የምርት አቅርቦትና የገበያ ማዕከላትን በማስፋት የበዓል ወቅት ገበያን ማረጋጋት

የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት በኢትዮጵያ ፈታኝ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል። ችግሩ ኅብረተሰቡን በእጅጉ እየፈተነ ሲሆን፣ ችግሩ በምርት አቅርቦት እጥረትና በሕገወጥ ነጋዴዎች እንዲሁም ደላላዎች እየተባባሰ ቀጥሏል።

በኢትዮጵያ እየተባባሰ ለመጣው የኑሮ ውድነት ዓለም አቀፍ ጫናዎችም በምክንያትነት ይጠቀሳሉ። የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጥሎት ያለፈው አሉታዊ ተጽእኖ እንዲሁም በዩክሬንና ሩሲያ መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድረዋል፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሸቀጦች ዋጋ በእጥፍ መጨመሩን መረጃዎች ያመለክታሉ። ኢትዮጵያም ከዚህ ዓለም አቀፍ ሁኔታ ውጭ አይደለችም።

መንግሥት ይህ የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት በሕዝቡ ላይ እያደረሰ ያለውን ችግር ለመፍታት የተለያዩ ርምጃዎችን ሲወሰድ ቆይቷል፤ እየወሰደም ይገኛል። እንደ ዘይትና ስኳር ያሉትን ሸቀጦች ከውጭ ሀገር በማስመጣት ጭምር ለኅብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ ነው። በግብርና ምርቶች አቅርቦት ላይም እንዲሁ በህብረት ሥራ ማህበራትና በንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን በኩል እየሰራ ነው። እንደ ስንዴ ያሉትን ሰብሎች በበጋ መስኖ ጭምር በማልማት በስንዴ ዋጋ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጫና ማስቀረት ችሏል።

የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረቱ በተለይ በበዓላት ወቅት ጎልቶ ይስተዋላል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ይህን ችግር ለመፍታት በየበዓላቱ ወቅት አቅርቦትን በማሳደግ ገበያውን ለማረጋጋት ይሰራል። በዚህም የዋጋ ንረቱ እንዳያሸቅብና የኑሮ ውድነቱ እንዳይባባስ ጥረት ያደርጋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከጥቂት ሳምንታት በኋላ መላው ኢትዮጵያውያን በጋራ በሚያከብሩት የዘመን መለወጫ በዓል ወቅት ይህ ችግር ሊያሳድር የሚችለውን ጫና ከወዲሁ ግምት ውስጥ በማስገባት እየሰራ ይገኛል። በዓሉን ምክንያት በማድረግ የዋጋ ማናር እና የአቅርቦት ክፍተት እንዳይከሰት ማድረግ የሚያስችሉ ተግባሮች በአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በኩል እየተሰሩ መሆናቸውን የቢሮው ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ መስፍን አሰፋ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አስታውቀዋል።

አሁን ያለው የኑሮ ውድነት ዓለም አቀፍ ጫና እንዳለው አቶ መስፍን ጠቅሰው፣ በተለይም በበዓላት ወቅት ተፈላጊነታቸው የሚጨምር የምርት ዓይነቶች ስለመኖራቸው ይናገራሉ። እነዚህ ምርቶች ቀድሞ ከነበረው ፍላጎት በተለየ በከፍተኛ መጠን እንደሚፈለጉና በአዲስ መልክ የሚፈለጉ የምርት ዓይነቶች ስለመኖራቸውም ገልጸው፤ ይህንኑ ፍላጎት መሠረት በማድረግም ከተማ አስተዳደሩ እየሠራ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ በዋናነት መሠረታዊ የሚባሉ የሰብል ምርቶች፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች፣ የተመረጡ የኢንዱስትሪ ምርቶች እና እንስሳትና የእንስሳት ተዋጽኦዎች በበዓላት ወቅት በስፋት ይፈለጋሉ። ከዚህ አንጻር በበዓላት ወቅት ፍላጎትን መሠረት ያደረገ የአቅርቦት ሥራ በስፋት ይሰራል። ለዚህም አቅርቦቱን ለማሳለጥ በትኩረት ይሰራል። ምርቶቹ ወደ ከተማ በስፋት እንዲገቡ ይደረጋል። ከዚህ ባለፈም ኅብረተሰቡ ምርቶቹን በአማራጭ የገበያ ማዕከላት አግኝቶ በተመጣጣኝ ዋጋ መሸመት የሚችልበት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በትኩረት እየተሠራ ነው።

በአሁኑ ወቅትም መጪውን የአዲስ ዓመት ወይም የዘመን መለወጫ በዓል ምክንያት በማድረግ የዋጋ መናርና የምርት አቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት ቀደም ብሎ በተጀመሩት የእሁድ ገበያዎች ላይ ምርት በስፋት እንዲቀርብ ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል። በመደበኛነት ካለው የእሁድ ገበያ በተጨማሪ በበዓሉ መቃረቢያ የአዘቦት ቀናትም እንዲሁ ግብይቱ የሚከናወንበት ሁኔታ ተመቻችቷል።

ምክትል ቢሮ ኃላፊው ባዛሮችንም በሁሉም ክፍለ ከተሞች በስፋት የማዘጋጀት ሥራ እየተሠራ ስለመሆኑ ተናግረዋል። በከተማ ደረጃም በተመረጡ አካባቢዎች ላይ ማለትም በሳርቤት፣ የካ አባዶ፣ ቃሊቲ አካባቢ አዲስ በተገነባው የገበያ ማዕከል ምርቶችን በስፋት በማቅረብ ገበያውን የማረጋጋት ሥራ ይሠራል ብለዋል።

ከዚሁ ጎን ለጎን ከተማ ውስጥ ከሚገኙ የህብረት ሥራ ማህበራት ጋርም እንደሚሠራ ጠቅሰው፤ የህብረት ሥራ ማህበራቱ ቀደም ሲል ምርቶቻቸውን ከሚሸጡባቸው ሱቆች በተጨማሪ በሱቆቹ አካባቢዎች ላይ አነስተኛ ድንኳኖችን በመትከል ምርቶችን በስፋት ለማቅረብ ዝግጅት ማድረጉን ነው ያመላከቱት።

‹‹የገበያ መረጋጋቱም ሆነ የዋጋ ንረቱን የማርገቡ ሥራ በዋናነት በምርት አቅርቦት መደገፍ አለበት›› የሚሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ ወደ ከተማ እየገባ ካለው የምርት መጠን በተጨማሪ የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም ምርቶችን በስፋት ወደ ከተማዋ ማስገባት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ለዚህም በከተማ ደረጃ ከአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን ጋር በመሆን በተለይም የእንስሳትና የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶችን ለአብነትም የዶሮና የእንቁላል አቅርቦት ከወዲሁ በስፋት እየቀረበ መሆኑን ጠቅሰዋል። ከተማ ውስጥ ከሚገኙና በአዲስ አበባ ዙሪያ ከሚገኙ አምራች አካባቢዎች በተለይም የዘይትና የዱቄት ምርቶች ወደ ከተማዋ እንዲገቡና በባዛሮች ላይ እንዲቀርቡ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ስለመሆኑም ገልጸዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ የህብረት ሥራ ማህራት የከተማ አስተዳደሩ የመደበውን ገንዘብ በመጠቀም ቀደም ብለው እያስገቡት ከነበረው ምርት በተጨማሪ በዓሉን አስመልክቶ እጥረት እንዳይከሰት የተለያዩ ምርቶችን ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጋራ በመሆን ወደ ከተማዋ የማስገባት ሥራ እየተሰራ ነው። ወደ ከተማ እንዲገቡ የተደረጉት ምርቶች በተለያዩ አማራጮች ለህብረተሰቡ እንዲቀርቡና ህብረተሰቡ ምርቶቹን በአቅራቢያው ማግኘት የሚያስችል ዕድልም ተፈጥሯል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አቅርቦት ላይ በስፋት መሥራት እንደሚያስፈልግም ነው ምክትል ቢሮ ኃላፊው ያመለከቱት፤ አቅርቦት ሲሰፋ ዋጋው ላይ ለውጥ ማምጣትና ገበያውን ማረጋጋት እንደሚቻል ተናግረዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ አቅርቦቱም በሕገወጥ መንገድ እንዳይመዘበርና በዋጋ ንረት ችግር እንዳይፈጠር ጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓት ተዘርግቷል። ለዚህም ከንግድ ቢሮ፣ ከገቢዎች ቢሮ፣ ከጸጥታ አካላት እንዲሁም ከምግብ፣ መድኃኒት ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ጋር በቅንጅት በመሆን የቁጥጥር ሥራ እየተሠራ ይገኛል። ይህም በዋናነት በዓላትን ምክንያት በማድረግ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ የተጋነነ ዋጋ እንዳይኖር፣ ምርትን በመከዘን ሰው ሰራሽ እጥረት እንዳይከሰት በተለይም ምርትን ከባዕድ ነገር ጋር በመቀላቀል የማኅበረሰቡን ጤና የሚጎዱ ችግሮች እንዳይፈጠሩ ለመከላከል በተቀናጀ ቡድን በኩል ይሰራል፤ ይህንኑ መሠረት በማድረግም ተገቢና ሕጋዊ ርምጃ ይወሰዳል።

የበዓል ገበያን ለማሳለጥ ከንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ጋር በመሆን በተለይም የስኳርና የዘይት ምርቶች ለበዓሉ በስፋት እየቀረቡ እንደሆነ የጠቀሱት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ ለበዓሉ ብቻ ሁለት ሚሊዮን ሊትር ዘይት እንዲሁም 36 ሺ ኩንታል ስኳር በአሁን ወቅት ወደ ከተማዋ እየገባ ስለመሆኑ ተናግረዋል። ይህ ምርት በመንግሥት ብቻ የሚቀርብ እንደሆነና ከዚህ ውጭ በመደበኛው ገበያም ተጨማሪ ምርት ይቀርባል ብለዋል። በተለይም በፍራንኮ ቫሉታ በተፈቀደው አግባብ መሠረት መጠነ ሰፊ ምርት ወደ ገበያው እየገባ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

የበዓላት ወቅቶችን ብቻ ጠብቆ በሚሰራ ሥራ የዋጋ ንረትን መከላከልና የኑሮ ውድነትን ማረገብ እንደማይቻል የገለጹት ምክትል የቢሮ ኃላፊው፤ በዋናነት ቋሚ በሆነ አግባብ መሥራት እንደሚገባ አስታውቀዋል፤ በተለይም ከንግድ ሥርዓቱ ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮችን ቋሚ በሆነ መንገድ መቅረፍና ማረም አስፈላጊ እንደሆነም አስረድተዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ ገበያውን ለማረጋጋት ዋናነት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ያስፈልጋል። ከዚህ አንጻር በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠል ተገቢ ይሆናል። ለአብነትም በከተማ ደረጃ የሌማት ትሩፋት በሚል የተጀመሩ ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠል፤ በተለይም በከተማ ግብርና እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችና የተለያዩ ፕሮጀክቶችንም እንዲሁ ማጠናከር ያስፈልጋል። ይህ ሥራ በከተማ ውስጥ ያለውን የምርት አቅርቦት እያሳደገ መምጣት ችሏል። በዚህም በከተማ ውስጥ ከእንቁላል ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር ለመቅረፍ በከተማ ግብርና በተሠራው ሥራ ውጤት ማምጣት መቻሉን ምክትል የቢሮ ኃላፊው አመላክተዋል።

በአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ላይም እንዲሁ በስፋት መሥራት እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ ከዚህ አኳያ የተጀመረውን ሥራ አጠናክሮ ማስቀጠል ተገቢ እንደሆነ ነው ያመላከቱት።

በከተማዋ ከንግድ ሥርዓት ጋር ተያይዞ ከሚስተዋሉ ችግሮች መካከል ሕገ ወጥነት አንዱ መሆኑን የጠቀሱት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ ሕገ ወጥ ንግድ የሚከናወነው በሕገ ወጥ ነጋዴዎችና በደላሎች መሆኑን ተናግረዋል፤ ይህንን ለማስቀረት በዋናነት የገበያ መሠረተ ልማቶችን ማስፋት አንዱ አማራጭና መፍትሔ መሆኑን ተናግረዋል።

ከተማ አስተዳደሩ በአዲስ አበባ ከተማ አምስት የመግቢያ በሮች ላይ ትላልቅ የገበያ ማዕከላትን ለማስገንባት አቅዶ እየሠራ ስለመሆኑ የጠቀሱት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ አምራቹ ራሱ ምርቱን በእነዚሁ የገበያ ማዕከላት ማቅረብ ያስችለዋል ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪም በሕገ ወጥ ደላላ ሰንሰለት ይመጣ የነበረውን ጫና የሚያስቀርለት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ትልቅ ትርጉም ያለው ስለመሆኑ ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅትም ገበያው በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ መጀመሩንና ውጤት የተመዘገበበት መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ በበጀት ዓመቱ ግንባታቸው ከተጠናቀቁ የገበያ ማዕከላት መካከል የአቃቂ ቃሊቲ እና የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የገበያ ማእከላት ግንባታዎች ይገኙበታል። በእነዚህ የገበያ ማእከላትም ማህበረሰቡ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ መሸመት የሚችልበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል። የገበያ ማዕከላት መሠረተ ልማቶች መስፋፋት ከተማ ውስጥ ያለውን የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የሰብል ምርቶች አቅርቦት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር ከማድረጋቸው በተጨማሪም በግብይት ሰንሰለት ውስጥ ያለውን በተለይም የሕገ ወጥ ደላላ ጣልቃ ገብነትን ማስቀረት የሚችል እንደሆነም ገልጸዋል።

በከተማ ደረጃ የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት በስፋት እየተሰራ ካለው ሥራ መካከል የዳቦ ፕሮጀክቶች ተጠቃሽ ናቸው ያሉት የቢሮ ኃላፊው፤ የሸገር ዳቦን ጨምሮ በከተማ ደረጃ የግል ባለሃብቶችን በማስተባበር ዳቦ ፋብሪካዎችን በማስገንባት የተሠሩ ሥራዎች ስለመኖራቸው ተናግረዋል። እነዚህን ሥራዎች በማጠናከር በተለይም ከአቅርቦት ጋር ተያይዞ ከኅብረተሰቡ የሚነሳውን ችግር ማቃለል እንደሚቻል ነው ያስገነዘቡት። አቅርቦት ሲሰፋ ግብይቱ ላይ ውድድር እንደሚፈጠር በመጥቀስም፣ አቅራቢ አካላት ሲበዙ ውድድር እያደገ ይመጣል። በዚህም የኑሮ ውድነት ችግርን ማቃለል ይቻላል ሲሉ አስታውቀዋል።

ምክትል የቢሮ ኃላፊው እንዳብራሩት፤ ሌላው በከተማ ውስጥ የሚስተዋለውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት 18 በሚደርሱ የምገባ ማዕከላት አቅም የሌላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች በቀን አንድ ጊዜ በነጻ መመገብ የሚችሉበት ዕድል ተፈጥሯል። የትምህርት ቤት ምገባም ሌላው የወላጆችን ጫና ለመቀነስ የተሠራ ሥራ ሲሆን፤ ከሰባት መቶ ሺ በላይ ተማሪዎች በቀን ሁለት ጊዜ እየተመገቡ ይገኛሉ። ከዚህ በተጨማሪም ማዕድ ማጋራት በሚል ፕሮጀክት ባለሃብቶችን በማስተባበር ሰፊ ቁጥር ያላቸውን የማኅበረሰብ ክፍሎች የማገዝ ሥራ ይሠራል። እነዚህ የአጭር ጊዜ መፍትሔ የተሰጠባቸውና ውጤት ማስመዝገብ የቻሉ ስለመሆናቸውም ተናግረዋል።

ከዚሁ ጎን ለጎን ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እየተሠራ ነው ያሉት ምክትል የቢሮ ኃላፊው፤ በዋናነት የሚከናወነው አንዱ ተግባር ምርትና ምርታማነትን በሀገር አቀፍና በከተማ ደረጃ ማሳደግ መሆኑን ጠቁመዋል። የገበያ ማዕከላትን መሠረተ ልማት ማስፋትና ማጠናከር እንዲሁም ሕገ ወጥነትን በመከላከል ርምጃ መውሰድ ለዘላቂ መፍትሔ ወሳኝ ነው ብለዋል።

የኑሮ ውድነትን ከማረጋጋት አንጻር የእሁድ ገበያ በከተማ ደረጃ አማራጭ መፍትሔ ሆኖ አገልግሏል ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ አንደኛ የገበያ ተደራሽነትን ከማስፋት አንጻር ኅብረተሰቡ በአቅራቢያው ምርት ማግኘት አስችሏል ብለዋል። ሁለተኛ አማራጭ ምርቶችን ከመደበኛው ገበያ በተሻለ ዋጋ ማግኘት ማስቻሉንም ጠቅሰዋል። እንዲሁም ኅብረተሰቡ የሚፈልጋቸውን ምርቶች በአንድ ቦታ በስፋት ከማግኘት አንጻርም ውጤት ተመዝገቧል ያሉት ኃላፊው፣ ከተማ ውስጥ በሁሉም ወረዳዎች ላይ ቢያንስ አንድ የእሁድ ገበያ መፍጠር ስለመቻሉ ነው የተናገሩት። ይህም በ2016 ዓ.ም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል። በተለይም በከተማው ውስጥ የሚገኙ 172 የገበያ ማዕከላትን አንደኛ ደረጃ የገበያ ማዕከል ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል።

በመጨረሻም በዓሉን አስመልክቶ ባዛሮች በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች እንደሚዘጋጁ ጠቁመው፣ በተለይም ከነሐሴ 27 እስከ ጳጉሜ 5 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ በሁሉም ክፍለ ከተሞች በተመረጡ አካባቢዎች ባዛሩ በቋሚነት ይካሄዳል ብለዋል። የእሁድ ገበያዎችም እንዲሁ በእነዚህ ቀናት በተከታታይ እንደሚቀጥሉ አመላክተዋል።

 ፍሬሕይወት አወቀ

 አዲስ ዘመን ነሃሴ 24/2015

Recommended For You