ብሪክስን በግራ የቤት ሥራን በቀኝ ፤

በጎርጎሮሳዊያኑ የዘመን አቆጣጠር በ1950ዎቹ የአሜሪካንና የሶቭየት ሕብረትን ጉተታ ለመቃወም 120 ሀገራት የገለልተኛ ሀገራትን ንቅናቄ ፈጥረዋል። ደርግ ጭልጥ ብሎ የሶቭየቱን ጎራ ተቀላቅሎ የነበር ቢሆንም ዛሬም ሀገራችን የዚህ ንቅናቄ አባል ናት። ይህ ስብስብ ከዓለም ሕዝብ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን የያዘ። ከጥቅል የዓለም ምርት ደግሞ የአውሮፓ ሕብረትን በልጦ 18 በመቶ ድርሻ ያለው ነው ። ይሁንና የተፈለገውን ያህል ውጤታማ ሊሆን አልቻለም። ለዚህ ነው ብሪክስ ወደፊት እየመጣ ያለው።

የብሪክ/BRIC ስረወ-ምህጻረ ቃልም ሆነ ጽንሰ ሀሳብ የተፈጠረው በጎልድማን ሳክስ የኢኮኖሚ ባለሙያ ጂም ኦኔል በጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር 2001 ዓ.ም ሲሆን፤ ብራዚልን፣ ራሽያን፣ ሕንድና ቻይናን ያካተተ የኢኮኖሚያዊ ስብስብ ሃሳብ ነው። ይህ እሳቤ በ2009 ዓ.ም እውን ሆነ። በዓመቱ 2010 ዓ.ም ደቡብ አፍሪካን አካቶ ብሪክስ/BRICS ሆነ። የምዕራባውያን ጉልሃን ወይም ኤሊቶች በስብስቡ የቻይናን የበላይነት ለመግለጽ ብሪክስን ቻይና ሲደመር አራት ወይም China + 4 ይሉታል። በደቡብ አፍሪካ ጆሀንስበርግ በተካሄደው የብሪክስ 15ኛ ጉባኤ ሀገራችንን ጨምሮ ስድስት አዲስ አባላትን ሲጨምር ደግሞ China + 10 ተለዋጭ ስያሜ ሰጥተውታል። ምዕራባውያን እነሱ ቡራኬ ያልሰጡትን ስብስብ እንዲህ በነገር ይሸነቁጡታል።

በ”The Ethiopian Economist View”ድረ ገጻቸው ቢዝነስ፣ ኢኮኖሚክስና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በመጻፍ፤ ማህበራዊ ሚዲያውን በተለይ ፌስቡክን ለበጎ ዓላማ በማዋል የሚታወቁት የኢኮኖሚክስ ባለሙያው አቶ ዋሲሁን በላይ፤ የተጨመሩት 6 አዲስ አባል ሀገራት በጠቅላላ 410 ሚሊየን ሕዝብ ያላቸው በመሆኑ የአባል ሀገራት ሕዝብ ብዛትን ወደ 4.2 ቢሊየን ያደርሱታል። ነባር አባል ሀገራቱ ያላቸው ጠቅላላ የምርት መጠን (GDP) 26 ትሪሊዮን ዶላር ይደርሳል (ከዓለም ጠቅላላ ምርት መጠን ውስጥ 26 ከመቶ ነው)። ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ጀምሮ እስከ ቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ድረስ የነበረው የዓለም ሀገራት በርዕዩተ ዓለም የመቧደን አይነት አዝማሚያ ያለው የሚመስል ሆኖ አባል ሀገራቱ በዚህ ወቅት ዓለም በጥቂት ሀገራት የበላይነት መመራቷ ማብቃት አለበት ሲሉ ይሞግታሉ።

አዲሱን አሰላለፍ ወይም BRICSን የመቀላቀል ዕድሎችንና ስጋቶችን ማመዛዘን ይገባል፡፡ እድሎች፦ የተሻሻለ የኢኮኖሚ ትብብር ሊፈጠር ይችላል። ለኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ንግድን፣ የውጪ ኢንቨስትመንትን እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማጎልበት ኢኮኖሚያዊ ትብብር እንዲጨምር ያደርግ ይሆናል። ይህ አጋርነት ቀጣይነት ያለው የኢንዱስትሪ ልማትን ማበረታታት፣ የሥራ እድል መፍጠር እና ፈጠራን ማጎልበት በመጨረሻም የረዥም ጊዜ የኢኮኖሚ እድገት አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይችላል። የመሠረተ ልማት ግንባታ ተስፋዎች ሊኖሩት ይችላል።

የቀደሙ የBRICS አባል ሀገራት (አዲስ የቀላቀሉትንም ጨምሮ) በመሠረተ ልማት ዝርጋታ ላይ ከፍተኛ እውቀት እና ሀብቶች አሏቸው። ኢትዮጵያ ህብረቱን በመቀላቀሏ ከፍተኛ የመሠረተ ልማት ጉድለትን ለመፍታት ወሳኝ የሆነውን ሀብት፣ እውቀት እና ልምድ ልታገኝ ትችላለች። ከአዲሱ የBRICS ልማት ባንክ (New Development Bank) የገንዘብ ድጋፍ በማግኘት የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ለማፋጠን አስደሳች ዕድል ሊፈጥርላት ይችላል ይሉናል ባለሙያው።

ለምሳሌ፡- የኢትዮጵያ ከዓለም ባንክ ብድር እና ድጋፍ ስታገኝ የኖረች ቢሆንም ጠንካራ ቅድመ ሁኔታ ያለው ብድር ከመሆኑ በተጨማሪ የበለጸጉት ሀገራት ብድሩን እንደ ርዕዩተ ዓለም ማስፈጸሚያ እና ጫና መፍጠሪያ አድርገው ይጠቀማሉ፡፡ ለነገሩ ረዘም ላሉ ዓመታት የብድር ፍላጎቶቿ/እድሎቿ ወደ ቻይና ዞረዋል (የብዙ አፍሪካ ሀገራት አጋርነት ወደ ቻይና የመዞር በቻይና አፍሪካ ጉባኤ እና በዩኤስ አፍሪካ ጉባኤ ላይ በተደጋጋሚ የሚነሳ ጉዳይ ነው)፡፡ ይህን እድል ወደ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነት ለመቀየር ጠንካራ የማምረት አቅም መፍጠር ያስፈልጋል።

ስጋቶች፦የምዕራባውያን ውጪ ባሉ ሀገሮች ላይ ተመሳሳይ ጥገኝነት መፍጠር አባልነትን ተከትሎ የምዕራብ ሀገራትም ሆኑ ዓለም አቀፍ ተቋማት በውሳኔው ደስተኛ ያለመሆን አዝማማያ ሊኖራቸው ስለሚችል (ቅጣታቸውን ብድር እና እርዳታ ወደ መከልከል የሚያዞሩት ከሆነ) ኢትዮጵያ ወደ ሌሎቹ የBRICS አባል ሀገራት ይበልጥ ጥገኝነቷን ማዞር ልትጀምር ትችላለች (በተለይ ወደ ቻይና! ይህ አዝማሚያ የBRICS አባል ከመሆንም በፊት እየታየ የመጣ ነው)፡፡

የንግድ ግንኙነት መዳረሻዎች መለወጥ፦ BRICSን መቀላቀል የንግድ መዳረሻዎችን ወደ አባል ሀገራት ገበያዎች አቅጣጫ እንዲቀይር ሊያደርግ ይችላል። ይህ ለረጂም ጊዜ የቆየውን የኢትዮጵያ እና የምዕራባውያን እና የአሜሪካ የንግድ ግንኙነቶችን ሊያደናቅፍ ይችላል፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ የውጭ ገበያ መዳረሻዎቿን በማስፋት የንግድ ልውውጥ እንዲጨምር እና በነጠላ የንግድ አጋሮች ላይ ያላትን ነባር ጥገኝነት እንዲቀንስ አዳዲስ ዕድሎችን ሊከፍትላትም ይችላል።

የመገለል ስጋት፡- BRICSን መቀላቀል እንደ የዓለም ባንክ እና የዓለም የገንዘብ ድርጅት ካሉ ምዕራባውያን ተቋማት ሊያስገልል እንደሚችል ማሰብ ያሻል። ይሁን እንጂ በBRICS ውስጥ የተመሰረተው አዲስ የልማት ባንክ (New Development Bank) ያሉ አማራጭ የፋይናንስ ዘዴዎች መፈጠራቸው እነዚህን ሥጋቶች ለመፍታት እና ለኢትዮጵያ ለመሠረተ ልማትና ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በጣም አስፈላጊ የሆነውን ካፒታል (የውጭ ምንዛሬ) እንድታገኝ ሊያግዛትም ይችላል።

ከዚህ ቀደም ዩናይትድ ስቴትስ እና አንዳንድ ምዕራባውያን ኃያላን የአፍሪካ ሀገራት ከBRICS ጋር መስማማታቸው ስጋታቸው መሆኑን ገልጸዋል። የBRICS ታዋቂነት እያደገ በመምጣቱ ዩናይትድ ስቴትስ በአፍሪካ ላይ ያላት ተጽእኖ እየቀነሰ እንዳይሄድ ትሰጋለች። ስለሆነም አጋርነትን ማጠናከር፣ የእርዳታ ፖሊሲዎቻቸውን ማሻሻል ወይም ጥቅሞቻቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ ጫና ፈጣሪ ርምጃዎችን ሊወስዱ ይችላሉ ይሉናል አቶ ዋሲሁን።

የአሜሪካው ኢንቨስትመንት ባንክ ጎልድማን ሳክስ በሚቀጥሉት 50 ዓመታት የብሪክስ አባል ከሆኑ ሀገራት ቻይናና ሕንድ አሜሪካንን ቀድመው እንደ ቅደም ተከተላቸው በኢኮኖሚያቸው ዓለምን ይመራሉ ሲል ይተነብያል። ኢትዮጵያም በ6 ነጥብ 2 ትሪሊየን ዶላር ጥቅል የሀገር ውስጥ ምርት 17ኛ ደረጃ ላይ እንደምትቀመጥ ባንኩ አክሎ ጠቁሟል። ይህን ተስፋ የሰነቀች ሀገር አበክራ ብሪክስን ለመቀላቀል ማመልከቷና ተቀባይነትን ማግኘቷ ተገቢ ውሳኔ ብቻ ሳይሆን አርቆ አስተዋይነት ወይም ስትራቴጂካል ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም ።

የዓለም የንግድ ድርጅትን ለመቀላቀል ደጅ ስትጠና ሶስት አስርት ዓመታትን ላሳለፈች ሀገር፤ አሜሪካ ኢፍትሐዊ በሆነ አግባብ ከአጎዋ ወይም AGOA/The African Growth and Opportunity Act/ማለትም ከሰሃራ በታች ለሚገኙ ሀገራት ምርቶቻቸውን ከቀረጥ ነጻ ለአሜሪካ ገበያ እንዲያቀርቡ ከሚያስችል ዕድል ለታገደች ሀገር ፤ ለሀገር በቀል ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያዋ ከዓለም ባንክና ከዓለማቀፉ የገንዘብ ተቋም ልታገኘው የነበረ ከ10 ቢሊየን ዶላር በላይ ድጋፍና እርዳታ በአሜሪካና በምዕራባውያን በመታገዱ ከፍተኛ ዋጋ እየከፈለች ላለች ሀገር ቢሪክስን መቀላቀሏ ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ድል ነው። ለመሆኑ ይሄ ለብልጽግና ለእድገት ስትራቴጂካዊ መነሻም መውጫም የሆነው ብሪክስ ማን ነው።

“ብሪክስ” ወይም “BRICS” የሚለው ምህጻረ ቃል በማደግ ላይ ያሉ የአምስት ሀገራትን ስብስብ የሚወክል ሲሆን የየሀገራቱን የመጀመሪያ ሆሄ በመውሰድ የተፈጠረ መጠሪያ ነው ። ‘B’ን ከBrazil ፣ ‘R’ን ከRussia ፣ ‘I’ን ከIndia ፣ ‘C’ን ከChaina በመጨረሻም ‘S’ን ከSouth Africa በመውሰድ “BRICS”የሚለው ስያሜ ተመሠረተ። መጠሪያው የተፈጠረው በ2001 ዓ.ም ጂም ኦኔል በተባለ የኢኮኖሚክስ ጠበብት ሲሆን እነዚህ ሀገራት በ21ኛው መክዘ በዓለም ኢኮኖሚ ተጽዕኖ ፈጣሪ እንደሚሆኑ ተንብዮ ነበር። ከ22 ዓመታት በኋላ ዛሬ ያረጋገጥነው ትንበያው ጠብ ያላለና ትክክለኛ ሆኖ መሆኑን ነው።

የብሪክስ ሀገራት በተለያየ የጆኦግራፊ ክልል የሚገኙ ሲሆኑ፣ የሕዝብ ብዛታቸው ከ3 ቢሊየን በላይ ወይም ከዓለማችን ሕዝብ 40 በመቶውን የያዙ ፤ ከዓለማችን መሬት ወይም የብስ 26 በመቶ የሚሸፍኑ፤ ከዓለማችን ጥቅል የሀገር ውስጥ ምርት 23 በመቶ ድርሻ ያላቸው ናቸው። የተመሠረተበት ዋና ዓላማ በሀገራቱ መካከል ትብብር ለመፍጠርና ለመመካከር ነው። እርስ በርስ ለመነገድ፣ ኢንቨስት ለማድረግና ኢኮኖሚያዊ ልማትን ለማሳለጥ የተቋቋመ ስብስብ ነው። በየጊዜው በመደበኛነት በመሰባሰብ ስለ ኢኮኖሚያዊ እድገት፣ ቀጣይነት ስላለው ልማት፣ ስለዓለማቀፍ አመራርና ጸጥታ ይመክራሉ። ውሳኔዎችን ያሳልፋሉ።

ብሪክስ ከተቋቋመበት ዓላማ አንዱ ብሪክስ ባንክ የተሰኘ አዲስ ባንክ ማቋቋም ነው። ባንኩ ለአባል ሀገራቱ ሆነ ለሌሎች ለመሠረተ ልማት ግንባታ እና ቀጣይነት ላላቸው ልማቶች ብድር ያቀርባል። በአሜሪካና በምዕራባውያን ቅድመ ሁኔታዎችና እጅ ጥምዘዛዎች ስር ከወደቁት የዓለም ባንክና ዓለማቀፉ የገንዘብ ተቋም ተጽዕኖ በመላቀቅና አማራጭ የፋይናንስ ምንጭ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ከዚህ በተጨማሪ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ ኢነርጂ፣ ጤናና ትምህርት ላይ በስፋት የመሥራት ዕቅድ አለው። በሀገራቱ መካከል ትብብርንና የልምድ ልውውጥን ለማሳለጥ የጋራ ፎረም መመስረቱን ሰነዶች ያወሳሉ።

በአባላቱ መካከል መተባበርና መደጋገፍ እንዳለው ሁሉ ተግዳሮቶችና ልዩነቶችም አሉ። እያንዳንዱ ሀገር የየራሱ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ባህሪ ያለው መሆኑ የመጀመሪያው ተግዳሮት ሲሆን የጋራ ፍላጎት የሚንጸባረቅበት ወይም የየሀገራቱ ፍላጎት በእኔ እብስ በእኔ እብስ የሚሳሳቡበትና የሚራኮቱበት መድረክ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋትም አለ። ጂኦፖለቲካው ውጥረት፣ የንግድ ግጭቶችና የሚከተሉት የኢኮኖሚ ሥርዓት ለስብስቡ አንድነት ስጋቶች ናቸው። ያም አለ ይህ ብሪክስ በማደግ ላይ ላሉት 11 ሀገራት ድምጽም መድረክም ነው። ስጋታቸውን የሚያሳስቡበት፣ ግንኙነታቸውን የሚያጠናክሩበት፣ በዓለማቀፍ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ተገቢውን ስፍራና ትኩረት እንዲያገኙ የሚጠይቁበት የጋራ መድረክ ነው።

የብሪክስ አባል ሀገራትን ከፖለቲካ ይልቅ ምጣኔ ሃብት እንዳስተሳሰራቸው ተደጋግሞ ታይቷል። ከሰሞኑ የአባል ሀገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በደቡብ አፍሪካ ተገናኝተው ነበር። በዚህ ወቅትም ዓለም በምዕራባዊያን ከሚዘወረው ሥርዓት መውጣት እንዳለባት አንስተዋል። የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶር፤ ቡድኑ በጂኦፖለቲካ ውጥረት፣ በእኩልነት አለመኖር እና በደኅንነት ስጋት ውስጥ ላለው ዓለም ሃሳብ ይዞ መቅረቡን ገልጸዋል። የሕንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩላቸው ሱብራህማንያም ጃይሻንካር ስብስቡ ዓለም ባለብዙ መልክ ስለሆነች ባረጀው መንገድ አዲሱን አጀንዳ መፈጸም አይቻልም። ከምንጋፈጣቸው ችግሮች አንዱ የምጣኔ ሃብት ጉዳይ ሲሆን ብዙ ሀገራት በጥቂቶች በጎ ፈቃድ እንዲኖሩም ሆነዋል ብለዋል።

ብሪክስ ሲቋቋም ጂኦኢኮኖሚያው አሰላለፍ ተደርጎ ቢወሰድም ራሽያና ቻይና በአንድ ወገን አሜሪካና ምዕራባውያን በሌላ ወገን የገቡበት ፍጥጫና ግብግብ ብሪክስ ወደ ጂኦፖለቲካዊ ኃይል እንዳያጋድል እያሰጋ ይገኛል። የኢራን ወደ ቡድኑ መቀላቀል ደግሞ ለእስራኤልና ለአሜሪካ ምቾት የሚሰጥ ጉዳይ ካለመሆኑ ባሻገር፤ ዩኤኢና ሳውዲ አረቢያ ከአሜሪካ ጉያ ወጥተው ወደ ቻይና ማዘንበል መጀመራቸው በተለይ አሜሪካ ላይ ስጋት መፍጠሩ አይቀርም። ራሽያና ቻይና በአደባባይ ብሪክስ G- 7 ለመገዳደር የተቋቋመ ነው ማለታቸው የተቋቋመለት ዓላማ እንዳያስተው ስጋት መፍጠሩ አልቀረም።

ይህን በመፍራት ይመስላል ሕንድና ብራዚል ተሽቀዳድመው ብሪክስ G-7 ለመገዳደር ሳይሆን በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት አለኝታ እንዲሆን ነው ሲሉ ያስተባበሉት። ዳሩ ግን አባል ሀገራቱ የቻይናም ሆነ የራሽያ መሳሪያ ተደርገው እንዳይታዩ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል። ሀገራችን የብሪክስ አባል መሆኗ ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ድል ቢሆንም ያን ያህል ደግሞ ብዙ መነሁለል አያሻም። በተለያዩ ምክንያቶች የቻይና ኢኮኖሚ በመቀዛቀዝ ላይ መሆኑን አዳዲስ መረጃዎች እየወጡ ከመሆናቸው ባሻገር ወደኋላ ይንሸራተታል ተብሎ እየተሰጋ ነውና ጥንቃቄ ያሻል።

በአንጻሩ የአሜሪካ ኢኮኖሚ ደግሞ ከመቼውም ጊዜ በላይ በአስተማማኝ ሁኔታ ላይ መሆኑም ሊዘነጋ አይገባ። እንደ ሀገር ከሁለት ያጣ መሆንም ሊመጣ ይችላልና ሰከን ብሎ ዓለማቀፋዊ ሁኔታውን መተንተን ያስፈልጋል። ይልቅ የዓለማቀፍ ግንኙነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ጉምቱ የሆነው ሪቻርድ ሃስ ደጋግሞ እንደሚያሳስበው፤ ዲፕሎማሲም ሆነ የውጭ ግንኙነት ከሀገር ቤት ነውና የሚጀመረው የቤት ሥራችን ላይ ልናተኩር ይገባል። ሀገራዊ አንድነትን ማጎልበትና ጦርነትን ማስቆም አለብን። ከሰሜኑ የሀገራችን ጦርነት በቅጡ ሳናገግም ሌላ ዙር ጦርነት ውስጥ መግባት ነገሩን አንድ ርምጃ ወደፊት ሁለት እርምጃ ወደኋላ እያደረገው ነውና ከጦርነት አባዜ ፈጥነን መውጣት አለብን።

ሻሎም ! አሜን ።

 በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን ነሃሴ 25/2015

Recommended For You