በሀገር ለመኩራት – ትምህርትን በጥራት

ከዓለማችን የሥልጣኔ መገለጫዎች አንዱ ደረጃውን የጠበቀ የትምህርት ሥርዓት መዘርጋት ነው። በትምህርት የበለጸገ አዕምሮ ሀገርን ይሰራል ፣ ዓለምን ይገነባል። ትምህርት ይሉት መሠሰረታዊ ጉዳይ ጥራቱ በወጉ ሲረጋገጥ ደግሞ የትውልድ ህልውና ያለስብራት ይቀጥላል።

የሰው ልጅ አሁን ለሚገኝበት የሥልጣኔ ደረጃ መነሻና መሠረቱ በወጉ የገነባው የትምህርት ሥርዓት ነው። ደረጃው ይለያይ እንጂ ከጥንት እስከዛሬ ያለው የትምህርት ሂደት የዓለማችንን የዕድገት ታሪክ በረጅም ርቀት አራምዷል።

ሀገራችን ዛሬ ለደረሰችበት ማንነት የተማሩ ዜጎቿ አስተዋጽኦ በእጅጉ የላቀ ነው። ያለፈችበትን የኋላቀርነት ታሪክ ከስሩ ፍቆ አዲስ የሚባል ምዕራፍ ለማስመዝገብም በትምህርት ዓለም ያለፉ ፣ የተማሩ፣ የተመራመሩ ልጆቿ ድርሻ የማይናቅ ሚና አበርክቷል። ይህን ያደረጉ መልካም ዜጎች ደግሞ ውለታቸውን ሀገርና ትውልድ አይረሳውምና ምስጋናውን ሊወስዱ ይገባል።

የትምህርት ጥራት ጉዳይ ሲነሳ መነሻውን ማሰብ ግድ ይላል። መሠረቱ በወጉ የተገነባ ቤት አቋሙ እንደማያሰጋ ሁሉ ከሥር ሲኮተኮት ያደገ ተማሪም የዕውቀት ፍሬው ያምራል። ለዚህ አስተዋጽኦ ደግሞ የአንድ ወገን እጅ ብቻ በቂ አይሆንም። የወላጆችን ትኩረት ጨምሮ የመምህራን የዕውቀት ደረጃ ሊፈተሽ ያስፈልጋል።

በኢትዮጵያ እየተስፋ ካለው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር ተያይዞ በየዓመቱ መጠነ ሰፊ የሚባል የተማረ ኃይል ይመዘገባል። ለነዚህ ዜጎች ሀገር የበዛ ዋጋ ከፍላባቸዋለች። ወላጆች ከሕይወታቸው ቀንሰው፣ ከኑሯቸው አጉድለው አ ስተምረዋቸዋል።

በየጊዜው በተለያዩ የትምህርት መስኮች የሚሰለጥነው የተማረ ኃይል ዕውቀትና ችሎታውን በተገቢው መንገድ እንደሚያውል ይጠበቃል። እንዲህ ሲሆን ይህች ድሃ ሀገር አትከስርም ። ዕውቀት አይባክንም። ተሞክሮው ለተተኪው ትውልድ ተሻግሮ የዕውቀት ቅብብሎሹ ሂደት በወጉ ይቀጥላል።

ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እየተስተዋለ ያለው እውነታ ግን ይህንን ሀቅ ከሥሩ እንዲያነቃንቅ ሆኖ ስጋትን አስከትሏል። አሁን ላይ በአብዛኞቹ ተቋማት ያለው የትምህርት ጥራት ማነስ ትውልድን በአግባቡ ለመቅረጽ እንደይቻል ጋሬጣ እየሆነ ነው።

ጥራቱን ያልጠበቀ ፣ ደረጃውን ያልመጠነ ትምህርት ሲኖር በዕውቀት ያልበለጸገ ትውልድ ይፈጠራል። መሠረት የሌለው ሥር ያልያዘ ሥርዓተ ትምህርትም ሀገርን ለድህነት ፣ ዕውቀትን ለብክነት ይዳርጋል። መሠረት በሌለውና ጥራት ባልጎበኘው የትምህርት መስመር ማለፍ ደግሞ ስለ ነገ የማያስብ ትውልድ እንዲፈጠር ምክንያት ይሆናል።

ስያሜን ብቻ በያዘ መነሻ የተንጠለጠለ ዕውቀት ርባና የለሽ ነውና ከመልካም ውጤት አያደርሰም። በእንዲህ አይነቱን ታሪክ የተሸከመ ‹‹ተምሪያለሁ›› ባይም ማንነቱን ለማጋለጥ የሚዘገይ አይሆንም ። ሁሌም የሀገር ኢኮኖሚን ለማናጋት የፈጠነ ነው። ከሙስናው መንደር፣ ከወንጀሉ ጓዳ ገብቶ ትውልዱን ይዘርፋል። ወገኑን ያደኸያል።

በአሁኑ ጊዜ በመንግሥት በኩል ለዘርፉ ጥራት የተሰጠው የተለየ ትኩረት ተቋማት የትምህርት አሰጣጥ ጓዳቸውን እንዲፈትሹ፣ የመምህራንና ተማሪዎቻቸውን የዕውቀት ደረጃና አቅም እንዲፈትኑ አስችሏል። እንደመነሻ ባለፈው ዓመት የተጀመረው የአስራሁለተኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ምርቱን ከግርዱ ለመለየት ያስቻለ ነበር።

በያዝነው ዓመት ተግባራዊ መሆን የጀመረው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመውጫ ፈተናም እስከዛሬ የነበረውን የትምህርት አሰጣጥና የጥራት ደረጃ በወጉ ለመለየት ያስቻለ ሆኗል።

ብዙ ጊዜ እንደሚስተዋለው በቂ ዕውቀትና ግንዛቤ የሌለው ሰው በራስ የመተማመን ብቃቱ አንካሳ ነው። እንዲህ አይነቱ ዕውቀት የለሽ ዜጋ ኃላፊነት በተሰጠው ጊዜ ማንነቱ ይጋለጣል። በተሸከመው ከፍ ያለ ሥምና ክብር የሚያስተዳድረውን ተቋም ይበድላል። የሚመራቸውን ሠራተኞች በተዋሰው ያልተገባ ዕወቀት ተመክቶ ይበድላል፣ ያሸማቅቃል።

እንዲህ አይነቱ ‹‹አለቃ›› ተብዬ እንደስሙ ኃላፊነትን የሚሸከም፣ ግዴታውን በብቃት የሚወጣ አይደለም። ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ለክብሩ እየሞተ ሀገሩንና ትውልዱን ያለኮሽታ ይገድላል። ለሙስና፣ በሩን ከፍቶ ስለራሱ ጥቅም ይዋደቃል።

ለእንዲህ አይነቶቹ ዕውቀት አልባ ማንነቶች መሠረት ከሚሆኑት መካከል ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎች ይጠቀሳሉ። አንዳንዶች ሳይለፉ ሳይደክሙ በቀላሉ የሚሸምቷቸው ማስረጃዎች የትምህርት ጥራቱን ዝቅተት አመላካች ናቸው። ማስረጃዎቹ በሐሰት ሚስጥር ተሸፍነው የዕውቀት ማንነትን እርቃን ያጋልጣሉ።

እንዲህ አይነቶቹ የትውልድ ጠንቆች የሚተማመኑት ኪሳቸውን እንጂ ጭንቅላታቸውን አይደለም። እግራቸው ለአንዲትም ቀን የትምህርትን ደጃፍ ሳይረረግጥ፣ ስሙን በወጉ አስተካክለው ከማይጠሩት ታዋቂ ዩኒቨርሲቲ የዲግሪ ማስረጃ ቤታቸው ድረስ ይመጣላቸዋል።

ይህ ብቻ አይደለም። ‹‹ተምረናል›› ባዮቹ የሚሰጣቸው ደረጃ ዓመታትን ከደከሙት እውነተኞቹ ተማሪዎች ውጤት በእጥፍ የላቀ ነው። እንዲህ መሆኑ ከሌሎች ይበልጥ ተመራጭና ተወዳዳሪ ያደርጋቸዋል። በያዙት የሀሰተኛ ሰነድ ባሻቸው መሥሪያ ቤት ተቀጥረው የመሥራት ዕድሉ በእጃቸው ይሆናል።

እንዲህ አይነቶቹ ህሊና ቢሶች በበረከቱ ቁጥር አእምሯቸው በትምህርት የበለጸገ ዜጎች ሥራ የማግኘት ዕድል ይጠባል። ዕውቀት በከንቱ ይባክናል፣ ሥራ አጥነት ይስፋፋል። ዕውቀት አልባዎቹ በጨመሩ ቁጥር ሀገር ከተማሩ ዜጎቿ የሚገባትን ጥቅም ታጣለች። ኢኮኖሚዋ ይቀጭጫል፣ ይቀነጭራል፣ ዕድገቷ ይዳከማል።

ዕውቀት ተፈጥሯዊ ነው። ገንዘብ የሚገዛው ሸቀጥ አይደለም። ትምህርት የደገፈው፣ ልፋት ያበሰለው አዕምሮ ደግሞ ተተኪዎችን እያስከተለ ዘመናትን ይሻገራል። ይህን እውነታ በተዳፈሩ የትምህርቱ ዓለም ሙሰኞች የሚፈጸመው ድርጊት ግን አሁን ላይ ከነውርነት ተሻግሯል። ትውልድን የመግደል ያህል የጀመሩት ጉዞ ተጋልጦ እስኪታይም እስካሁን ብዙ ተራምደዋል።

ከዓመታት በፊት መንግሥት በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎቹ ዙሪያ ማጣራት ሲያካሂድ መቆየቱ ይታወሳል። በዚህ ሂደት አስቀድመው ራሳቸውን ያጋለጡ፣ ከሥራ ገበታቸው የጠፉ ሠራተኞች እንደነበሩ ተሰምቷል። በእነዚህ ሠራተኞች ላይ የተወሰደ ሕጋዊ ርምጃ ስለመኖሩ ባይታወቅም ድርጊቱ ግን አሁንም ድረስ ቀጥሏል።

በቅርቡ በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ በተገኘው መረጃ በዩኒቨርሲቲው ተምረው ተመርቀዋል የተባሉና በቁጥር ሃያአንድ የሚሆኑ ግለሰቦች ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ተረጋግጦ ይፋ ሆኗል። ዩኒቨርሲቲው በ2015 ዓ.ም ባደረገው የማጣራት ሂደት ሕጋዊነት የሌላቸውን ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎች ስለማግኘቱ አሳውቋል።

ዩኒቨርሲቲው ይህን ማረጋገጫ ይፋ ያደረገው ከተቋሙ ተምረዋል የተባሉ ግለሰቦችን የቀጠሩ ድርጅቶች ማስረጃቸው ‹‹ይጣራልን›› ሲሉ ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት ነው በተለያዩ ጊዚያት የዩኒቨርሲቲውን ምሩቃን ከሚቀጥሩ መንግሥታዊና ዓለምአቀፋዊ ድርጅቶች የሚቀርቡ ጥያቁዎችን ተቀብሎ የማጣራት ሂደት የተለመደ ነው።

ዘንድሮ በተደረገው ተመሳሳይ ማጣራትም በዩኒቨርሲቲው ሳይማሩ ዲግሪ የተሰጣቸውን ጨምሮ በተማሪ የውጤት ኮፒ አጠቃላይ የነጥብ ለውጥ የተደረገባቸው ማስረጃዎች ተይዘዋል። በዩኒቪርሲቲው ስምና ሎጎ ተጠቅመው ባልያዙት ዕውቀትና ዲግሪ ማጭበርበር የፈጸሙት ግለሰቦችን ያገዛቸው ደግሞ የዘመኑ ቴክኖሎጂ ዕድገት ስለመሆኑ ዩኒቨርሲቲው አጋልጧል። በማህበራዊ ድህረ ገጽ ላይ ሙሉ ስማቸውና ተያያዥ ማስረጃዎቻቸው ይፋ የሆነው ግለሰቦች በያዙት የሀሰተኛ ትምህርት ማስረጃ በየትኛውም ተቋም የመቀጠር ሕጋዊነት እንደሌላቸውም ተጠቅሷል ።

እንደ አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሁሉ በአቻ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች የትምህርት ማስረጃዎችን የማጣራት ሂደት ሊጠናከር ይገባል። ይህ ብቻ አይደለም በየመሥሪያቤቱ ለሥራ ቅጥርና ለደረጃ ዕድገት ሲባል በገንዘብ የሚመነዘሩ ማስረጃዎች ጭምር ሊፈተሹ ግድ ነው።

ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎችን ከማጣራት ባለፈ በድርጊቱ የተሳተፉ አካላትን በሕግ አግባብ በመጠየቅ የፍርድ ሂደቱን ደረጃ ይፋ ማድረግ ያስፈልጋል። እንዲህ ሲሆን ሀገርን መታደግ ትውልድን ካልተገባ ጥፋት ማዳን ይቻላል። በተማረ የሰው ኃይል፣ የታመነ ዕውቀትን ለመገንባት ያስችላል። ሀገርና ወገን የሀሰተኞች፣ የወንጀለኞች መናኸሪያ ልትሆን አይገባምና።

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 23/2015

Recommended For You