ላለፉት 9 ቀናት በሃንጋሪ ቡዳፔስት ሲካሄድ በሰነበተው በ19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ኢትዮጵያ ከዓለም 6ኛ ከአፍሪካ 2ኛ ደረጃ ይዛ አጠናቃለች፡፡ ኢትዮጵያ በቻምፒዮናው 2 የወርቅ፤ 4 የብርና 3 የነሐስ በድምሩ 9 ሜዳልያዎችን ማስመዝገብ ችላለች።
በቻምፒዮናው የተመዘገበው ውጤት እንደሁልጊዜውም በጀግኖች አትሌቶቻችን እንዲሁም በአሠልጣኞች ጥረት፣ ልፋትና ተጋድሎ የተገኘ እንደመሆኑ ትልቅና መላ ኢትዮጵያውያንን ያኮራ ነው። በተለይም በሴቶች 10ሺ ሜትር የታየው አረንጓዴ ጎርፍ እንዲሁም በሴቶች ማራቶን የታየው የቡድን ሥራና የመረዳዳት ባህል ከውጤቱም በላይ የኢትዮጵያውያን አንገት በዓለም አደባባይ ቀና ያደረገ፣ ያልሸነፍ ባይነት ወኔያችንን አጉልቶ ያሳየ፣ ኢትዮጵያውያን ከተደጋገፍን ያሰብነውን ሁሉ ማሳካት እንደምንችል ያስመሰከረ ነውና ጀግኖች አትሌቶቻችን ሊመሰገኑ ይገባል። ጀግኖቻችን አኩርታችሁናል እናመሰግናለን!
የተመዘገበው ውጤት የሚያኮራና ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው ነው፡፡ ሆኖም በቂ ነው ብለን እጃችንን አጣጥፈን የምንቀመጥበት ሳይሆን ከድክመቶች ተምረን ጠንካራ ጎናችንን ይዘን ይበልጥ ልንሠራበት የሚገባም ነው። በዘንድሮው ቻምፒዮና ብዙ ትምህርት ያገኘንባቸው ድክመቶች ነገ ጠንክረን ለመመለስ እንደ ዕድል ልንጠቀምባቸው ይገባል፡፡ የነበረንን ጠንካራ ጎንም አጎልብተን ይበልጥ ተሽለን ለመገኘት መጠቀም ተገቢ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም በተለያዩ የዓለም መድረኮች ስኬታማ ያደረገን የቡድን ሥራ ባለፉት ዓመታት እየደበዘዘ መምጣቱ ብዙ ሲባልበት ቆይቷል። ዘንድሮ ይህን የቡድን ሥራ በአንዳንድ ውድድሮች ለመመለስ የተደረገው አበረታች ጥረት ውጤት ያመጣና ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባ ነው። ያም ሆኖ በበርካታ ውድድሮች በቡድን የመሥራትና ከግል ይልቅ ለሀገር ውጤት ቅድሚያ የመስጠት ጥረት ገና ብዙ እንዳልተሠራበት በብዙ አጋጣሚዎች ታዝበናል። ይህ ከፊታችን ለሚጠብቁን በርካታ ዓለም አቀፍ ውድድሮች እንቅፋት እንደመሆኑ ከወዲሁ ትኩረት ሰጥተን በመሥራት ፈር ልናስይዘው የሚገባ ቁልፍ ጉዳይ ነው። ለዚህም ከአትሌቶች ምርጫ ጋር በተያያዘ ዘወትር ውድድር ላይ የሚገጥመንን ውዝግብ ግልፅና ተጠያቂነት ባለበት መንገድ መልክ ልናስይዘው ግድ ይላል። ይህም በአትሌቶች መካከል እንዲኖር የምንፈልገውን የቡድን ስሜት በማጠናከር ረገድ የመከፋፈልና የጥርጣሬ ስሜትን በማስወገድ ለውጤታችን ማማር ጉልህ ድርሻ አለውና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሥራ ኃላፊዎች ሊያስቡበት ይገባል።
ኢትዮጵያውያን ቀደም ሲል በውጤታማነት በሚታወቁባቸው እንደ 5 እና 10ሺ ሜትር ርቀቶች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሌሎች ሀገራትም ውጤታማ እየሆኑ ፉክክሩም እየበረታ ይገኛል። ኢትዮጵያውያን በአንፃሩ ቀደም ሲል በማይታወቁበት እንደ 3ሺ ሜትር መሰናክል ባሉ ውድድሮች ወደ ውጤታማነት እየመጡ ቢሆንም ቀድሞ ውጤታማ በሆኑባቸው ርቀቶች መዳከም ታይቷል።
የአትሌቲክስ ጉዟችን አንዱን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ መሆን የለበትም። ያለንን ጥንካሬ ይዘን በአዳዲስ ውድድሮች ወደ ውጤት መምጣት ግዴታ ነው። ነባራዊው የዓለም አትሌቲክስ ሁኔታም ለዚህ ያስገድደናል። ለረጅም አመታት ውጤታማ በሆንባቸው ርቀቶች ተፎካካሪ ያልነበሩ አውሮፓውያን ሳይቀሩ ወደ ውጤት መጥተዋል። ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ምክንያት ጠንክረው መሥራታቸውና ጊዜውን የዋጀ ዘመናዊ የሥልጠና ሳይንስ መከተላቸው ነው። እኛ ባለፈው የውጤታማነት ታሪክ ብቻ ተኮፍሰን ከቀጠልን ውጤቱ ምን እንደሚሆን ተመልክተናልና መለስ ብለን ራሳችንን መመልከት ያለብን ጊዜ አሁን መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል። ኢትዮጵያውያን በምንታወቅበት የረጅም ርቀት ውድድሮች ተፈጥሮ በራሷ አቅሙንም ብቃቱንም እንዳደለችን ታሪክም ዓለምም ይመሰክራል። አትሌቶቻችን በግላቸው በሚያደርጓቸው ውድድሮች የሚያስመዘግቡት ውጤትም ይህንኑ ያረጋግጥልናል። ትናንት ከእኛ ጋር መፎካከር ቀርቶ ውድድር ላይ መቅረብ የሚሳናቸው ሀገራት በጥቂት አመታት ውስጥ ውጤታማ ለምን እንደሆኑ ቆም ብለን መመርመር አለብን። ከሌሎች የተለየ አቅምና ብቃቱ እያለን ውጤታማ መሆን ከከበደን አንዳች ችግር ወይም ትክክል ያልሆነ ነገር አለ ማለት ነው። ያንን ችግር ማወቅ ለመፍትሔው አንድ ርምጃ ነው፣ ቀጣዩ ችግሩን በተገቢው መንገድ ለመቅረፍ ጥረት ማድረግ ነው። ይህን አምነንና ተስማምተን እንደገና መጀመር ይኖርብናል።
የቀድሞ ታሪካችን እንደ መነሻ እንጂ ለወቅታዊ ውጤት ምንም እንደማይፈይድልን እንመን። አትሌቲክስ ሥልጠናውም፣ ዝግጅቱም፣ አስተዳደሩም፣ ውድድሩም ሳይንስ ሆኗልና ያንን መንገድ መከተል ለነገ የምንተወው የቤት ሥራ አይደለም።
አትሌቲክስ ለኢትዮጵያ ከስፖርትም የዘለለ ትርጉም አለው። አትሌቲክስ ለኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ለዘመናት ሥሟ ከፍ ብሎ ከሚሰማባቸውና ገናናነቷ ከሚታይባቸው መድረኮች አንዱና የሀገርን ገፅታ የሚገነባ ትልቅ የዲፕሎማሲ መሣሪያ ጭምር ነውና የተገኘውን ድል እያጣጣሙ ለነገ የተሻለ ውጤት ከዛሬ ጀምሮ መሥራት ይገባል!
አዲስ ዘመን ነሐሴ 23/2015