‹‹የብሪክስ አባል መሆናችንን ከዲፕሎማሲው አንጻር ባለፉት አምስት ዓመታት ያላየሁት ስኬት ነው›› አምባሳደር ጥሩነህ ዜና የቀድሞ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር

ኢትዮጵያ በዘመኗ ሁሉ የሚገዳደራት እንዳልጠፋ በብዙዎች ዘንድ የሚታወቅ ነው። ባሳለፈቻቸው ዓመታት አንዱን ችግር በድል ተወጣሁት ስትል ሌላ መከራ ሲደቀንባት ቆይቷል። ከተለያዩ ሀገራትም ዓይን ያፈጠጠና ጥርስ ያገጠጠ ተጽዕኖም በየጊዜው ሲፈታተናት ከርሟል። ይሁንና ላጋጠማት ፈተና ሁሉ እንደየአመጣጡ ምላሽ በመስጠትና በድል ከማለፍ በዘለለ ለአፍታም ቢሆን ተንበርክካ አታውቅም።

ሆኖም አሁንም ድረስ ይህ ፈተና ያልተላቀቃት ስለመሆኑ ከማንም የተሰወረ አይደለም። በዚህ ፈተና ውስጥ ሆና ግን በርካታ ስኬቶችን በማስመዝገብ ላይ ትገኛለች። ከልማቱ ባሻገር በዲፕሎማሲውም ረገድ ውጤታማ በመሆን ላይ ናት። ከዚህ ከዲፕሎማሲው ጋር ተያይዞ ያለፈችበት ሒደትና ከሰሞኑን የብሪክስ ጥምረትን የተቀላቀለችበት አካሄድ በተመለከተ ከቀድሞው ዲፕሎማትና የሰብአዊ መብት ኮሚሽነር ከአምባሳደር ጥሩነህ ዜና ጋር አዲስ ዘመን ቆይታ አድርጓል። መልካም ንባብ።

አዲስ ዘመን፡- ዲፕሎማሲ ምንድን ነው? ከጊዜ ወደጊዜ የሚያሳየው ለውጥስ እንዴት ይገለጻል?

አምባሳደር ጥሩነህ፡– ጥቅል ጥያቄ ነው፤ ቢሆንም በአጭሩ ስመልሰው ዲፕሎማሲ አንድ ሀገር የራሱን ፍላጎትና ጥቅም ሌላው እንዲቀበለውና ከዛ አንጻር ጥቅሙን ለማዳበር፣ ወዳጅን ለማብዛት እንዲሁም ጠላቶቹን ለመቀነስ የሚደረግ ጥረት ነው።

ቀደም ሲል ከመንግሥታት ዘንድ ብቻ ይደረግ የነበረው ዲፕሎማሲ አሁን አሁን ሰፋ ብሎ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ በሚል ሕዝብ ለሕዝብ የሚደረግ ዲፕሎማሲም አለ። ደግሞ ጠበብ ብሎ በአሁኑ ጊዜ ኢኮኖሚው ቅድሚያ ስለያዘ ከሁሉም በላይ የኢኮኖሚ ጥቅም አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ መንግሥታት የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲን ለይተው እየሰሩበት ይገኛሉ።

አዲስ ዘመን፡- የዲፕሎማሲ መርህ ምንድን ነው?

አምባሳደር ጥሩነህ፡- አንድ ሀገር ዲፕሎማሲን ሲሠራ መከተል ያለበት መርህ አለ። ይኸውም ከሁሉም ጋር ወዳጅ ለመሆን መሞከር፤ ሁሉንም ወዳጅ ማድረግ ፋይዳው ከፍ ያለ ነው። ወዳጅ መሆን ካልተቻለ ደግሞ ግንኙነቱን ሀገሪቱ በማትጎዳበት ሁኔታ ማድረግ ነው። በዚህ ጊዜ ገለልተኛ መሆኑ መልካም ነው፤ ይህ የማይሆን ከሆነና አሻፈረኝ የሚል ከሆነ ያ ሀገር ከጠላት ጎን እንዳይቆም ለማድረግ መጣር የሚል ነው።

ለዚህ ምክንያቴ አንዳንድ ጊዜ ጠላቶች እንዲተባበሩ ራሳችን የምናደርገው ግፊት አለ፤ ለምሳሌ በደርግ ጊዜ ከሁሉም ጋር መነታረክ፣ ሁሉንም መውቀስና ሁሉንም መዝለፍ ይስተዋል ነበር። ለምሳሌ አረቦች እንደዚህ ናቸው፤ ወይም ደግሞ ምዕራባውያን እንደዚህ ናቸው ተብሎ ሁሉንም በአንድ ጎራ መፈረጅ ይበዛ ነበር። እንደዛ በምናደርግበት ጊዜ ሁሉም ተጠቅልሎ ወደ አንድ ጎተራ ይገባል። በዚህ ጊዜ እኛው ራሳችን አዘጋጅተን ለጠላት ራሳችንን አሳልፈን እንደመስጠት ይቆጠራል።

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ቀደም ባሉ ጊዜያት ከሀገራት ጋር የነበራት ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ በአጭሩ እንዴት ይገለጻል?

አምባሳደር ጥሩነህ፡– ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመረችው ራቅ ባለ ዘመን ሲሆን፤ ጅማሬዋንም ያደረገችው በሃይማኖቱ ረገድ ከግብጾች፣ ከእስራኤሎችና ከግሪኮች ጋር ነበር።

በተለይ አጼ ቴዎድሮስ ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ በተነሱ ጊዜ ከውጪዎቹ ጋር ግንኙነት ለመፍጠር ጥረዋል። በዚያን ወቅት የጠየቁትም ከሃይማኖቱ ጋር ተያይዞ እርዱን በሚል ነው። በወቅቱ ጥያቄው የቀረበውም ለእንግሊዝ፣ ጀርመን፣ ጣሊያንም ጭምር ደብዳቤ በመጻፍ ነበር።

በአጼ ቴዎድሮስ ጊዜ በሒደት ዲፕሎማሲው ከሃይማኖቱ ጉዳይ አልፎ ኢኮኖሚ ጥቅም ላይ አዘንብሏል። እነርሱም ሀገራችንን በቅኝ ለመግዛት እያቆበቆቡ የነበረበት ወቅት ነው። ስለዚህ ጉዳዩ ከሃይማኖት ጥቅም ወደ ኢኮኖሚ ጥቅም ማተኮር የጀመረበት ጊዜ ነው።

ከዚያ በኋላ ዲፕሎማሲው ጠንካራ ሆኖ የመጣው በአጼ ምኒልክ ዘመን ነው። አጼ ምኒልክም በአጼ ቴዎድሮስ ጊዜ ሩቅ የነበረው የምዕራቡ ግፊት ደጃፋቸው መድረሱን ባዩ ጊዜ አስልተው መንቀሳቀስ ጀመሩ። በወቅቱም አጼ ምኒልክ ምዕራባውያኑን ወደእርሳቸው አስጠግተው እንደአማካሪም ይጠቀሙባቸው ስለነበር ፖለቲካዊ ዲፕሎማሲውን በአግባቡ ጀመሩት ማለት ይቻላል። በወቅቱ በ1907 ዓ.ም ገደማ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን ማቋቋም ጀመሩ። በዚያን ጊዜ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤትንም አቋቋሙ።

በወቅቱ አጼ ቴዎድሮስ በሃይማኖቱ በኩል ሲያካሂዱት የነበረው የዲፕሎማሲው ጉዳይ እምብዛም ባለመሳካቱ አጼ ምኒልክ ደግሞ ከጥቅም አኳያ ማስኬድ ፈለጉ። በዚህ ወቅት እርስ በእርስ ይጎሻሸሙ እና ይዋጉ የነበሩት ፈረንሳይና እንግሊዝ ናቸው። በመሆኑም አጼ ምኒልክ ሁለቱን ሀገራት ያጫውቱ ነበር።

በወቅቱ ደግሞ አካባቢውን በደንብ የተቆጣጠረችውና በኬንያም በሱዳንም የነበረችው እንግሊዝ ናት። ከዚያም አልፋ ኢትዮጵያንም ትፈልግ ነበር። አጼ ምኒልክ ያደረጉት ነገር ቢኖር እንግሊዝና ፈረንሳይ ያልመስማማታቸውን ጠንቅቀው ያውቁ ነበርና ዓይናቸውን ወደፈረንሳይ አደረጉ። ጣሊያን ኢትዮጵያን እስከ ወረረችበት ጊዜና ፈረንሳዮችም የኢትዮጵያን ጓደኝነት ክደው እኛን ለእንግሊዞችና ለጣሊያኖች አሳልፈው እስከ ሰጡበት ጊዜ ድረስ የነበርነው ከፈረንሳይ ጋር ነው።

በመጨረሻም ጣሊያኖቹ ኢትዮጵያ ላይ እያየሉ መምጣታቸውን ሲያስተውሉ ፈረንሳዮች ጣሊያን ኢትዮጵያን በቅኝ ብትይዛት አይከፋንም ማለት ጀመሩ። ‹‹ሊግ ኦፍ ኔሽን››ም የእነርሱ ስለሆነ ወደእነርሱ አዘነበለ። ስለዚህ ኢትዮጵያ የጣሊያን ግዛት ናት የሚለውን ተቀበሉ። ኢትዮጵያ ላይ የመጀመሪያውና ትልቁ ክህደት የተፈጸመብን በፈረንሳይ ነው።

አዲስ ዘመን፡- አጼ ኃይለሥላሴም ከመጡ በኋላ?

አምባሳደር ጥሩነህ፡– በወቅቱ ንጉሱ አቤቱታ ቢያቀርቡም ምንም ሊፈይድ አልቻለም። አጼ ኃይለሥላሴ ‹‹ሊግ ኦፍ ኔሽን›› ያድነናል፤ ምክንያቱም ይህ ድርጅት ጉልበት የሌላቸውን ታዳጊ ሀገራት ያግዛል በሚል ‹‹ሊግ ኦፍ ኔሽን›› ለመቀላቀል ጥያቄ አቀረቡ። በወቅቱ ኢትዮጵያ አልሰለጠነችም፤ ከዚያም የተነሳ የዓለም አቀፍ ማኅበር አባል ልትሆን አትችልም፤ አሁንም ባሪያ እየነገደች ነው፤ ዴሞክራሲ የለም፤ ሰብዓዊ መብትም የሚባል ነገር የለም በሚሉ ምክንያቶች ኢትዮጵያን ላለመቀበል ከፍተኛ ውዝግብ ተፈጥሮ ነበር። ይሁንና ቀደም ሲል በብዙ ነገር ይረዱን እንደነበሩት ፈረንሳዮች አይነት ሩሲያ ረድታን ወደ ‹‹ሊግ ኦፍ ኔሽን›› ገባን።

ቀደም ሲል እንደገለጽኩልሽ ፈረንሳይ ደጋፊያችን የነበረች ብትሆንም በኋላ ላይ ግን በወቅቱ አብረን በጋራ ለመጠቀም የሠራነውን የባቡር መስመር ዘጋችብን። እንግሊዝም ብትሆን ጣሊያን በወረረችን ጊዜ ከኢትዮጵያውያን አርበኞች ጋር ጣሊያንን ተዋግታ ያስወጣችው ለእኛ ብላ አይደለም። አስቀድሜ እንደጠቀስኩልሽ ሁሉም ተስማምቶ እንደመስዋዕት በግ አሳልፈው ከሰጡን በኋላ ነው የማስመሰል ትግበራውን የቀጠሉት።

እኛ ሁሌም ቢሆን አንዱ ሲገፋን ወደሌላ እንጠጋለን። እንግሊዝን ለመቋቋም ስንል ምንም እንኳ ከድተውን የነበሩ ቢሆንም ከፈረንሳይ ጋር ቆመን ነበር። እንግሊዞች ደግሞ ሊረዱን በመጡ ጊዜ ከቅኝ ግዛት ትንሽ በተሻለ እንደ ፕሮቴክቶሬት (ጥበቃ) አይነት ያዙን።

በወቅቱ እኛ ማድረግ የጀመርነው ፊታችንን ወደ አሜሪካ ማዞር ነው። ብር ስጡንና የራሳችንን ገንዘብ እናሳትም ማለትም ጀመርን። ምንም እንኳ እንግሊዞች ሳይፈቅዱ ከሌላ ሀገር ጋር መገናኘት አይቻልም የሚል እሳቤ ቢኖርም ጥበብ በተሞላበት መንገድ ንጉሱ ይነጋገሩ ነበር። ከዚያም የአሜሪካን ድጋፍ እያየለ መምጣት ጀመረ። ስለዚህም የኢትዮጵያን ነጻነት ማረጋገጥ የቻልነው ብልጠት በተሞላበት የአመራር ጥበብ ነው።

ኢትዮጵያን ከፍ ያለ ፈተና ባጋጠማት ጊዜ የደርግ መንግስት ወደስልጣ ሊመጣ በተቃረበ ጊዜ ነበር። ወቅቱ በጣም ግራ የሚያጋባ ነበር። መሳሪያ ከአሜሪካኑ ዘንድ ለማግኘት ችግር የሆነበት እና ከዚህ የተነሳ እርዳታም ለማግኘትም መሯሯጥ የበዛበት ነበር፤ ይሁንና አልተሳካም።

በወቅቱ ሩሲያ ሱማሊያን እስከአፍንጫቸው አስታጥቃ ነበር። በኢትዮጵያ አካባቢ ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ደግሞ በአረቦች እርዳታ በጣም አይለው ነበር። በአንድ በኩል ሩሲያ ያስታጠቀቻት ሱማሊያ አለች፤ በሌላ በኩል ደግሞ አረብ ያስታጠቀው በኢትዮጵያ አካባቢ ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ተዋጊዎች አሉ። ከዚህ የተነሳ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በእጅጉ ተዳከመ፤ አሜሪካ መሣሪያ ከለከለችን። በሀገር ውስጥም ውንዥብር ነበር፤ ሁኔታው ሀገሪቱን ከቀውስም በላይ አደረጋት። በዚህ ላይ ደግሞ እኛ ኢትዮጵያውያን የሌሎች ሴራ እምብዛም አይገባንም ነበር። ኮሚኒዝም ይምጣ አንዴ ሶሻሊዝም ይምጣ እንበል እንጂ በምን መልኩ እንደሚመጣ ብዙም እውቀቱ አልነበረንም።

በደርግ ጊዜ ከሩሲያ ጋር በመሆን ሶሻሊስት ሀገር ሆነን። በወቅቱ ከዚህች ሀገር መሣሪያ እናገኝ ነበር፤ የቀድሞው የሶቬት ኅብረት መሪ ሚካኤል ጎርቫቾቭ መጥተው ከምዕራባውያኑ ጋር ስምምነት ፈጠሩና እኛ ዝም ብለን መሳሪያ አንሰጥም ወደማለቱ አዘነበሉ። ልክ አሜሪካውያኑ እንደከለከሉን ሁሉ መሳሪያ ከፈለጋችሁ ከፍላችሁ ወስዱ አሉን። ምክንያቱም እርሳቸው ግንኙነታቸውን ከምዕራባውያኑ ጋር በማድረጋቸው ነው።

ሀገራቸውንም ለምዕራባውያኑ አሳልፈው በመስጠታቸው ተፍረከረኩ፤ ተከፋፈሉም። ከምዕራባውያኑ ጋር ኅብረት ፈጥረው የነበረውም ሀገሬን ሀብታምና ዴሞክራሲያዊ አድርጋለሁ በሚል እሳቤ ነበር። ነገር ግን ምዕራባውያኑ በብልጣብልጥነት ሲያጨበጭቡላቸው መሪው የማያውቁበትን ዳንስ መደነስ ጀመሩ። ከዚያ የተነሳ እነዩክሬንን በወቅቱ ነጻ እንዲወጡም ያደረጉት እርሳቸው ናቸው። ስለዚህም የደርግ የሶሻሊዝም ምርጫ ውጤት ሳያመጣ ለውድቀቱም መንስኤ ሆነ። በኢህአዴግ ዘመን ኢትዮጵያ ከሁሉም ጋር የተሻለ ግንኙነት አላት ማለት ይቻላል። በወቅቱ ከአሜሪካኖች ጋር ከፍተኛ ግንኙነት እንድንፈጥርም አስችሏል።

አዲስ ዘመን፡- ባለፉት አምስት ዓመታት ከለውጡ በኋላ ያስተዋሉት የዲፕሎማሲው ሥራ እንዴት ይገለጻል?

አምባሳደር ጥሩነህ፡- የዶክተር ዐቢይን አገዛዝ ፈተና የሆነበት የውጪው ዓለም ሳይሆን የውስጡ ጉዳይ ነው። በኢህአዴግ እምቢታ የቆየውን ሊበራል የማድረግ ሁኔታ እና ከኤርትራ ጋር ሰላም ማስፈኑን እርሳቸው ማሳካት ችለዋል። በዚህ ወቅት ደግሞ በምዕራባውያኑ በኩል የመማረክ ሁኔታ መስተዋል ጀመረ።

ይሁንና በመሀል መሸካከር መጣ፤ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ የኢትዮጵያን መንግሥት ለግብጽ ፈርም በማለታቸው ነው።

ይህ ደግሞ ለመንግሥት ቀይ መስመር የማለፍ ያህልና የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ ዓይን ብሌኑ የሚጠብቀው ጉዳይ በመሆኑ ሕዝቡ ከኪሱ ገንዘብ እያወጣ የሠራውንና የስንት ዓመት ሕልሙን ለግብጽ አሳልፌ አልሰጥም በሚል ዶክተር ዐቢይ አቋም ያዙ።

ግብጽ ፍላጎቷ የነበረው አብረን እናስተዳድር፤ በጋራ ስም ይሁን የሚል ነው። በተለይ ኢትዮጵያ የምትሠራው ነገር ሁሉ ግብጽን እያስፈቀደች ይሁን ብለውም ነበር። ይህ ደግሞ በፍጹም የማይሆን ነው። በዚህ ሁሉ ግን የዶክተር ዐቢይ ጥንካሬ ያስደነግጣቸው ነበር። በመሆኑም በኢኮኖሚው አዳክመው ሌላ መንግሥት እንዲመሠረት ፍላጎት ነበራቸው፤ ከዚህ የተነሳ የቀድሞው ኢህአዴግ ተመልሶ እንዲመጣ ይፈልጉ ነበር። ይህን ለማድረግ ደግሞ እርስ በእርስ እንድንናከስ እያደረጉን ነው።

አዲስ ዘመን፡- ባለፉት አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ እንደ ዓለምም ያጋጠማት የኮቪድ ችግር፤ ብሎም ጦርነቱም ነበር፤ ይህ በመሆኑ ኢኮኖሚዋን ፈትኗል፤ በዚህ ጊዜ ያስተዋሉት የዲፕሎማሲ አካሄድ እንዴት ይገለጻል?

አምባሳደር ጥሩነህ፡– ያ ሁሉ ግፊት ቢኖርም ከዚያ በተጨማሪ በእኛ ላይ የተመዘዘብን ጎራዴ ስለታም ነው፤ ይሁንና አንገታችንን ሊቆርጠው አልቻለም። እርግጥ ነው ኮቪዱም ሆነ ጦርነቱ እንኳ እያለ በአፍሪካ ኢኮኖሚያቸው እያደገ ነው ከሚባሉት ሀገራት መካከል እንገኛለን። ምንም እንኳ ኮቪዱ ከሌላው የዓለም ክፍል ጋር እኩል የነካን ብንሆንም ጦርነቱ፣ በሕዳሴ ግድብ ላይ ሲያደርስብን የነበረው ጫና እና የውስጥ ሽኩቻ ሁሉ እያለ ኢኮኖሚያችን ከፍ ያለ በመሆኑ ይህ የሚያሳየን የመንግሥትን ትጋትና በቁርጠኝነት እንዲሁም ትጉ አመራርነትና ጥበብ ነው።

በተለይ ደግሞ ቴሌንና ባንክን የመሰሉ ተቋማትን ሊበራላይዝ ማድረግ መጀመራችን ሀገሪቱ አጥብቃ የዘጋችውን በሯን እየከፈተች ነው በሚል ተስፋ የሚጣልባት ሀገር መሆን ችላለች። ኢትዮጵያ እያሳየች ባለው ዲፕሎማሲያዊ አካሄድም የተቀረው የዓለም ክፍል ሊያጣት አይፈልግም። ኢትዮጵያን ማጣት ማለት ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትን ማጣት ነው በሚልም እሳቤ ከእኛ ጋር የሚሠሩ በርከት እያሉ ነው።

አዲስ ዘመን፡- እንደሚታወቀው ሩሲያ ኢትዮጵያን በተመለከተ በጸጥታው ምክር ቤት በሚነሱ ጉዳዮች ድጋፏን በመስጠት ከጎናችን ስትቆም ነበር፤ ቻይናም እንዲሁ ድጋፍ ስታደርግ ነበር፤ የሁለቱን ወዳጅነት እንዴት ያዩታል?

አምባሳደር ጥሩነህ፡– ለምሳሌ ሩሲያን ብንጠቅስ ከምታደርገው ነገር በመነሳት ገሚሱ ሀገሪቱ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ በመሆኗ ነው ያንን የምታደርገው ይላሉ፤ ሌላው ደግሞ ሌላ ይላል፤ በእኔ በኩል ግን የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ መሆኗ አንድ ነገር ሊሆን ይችላል። ከዛ ሌላ ግን ምዕራባውያኑን ለመጋፋት የምትችል ሀገር ኢትዮጵያ ናት የሚል ድምዳሜም ስላላቸው ይመስለኛል።

ሩሲያዎች ከድሮ ጀምሮ አንድም ጊዜ ቢሆን ከእኛ ተለይተው አያውቅም። ከሱዳን ጋር በነበረው ጦርነት በአጼ ዮሐንስ ጊዜ መሣሪያ ሰጥተውናል። በአድዋ ጊዜም እንዲሁ መሣሪያ በመስጠት ድጋፋቸውን አሳይተውናል።

በጣሊያን ጦርነት ጊዜም ሁሉም ሀገራት የጣሊያን ቅኝ ተገዥ ናት ብለው በ‹‹ሊግ ኦፍ ኔሽን›› አውጀውብን ነበር። በወቅቱ አይሆንም ካሉ አምስት ሀገራት መካከል አንዷ ሩሲያ ነበረች። በሱማሊያ ጦርነት ሆነ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ድርድርም ጊዜ ድጋፋቸው አልተለየንም። በተለይ ማዕቀብ እንዳይደረግብን በብዙ ደግፈውናል። ለመጣብን መከራ ሁሉ የደረሱልን ናቸው ማለት የሚቀል ነው። በምላሹ ግን በእኛ በኩል ብዙም አላደረግንላቸውም። በዩክሬንና በሩሲያ መካከል በተደረገው ጦርነት የሚመለከት ጉዳይ ላይ እንኳ ትልቁ ያደረግነው ነገር ቢኖር ድምጸ ተአቅቦ ማድረግ ነው፤ ከዚያ በፊት ደግሞ ምንም አይነት ድምጽ ላለመስጠት ትተን መውጣታችን የሚታወስ ቢሆንም የተሻለ እርምጃ ነው ለማለት አልሞክርም።

ከቻይና ጋር ያለን ግንኙነት የሚያስፈልገን ነው፤ እኛ ብቻ ሳንሆን አሜሪካ ራሷ ያለቻይና መኖር አትችልም። ከጥቂት ጊዜ በኋላ በዓለም ኢኮኖሚ የበላይ የምትሆነው ቻይና ናት። በተለይ ለታዳጊ ሀገሮች ብድርም ሆነ ድጋፍ በማድረግ ላይ ናት። ፖሊሲዋም ጥሩ የሚባል ዓይነት ነው፤ እንዲህም ስል ለምሳሌ በሀገር የውስጥ ጉዳይ መግባት አትፈልግም፤ የምትለው ነገር ቢኖር ዓለምን ለሰው ልጅ ምቹ እናድርግ ነው። የኢኮኖሚ ማዕቀብ ማድረግም አትፈልግም። ከዚህ የተነሳ የምዕራቡ ጫና ያንገሸገሸው ሁሉ ፊቱን ወደቻይና በማድረግ ላይ ነው።

ቻይና ብዙ እያደረገችልን ነው። ከቻይና ብድር ሳናገኝ የሰራነው ልማት የለም፤ ስለሆነም የሁለቱንም ሀገር ጉዳይ አጥብቀን መያዝ አለብን። ለነገም ተገን የሚሆኑ ናቸው።

አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት ዲፕሎማሲያችን ምን መሆን አለበት ይላሉ?

አምባሳደር ጥሩነህ፡- መጥፎውን አስወግደን ጥሩ ነገር ለመጠቀም ምን ማድረግ አለብን የሚለውን ማጤን መልካም ነው። መፍትሔው ሌትና ቀን የዓለምን ሁኔታ ሒደት መመርመር፣ ማየት፣ ማጤን ነው። ከዚያም እንደየአስፈላጊነቱ መፍትሔ ደግሞ ማበጀት ያስፈልጋል። እያንዳንዱን ጉዳይ በማየት እርምጃ ለመውሰድ አስቀድሞ የሁኔታዎችን አቅጣጫ ማጤን ይገባል። እስካሁን እየተጓዝንበት ያለው መስመር ጥሩ የሚባል ነው፤ የበለጠ ግን ማጠናከር ያስፈልጋል።

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ሀገር መሆኗ ከምዕራቡ ዓለም ይነጥላታል የሚሉ አካላት አሉ፤ የእርስዎ አተያይ ምንድን ነው?

አምባሳደር ጥሩነህ፡– ምዕራባውያኑ የኢትዮጵያ ነፍስ አባት አይደሉም። ጥቅማችንን የምናሰፋበትን አቅጣጫ ሁሉ የመቃኘት መብት አለን። ደግሞም እኛ የዚያን ያህል ከምዕራቡ ክፍል የፖለቲካም ሆነ የኢኮኖሚ ጥቅም የምናገኝ አይደለንም። እኛ ለራሳችን ጥቅም የምናደርገው ሁሉ ምዕራቡን ያስቀይመዋል ከተባለ ጥቅማችንን አሳልፈን ለእነርሱ ለመስጠት ዝግጁ የሆንን ሀገር ነን ማለት ነውና ይህ መሆን የለበትም።

በቅርቡ በፖለቲካም ሆነ በመሳሪያ ለመደገፍ አሜሪካ ከሕንድ ጋር ተዋውላለች። ሕንድ ይህን ማድረጓ የብሪክስ አባልነቷን እንድትለውጥ አላደረጋትም። እኛ ዘንድ ሲሆን ምን አዲስ ነገር አለው? ከምዕራባውያን ጋር ያለን የተለየ ግንኙነትስ የሚባለው ምንድን ነው? እርግጥ ነው የእህል እርዳታ ይሰጡናል። ይህ ሁሉ መሬትና ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ይዘን በአግባቡ በማቀናጀት ራሳችንን መመገብ ባለመቻላችን እየለመንን እንበላለን። ልመናው ደግሞ እኛን ይጎዳል።

ሌላው ደግሞ ሌሎች ሀገሮች ሁሉ ለምሳሌ ከሳዑዲ አረቢያ ጋር እንዲሁም ከአረብ ኢሜሬቶች ጋር ምዕራባውያኑ ያላቸው ግንኙነት በጣም ስትራቴጂያዊ ነው። በብዙ ጥቅምም የተቆላለፈ ነው። በዶላር ካልሆነ በስተቀር ጋዝን ለሌላ አልሸጥም እስከሚል ቃል መገባባት የደረሰ ነው። እነርሱም የደህንነት ዋስትና ለመስጠት ተስማምተዋል። ይህ የሆነው ምናልባትም ከግማሽ ምዕተ ዓመት አካባቢ በፊት ነው። ይህ ሆኖ እያለ እነርሱ ላይ ጫና ሳይፈጠር ኢትዮጵያ ላይ የተለየ ነገር የሚመጣበት ምክንያት አይታየኝም። ከእነዚህ ሀገራት በላይ ኢትዮጵያ ከምዕራባውያኑ ጋር ያደረገችው የጥቅም ትስስር እንኳ የለም።

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ሀገር ሆና የመመረጧን ጉዳይ ከዲፕሎማሲው አኳያ እንዴት ይመዝኑታል

አምባሳደር ጥሩነህ፡– እጅግ በጣም ከፍተኛ ጥቅም የሚሰጥ እና ትልቅ ደረጃ ያለው እንደሆነ ነው የምረዳው። ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗን ባለፉት አምስት ዓመታት ከተደረገው የዲፕሎማሲ ስኬት ልቆ ያገኘሁት ድል ነው። እጅግ በጣም ከፍተኛ ውጤት ነው። ከዚህ በፊት እንዲህ ዓይነት ድልን አልተቀናጀንም ማለት እችላለሁ።

እንዲህ ዓይነቱ ሥራ በከፍተኛ ደረጃ የሚሠራ እንደመሆኑ በተሠራው የላቀ ሥራ የኢትዮጵያ መንግሥት ሊመሰገን ይገባዋል ባይ ነኝ። የተገኘው ውጤት ግዙፍ ነው። በመሆኑም ይህ ከዲፕሎማሲው አንጻር እስካሁን ድረስ ባለፉት አራትና አምስት ዓመታት ውስጥ ያላየሁት ዓይነት ስኬት ነው። የብሪክስ አባልነት ጉዳይ ከዲፕሎማሲው አንጻር ባለፉት አምስት ዓመታት ያላየሁት አይነት ስኬት ነው።

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል በመሆኗ በኢኮኖሚው በኩል ምን ልትጠቀም ትችላለች?

አምባሳደር ጥሩነህ፡- አንዲት አገር ከሌላ አንድ አገር ጋር እንኳ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቴን አሻሽዬ ሁለንተናዊ የሆነ ጥቅም አገኛለሁ በሚል አምባሳደሯን ወደሌላ ሀገር በመላክ ተጠቃሚ ለመሆን ትጥራለች።

ብሪክስ የሚባለው ጥምረት ደግሞ በዓለም ላይ እየወጡ ያሉ ኃያላን ሀገራት እየተሰባሰቡበት ያለ ነው። ይህ ጥምረት በዓለም ላይ ከሚገኘው የሕዝብ ብዛት አኳያ ሲታይ ከ40 በመቶ በላይ ነው። ሁለተኛው ደግሞ በሀብት ሲታይ በዚህ ጥምረት ያሉ ሀገራት ሀብት 31 በመቶ ነው።

ጂ7 የሚባሉ ሀገራት ሀብታም እና ኃያል የሚባሉ ሀገራት ስብስብ ሲሆኑ፤ የዚህን ያህል ሀብት የላቸውም፤ ከዚህ በተጨማሪ ከጂ7 ሀገራት ይልቅ የብሪክስ ስብስብ በፍጥነት እያደጉ ያሉ ሀገራት ናቸው። ለማደግም በጣም ከፍተኛ ተስፋ የተጣለባቸው ናቸው። እነቻይና እና ሕንድ የበለጠ ለማደግ ምቹ ሁኔታ ያላቸው ሀገራት ናቸው።

እንዲያውም በዓለም ላይ በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት እነዚህ ሀገራት በአግባቡ ሲቆራኙ 60 በመቶ የዓለምን ኢኮኖሚ ይይዛሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከዚህ በተጨማሪ ጥምረቱን ለመቀላቀል ያመለከቱ ሌሎች በኢኮኖሚያቸው ከፍ ያሉ እንደ ቬኒዜዌላ ዓይነት ሀገራት ሲቀላቀሉ ኢኮኖሚው 70 እና 80 በመቶ ይሆናል የሚል ግምት አለ።

እኛ እነዚህ ሀብታም ከሆኑ እና ከእኛ በጣም ከተሻሉ እንዲሁም በጣም በፍጥነት እያደጉ ካሉ ሀገራት ጋር መወዳጀትና መቧደን የሚፈጥርብን ችግር ሳይሆን ከፍ ያለ ጥቅምን ነው።

አንዳንዶች ይህ መንግሥት የሚያደርገውን መልካም ነገር ሁሉ መጥፎ ነው የሚሉ ናቸው። ይህንንም ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ይናገራሉ። አንዳንዶቹ የሚናገሩት ለምዕራባውያኑ ጥብቅና ቆመው ነው። መንግሥት ግን እየሠራ ያለው ለሕዝብ የሚጠቅም ሥራ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም።

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነቷ የተረጋገጠ በመሆኑ በጥምረቱ ብርቱ ተዋናይ ለመሆን ምን ይጠበቅባታል? ከጥምረቱ የምናገኘው ጥቅም እንደተጠበቀ ሆኖ እኛስ ምን እናበረክታለን?

አምባሳደር ጥሩነህ፡- በመጀመሪያ ደረጃ ኢትዮጵያን የብሪክስ አባል አድርገው ሲቀበሏት ዓይናቸውን ጨፍነው አይደለም። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሀገራት ተጽዕኖ መፍጠር የምትችል ሀገር ነበረች፣ አሁንም እየፈጠረች ናት። ወደፊትም ትፈጥራለች። ያንን ያላትን ተጽዕኖ ፈጣሪነቷን ይዛ ትመጣለች የሚል እምነት ስላላቸው ነው።

የፖለቲካ ተጽዕኖ ፈጣሪነቷ አለ። በሰላምና ደህንነት ዙሪያ የሠራቸው ሥራ እና እየሠራችው ያለ ሥራ በራሱ ከፍተኛ ነው። የብሪክስ አባል ሀገራት የሚመሩበት ዋና መርሆዎች ሦስት ናቸው። የመጀመሪያው ተከታታይነት ያለው እድገት ሁለተኛው ሰላምና ደህንነት ሲሆን፤ ሦስተኛው ደግሞ በቴክኖሎጂ መዘመን ነው። እነዚህ ሦስቱም ለእኛ የሚስማሙና የሚጥቅሙ ናቸው።

ከዚያ ውስጥ ሰላምና ደህንነት ላይ እኛ እየደረሰብን ያለ አሳዛኝ ነገር አለ። ይሁንና በቅርቡ እንደሚፈታ ተስፋ አደርጋለሁ። ነገ የተሻለ ደረጃ ላይ እንደርሳለን። ስለዚህ በአፍሪካ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሰላምና ጸጥታ በከፍተኛ ሁኔታ የድርሻችንን እንወጣለን። ይህንን የላቀ ድርሻችንን ይዘን እንቀርባለን።

ሌላው በኢኮኖሚ ደረጃ ሲመዘን ደግሞ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ እድገት ፈጣን የሚባል ነው። ከ15 እና ከ20 ዓመት በፊት ኢትዮጵያ ከዓለም ሀገራት ኢኮኖሚያቸው ከመጨረሻው ናቸው ከሚባሉ ሦስተኛ ላይ የምትገኝ የነበረች ሀገር ናት። በተመሳሳይ ከአፍሪካ መጨረሻዎቹ ሀገራት ሦስተኛ ደረጃ ላይ ነበርን።

በአሁኑ ወቅት ከአፍሪካ በኢኮኖሚ ከላይ ወደታች ሲቆጠር ሦስተኛ ደረጃ ላይ እንገኛለን። ትንሽ እኛን አልፈው የሚታዩት ግብጽ፣ ናይጄሪያና ደቡብ አፍሪካ ናቸው። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ ያላትን ትልቅ ተስፋ የሚያሳይ ነው። ጥምረቱም አባል እንድንሆን ያደረገን ያንን ይዘን እንደምንመጣ ስላወቀ ነው። ምክንያቱም በአሁኑ ደረጃ በአፍሪካም ሆነ በሌላው አህጉር ለአባልነት መመረጥ የሚችሉ በኢኮኖሚያቸው ከእኛ የተሻሉ አሉ። እኛ እንሻላለን እንዴት ኢትዮጵያን ትቀበላለችሁ ብለውም የተከራከሩ ሀገራት አሉ። ነገር ግን ጥምረቱ ኢትዮጵያን የተቀበለው ይህን ሁሉ እያየ ነው። ስለዚህ የእኛ የሆነን እና ልንሰጣቸው ያለውን ነገር መኖሩን አምነው ነው የተቀበሉን ማለት እችላለሁ።

አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ ‹‹የዲፕሎማሲ ፋና›› በሚል ርዕስ ያልዎን ልምድና እውቀት በመጠቀም ለአንባቢያን መጽሐፍ እነሆ ብለዋል፤ አንኳር ጉዳዩ ምንድን ነው?

አምባሳደር ጥሩነህ፡– መጽሐፉን መጻፍ የጀመርኩት ከሁለት ዓመት በፊት ነው። ይሁንና አንድ ዓመት ከጤና ጋር ተያይዞ ትንሽ አመም ስላደረገኝ ጥቂት ጊዜ ተጓትቷል፤ መጽሐፉ ዲፕሎማሲያችን ቀደም ሲል ምን አይነት ነበር? ምን ዓይነት ችግርስ አጋጥሞን ነበር? የሚለውን ለመዳሰስ ሞክሯል። በችግራችን ወቅት ከጎናችን የቆመው ማን ነበር? ማንስ ከዳን? የሚሉትንም ለማሳየት ሞክሯል።

በተለይ አንድ 15 ዓመት ያህል ሳገለግል የነበረው በብራስልስ እና በኒዮርክ ነው። በዛ ቦታ በርካታ ነገር ይነሳል፤ ይሰማልምና ያንን አካባቢም ለመግለጽ ሞክሬያለሁ። በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ በብዙ የምትወደድ ሀገር አይደለችም፤ ኢትዮጵያ የነጮች የበላይነት እንዳይኖር ለጥቁሮች አርዓያ የሆነች ሀገር ናት፤ ከዚህ የተነሳ ምዕራቡ ብዙም አይወደንም። ግብጽና እነግብጽ አካባቢ ያሉት በእኛ ላይ የበላይነታቸውን ለማሳየት ሲጥሩ በፈለጉት መንገድ አንሄድላቸውም። ግብጽም የአረብ ሀገሮች በውሃችን ላይ ጫና ለመፍጠር ይጥራሉ። ከዚህ የተነሳ በቅርብም በሩቅም ብዙ አንወደድም። ያሉን ከሰሀራ በታች ያሉ ሀገራት ሲሆኑ ከእነርሱ ጋር ሰላም ነን።

አዲስ ዘመን፡- መጽሐፍዎን በዲፕሎማሲው ዘርፍ ከጻፉ ጸሐፍት ምን ልዩ ያደርገዋል?

አምባሳደር ጥሩነህ፡- እኔ የዲፕሎማሲውን ሥራ በንባብ ከሚገኘው እውቀት በዘለለ ተዋናዩ ስለሆንኩ በተግባር ማወቄ ልዩ ያደርገዋል። ለጉዳዩ ባይተዋር አይደለሁም። በመጽሐፌ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ጉዳት አድርሰዋል ያልኳቸውን አካላት ስም በመጥራት እውነቱን ለመጻፍ ሞክሬያለሁ። ማንም ይጎዳኛል በሚል የተውኩት ነገር የለም፤ እውነቱን ጽፌያለሁ። መጽሐፉን ሰው አንብቦ ከሚሰጠው አስተያየትም በመነሳት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ዘርዘር አድርጌ ለመጻፍ እሞክራለሁ።

አዲስ ዘመን፡- ከልብ አመሰግናለሁ።

አምባሳደር ጥሩነህ፡- የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ደጋግሞ እንዲህ አይነት እድል ስለሰጠኝ እኔም ከልብ አመሰግናለሁ።

 አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ነሃሴ 25/2015

Recommended For You