ኢትዮጵያውያን በሀገራችን ህልውና ለመጣ ቀልድ አያውቁም። ቤቴ፣ ርስቴ፣ ሚስቴና ልጆቼ ሳይሉ ሀገራችንን አስቀድመው ራሳቸውን ለመስዋዕትነት ያቀርባሉ።
በደምና አጥንታቸውም ሉዓላዊነታቸውን ያስከብራሉ፤ ነጻነታቸውንም ያረጋግጣሉ። አልፎ ተርፎም በኮሪያ፣ በኮንጎ፣ በላይቤሪያ፣ በሶማሊያ፣ በሩዋንዳና ብሩንዲ እንዲሁም በሱዳን በመዝመት በግጭትና በጦርነት ውስጥ የገቡ ሀገራትን አረጋግተው ወደ ሰላማቸው መልሰዋል።
ሆኖም የጀግንነታችንና ለሌሎች ሀገራት ጭምር የነጻነት ተምሳሌት የመሆናችን ያህል የውስጥ ሰላማችንን በማረጋገጥ ግን ብዙም አልተሳካልንም። በጀግንነትና በሰላም ማስከበር የገዘፈ ታሪክ ያለንን ያህል በሰላም የመኖር ጥበብ ርቆን ብዙ ተቸግረናል። የኢትዮጵያን ታሪክ መለስ ብሎ ላየው የውስጥ አለመግባባት፣ ግጭትና ጦርነት የበዛበት ነው። ተነጋግረን መፍታት በምንችላቸው ጉዳዮች መነጋገርና መግባባት ሳንችል በግጭትና ጦርነት ውድ ዋጋ ከፍለናል።
ይህ ደግሞ ሀገሪቱን በማያባራ ግጭትና ጦርነት ውስጥ ከቷል፤ ለበርካታ ሰዋዊና ቁሳዊ ኪሳራም ዳርጓል። ለሀገሪቱ ዕድገትም ፈተና ሆኗል። ይህ የታሪካችን አንዱ ክፋይ ግን አንድ ቦታ መቆም አለበት። የግጭት፣የጦርነት፣ ያለመግባባት ታሪካችን ተዘግቶ በጋራ ታሪኮቻችን ላይ የምንግባባ፤ ለጋራ ሀገራችን የምንተጋ፤ ለልጆቻችንም የበለጸገች ኢትዮጵያን ለማውረስ የጋራ ዕሳቤ የጨበጥን አዲስ ትውልድ መሆን ይገባናል።
ይህ ሊሆን የሚችለው ደግሞ በምክክርና በመግባባት ነው። ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባትም እንደሀገር የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባ አንድ ዓመት ከስድስት ወራት አስቆጥሯል። በእነዚህ ጊዜያትም ምክክሩ የሚመራበትን አቅጣጫ ከመቀየስ ጀምሮ የሌሎችን ሀገራት ተሞክሮዎችን የመቀመርና በምክክሩ የሚሳተፉ ሰዎችን የመለየት ሥራዎች ተከናውነዋል። በቀጣይም የምክክሩን አጀንዳዎችን ከኅብረተሰቡ የመቀበልና ምክክሩን ወደ መሬት የማውረድ ሥራዎች ይከናወናሉ።
ስለሆነም ሀገራዊ ምክክሩ የቀድሞ ችግሮቻችን፣ አሁን ያሉት ችግሮቻችን መፍቻና በቀጣይም ተመሳሳይ ችግሮች እንዳያጋጥሙን የመፍትሔ አቅጣጫን የሚጠቁመን መሠረታዊ ነገር መሆኑን ማመን ይጠበቅብናል።በሀገሪቱም መተማመን የሰፈነበት የፖለቲካ ሥርዓት ለመመስረትም እርሾ ሆኖ እንደሚያግዝ እምነት መጣል አለብን።
ለዚህም ሁሉም ነገር በንግግር እና በምክክር ይፈታል የሚል እምነት ማዳበር ይጠበቅብናል። ወሰንም ሆነ የማንነት ጥያቄ እንዲሁም ራስን በራስ ማስተዳደር እና የፍትህ ጥያቄዎች በአጠቃላይ የፖለቲካ ጥያቄዎች እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በሙሉ በሀገራዊ ምክክር ሊፈቱ የማይችሉበት ምክንያት አይኖርም።
አሁን እዚህም እዚያም ያሉት አለመግባባቶች ተወግደው በፍቃደኝነት እና በመግባባት ላይ የተመሰረተች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ምክክሩ የማይተካ ሚና አለው። ሀገራዊ ምክክሩ ከዘመን ወደ ዘመን ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮችን የመፍታት፣ የመወያየትና የመነጋገር ባህልንም ለማዳበር ይረዳል። በመወቃቀስ ላይ የሚያተኩረውንም የፖለቲካ ባህላችንን ወደ መነጋገር፤ መተባበርና መደጋገፍ እንዲመጣ ያደርጋል።
ኋላ ቀሩ የፖለቲካ ባህላችን በርካታ ችግሮችን አስከትሎብናል። ከመነጋገር ይልቅ ለንትርክ አልፎ ተርፎም ነፍጥ እስከማንሳትና መገዳደል ድረስ አድርሶናል። አሁን ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ግጭት፣ ጦርነትና መወነጃጀል ሳይሆን ውይይትና ምክክር ብቻ ነው።
ስለዚህም ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህልም እንደ ሀገር ሊጎለብት ይገባል። የስልጣኔም አንዱ መለኪያም ይኸው ነውና። በኢትዮጵያ የፓርቲ ፖለቲካ ሥራ ውስጥም ሆነ በሌሎች መስኮች የተሰማሩ ወገኖች፣ ለውይይት ቅድሚያ መስጠት አለባቸው።
ኢትዮጵያ ከፊቷ የተጋረጡ በርካታ ችግሮች ያሉባት ሀገር ናት። የሀገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ ለመነጋገርና ለመደማመጥ ጊዜ መስጠት አለባቸው። ጽንፍ ለጽንፍ ሆኖ ቃላት መወራወርና ይዋጣልን ማለት እንደሀገር ዋጋ አስከፍሎናል። በዚህም መንገድ ለዘመናት ተጉዘን ያተረፍነው ድህነትን፣ኋላቀርነትና ዕልቂትን ብቻ ነው።
ስለሆነም የታሪካችን አንዱ ክፋይ ሆኖ ዘመናትን የተሻገረውን አለመግባባትንና ግጭትን ለማስወገድና የተረጋጋች፣ ሰላሟ የተጠበቀ እና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ለማውረስ ሀገራዊ ምክክሩ ይዞ የመጣውን ዕድል በሚገባ ልንጠቀምበት ይገባል!
አዲስ ዘመን ነሃሴ 24/2015