የብሪክስ ተስፋና ስጋት

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሁለንተናዊ ብልፅግናን እውን ለማድረግ የጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ፖለቲካዊ የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አጋርነት ፋይዳው ጉልህ ነው። አንድነት ኃይል፣ ህብረትም የሁለንተናዊ ድል ምስጢር ነው።

ይሁንና ሀገራት ከጋራ ይልቅ በተናጥል ጉዞ እየዳከሩ ከመደጋገፍ ይልቅ መገፋፋት በሚመስል መልኩ በተናጥል ለመጓዛቸው ድክመት ታዲያ በርካታ ምክንያቶች ይዘረዘራሉ። የፖለቲካ ውሳኔና ፍላጎት ማጣት ብሎም ‹‹ከባልሽ ባሌ ይበልጣል›› ራስ ወዳድ ስግብግብነት ከሁሉ ቀድሞ ይጠቀሳል።

በተለይ በኢኮኖሚ አውድ የጋራ ተጠቃሚነት መርህን በሚጥስ መልኩ እርስ በእርስ በር መዘጋጋትም ብዙ ርቀት አያስኬደንም። የግል እድገትን ከመሻት ይልቅ ዓለም አቀፉን የንግድ መርህና ሕግ በማክበር ትስስርን ይበልጥ ማጠንከርና በጋራ ሰርቶ በጋራ ማደግ የግድ ይላል።

ብራዚል፣ ሩስያ፣ ሕንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ ይህ መርህ ከገባቸው 14 ዓመታት ተቆጥረዋል። በአሁኑ ወቅት ምጣኔ ሀብታቸው በፍጥነት በማደግ ላይ የሚገኘው እነዚህ ሀገራት በዓለም አቀፍ ግንኙነትና ኢኮኖሚ ምህዋር እንቅስቃሴ ውስጥ ያላቸው ሚና እጀጉን ግዙፍ ነው።

አምስቱ ሀገራት በጋራ ያላቸው ምጣኔ ሀብታዊ አቅም ደግሞ የዓለምን 30 በመቶ ይስተካከላል። ሶስት ቢሊዮን አሊያም አርባ በመቶ የዓለም ሕዝብ በጉያቸው የሚኖርባቸው እነዚህ ሀአገራት በየጊዜው በሚያስመዘግቡት ሁለንተናዊ እድገት በዓለም አቀፍ ተጽዕኗቸው ጎልቶ እንዲታይ ምክንያት እየሆነ ይገኛል።

አምስቱን ሀገራት በጋራ የሚያስተሳስራቸው የአጋርነት ቡድንም አላቸው። «ብሪክስ» ይባላል። የብሪክስ ጉባዔ በየጊዜው የአባል ሀገራቱን የሀገራት ርዕሳነ ብሔርና መራሕይት መንግሥታት ፊት ለፊት ያገናኛል። በጉባዔው የአባል ሀገራት መሪዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ የጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ አጋርነት አንድነትና ጥንካሬ ማሳየት ይፈልጋሉ።

አባል ሀገራቱ በየጊዜው ተደማጭነታቸውና ተጽእኖ ፈጣሪነታቸውን ማሳዳግ ዋነኛ ምኞታቸው ነው። የጥምረቱ ዋነኛ ዓላማ እና ፍላጎትም በአንድ ሀገር የበላይነት ብቻ የማይዘወር ሳይሆን የተለየና አማራጭ የሆነ ዓለም የኢኮኖሚና የፖለቲካ ህብረትን መፍጠር ነው።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የብሪክስ የጥምረት በዓለም አቀፉ መድረክ ያለው ተቀባይነት እያደገ መምጣቱን ተከትሎ በርካታ ሀገራት ለቡድኑ ያላቸው ምልከታ እየተስተካከለ አባል የመሆን ፍላጎታቸውም በእጅጉ ጨምሯል። ፍላጎት ብቻ አይደለም ከመላ ዓለም የአባል አድርጉን ጥያቄ ይበልጥ ማስተጋባት ጀምሯል።

በአሁኑ ወቅት ከ40 በላይ ሀገራትም ጥምረቱን ለመቀላቀል ጥያቄ ማቅረባቸውም ብሪክስ ምን ያህል ጠንካራ እንደሆነ በቂ ምስክር የሚሠጥ ነው። ይህ የሀገራቱን ፍላጎት በየፈርጁ ሊመደብ የሚችል ሲሆን፤ አንደኛው ፍላጎት ያሳየና ሀገራት በሚል ሁለተኛው ደግሞ ጥምረቱን ለመቀላቀል በይፋ ማማልከቻ ያስገቡ ሀገራት በሚል ሊታይ የሚችል ነው።

ለአብነት ቱርክና ናይጄሪያ የመሳሰሉ ሀገራት ጥምረቱን ለመቀላቀል ፍላጎት ያሳዩ ሀገራት በሚለው ወገን ሲቀመጡ ኢትዮጵያ በአንፃሩ የጥምረቱን ሁለንተናዊ አስፈላጊነት በመረዳት ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ጥያቄ ካቀረቡ በርካታ ሀገራት መካከልም አንዷ ናት።

ኢትዮጵያም ጥቅሞቿን ሊያስጠብቁ ከሚችሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር መሥራቷን እንደምትቀጥልና ብሪክስን ለመቀላቀል በይፋ ጥያቄ ማቅረቧን ከጥቂት ወራት በፊት አሳውቃ ነበር። ባሳለፍነው ሳምንት 15ኛውን ጉባዔ በደቡብ አፍሪካዋ የንግድ መዲና ጆሃንስበርግ ሲካሄው የኢትዮጵያ ጥያቄ ምላሽ አግኝቷል።

ጉባዔው ከኢትዮጵያ በተጨማሪ የአባልነት ጥያቄያቸውን የተቀበላቸው ግብፅ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ኢራንና አርጀንቲና ናቸው። አዲሶቹ ሀገራትም በሚቀጥለው የአውሮፓውያን አዲስ ዓመትም የቡድኑ አባላት ይሆናሉ። ጉባዔው ስድስቱን ሀገራት የተቀበለው የአባልነት ጥያቄ ካቀረቡ ከ40 በላይ ሀገራት መካከል መርጦ ነው።

ኢትዮጵያ ቡድኑን ለመቀላቀል በቀዳሚነት ጥያቄ ካቀረቡ ሀገራት ለመሆን ያበቃት ምክንያት በርካቶች በራሳቸው መነፅር ይመለከቱታል። አንዳንዶቹ ከኢኮኖሚ ይልቅ ከፖለቲካዊ ጋር ሲያጎዳኙት ሌሎች ደግሞ ከፖለቲካ ይልቅ ኢኮኖሚያዊ የመሆን ዕድሉ እንደሚጎላ ያነሳሉ።

የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር የሆኑት ፕሮፌሰር ብሩክ ሃይሉ በሻህን ጨምሮ አንዳንዶች የኢትዮጵያን ተቀባይነት ማግኘት ከዲፕሎማሲ ድል ጋር አስተሳስረውታል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም ዶ/ር ቢሆን ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ በባለ ብዙ ወገን ዲፕሎማሲ መስክ ያላትን ተደማጭነት የሚያሳይ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በአረንጓዴ ዐሻራ፣ ግብርና እንዲሁም በሀገር ውስጥ ጥቅል ምርት እድገት እያስመዘገበች ያለው ስኬት የአባልነት ጥያቄዋ ተቀባይነት እንዲያገኝ ከፍተኛ ሚና ማበርከቱን አመልክተዋል። ‹‹ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ ከራሷ ባለፈ ለመላ አፍሪካውያን ትልቅ የዲፕሎማሲ ድል ነው›› ብለዋል።

ፋይዳው

ዓለም አቀፍ ገበያና የንግድ ሥርዓተ ሚዛን በመንገጫገጭ ላይ ባለበት በዚህ ወቅት መሰል የአባል ሀገራቱን የጋራ መግባባትና በአንድነት ገመድ ይበልጥ መጥበቅ ትርጉሙ ላቅ ያለ ነው። ከሁሉ በላይ የአባል ሀገራቱ ሁለንተናዊ ትስስርም የዓለም የኢኮኖሚ ትስስርን በመልካም ጎዳና ላይ ለማስኬድና ወቅታዊ የዓለም ኢኮኖሚ ሚዛንን ለማስተካከል ሁነኛ አበርክቶ ይኖረዋል።

አባል ሀገራቱ በተለያዩ አህጉር እንደ መገኘታቸውና በመካከላቸው ረጅም ርቀት በመኖሩ ትስስሩ ሌሎች ሀገራትን ስለሚያካልል ዓለም አቀፍ ንግድን ለማሳለጥ ያለው አቅሙም ዝቅተኛ ግምት ሊሰጠው የሚገባ አይደለም።

የብሪክስ ጥምረት ተናጥላዊም ሆነ ቡድናዊ ፋይዳው ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም። በሀገሮች መካከል ተመጋጋቢ የሆነ የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠር፣ የኢንዱስትሪ ዕድገት እንዲመጣ፣ የግል ባለሀብቱ ተሳትፎ እንዲያድግ፣ ለሥራ ፈጠራ እና ሚዛናዊ የንግድ ሥርዓትን ለመፍጠር ከፍተኛ ፋይዳ አለው።

ጥምረቱ ከተናጥል ጉዞና እድገት ይልቅ ተያይዞ መበልፀግን በማፋጠን በተለይ ኢትዮጵያ በዓለም የንግድ ሥርዓት ውስጥ ያላትን ቦታ በማሳደግ ከዓለም አቀፉ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ጋር በእኩል ደረጃ መወዳደርም ሆነ መደራደር የሚያስችላትን አቅም ያጎለብታል።

የጥምረቱ አባል ሀገራት በኢኮኖሚ ብልፅግና አንቱ የሚባሉ እንደመሆናቸው ኢትዮጵያ ከዚህ ጥምረት ብዙ ታተርፋለች። የኢንቨስተሮች ተመራጭ መዳረሻ እንድትሆን ያስችላታል። የኤክስፖርት አማራጮችን ያሰፋል። በአንዳንድ ምዕራባውያን ላይ የተንጠለጠለውን የሀገሪቱን የወጭ ንግድ ከስጋት ያወጣዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ የመወዳደር መንፈስን ያጎለብታል። ኢንዱስትሪያል ፓርኮች በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ በማድረግ የገበያ ዕድሎችን ይፈጥራል።

ስጋቶች

መሰል ህብረት ዘርፈ ብዙ ትሩፋቶች እንዳሉት ሁሉ የራሱ ተግዳሮቶች ብሎም በጥንቃቄ መታየት ያለባቸው አደጋዎችም አሉት። በዚህ ርእሰ ጉዳይ ላይ የተለያየ ትንታኔዎች የሚሰጡ የምጣኔ ሀብት ምሁራንም፣ ቡድኑ በዓለምአቀፍ ደረጃ የጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ አጋርነት፣ አንድነትና ጥንካሬ ለማሳየት በሚያደርገው ትስስር ላይ ሊጋጥሙት ከሚችሉት ተግዳሮቶች መካከል ዋነኛው የዩናይትድ እስቴትስ ተፅእኖ መሆኑን ይስማሙበታል።

 የግሎባል ታይምሱ ተንታኝ ዋንግ ዮንግዞንግ በበኩሉ አባል ሀገራቱ ከንግድ ተፅእኖው ጫና በመላቀቅ ራሳቸውን ይበልጥ ለማስተሳሰር መከወን ስላለባቸው ተግባራት ሲያስቀምጥ፤ በቀዳሚነት በመካከላቸው ፖለቲካዊ እምነት መስረፅ እንዳለበት አፅእኖት ይሠጠዋል።

በእርግጥም በአንዳንድ አባል ሀገራት መካከል የሚስተዋለው ልዩነትና የእርስ በእርስ ፍጥጫ እንዲሁም ልዩነት እስካላስወገደም በተለይ የአሜሪካን የንግድ ጦርነት ፍልሚያ ኢኮኖሚያዊም ሆነ ፖለቲካዊ ጫና ማምለጥ ቀላል አይሆንም።

በዚህ ረገድ ሃሳባቸውን የሚያጋሩ ስመጥር ፀሃፍት ብሎም ምሁራንም ለአብነት በቻይና የአንድ መቀነት የኢኮኖሚ አብዮት መርሃ ግብር ብዙም ደስተኛ ስትሆን የማትታየው ህንድ አቋምና እምነቷን ማስተካከል እንዳለባት እምነታቸው ፅኑ ነው።

በእርግጥ አሁን ላይ በቻይናና ሩሲያ መልካም የሚባል ግንኙነት አለ። የዩናይትድ እስቴት አምባገነን የመሆን አባዜ ደግሞ ሩሲያና ቻይናን ይበልጥ እንዲፋቀሩ መልካም አጋጣሚን የፈጠረ ይመስላል። ሩሲያና ህንድም ወዳጆች ናቸው። ምንም እንኳን የኒው ደህሊው መንግሥት ወደ ዋሽንግተን ጠጋ ጠጋ ማለቱ ባይስደስታትም አብዛኛውን ጊዜ ሩሲያ ለህንድ ጀርባዋን አትሰጥም።

ይሁንና የቻይና ህንድ ወዳጅነት አሁንም ቢሆን ከአንገት በላይ ይመስላል። በሁለቱ ሀገራት መካከል ሲያወዛግብ የነበረውን የሂማሊያ የድንበር ችግር አሁንም ፍቱን መድሃኒት የተሠጠው አይመስልም። ቤጂንግ በህንድ ውቅያኖስና በአካባቢው ያላት ወታደራዊ እንቅስቃሴ በኒው ደልሂ አይወደድም። ይህ በሆነበት የብሪክስን የትስስር ገመድ ይበልጥ በማጥበቅ የአሜሪካን የንግድ ጦርነት ጫና ለመቋቋም ሀገራቱ ለመሰል ልዩነቶችን ጀርባ መስጠት ግድ ይላቸዋል።

እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ለዓመታት የምትታወቅበት የዲፕሎማሲ ስልት ጎራን ያልለየና ከሁሉም ወገን ጋር ብሄራዊ ጥቅምን የማስጠበቅ መርህ ላይ የተመሠረተ ግንኙነት መሆኑ እሙን ነው።

ይሁንና ሀገሪቱ የዓለም ጂኦፖለቲካል ለውጥን ይፈጥራል ተብሎ የሚሰጋውን ብሪክስን መቀላቀላል በስጋትነት የሚመለከቱት አይጠፉም። ስጋት የሚሉት ደግሞ ምናልባት ይህ ሀገሪቱ ከምዕራቡ ዓለም ጋር ለዘመናት መሥርታ የቆየችውን ዲፕሎማሲ ሊጎዳባት ይችላል የሚል ነው።

በእርግጥ የኢትዮጵያ በብሪክስ አባልነት ውስጥ መግባት ከምዕራባውያን ጋር ባለው ግንኙነት ላይ ምንም መልእክት አያስተላልፍም ለማለት አያስደፍርም። ይሁንና አንድ መታወቅ ያለበት ሃቅ ቢኖር ለዋሽንግተን መንግሥት ቀኝ እጅና የቻይና ተገዳዳሪ የሆነችው ህንድ እንዲሁም የነጩ ቤተ መንግሥት ትኩረት የሆነችው ግብፅ የቡድኑ አባል መሆናቸው ሊዘነጋ አይገባም።

ኢትዮጵያም የብሪክስ አባል ትሁን እንጂ እንደትናንቱ ሁሉ ነገም ጎራን ያልለየና ከሁሉም ወገን ጋር ብሄራዊ ጥቅምን የማስጠበቅ መርህ ላይ የተመሠረተ ግንኙነት እንዲሁም ጥቅሞቿን ሊያስጠብቁ ከሚችሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ብሎ ሀገራት ጋር መሥራቷን እንደምትቀጥል መጠራጠርም አይገባም።

መሰል ተጨባጭና ተጨባጭ ያልሆኑ ስጋቶች እንደተጠበቁ ሆነው ከሁሉ በላይ በአባል ሀገራቱ ውጤታማ አጋርነት ለዓለም ማሳየት ከፈለጉ በመካከላቸው የእርስ በእርስ ትስስር እንዳይሳለጥ የሚያስሩ መሰል ሸምቀቆዎች እንዲበጣጠሱና የተደቀኑ ስጋቶችም እንዲቃለሉ ይበልጡን መድከም ግድ ይላቸዋል።

የጥርጣሬ እይታን ከማስተካከል ባለፈ በመካከላቸው ያለውም የንግድ ትስስር በዝቅተኛ የቀረጥ ታሪፍ ማጀብ ከቻሉ ደግሞ ስኬታማነታቸው ይበልጡን ጎልቶ ከመታየት የሚያስቆመው አይኖርም።

በኢትዮጵያም ጥቅም ባገናዘበ መልኩ ተፎካካሪ ሊያደርጉ የሚችሉ ለብልፅግናዋ መሠረት የሆኑ ዘርፎችን አማራጮችን በጥናት ለይታ ጥምረቱን መቀላቀል፣ ኢንቨስትመንቱ ከወዲሁ ተወዳዳሪና ተፎካካሪ መሆን የሚያስችለውን አቅም ስለማጎልበት እንዲሁም አቅጣጫዎችን ስለማመላከት ልታስብበት ይገባል። የንግድ ማህበረሰቡን ማንቃት፣ አምራች ድርጅቶችን ብቁና ተወዳዳሪ ማድረግ የግድ ይላል።

ታምራት ተስፋዬ

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 23/2015

Recommended For You