ብሪክስ- ሌላኛው የኢኮኖሚና የንግድ ልውውጥ አማራጭ

የዓለም መንግሥታት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ግብ በማስቀመጥ ብሔራዊ ጥቅማቸውን በሚያስጠብቅ መልኩ በርእዮተ ዓለም ከሚመስሏቸው አጋሮቻቸው ጋር ይሰባሰባሉ። ከዚህ መሰል ስብስብ ውስጥ ደግሞ በኢኮኖሚ፣ በቴክኖሎጂና በወታደራዊ አቅማቸው በፈረጠሙ አራት ሀገራት (ራሺያ፣ ብራዚል፣ ሕንድ እና ቻይና) ይሁንታ የተመሰረተው፤ በኋላም ደቡብ አፍሪካን ያካተተው የ”ብሪክስ” ቡድን ይገኝበታል።

ይህ ስብስብ በሀገራቱ መካከል የሚደረግ የንግድ ልውውጥ፣ እየተቀየረ የመጣውን ጂኦ- ፖለቲካዊ አሰላለፍ ቅርፅ የሚወስን እንዲሁም በምዕራባዊያኑ ተፅእኖ ስር የሚገኘውን የዓለም ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የማኅበራዊ ተፅዕኖ የሚቋቋምና የሚገዳደር ጭምር እንደሆነ ይታመናል።

የዓለምን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ቅርፅ ከመወሰን ባለፈ የመቆጣጠርና የመምራት አቅምን የሚፈጥር ይህን መሰል ስብስብ ውስጥ መሳተፍ ደግሞ የሁሉም ሀገራት ፍላጎትና ምኞት ነው። ለዚህም ነው የምድራችንን 40 በመቶ የሚሆነውን የሕዝብ ቁጥር እንዲሁም 26 በመቶ የኢኮኖሚ ድርሻ በቅንጅት የያዙት አምስት ሀገራት “ብሪክስ” የሚል ስያሜ ያለው ቡድን የመሰረቱት።

ሀገራቱ በዚህ ሳይገደቡ እድማሳቸውን እያሰፉና አዳዲስ አባላትን እያካተቱ የዓለምን የኃይል አሰላለፍ ለመቀየር እየተንቀሳቀሱ ነው።

ኅብረቱ የወጪ ገቢ ምርቶችን ገበያ አማራጭን፣ የፋይናንስ የብድር ምንጭን ለማስፋት፣ በጥቂት ሀገራት በሚዘወርና ርእዮተ ዓለምና ፖሊሲ ተፅዕኖ ውስጥ ላለመውደቅ እንዲሁም ከቅድመ ሁኔታ ጋር የሚመጣ የድጋፍ ተፅዕኖ ውስጥ ላለመውደቅ ሰፊ እድል ይዞ እንደሚመጣ ይታመናል። ለዚህም ነው ባሳለፍነው ሳምንት ኢትዮጰያ እነዚህን እድሎች የሚከፍትላት “የብሪክስ” አባልነት ይሁንታን ስታገኝ ብዙ ያነጋገረው።

ከዓለም የንግድና የፖለቲካ ሥርዓት የአንበሳውን ድርሻ ለመያዝና ተፅእኖ ፈጣሪ ሆኖ በቀዳሚነት ለመሳተፍ ቀላል የማይባል ፍትጊያ መደረጉ የማይቀር ነው። በገቢና ወጪ ምርት ዳጎስ ያለ ሀብትን የሚያጋብሱ ኃያላን ሀገራት በንግድ ሂደቱ የሚኖራቸው ሚና ድንበር የተሻገረ፣ ሀገራትን፣ አህጉርን ያቆራረጠ የጂኦ- ፖለቲካ አድማሱን ያሰፋ ነው። በዚህ ድምፅ አልባ ሽኩቻ ውስጥ የራስን ድርሻ ማንሳት ተገቢና ፍትሐዊ ነው። ኢትዮጵያም ከዚህ የተለየ ፍላጎት እንደሌላት ግልፅ ነው።

ብሪክስ “አፍሪካ አውት ሪች” እና “ብሪክስ ፕላስ” የሚል ስያሜ የሰጠውን ስብሰባ የደቡብ አፍሪካ የንግድ መዲና በሆነችው ጆሀንስበርግ ባካሄደበት ወቅት ኢትዮጵያን በአባል ሀገርነት መቀበሉን አብስሮናል። ከኢራን፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ግብፅ፣ አርጀንቲና እና ሳውዲ አረቢያ ጋር ከሚቀጥለው ዓመት ጥር ወር ጀምሮ በሙሉ አባልነት በመቀበል የምትሳተፈው ኢትዮጵያም በኢኮኖሚ፣ ፖለቲካዊ ጥቅምን ከማስጠበቅ አኳያ ታላቅ ዲፕሎማሲያዊ ድል ማስመዝገብ ችላለች።

የብሪክስ ጥምረት አባል የሆነችው ኢትዮጵያ የአባልነት ይሁንታ ማግኘቷ ምን አንድምታ ይኖረው ይሆን? ምንስ አይነት እድሎች ይዞ ይመጣል? ይህንን ለመገንዘብ የሀገራቱን የኢኮኖሚ ተፅዕኖ በቁጥር አስደግፈን ከዚህ እንደሚከተለው ለመመልከት እንሞክር።

በአውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር በ2021 የወጣ መረጃ እንደሚያመለክተው የብሪክስ ሀገራት በጋራ 3 ነጥብ 24 ቢሊዮን ሕዝብ ብዛት ነበራቸው ( ይህ ቁጥር እየጨመረ እንደሚመጣ ልብ ይሏል።) አሀዙን በመቶኛ ስናስቀምጠው ከዓለም ሕዝብ ከ40 በመቶ በላይ እንደሆነ እንረዳለን። ከዚህ የምንገነዘበው ከፍተኛ አምራችና ሸማች ኃይል በብሪክስ ሀገራት ውስጥ መኖሩን ነው። ይህ የሕዝብ ቁጥር ኢትዮጵያ በግብርናና በመሰል ምርቶች በኢምፖርት ኤክስፖርት ዘርፉ ላይ ትልቅ እድል ይዞ የሚመጣ ይሆናል።

አሁንም ከሁለት ዓመት በፊት ያለውን የሀገራቱን ጥቅል ኢኮኖሚ አቅም ስንመለከት የብሪክስ አባል ሀገራት በዓለማችን ላይ ግንባር ቀደም የኢኮኖሚ ባለቤት መሆናቸውን እንገነዘባለን። በሀገር ውስጥ ምርት ጥቅል መረጃ መሰረት ሀገራቱ በጥምረት ከ26 ነጥብ 03 ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የሚለካ ምርት አላቸው። ይህም ከዩናይትድ ስቴትስ አጠቃላይ ምርት ብልጫ ያለው ነው። በዚህ ስብስብ ውስጥ መካተት እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅምን በሚያስጠብቅ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መሳተፍ ከብሔራዊ ጥቅም አንፃር ፋይዳው ጉልህ መሆኑን መገንዘብ አያዳግትም።

ከአውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር ከ2000 ጀምሮ ቻይና ከብሪክስ ሀገራት ቀዳሚዋና ትልቋ የሸቀጦች ላኪ ነች። አሁንም ድረስ ከኅብረቱ የወጪ ንግድ ድርሻዋ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። የቻይና ኤክስፖርት ድርሻ በ2000 ከ50 በመቶ በላይ የነበረ ሲሆን፤ በ2020 ይህ ድርሻ ወደ 74 በመቶ ከፍ ብሎ ነበር። ሩሲያ ደግሞ ወደ ውጪ በምትልካቸው ምርቶች ሁለተኛ ደረጃ ትቅመጣለች።

ይህ እውነታ ኢትዮጵያና በኅብረቱ ይሁንታን ያገኙት አዳዲስ አባላት በዓለም የንግድ ልውውጥ ውስጥ የመደራደር አቅማቸውን ተጠቅመው የገቢ ንግድ አድማሳቸውን ማስፋት የሚያስችላቸው ታላቅ ስብስብ ውስጥ መሆናቸውን የሚያስገነዝበን ነው። ጉዳዩን በዝርዝር ለማጤን እንዲያስችለን የንግድ ልውውጡን ሀገራቱ ካላቸው የመግዛት ፍላጎትና አቅም አንፃር እንደሚከተለው ለመመልከት እንሞክር።

የብሪክስ አባል ሀገራት በዓለም ላይ ያሉ ሸቀጦችን ወደ ሀገራቸው በማስገባት እረገድ 14 በመቶ ጥቅል ድርሻ እንዳላቸው መረጃዎች ያመለክታሉ። የቻይናን የገቢ ንግድ ብቻ ነጥለን ስንመለከት እስከ ሁለት ትሪሊዮን ዶላር ሲደርስ በጥቅሉ አምስቱ ሀገራት ደግሞ 3 ነጥብ 6 ትሪሊዮን ዶላር የገቢ ንግድ ልውውጥ እንዳላቸው ቁጥሮች ይናገራሉ።

ኢትዮጵያ ወደ ውጪ የምትልካቸውን ምርቶች መጠን ማሳደገ ከቻለችና የብሪክስ አባልነት አጋጣሚውን ለዲፕሎማሲያዊ የድርድር መድረክ በተገቢው መንገድ ከተጠቀመችበት በንግድ ትስስሩ (በኤክስፖርት ዘርፉ) ግዙፍ እመርታን እንደምታሳይ ነው። በተለይ ምርቶችን ከቀረጥ ነፃ በሆነ መድረክ ለገበያ እንድታቀርብ መሰል እድሎች የሚከፍቱት በር ቀላል አንዳልሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል።

የብሪክስ ቡድን አባል ሀገራትን ኅብረት መቀላቀል ከላይ ካነሳነው ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ የዘለለ ፋይዳም አለው። በተለይ የእጅ መንሻን ከፊት ለፊት አድርጎ ከጀርባ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ድብቅ ሴራና አላማን ለማስፈፀም ፍላጎት ያላቸው ምእራባውያንን ቆም ብለው እንዲያስቡ የሚያደርግ ነው። ይህንን ጉዳይ ዘርዘር ባለ መልኩ ወደ ሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ መልሰነው ለመመልከት እንሞክር።

ምእራባውያን በፋይናንስ ተቋማቶቻቸው፣ በእርዳታ ድርጅቶች እንዲሁም (በጂ 7፣ በዓለም ባንክ በአውሮፓ ኅብረት…) በልዩ ልዩ ስብስቦቻቸው አማካኝነት ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ፍላጎቶቻቸውን ለማስፈፀም ይፈልጋሉ። ለፕሮጀክቶች ግንባታ ብድር አሊያም እርዳታን ሲሰጡ ከጀርባ የባህል ተፅዕኖ፣ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት፣ ሊበራላይዜሽን፣ የፋይናንስ ተቋማት ጣልቃ ገብነት፣ መንግሥት የመሾምና የመሻር አጀንዳን አግተልትለው ይመጣሉ።

በተለይ ከባህልና ከወግ ጋር ፍፁም ተቃራኒ የሆኑ አፈንጋጭ ልምዶችን ለማስረፅ የኢኮኖሚ ጡንቻቸውንና ማእቀባቸውን እንደ መሳሪያ ይጠቀሙበታል። ይህንን በማር የተለወሰ መርዝ በጣጥሶ ማለፍ የሚቻለው ከእነርሱ በተቃራኒው ከቆመ ስብስብ አሊያም አማራጭ ጋር ራስን በማወዳጀት መሆን አለበት (እንቁላልህን በአንድ ቅርጫት ውስጥ አታስቀምጥ ይሉትን ይትብሃል ልብ ይሏል)።

ከበላያችን ያነሳነውን ጉዳይ የሚያስረዱልን ሁለት የቅርብ ጊዜ ምሳሌዎች ለማንሳት ስንሞክር “የዓለም ባንክ፣ አጎአ” ጋር ያደርሰናል። ከሰሞኑ ኡጋንዳ የተመሳሳይ ፆታ (አፀያፊ ተግባርን) በሕግ በመከልከሏ የተነሳ በዓለም ባንክ ምንም አይነት እርዳታና ብድር እንዳታገኝ መታገዷን ሰምተናል። ምእራባዊያኑ “የአንድ ዓለም ሥርዓት” በመዘርጋት በመረባቸው ውስጥ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን ለመክተት እንደሚሞክሩ አንዱ ምሳሌ የኡጋንዳ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ቁልጭ ባለ ምሳሌ ያሳየናል።

ሌላው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ኢትዮጵያ በገጠማት የውስጥ ችግር ምክንያት አሜሪካ እንድንከተለው የፈለገችውን ፖሊሲ ባለመቀበላችን ምክንያት እንደ ዳረጎት የሰፈረችልን ከቀረጥ ነፃ ሸቀጦችን ወደ ሀገሯ የማስገባት (አጎአ) እድል መሰረዟ ነው። ይህ ዓይነት ስልት የአሜሪካ፣ አውሮፓ፣ የዓለም ባንክ እና መሰል ስብስብ ታዳጊ ሀገራትን በተፅዕኖ ስር ለመጣል የሚከተሉት ፖሊሲ ነው።

በመሆኑም በራስ አቅም ምርትን በመሸፈን፣ ቴክኖሎጂና የፈጠራ ሥራ ላይ በማተኮር ከሚደረግ ቀጥተኛ ትግል ባሻገር የእነዚህን ኃያላን ብርቱ የማሽመድመድ አቅም ሊያዳክም የሚችል ስብስብና ኅብረት ውስጥ ያለማቅማማት መሳተፍ ተገቢ ነው። ይህ አካሄድ ብዙ አማራጭ በጠረጴዛው ላይ እንድናገኝ ያስችለናል። ከሰሞኑ የሰማነው የብሪክስ አባል ሀገራት ዓለም አቀፍ ተፅእኖና ቡድኑን ለመቀላቀል ፍላጎት ያላቸው ሀገራት እየጨመረ መሄድ አንድምታም ከዚህ መሰል ተፅዕኖ የመላቀቅ ጉጉትን የሚያመላክት ነው። ኢትዮጵያም ሳይረፍድ ከአምስቱ አባል ሀገራት ጋር መቀላቀሏ ይህንኑ ያሳያል።

በጥቅሉ የዓለም የኢኮኖሚና የፖለቲካ ቅርፅ ከአንድ ወገን የበላይነት እየተላቀቀ በፍጥነት ቅርፁን እየቀየረ የመምጣቱ ጉዳይ እውነታ ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል። ሂደቱ በማደግ ላይ የሚገኙ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት ቀላል አንድምታ አይኖረውም። የፖሊሲ ጫናና በቅድመ ሁኔታ ላይ የተመሰረተ ብድርና ድጋፍ የሚታወቁት ምእራባውያን በተለይ አፍሪካ ላይ የሚኖራቸው ፖሊሲ በድጋሚ እንዲያጤኑት የሚያስገድድም ነው። ኢትዮጵያ ለምትከተለው ባለብዙ መድረክ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትም እንደ ተጨማሪ አማራጭ ልናየው የሚገባም ነው። ሰላም!

ሰው መሆን

 አዲስ ዘመን ነሃሴ 24/2015

Recommended For You