ጦርነት፣ በተለይም የእርስ በርስ ጦርነት የትም የሁን የት ቅጥ ኖሮት ለህዝብ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊም ሆነ ፖለቲካዊ ፋይዳን ሲያስገኝ ታይቶም ሆነ ተሰምቶ አይታወቅም። ግራም ነፈሰ ቀኝ፤ ከሂደቱም ሆነ ውጤቱ የሚተርፍ ነገር ቢኖር የህዝብ እልቂትና ሰቆቃ፤ የመሰረተ-ልማት፣ ሀብትና ንብረት ውድመት ብቻ ነው። በአትራፊና አዋጭነቱ የተመሰከረለት የመፍትሄ መንገድ ቢኖር የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይትና ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ ይሆናል። ሌት ተቀን የሚዘመርለት ዴሞክራሲም ይሁን ዴሞክራሲዊ አሰራር ይህንኑ ነው አበክሮ የሚያስተምረው። የጦርነትን ያፈጠጠና ያገጠጠ እውነት በግልጽ ለመረዳት በርካታ አስከፊ ምሳሌዎችን መጥቀስ ቢቻልም ለጊዜው እንለፈውና ወደዛሬው ርዕሰ-ጉዳያችን ወደሆነው ወደ የመን እንምጣ።
ቢቢሲ እንደዘገበው፤ በአሁኑ ሰዓት የመን እጅግ የከፋ ሰብዓዊ ቀውስን በማስተናገድ ያለተወዳዳሪ ዓለምን እየመራች ነው። ንፁሀን የአገሪቱ ዜጎች በከፋ ሁኔታ ውስጥ ሲሆኑ፤ አስከፊ ችግሮችንም እያስተናገዱ ይገኛሉ፡፡ ከርሃብ እስከ ቦምብ እንዲሁም እንደ ኮሌራ ወረርሽኝ ያሉ ተላላፊ በሽታዎች እየተፈራረቀባቸው ሲሆን፤ በተለይ ህፃናትና ሴቶች በከፋ አደጋ ላይ ናቸው።
የዓለም ጤና ድርጅት ሰሞኑን ይፋ ባደረገው መግለጫው እስካሁን ድረስ ባለው መረጃ በአስከፊው የእርስ በርስ ጦርነት ሳቢያ 6 ሺ 660 ንፁሀን ዜጎች ሞተዋል፤ 10ሺ 560 ለከባድ የአካል ጉዳት ተዳርገዋል፤ በየሳምንቱ 10ሺ አዳዲስ ኮሌራና ኮሌራ-ወለድ ወረርሽኝ ይመዘገባል፤ በሺዎች የሚቆጠሩ በወረርሽኙ እየተጠቁ ለሞት በመዳረግ ላይ ናቸው።
ሴቭ ዘ ችልድረን፣ የተባበሩት መንግሥታት እና ሌሎች ግብረ-ሠናይ ድርጅቶች በተደጋጋሚ ሪፖርታቸው እንደሚገልፁት ጦርነቱ በቀጥታ ከፈጀው ሕዝብ በተጨማሪ ለረሃብና ለኮሌራ ያጋለጠው በርካታ ሕዝብ እየሞተ ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ‹‹ባለፉት 100 ዓመታት በዓለማችን ተወዳዳሪ ያልተገኘለትን ረሀብ አስከትሏል›› ያለለትና ጥንታዊቷን ሀገር ወደ ፍርስራሽ ክምርነት የለወጠ ጦርነት አራት ዓመቱን ሊደፍን ጥቂት ጊዜ ቀርቶታል፡፡ የሌሎች አገራት ጣልቃ ገብነት በጦርነቱ ለደረሰውና ለሚደርሰው ጥፋት ሰበብ እንደሆነ የእርዳታ ድርጅት ተቋማት ቢያስጠነቅቁም እስካሁን የሚሰማቸው አላገኙም።
የጀርመኑ ዶቼ ቬል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አጥኚ ቡድንን ጠቅሶ እንደዘገበው አብዱራቢ መንሱር ሲመሩት በነበረው የየመን መንግሥት፤ የአካባቢው አገራት ጣልቃ ገብነት ህዝቡን ለእልቂት እየዳረገው ነው። የአጥኚው ቡድን ተወካይ እንዳሉት ጣልቃ የሚገቡት መንግሥታት እና የተደራጁ ቡድኑ አባላት የጦር ወንጀል ሳይፈፅሙ አይቀርም። «የየመን መንግሥት፣ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን ጨምሮ የተባባሪዎቹ ሀገራት መንግሥታት ባለሥልጣናት የጦር ዒላማዎችን ከሌላው የመለየት፤ የኃይል ተመጣጣኝነትን፤ እና የጥንቃቄ መርሆዎችን ጥሰው ጥቃት አድርሰዋል። ይህ ከጦር ወንጀለኝነት እኩል ሊቆጠር ይችላል።»
ቢቢሲ እንደዘገበው፤ ከትናንት በስቲያ በተደረገው የአየር ድብደባ በአማፂው ቡድን ላይ ከፍተኛ አደጋ ደርሷል። በበርካታ አማፂያኑ አባላት ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን፤ ተጎጂዎች በተባበሩት መንግሥታት አውሮፕላን ወደሆስፒታል በማመላለስ አስቸኳይ እርዳታ እንዲያገኙ ተደርጓል። ይህንንም ተከትሎ ተፋላሚ ወገኖቹ ወደ ድርድር ይመጡ ዘንድ ለሌላ የሰላም ድርድር ለመገናኘት ስምምነት እንዲፈጥሩ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አማካይነት ጥረት እየተደረገ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ በጦርነት ለዓመታት እየታመሰች ላለችው የመን እና ተፋላሚዎቹ ወገኖች ወደ ሰላም እንዲመጡ፣ እንዲሁም በስቃይ ውስጥ ያለውን ሕዝባቸውን ከከፋ ችግር እንዲታደጉት የሚጠይቅ፤ እንዲሁም ከተለመደው ፖለቲካዊ ዘዬ ወጣ ያለ ይዘት ያለው ደብዳቤ መፃፋቸው ታውቋል።
‹‹ይህ በአንድ አምላክ የሚያምንና አንድ ሃይማኖት የሚከተል ሕዝብ ስለምን ጦርነት ውስጥ ይዘፈቃል?›› በማለት የሚጠይቀው የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ ደብዳቤ በጥንታዊ ዓለም ሥልጣኔ ውስጥ የየመን ታላቅ ሥፍራ በመዘርዘር አገሪቱን በሁለቱ ቅዱሳን መጻሕፍት የነበራትን ቦታና ክብር አጉልቶ ለማሳየት ጥረት ሁሉ አድርጓል። በተለይም በብሉይ ኪዳን ‹‹የብልጽግና ምድር›› መባሏን፤ በጥንታዊ ግብጻውያን ‹‹ቅዱስ ምድር›› እየተባለች መሞካሸቷን፤ በቁርዓንም እንዲሁ መጠቀሷን በመግለጽ የሚጀምረው ደብዳቤ ‹‹ለእናንተ ለየመን ሕዝቦች፤ ለደስተኞቹ፤ ማንም አገር በነብዩ መሐመድ የናንተን ያህል አልተጠቀሰም›› ካለ በኋላ ነብዩ መሐመድ ‹‹ . . . የየመን ሕዝቦች ወደናንተ ይመጣሉ፤ የቅን ልቦና ባልተቤቶች፣ ገራገሮች… እና ብልህ ሕዝቦች . . .›› ሲሉ የተናገሩትን በመጥቀስ የጭብጡን መሰረት ይተክላል።
በዚሁ ደብዳቤያቸው ‹‹ጦርነት ክልክል (ሐራም) ነው›› የሚሉት ዶክተር አቢይ የየመንን ህዝብ፤ ስለምን ሥልጣኔያችሁን በገዛ እጃችሁ ታወድማላችሁ? ስለምን ክብራችሁን ታዋርዳላችሁ? ስለምን ልጆቻችሁን ወላጅ አልባ ታደርጋላችሁ? ስለምን ከልጆቻችሁ ደስታን ትሰርቃላችሁ? እናንተ በቅዱሳን መጻሕፍት ‘ደስተኛ ሕዝቦች’ ተብላችሁ የተወደሳችሁ አልነበራችሁምን? በአንድ አምላክ የሚያምንና አንድ ሃይማኖት የሚከተል ሕዝብ ስለምን ጦርነት ውስጥ ይዘፈቃል? ›› በማለት ወቀሳዊ ጥያቄን አቅርበዋል። ‹‹እናንተ አሁን በጦርነት ለፈረሰችው የመን ኃላፊዎች ናችሁ›› ሲሉም ወቅሰዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ትናንት በድረ ገጹ በይፋ ባደረገው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ደብዳቤ ሁለቱን ወገኖች በከንቱ ጦርነት ላይ መሆናቸውን የሚናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተዋጊ ወገኖቹን በተመሳሳይ፤ አገሪቱን በሁሉም አቅጣጫ እያፈራረሳችሁ ያላችሁት ምን ለማግኘት ይሆን? ስለምን ምክንያት አልባ ትሆናላችሁ? በታላቁ ነቢይ ብልሆች ተብላችሁ አልነበረምን? ስለምን የጦርነት ነጋሪት ትጎስማላችሁ? መነጋገርና መወያየትን እየቻላችሁ? በማለት ወቀሳዊ ጥያቄዎችን አቅርበዋል። ‹‹አሁን ተጨባበጡ፤ በፍቅርና በንጹሕ ልብ ተዋደዱ፤ ብልህነታችሁ ብርሃን ይሁናችሁ…›› ሲሉም ተማጽነዋል።
በመጨረሻም፤ እርሳቸው የሚመሯት ሀገር ኢትዮጵያ የሚፈለግባትን ለማድረግ፣ እርቅን ለማምጣት፣ የደም መፋሰስን ለማቆም፤ የመንን ወደ ሰላምና ብልጽግና ለመመለስ የሚፈለግባትን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ በደብዳቤያቸው አስታውቀዋል።
ይህ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ደብዳቤ በበርካታ ያገር ውስጥና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀን በስፋት እያሰራጨ ሲሆን፤ እኛም የመኖች ልብ እንዲሉት፤ የሁቱ አማፂያን የአገሪቱን ምዕራባዊ ግዛት ከተቆጣጠሩበትና ፕሬዚዳንት አብዱራቢ መንሱር ሃዲ ከአገር ከተሰደዱበት 2015 ጀምሮ እስካሁን የዘለቀው አስከፊ እርስ በርስ ጦርነት እንዲቆምና ሃሳባቸው እንዲሳካላቸው እንመኛለን።
ግርማ መንግስቴ
አዲስ ዘመን ህዳር 26/2011