እንደየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢዎች በአማራ ክልል በተለያየ መልኩ የሚነሱ የሕዝብ ጥያቄዎች መኖራቸው የሚታወቅ ነው፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህን መሠረታዊ የሕዝብ ጥያቄዎች በልካቸው ተገንዝቦ ከመፍታት አኳያ የሚታዩ ክፍተቶች፣ የሕዝቡ ጥያቄ ላልተገባ ጥቅም ማግኛ ለሚንቀሳቀሱ ኃይሎች መጠቀሚያ እንዲሆን ዕድል ፈጥሯል፡፡ የአማራ ክልልም በዚህ ረገድ ከሚጠቀሱ አካባቢዎች አንዱ ሆኗል፡፡
ይሄ የሕዝብን መሠረታዊ ጥያቄዎች በልካቸው ተገንዝቦ መልስ ያለመስጠት የፈጠረው የሕዝብን አጀንዳ ጠልፎ ለጥፋት ዓላማ ማስፈጸሚያ ጉዳይ አድርጎ የመጠቀም አዝማሚያ ደግሞ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ክልሉ እንዳይረጋጋ ከማድረጉም በላይ፤ ችግሩን ለመቀልበስ ይቻል ዘንድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ እንዲተገበር ግድ ብሏል፡፡
አሁን ላይ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታግዞ በተወሰደ የሕግ ማስከበር ርምጃ ምክንያት ክልሉ ወደሰላማዊ እንቅስቃሴው የተመለሰ ሲሆን፤ ይሄን ተከትሎም በክልሉ ያለውን እና ለክልሉ አለመረጋጋት ምክንያት እንዲሆኑ ተመቻችተው የተጠለፉ የሕዝብ ጥያቄዎችን መመለስ የሚያስችል የክልል አመራር ለውጥም ተደርጓል፡፡
ይሄን የአመራር ለውጥ ተከትሎም፣ አዲስ የክልሉ ካቢኔ የተዋቀረ ሲሆን፤ ይሄ ካቢኔም የክልሉን ሰላምና ፀጥታ የማረጋጋት ብቻ ሳይሆን፤ ልማቱን የማስቀጠል እንዲሁም በሕዝቡ የሚነሱ መሠረታዊ ጥያቄዎችን በልካቸው ተገንዝቦ የመመለስ ከፍ ያለ የቤት ሥራ ተሰጥቶታል፡፡ ካቢኔውም ይሄንኑ የማድረግ ቁርጠኝነትን ተላብሶ መሥራት፣ የክልሉን ሰላም ማረጋገጥ ብሎም ከሕዝቡ ጋር ሰርቶ የሕዝቡን ልብ ማሸነፍ ይጠበቅበታል፡፡
ካቢኔው ይሄን ኃላፊነቱን በልኩ ተገንዝቦ እንዲሰራም ሆነ በየደረጃው ያለውን አመራር እንዲያሰራ ከማድረግ አኳያ አዲሱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ የመሪነቱን ሚና በተረከቡ ማግስት ለካቢኔያቸው ያሳሰቡትም ይሄንኑ እውነት ነው፡፡
ሰሞኑን የክልሉ ካቢኔ በክልሉ ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ ላይ ውይይት ባካሄደበት ወቅት «የሕዝብን መሠረታዊ ጥያቄዎች ለይተን በቅደም ተከተል ለመፍታት እንሠራለን» ሲሉ ቃላቸውን የሰጡት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በክልሉ በተፈጠረው ግጭት ምክንያት የተፈጠሩ ዘርፈ ብዙ መስተጓጎሎችን በመግለጽ፣ የክልሉ ካቢኔ እነዚህን ተገንዝቦ ኃላፊነቱን እንዲወጣም ነው ያሳሰቡት፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳነሱትም ሆነ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ አሁን ላይ በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት በአንዳንድ አካባቢዎች ለአርሶ አደሩ በወቅቱ ሲቀርብ የነበረው የአፈር ማዳበሪያ ሥርጭት ተስተጓጉሎ በመቆየቱ ምክንያት በመኸር ሰብል ልማት ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል፡፡
በተመሳሳይ ከመሃል ሀገር ወደ ክልሉ የሚገቡ ነዳጅና ልዩ ልዩ የኢንዱስትሪ ውጤቶች፣ ሸቀጦችና የፍጆታ ምርቶች በጸጥታ ስጋት ምክንያት በሚፈለገው ደረጃ እንዳይቀርቡ ጫና ፈጥሯል፡፡ ለሕዝቡ አገልግሎት የሚሰጥባቸው የመንግሥት ተቋማትና ሌሎችም መሠረተ ልማቶች ለጉዳት ተዳርገዋል፡፡
ችግሩ በአጭር ካልተቋጨና በአንድ በኩል የግብርና ሥራው በሚፈለገው ልክ እንዳይከናወን ከሆነ፤ በሌላ በኩል ሕዝቡ ከመንግሥት የሚያገኘውን አገልግሎት ማግኘት ካልቻለ እና ጥያቄዎቹ ካልተመለሱለት፤ በክልሉ የሚፈለገው የተሟላ ሰላምም ሆነ የኢኮኖሚ እድገትና የመልካም አስተዳደር እውን ሊሆን አይችልም፡፡
በመሆኑም እነዚህንና ሌሎችም በክልሉ እና በክልሉ ሕዝብ ላይ የተጫኑ ችግሮችን ማስወገድ፤ ለሕዝቡም ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት የሚቻለው በመጀመሪያ የክልሉን ሰላም ማረጋገጥ ሲቻል ነው፡፡ በዚህ ረገድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚፈለገውን ሰላም ቶሎ ለማምጣት የሚያግዝ ቢሆንም፤ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥር መቆየት ብቻውን የሚፈለገውን ሰላም እንደማያመጣም ተገንዝቦ መሥራት የተገባ ነው፡፡
ከዚህ አኳያ የክልሉን ሰላም ማረጋገጥ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ቢሆንም፤ የሕዝቡን ጥያቄዎች በልካቸው ተገንዝቦ ምላሽ የመስጠት ሥራውም ለነገ የማይባል ከሰላሙ ጎን ለጎን ሊሠራ የሚገባው ጉዳይ ነው።
ይሄን ማድረግ ደግሞ የአዲሱ የክልሉ አመራርና ካቢኔ የቤት ሥራ ብቻ ሲሆን፤ የክልሉ መስተዳድር ጥረት እንዲሳካ የሰላም መስፈንና የሕዘብ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን መገንዘብ ይገባል!
አዲስ ዘመን ነሃሴ 25/2015