ሥራ ፈላጊነትን ሳይሆን ሥራ ፈጣሪነትን ማስቀደም ይገባል!

መማር የእውቀትም የክህሎትም ባለቤት ያደርጋል። ምክንያቱም መማር የሃሳብ አድማስን ያሰፋል፤ የመመራመርና የመፍጠር ክህሎት ባለቤትም ያደርጋል፤ የማድረግ አቅምን ያጎናጽፋል። ለዚህም ነው ከልጅነት እስከ ወጣትነት፤ አልፎም እስከ ጉልምስናና እርጅና እድሜ ድረስ የሰው ልጆች ለመማር እና እውቀት ለመቅሰም ዘወትር ከትምህርት ጋር ተቆራኝተው የሚታዩት።

አሁን ያለንበት ወቅት ደግሞ ወጣቶች ከልጅነት እስከ ወጣትነት እድሜ የቆዩበትን የትምህርት ዘመን የየምዕራፍ ፈተናዎች ተሻግረው አዲስ የሕይወት ጊዜን ለመጋፈጥ የተዘጋጁበት ነው። አንድ ብለው የጀመሩት የቀለም እውቀት ቀሰማ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አሸጋግሮ የክህሎት አቅማቸውን ማጎልበቻ እድል ፈጥሮላቸው እነሆ የበቁትን አብቅቶ ለምርቃት አድርሷቸዋል።

ከቀለም አውድ ተሻግረው፣ ከክህሎት ማዕድ ተቋድሰው ከትምህርት ዓለም ወደ ሥራ ዓለም መሸጋገሪያቸውን ለማብሰርም ሰሞኑን እነኚህ ምሩቃን “እንኳን ደስ ያላችሁ” ተብለው ተዘምሮላቸዋል። ይሄ የ”እንኳን ደስ ያላችሁ” ዝማሬ ደግሞ ሁለት መልዕክት አለው። አንዱ የትምህርት ጉዟችሁን የመጀመሪያ ምዕራፍ በስኬት አጠናቅቃችኋል እና ደስ ይበላችሁ ነው።

ሁለተኛው መልዕክት ግን ከዚህ የተለየ የኃላፊነት ብስራት መልዕክት ነው። ምክንያቱም ከትምህርት ዓለም በኋላ አዲስ ዓለምን ለመቀላቀል፤ አዲስ ኃላፊነትን ለመሸከም፤ አዲስ የሕይወት ልምምድን ለመጀመር የበቃችሁ ሆናችኋል እና ደስ ይበላችሁ የሚል ነው። እናም የተመራቂዎች፣የአስመራቂ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም የወላጆች ጭምር ጉዳይ ሊሆን የሚገባውም ይሄኛው ነው።

ምክንያቱም ተማሪዎች ከዓመታት የእውቀትና ክህሎት ግብይት ማግስት የደረሱበት አዲስ የሕይወት ምዕራፍ በመሆኑ አዲሱን ምዕራፍ በሌላ ስኬት ማጀብ ስለሚጠበቅባቸው ነው። ዩኒቨርሲቲዎችም ከዓመታት ድካም በኋላ በእውቀት ያነጿቸውን ወጣቶች ለአዲሱ የሕይወት ጉዟቸው ስንቅ አስይዘው ለምርቃት አብቅተዋልና በሥራቸው ልክ ሊኮሩ ስለሚገባቸው ነው። ወላጆችም ልጆቻቸው ከዓመታት ጥረታቸው በኋላ ሙሉ ሰው የመሆን መንገድን መጀመሪያቸው እለት ላይ በመድረሳቸው በልጆቻቸው ስኬት መደሰቻቸው ወቅት ስለሆነ ነው።

ይሄ የተመራቂዎች አዲስ ምዕራፍ የሚሰምረው፤ የዩኒቨርሲቲዎች የእውቀትና ክህሎት ባለቤት ወጣቶችን አፍላቂነት ኩራት የሚሆነው፤ የወላጆች በልጆቻቸው ጉዞ የሚገኝ ደስታ ምሉዕ የሚሆነው ግን ተመራቂዎች ከምርቃታቸው ማግስት የሚኖራቸው ማንነት ነው። ይሄ ማንነት ደግሞ በአዲሱ የሕይወት ምዕራፋቸው ውስጥ በምግባር የሚገለጥ ነው። እናም ምግባራቸው ጠባቂነት ወይስ በራስ ቆሞ መራመድ ላይ ይገለጣል የሚለውን የመመለስ ኃላፊነት ከእነሱ ይጠበቃል።

ምክንያቱም እነዚህ ተመራቂዎች “እንኳን ደስ ያላቸው” ተብሎ በምርቃታቸው እለት ሲዘመርላቸው፤ ዝማሬው ስለመመረቃቸው ፌሽታ ለማድረግ ብቻ አይደለም። ይልቁንም የቀጣይ የኃላፊነት ጉዟቸው አቅም መፍጠሪያ የሞራል ስንቅ እንጂ። ይልቁኑም የአዲስ ሕይወት መንገዳቸው ከፍ ያለ ኃላፊነትን የሚጠይቅ እንደመሆኑ ይሄን ከፍ ያለ ኃላፊነት ለመቀበል የመዘጋጀታቸውን የሙሉ ሰውነት ተጎናጽፈው የመገኘታቸውን ሃቅ የመግለጽ ሁነት በመሆኑ ነው።

ይሄ የሙሉ ሰውነት መገለጫ ደግሞ በራስ መቆም ነው። በራስ መቆም ማለት ደግሞ ከጠባቂነት ራስን ነጻ ማውጣት ነው። ከጠባቂነት ራስን ማውጣት ሲቻል ደግሞ ከራስ አልፎ ለሌሎች አቅም መሆንን፤ ለሌሎች እድል መፍጠርን፤ ለሃገርና ሕዝብ የሚተርፍ ምግባር ባለቤት ሆኖ መገኘትን በተግባር መግለጥ ማለት ነው።

ይሄ ምግባር የሚገለጠው ደግሞ እንደ ተራው ተመራቂ፤ እንደ ቀድሞው ተለምዷዊ አካሄድ በየተቋማቱ ደጃፍ የትምህርት ማስረጃን ይዞ ደጅ መጥናትን፤ በየማስታወቂያ ሰሌዳው ሰልፍ ይዞ የሥራ ቅጥር ማስታወቂያዎችን ማሰስን አብዝቶ በመጠየፍ ነው።

ከዚህ ይልቅ በትምህርት ቆይታው ያገኘውን እውቀት፤ ከሕይወት ተሞክሮው የገበየውን ክህሎትና አመለካከት ደምሮ፤ ከሥራ ፈላጊነት ይልቅ ሥራ ፈጣሪነት ላይ ያተኩራል። ያገኘውን እድል ተጠቅሞ የሥራ ፈጣሪነት መንገዱን ይጀምራል። ሥራን ሳይንቅ፣ ሥራን ሳይመርጥ የሕይወት መንገዱን የተሻለ እንዲሆን ይተጋል። መማሩ ለለውጥ፣ መማሩ ለተሻለ ሕይወት እንዲያበቃው ይጠቀምበታል።

የመማር እውነትም፤ የተማረ መገለጫም ይሄው ነው። ጠባቂነት ሳይሆን ፈጣሪነት፤ ጥገኝነት ሳይሆን በራስ የመቆም ነጻነት። ሥራ ፈላጊነት ሳይሆን ሥራን ሳይንቁና ሳይመርጡ ሠርቶ አሸናፊ መሆን። የሕይወት መንገድን፤ የኑሮ ስኬትን ከሌሎች የሚሰጥ ምንዳ አድርጎ ከመጠበቅ ተላቅቆ፤ የሕይወት መንገዱ ወደ ስኬት እንዲያመራው የማድረግ የራስ ከፍ ያለ ሰብዕናን በሙሌት መገንባት ነው። በመሆኑም ተመራቂዎች ሥራ ፈላጊነትን ሳይሆን ሥራ ፈጣሪነትን ማስቀደም፤ ለዚህ ከፍ ያለ የምሉዕነት መገለጫም ራስን ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል።

 ምንይሻው

አዲስ ዘመን ነሃሴ 25/2015

Recommended For You