእራፍ ነው፡፡ ለዚህ ክብር ያበቃት ደግሞ የደፋር መሪዎች እና ጀግና ሕዝቦች አገር መሆኗ ነው፡፡

በወቅቱ ይህ የኃያል ህዝቦች ሀገር የመሆኗ እውነታ ወደ ኃያላን ስብስብ ወስዷታል፡፡ በቀጣይም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በመመስረት ሂደት ውስጥ ግንባር ቀደም በመሆን መሥራች ሆናለች፤ ዛሬ ድረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቀው የአፍሪካ ሕብረት ዋና መቀመጫ ሆናለች፡፡

በየትኛውም አፍሪካዊ ጉዳይ ላይ የአፍሪካ ሕብረት ስሙ በተነሳ ቁጥር ኢትዮጵያ ስሟ ይነሳል። ከእነዚህ ሁሉ ታሪካዊ ሁነቶች ጋር የኢትዮጵያውያን ስለነፃነታቸው ያላቸው ቀናኢነት ይታወሳል። ኢትዮጵያ ቅኝ አለመገዛቷ ከአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ልዩና ገናና ያደርጋታል፡፡

እነሆ ይቺ አገር አሁን ደግሞ የአምስት አገራት ጥምረት የነበረው የብሪክስ አባል አገር መሆን የሚያስችላትን እድል አግኝታለች፡፡ በመጪው ታህሳስ 22 ቀን 2016 ዓ.ም (በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ጥር 1 ቀን 2024) የጥምረቱ አባል ትሆናለች፡፡ ይህን ዕድል ያገኙ የአፍሪካ አገራት ከደቡብ አፍሪካ በመቀጠል ኢትዮጵያና ግብጽ ናቸው፡፡

ይህ ትውልድ ሀገሩ የዚህ ጥምረት አባል በመሆኗ ሊኮራ ይገባል፡፡ አባል ለመሆን ያስቻላትን ተስፋም እውን የማድረግ ጥልቅ ኃላፊነት አለበት፤ ምክንያቱም ተስፋው እውን የሚሆነው በዜጎች ትጋት ነው፡፡

የጥምረቱ አባል ለመሆን ዋናው መስፈርት ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ አንዱ መስፈርት ነው። የጥምረቱ ዓላማም ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ያላቸው አገራት በትብብር እድገታቸውን እንዲያስቀጥሉ ነው፡፡ ከዛም ባለፈ የምዕራባውያንን የሚያደርሱትን ሁለንተናዊ ጫና መመከት ነው፡፡

ኢትዮጵያም ለዚህ ዓለም አቀፍ ጥምረት አባልነት ከተመረጠችበት መስፈርቶች አንዱ በፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገቷ ውስጥ በመገኘቷ ነው፤ በአፍሪካ ቀንድ ያላት የጂኦ ፖለቲካል ድርሻ፤ የአህጉሩ ሕብረት ዋና መቀመጫ መሆኗ ወዘተ የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይገመታል።

እዚህ ላይ ዋናው ጉዳይ ሀገሪቱ የህብረቱ አባል፤ መሆኗ ሳይሆን፤ ከዚህ ባለፈ በዚህ እድል የኢትዮጵያ ከፍታ እንዴት እናስቀጥል የሚለው ነው። መሥራቾቹ የደቡብ አሜሪካዋ (ላቲን) ብራዚል፣ የአውሮፓና እስያዋ አካል የሆነችው ሩሲያ፣ የእስያዋ ህንድ፣ የእስያዋ ቻይና እና የአፍሪካዋ ደቡብ አፍሪካ ያደገ ኢኮኖሚ ባለሀብቶች ናቸው፡፡

አሁን ደግሞ ከኢትዮጵያ ጋር የጥምረቱ አካል የተደረጉት የአረቡን ዓለም የያዙት ግብጽ፣ ሳውዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኢሜሬትን ጨምሮ አርጀንቲና እና የፋርሷ አገር ኢራን ናቸው እነዚህ አገራትም ቢሆኑ በዓለም የኢኮኖሚም ሆነ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ እነዚህ አገራት አባል በሆኑበት ህብረት ውስጥ የመኖሯ እውነታ ምን አንደምታው ምን ሊሆን እንደሚችል ግልጽ ነው፡፡

የህብረቱ አባል መሆን የሚያሰጠውን እድል በአግባቡ ለመጠቀም ከሁሉም በላይ፤ የውስጥ ሰላምን ለማረጋገጥ ጠንክሮ መሥራት ያስፈልጋል፤ አሁን ባለው ሁኔታ እንኳን አሁን ያጋጠመንን እድል ቀርቶ ቀድሞውንም በእጃችን ያሉ እድሎችን ወደ ልማት ቀይረን ሀገር እና ህዝብን ተጠቃሚ ማድረግ አንችልም።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በብዙ መልኩ ተጠባቂ የሆነችውን ሀገራችንን በአገር ውስጥ የሰላም ችግር ወደኋላ መጎተት የክፍለ ዘመኑ አሳፋሪ ክስተት ነው፡፡ ከትናንት የሁከት፤ የጦርነት እና የብጥብጥ ታሪኮቻችን በአግባቡ ተምረን ለሰላማችን አብዝተን ልንሰራ ፤ ለዚህም ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ሚና ሊወጣ ይገባል፡፡

አሁን ላይ እንደሀገር እያጋጠሙን ያሉ መልካም የመልማት እድሎችን በአግባቡ ለመጠቀም እያንዳንዱ ዜጋ ለሰላም ያለው አስተሳሰብ ከመሰረቱ ሊቀየር ይገባል። ይህን ባለማድረጋችን ለሚፈጠር ሀገራዊ ውድቀት ይህ ትውልድ ተወቃሽ ነው። ከቀጣይ ትውልዶች ተወቃሽነትን የሚታደገው አይኖርም።

ይህን አጋጣሚ በመጠቀም የተሻለች ሀገር መፍጠር ከቻልንም ዛሬ እኛ አያት ቅድመ አያቶቻችን በነጻነት አጥንተው ባስቀመጡልን ሀገራችን እንደምንኮራባቸው ሁሉ መጪዎቹ ትውልዶች በኛ ስራ የሚኮሩበት የአዲስ ታሪክ ትርክት ምዕራፍ መጀመር እንችላለን፡፡

ለዚህ ደግሞ ከሁሉም በላይ ሀገራዊ የፀጥታ ሁኔታውን ፈጥነን ማስተካከል ይጠበቅብናል። በዚህም እድሉን በአግባቡ በመጠቀም የኢትዮጵያን ታሪካዊ ዝና ልናስቀጥል ! አዲስ ታሪክም ልንጽፍና ልናሳውቅ ይገባል !

 ሚሊዮን ሺበሺ

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 26/2015

Recommended For You