ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አባልነት በማህበረሰቡ በእጩነት ከቀረቡ ከ600 በላይ ሰዎች መካከል ብዙ ሂደቶችን አልፈው 11 ኮሚሽነሮች ከተመረጡ አንድ ዓመት ከአምስት ወራት ተቆጠሩ። ከኮሚሽነሮቹ መካከል በዓዕምሮ ሕክምና ዘርፍ የካበተ ልምድ ያላቸው እና ከ30 በላይ ጥናታዊ ፅሁፎችን ያቀረቡት፤ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በመዘዋወር ሀገር ያገለገሉት ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ በአስተማሪ እና በመካሪነታቸው ታዋቂነትን ማትረፋቸውን ተከትሎ የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ሆነው መመረጣቸው አይዘነጋም።
በኢትዮጵያ ሀገራዊ መግባባትን የመፍጠሪያ መድረክን ለመምራት የተቋቋመው ይኸው 11 አባላትን የያዘው ኮሚሽን፤ የሠራቸውን ሥራዎች በተለይም ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የተሳታፊ ልየታ ሥራው የደረሰበትን ደረጃ እና ወደ ፊትም በሚሠራቸው ሥራዎች ዙሪያ ከኮሚሽኑ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ጋር ቆይታ አድርገን፤ እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።
አዲስ ዘመን፡- ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የተሳታፊ ልየታ ሥራው ምን ላይ ደረሰ?
ፕ/ሮ መስፍን፡- እስከ አሁን በአምስት ክልሎች እና በአንድ የከተማ መስተዳድር ላይ ሲሠራ ቆይቷል። በተለይ በሐረር እና በድሬዳዋ በደቡብ ምዕራብ እና በሲዳማ ሰፊ የተሳታፊዎች ልየታ ሥራ ተሠርቶ፤ በአብዛኛው አልቋል። በአዲስ አበባ፤ በጋምቤላ እና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ደግሞ የተባባሪዎች ሥልጠና ተጠናቆ ወደ ተሳታፊዎች ልየታ እየሔድን ነው።
ከዚህ በኋላ ያለው የሥራ ሒደት ምን ያህል አዋጭ ነው? ምን ምን ተግዳሮቶች አጋጠሙ? በዚህ ፍጥነት ከሔድን ምን ያህል ጊዜ ሊፈጅብን ይችላል? የተባባሪ አካላትን ቁጥር ምን ብናደርገው ይሻላል? በተለይ ባስተዋልነው ሒደት ውስጥ አሁንም የሴቶች ተሳትፎ አመርቂ አይደለም። በተባባሪ አካልነት ወይም ሴቶች በጥሩ ሁኔታ እንዲሳተፉ ለማድረግ መውሰድ ያለብን ርምጃ ምንድን ነው? ብለን ለይተን እንሠራለን።
ተሳታፊዎች በሺ የሚቆጠሩ ሲሆኑ፤ ከየወረዳው ተሰብስበው ከአንድ ዞን 450 ሆነው ሲመጡ፤ የእነርሱን ማቆያ፣ መሰብሰቢያ አዳራሽ እና የትራንስፖርት ወጪያቸውን እና አጠቃላይ የአበል ክፍያ ራሱ በደንብ መታየት ያለበት ጉዳይ ነው። በሌላ በኩል እንዲሁ የመንግሥትን ገንዘብ መበተን አይቻልም፤ የሚያስፈልጉ ዶክሜንቶች መሟላት አለባቸው። ይህን ሁሉ ባለው የሰው ሃይል እንዴት መሥራት ይቻላል? የሚለውን ገምግመን ባለው ሁኔታ አስተካክለን፤ በቀጣይነት የጀመርናቸውን መጨረስ፤ ወደ አፋር ወደ ሱማሌ ፣ ወደ አዲሱ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፤ ወደ አማራና ኦሮሚያም ክልሎች በስፋት እንሔዳለን።
በአጠቃላይ ሥራችንን በዚህ ሁኔታ እያስኬድን ነው። ከተባባሪዎቻችን ጋር ማለትም ከሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከመምህራን፣ ከሲቪክ ማሕበረሰብ፣ ከእድሮች እና ከሃይማኖት ተቋማት ጋር እንሠራለን፤ እናሳትፋቸዋለን። ከዚህ በተጨማሪ ሴቶች እና ወጣቶች እንዴት ሊሳተፉ ይችላሉ? የሚለውን እናያለን። ተሳትፎ ላይ ሴቶች አሉ፤ ነገር ግን በተባባሪነት ባለድርሻ ሆነው እንዲመጡ ለማድረግ እንፈልጋለን። ይህ እንዲሆን ሥልጠና እና ሌሎችም ብዙ መሠራት ያለባቸው ሥራዎች አሉ፤ እየተሠሩ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- ምክክሩን ለማካሔድ የተዘጋጀ ፕሮግራም አለ? ለምሳሌ አዲስ አበባ ላይ መቼ ይጀመራል?
ፕ/ሮ መስፍን፡– አዲስ አበባ ላይ አበረታች ሥራዎች እየተሰሩ ነው። በአዲስ አበባ ከተማ በሀገራዊ ምክክር ላይ ተሳታፊ የሚሆኑ ተወካዮችን የመለየት ሥራ ተከናውኗል። እገዛ የሚያደርጉ ተባባሪ አካላትን የመለየት ሥራም ተሰርቷል። ተባባሪ አካላት የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበራት ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር፣ የኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ የዕድሮች ማህበራት ጥምረት፣ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋሟት ጉባዔ እና የወረዳ አስተዳደሮች ናቸው።
ኮሚሽኑ በከተማዋ በሚገኙ ወረዳዎች የህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች ልየታን በሁለት የተለያዩ ምዕራፎች የሚያከናውን መሆኑን ገልጸው፤ በመጀመሪያው ምዕራፍ ለተባባሪ አካላቱ ስለሂደቱ ግልፅ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ኮሚሽኑ የሶስት ቀናት ሥልጠና ሰጥቷል።
በሥልጠናው ተሳታፊ የሚሆኑት ተባባሪ አካላት በየአካባቢያቸው ተሳታፊዎችን በብቃትና በገለልተኝነት በመለየቱ ሂደት ለኮሚሽኑ እገዛ ያደርጋሉ።
ሁለተኛው ምዕራፍ ኮሚሽኑ የተሳታፊዎች ልየታን በመምራት እና በማስተባበር የሂደቱን ውጤታማነት የሚከታተልበት መሆኑን አመልክተው፤ በዚህ ምዕራፍ በከተማ አስተዳደሩ ስር ከሚገኙ 119 ወረዳዎች የተውጣጡ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍል ተወካዮችን የማስመረጥ ተግባር የሚፈጸምበት ነው ።
ተመራጮቹም በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት እና በዋና ምክክሩ የሚሳተፉ ተወካዮቻቸውን እንዲመርጡ የሚደረግ ይሆናል። ለሀገራዊ ምክክሩ አመቺነት ራሳቸውን የሚገልፁበት ዋና መተዳደሪያ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን ተሳታፊ የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመው፤ እነዚህም የሃይማኖትና የማህበረሰብ መሪዎች፣ ሴቶች፣ መምህራን፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ የግል ዘርፍ ተቀጣሪ ሠራተኞች፣ የንግድ ማህበረሰብ አባላት፣ ወጣቶች፣ ዕድሮች፣ በባህል እና በሙያቸው ምክንያት የተገለሉ የህብረተሰብ ክፍሎች እና ተፈናቃዮች በወረዳ ደረጃ የሂደቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ ተለይተዋል።፡
በሌሎችም አካባቢዎች ወቅቱን ያገናዘበ ሥራ እንሰራለን። ክረምቱ የማይበረታባቸው አካባቢዎች ለምሳሌ አፋር ላይ መሥራት እንችላለን። የአፋር ተሞክሮ እንደሚያሳየው የአፋር አንዳንድ ዞኖች በጣም ሩቅ ናቸው። ዞሮ ዞሮ ግን ወደ አፋር ወደ ሱማሌ፣ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ እያልን እንሔዳለን።
የሠላሙ ሁኔታም መረጋጋት ይኖርበታል። ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ወረዳ እና ዞን ድረስ ስንሔድ ሰላም ያስፈልጋል። ለትጥቅ ትግሉም ሆነ ለሁሉም መፍትሔ ሊሆን የሚችለው ጠመንጃ ሳይሆን፤ ወደ ትጥቅ ትግል የተገባበትን አጀንዳ አምጥቶ በሰላም ተነጋግሮ የጋራ መፍትሔ መፈለግ ነው። መፍትሔው ጠመንጃ ሳይሆን ዋነኛው አማራጭ ምክክር ብቻ ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ በምክክር ሁለቱም ወገኖች አሸናፊ ሆነው የሚወጡበት ነው።
በትጥቅ ትግል የሰዎች ሕይወት ይጠፋል፤ አካል ይጎድላል፤ ንብረት ይወድማል። በዚህ ድህነት ላይ ጦርነት እንደገና መጀመር፤ ከድህነት ወደ ባሰ ድህነት ማምራት እንጂ ምንም የሚተርፍ ነገር የለም። ትርፍ አለማግኘት ብቻ ሳይሆን አሸናፊ እና ተሸናፊ ይፈጠራል። በእርግጥ እንዳስተዋልነው ዛሬ አሸናፊ የሆነው ነገ ተሸናፊ ይሆናል። ጦርነት ዞሮ ዞሮ ከውድመት በስተቀር ምንም ጥቅም የማይገኝበት ነው። ዋናውና ትልቁ አማራጭ መፍትሔውም ጠመንጃ ሳይሆን አማራጩ ምክክር ብቻ ነው ብዬ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡- አዲስ አበባ ላይ ምን ያህል ተሳታፊዎች ይኖራሉ? እንደሌሎቹ ክልሎች ከየወረዳው የተወሰኑትን መምረጥ ነው? ወይስ አዲስ ነገር ይኖራል?
ፕ/ሮ መስፍን፡– ከየወረዳው 450 ተሳታፊ ለማድረግ አስበን ነበር። ነገር ግን ይህንን ቁጥር እንደገና እየከለስን ነው። ምክንያቱም በጣም ብዙ የሰው ሃይል እና ብዙ ገንዘብ ይፈልጋል። ቁጥሩን እያየነው ነው። ከዚህ በኋላ ከ450 በታች ይሆናል ብዬ አስባለሁ። አዲስ አበባ ውስጥ 120 ወረዳዎች አሉ። ከ120 ወረዳዎች ውስጥ ከእያንዳንዳቸው ወረዳ በርከት ያለ የሕዝብ ቁጥር ይመጣል። በአጠቃላይ ቁጥሩ በጣም ብዙ ይሆናል። በ120 ወረዳ ቢበዛ 20 ሺህ አካባቢ እና ከዛ በላይ ሊሆን ይችላል።
አሁን ጥያቄው በዛው በወረዳ እንጨርሰው ወይስ ወደ ክፍለ ከተማ እንሂድ? የሚለውን እያየን ነው። በየወረዳው ካሉ ዘጠኝ ባለድርሻ አካላት ውስጥ ተለይተው ከየባለድርሻ አካላቱ ሁለት ሁለት ይመረጣሉ፤ ስለዚህ በአጠቃላይ ከየወረዳው ወደ አስራ ስምንት ሰዎች ቁጥሩ ከፍ ሲል ወደ ሃያ ሰዎች ይመረጣሉ። እነዛ ሃያ ሰዎች ከክልሉ ወይም በአዲስ አበባ ደረጃ ደግሞ ከከተማ አስተዳደሩ ከሚመረጡ ሰዎች ጋር ሆነው አጀንዳ ይሰጣሉ።
የአዲስ አበባ አጀንዳ ከእነዚሁ ተሰብሳቢዎች ይመረጣል። እነዚሁ ተሰብሳቢዎች እንደገና ለዋናው ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሚወክሏቸውን ሰዎች ይመርጣሉ። በክልልም በከተማ መስተዳድርም ተመሳሳይ ነው። ምናልባት ሊለይ የሚችለው ከኢትዮጵያ ውጪ የሚኖሩት ዳያስፖራ የሚባሉት ላይ ካልሆነ በስተቀር በኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረጉት ነገሮች እና ሂደቶቻቸው ተመሳሳይ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ በአጠቃላይ ሃያ ሺህ የሚሆኑት ተመርጠው ከእነርሱ ውስጥ እንደገና ለሀገራዊ ምክክሩ ይመረጣሉ።
ፕ/ሮ መስፍን፡– 120 ወረዳዎች ቢኖሩ ከየባለድርሻ አካላት ከየወረዳው 18 ሰዎች ይመርጣሉ። ከመስተዳድሩ ተሳታፊዎች ጋር ይገናኛሉ። ከዛ ውስጥ ደግሞ በፌዴራል ደረጃ በሀገራዊ ምክክሩ ደረጃ ተመርጠው ይወጣሉ። የመንግሥት ተወካዮች፣ የሕዝብ ተወካይ ምክር ቤት አባላት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሠራተኛ ማህበራት ፣ የንግዱ ማሕበረሰብ፣ ሴቶች በከፍተኛ ሁኔታ ይበረታታሉ። ልሂቃን፣ አርብቶ አደር፣ አርሶ አደር፣ ማንም ወደ ኋላ የሚተው የለም። እስከ አገራዊ ምክክሩ ድረስ በዚህ መልኩ የሚቀጥል ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- በአማራ ክልል እና በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች የፀጥታ ችግር መኖሩ እየተገለፀ ነው። በእነዛ አካባቢ ምክክሩን የምታካሂዱት መቼ እና በምን መልኩ ነው?
ፕ/ሮ መስፍን፡- ቀናት ለመቁረጥ አሁን ላይ ያስቸግራል። ምክንያቱም የተለያዩ የየራሳቸው ምክንያቶች ይኖራሉ። ከላይ እንደገለፅኩት የመማከሪያው መንገዱን በተመለከተ በቅርቡ ይፀድቃል። ከፀደቀ በኋላ የውሎ አበል ክፍያ በደንብ ሥርዓት አስይዘን እስካሁን ያልተከፈላቸውን ተሳታፊዎች በሙሉ ከጨረስን በኋላ በአዲስ መልክ የሂሳብ ባለሙያዎችንም እንድንቀጥር ፍቃድ ተሰጥቶናል። በሚገባ ተጠናክረን መሥራት በሚገባን ደረጃ ላይ ስንደርስ እንሄዳለን። ዞሮ ዞሮ በቀጣዮቹ ስድስት ወራት ውስጥ ተሳታፊዎችን ለይተን፤ ቀርፀን፤ አውጥተን መጨረሻ ላይ ሀገራዊ ምክክር ይጀመራል የሚል ዕቅድ ይዘናል።
አዲስ ዘመን፡- ምክክሩ የሚካሔደው በተመሳሳይ ጊዜ ነው?
ፕ/ሮ መስፍን፡- ሀገራዊ ምክክሩ በተመሳሳይ ጊዜ የሚካሄድ ነው። ማንንም የሚያገል አይደለም። ሰላም የደፈረሰባቸው አካባቢዎችም በሂደት ከጠመንጃ ይልቅ የምክክሩን ሂደት ተገንዝበው ይመጣሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን። በሰሜንም፣ በደቡብም በምዕራብም በምስራቁም ያለው ሁሉም ወደ ሰላም መጥቶ የሚሻለው መመካከር ነው። ተስፋ የማደርገው ጠመንጃ ቀርቶ በሃሳብ ልውውጥ ችግር ለመፍታት ትኩረት ይሰጣል ብዬ ነው።
ሁሉም ነገር በንግግር ይፈታል የሚል እምነት አለኝ። ወሰንም ሆነ የማንነት ጥያቄ እንዲሁም ራስን በራስ ማስተዳደር እና የፍትህ ጥያቄዎች በአጠቃላይ የፖለቲካ ጥያቄዎች እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በሙሉ በትክክለኛ ምክክር ሊፈቱ የማይችሉበት ምክንያት አይኖርም።
አዲስ ዘመን፡- ምክክሩ ምን ያህል ጊዜ ይፈጃል? መቼ ይጠናቀቃል?
ፕ/ሮ መስፍን፡- እርሱ አሁን አይታወቅም። ምክንያቱም ብዙ የመወያያ ርዕሶች ይመጣሉ። ቅድሚያ እና የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ርዕሶች ይኖራሉ። ምክረሃሳቡ ለተርጓሚው እና ለፈፃሚው ክፍል እያለፈ በቀጣይነት ይሔዳሉ። አንዳንዶቹ ከእኛ የጊዜ ዘመንም ሊያልፉ እንደሚችሉ እርግጠኛ ነኝ። ቢያንስ የተወሰኑት ላይ በእኛ የሥራ ዘመን እጅግ ዋና ዋና አንኳር የሆኑ፤ ሕዝብን ለማባላት በደረሱት በተወሰነ መልኩ መፍትሔ እንዲያገኙ ከፍተኛ ጥረት እናደርጋለን።
አንዳንድ ርዕሶች በጣም ጊዜ ሊፈጁ ይችላሉ። ዝም ብለው በአንድ ጊዜ ተወያይተው ተማክረው እጅ አውጥተው የሚለያዩበት አይደለም። ምክክር የራሱ ሥርዓት አለው። ዝግጅቱ እና ቅድመ ዝግጅቱ ስድስት ወር የፈጀው ለዚህ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የዳያስፖራው ተሳትፎ በምን መልኩ ይካሔዳል? በበይነ መረብ ነው ወይስ በምን መልኩ ይሆናል?
ፕ/ሮ መስፍን፡– በበይነ መረብ መሳተፍን በተመለከተ ቀደም ብለን አስበን ነበር። ነገር ግን አሁን የሀገር ውስጡ ሥራ ውጥረት ውስጥ ስለከተተን እንጂ፤ በቅድሚያ ዳያስፖራው ስለእኛ ሥራ በደንብ ማወቅ አለበት። ልክ ከሌሎች ምክረ ሃሳብ እንደምንሰበስበው ሁሉ፤ ከዳያስፖራውም ምክረሃሳብ እንሰበስባለን። አሜሪካን ያሉትን ለብቻቸው፣ አውሮፓ እና አፍሪካ መካከለኛው ምስራቅ ከዛ እሲያ እና የፓስፊክ ውቅያኖስ ውስጥ ያሉትን ለይተን እንቀርባለን።
በስደት ላይ ያሉ የመጀመሪያ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ሁለተኛው ትውልድ የሚባሉ የተለያዩ አሉ። ስለዚህ ሕግ እና መመሪያው በሚፈቅድላቸው መሠረት ሁላቸውም ምክረሃሳብ እንዲሰጡ ይደረጋል። በመጨረሻም ሕግ እና መመሪያው የሚፈቅድላቸው ደግሞ እርስ በእርሳቸው ተመራርጠው ዋና ሀገራዊ ምክክሩ ላይ ኢትዮጵያ መጥተው እንዲሳተፉ ይደረጋል።
አዲስ ዘመን፡- ዳያስፖራዎች ተወካዮቻቸውን የሚመርጡት እንዴት ነው?
ፕ/ሮ መስፍን፡– እርሱን አልለየንም፤ ሀገራዊ ምክክር ውይይት ላይ የሚሳተፉትን በቁጥር ለመወሰን ገና ስምምነት ላይ አልደረስንም። እያብላላነው ነው። በአጠቃላይ በሀገራዊ ምክክር ሂደት ላይ ስንት ሰዎች ቢመካከሩ ያዋጣል? የሚለው በጣም ወሳኝ ነው። ምክንያቱም አስር ሺ ቢሆን በጣም ይበዛል። 100 ቢሆኑ፤ ለ120 ሚሊዮን ሕዝብ በጣም ያንሳል። ለሕዝቡ አሳታፊ ሊሆን የሚችለው ስንት ሰው ነው? የሚለውን በምክክር ውስጥ ዝም ብሎ ንግግር ሳይሆን በመረጃ የተደገፈ የሚጠቅም ንግግር፤ ተአማኒነት ያላቸው አወያዮች ያሉበት ምክክር፤ ከዚህም ባሻገር አመቻች ትልልቅ ሰዎች የማህበረሰብ መሪዎች ያሉበት ምክክር ይሆናል።
ምክክሩ የራሱ ሥርዓት እና ሒደት አለው። ቁጥሩም ከዛ ጋር በተያያዘ ሁኔታ ሰፊ ጊዜን ሊፈጅ የሚችል ሲሆን፤ እንዳልኩት የሚፈጀው ጊዜ አይታወቅም። ሌላ ሀገራት ላይ የተካሔደው ለምሳሌ አስር ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ቱኒዚያ ወይም ትልቅ ሕዝብ ያላት ኬንያ 40 ሚሊዮን ሕዝብ ያውም በተወሰነ አጀንዳ ላይ እንዴት ተመካከሩ ብሎ ማየት ይቻላል። ብዙዎቹ ከእኛ እጅግ ያነሰ ቁጥር ያላቸው ሕዝቦች ናቸው። እኛ ግን ከአፍሪካ ትልቅ ቁጥር ያለውን የሕዝብ ብዛት ይዘን የተነሳን ነን።
ፓርቲዎችን ጨምረን ሁሉም እንደየሁኔታው ከየማህበረሰቡ ንቁ ተሳታፊ መሆን ስለሚገባው በጣም ሰፍቶ ለመሰብሰብ አስቸጋሪ እንዳይሆን እንጠነቀቃለን። በጣም ያነሰ እና ለጥቂቶች ብቻ የሚተውም ሳይሆን፤ በጥንቃቄ መቀመርን ስለሚፈልግ አሁን እዛው አካባቢ ደርሰናል። ነገር ግን ዋናው ስምምነት ላይ በሚደረስበት ጊዜ ይገለፃል።
ከዛ ላይ በመነሳት የዲያስፖራው ቀመርም ይወጣል። ከአምስት እስከ አስር ሚሊዮን የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ውጪ ይኖራሉ፤ ከዛ ውስጥ አዋቂዎቹ እና ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ ለንግግር የሚበቁ ምን ያህል ናቸው? የሚለው ታይቶ ፤ ከዛ ውስጥ ደግሞ ምን ያህሉ ኢትዮጵያውያን ናቸው? የሚለው ይለያል። ምክንያቱም ሁሉም ኢትዮጵያውያን በትውልድ ይሁኑ እንጂ በዜግነት የሌላ ሀገር ዜጎች ናቸው።
በዜግነት የሌላ ሀገር የሆኑ ሰዎች በትውልድ ኢትዮጵያዊ በመሆናቸው እና እትብታቸው ኢትዮጵያ ውስጥ በመሆኑ ኢትዮጵያ የምትባለው ሀገር ታሳስባቸዋለች። ስለዚህ ምክረሃሳብ የመስጠት መብታቸውን እናከብራለን። ነገር ግን ሊሳተፉ የሚገባቸውን በተመለከተ መወሰን አለበት። ምክንያቱም እዛ ላይ በጣም ሚስጥራዊ ሀአገራዊ ጉዳዮች ይኖራሉ።
የአሀገሬው ሰው ብቻ የሚሳተፍባቸው ጉዳዮች ይኖራሉ። ለምሳሌ ውይይቱ የሚካሔደው ስለሕገመንግሥት ከሆነ ዜግነታቸው ኢትዮጵያውያን ያልሆኑ ሰዎች አይወያዩበትም፤ እነርሱ የራሳቸው የሚተዳደሩበት ሕገመንግሥት አላቸው። በማይተዳደሩበት ሕገመንግሥት ላይ ይህንን አድርጉ ማለት ያስቸግራል። ሃሳብ መስጠት ግን ይቻላል። በምክክሩ ግን የውሳኔ ሃሳብ ስጡ ለማለት ይቸግራል። እንዲህ ዓይነት ነገሮች ይኖራሉ። ዞሮ ዞሮ መመሪያው ተዘጋጅቷል። ይህንን ግልፅ እናደርገዋለን።
አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ በውጭ የሚኖሩ የኢትዮጵያውያን ዜግነትን የቀየሩ፤ ይሳተፋሉ ማለት ነው?
ፕ/ሮ መስፍን፡- በሁሉም ላይ የመሳተፍ መብት ያላቸው አሉ። ምክረሃሳብን በተመለከተ ግን ማንኛቸውም ወገን የመስጠት መብት አላቸው ብዬ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ በዚህ ስድስት ወር ውስጥ ዲያስፖራውም ይለያል ማለት ነው?
ፕ/ሮ መስፍን፡- አዎ! ልየታው ላይ ከአጀንዳው ጋር አብሮ ቀድሞ ይሠራል።
አዲስ ዘመን፡- እስከ አሁን ለአጀንዳ የሚሆን ሃሳብ መሰብሰቡ ምን ደረጃ ላይ ነው?
ፕ/ሮ መስፍን፡– ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በፈለገበት ሰዓት ባለው አማራጭ አጀንዳ መላክ ይችላል። ፅሕፈት ቤት በመምጣት በተዘጋጀው ሳጥን ውስጥ መክተት መብቱ ነው። ወደ ፊት ደግሞ እያዘጋጀን ባለነው በይነ መረብ ውስጥ በዛም መላክ ይቻላል። ይህ አንዱ ሲሆን፤ ሁለተኛ አዋጁ ላይ በጥናቶች የሚለዩ አጀንዳዎች ይኖራሉ ይላል። ለዚህ እኛም ባለሙያዎች አሉን። በጥናት የሚለዩም ካሉ እርሱንም እናያለን። ነገር ግን በአጠቃላይ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ እና ማንኛውም ወገን፤ ለሀገሩ መልካም የሚያስብ፤ የሀገሩ የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚያስጨንቀው ሁሉ፤ ‹‹ ወደ ፊት በጋራ እንድንሔድ የሚፈልግ ሁሉ፤ ተከባብረን እንዳንኖር የሚያደርጉ እንቅፋቶች ናቸው›› የሚላቸውን ጉዳዮች ለይተው መላክ፣ ፅፎ ማስገባት ይችላል።
አዲስ ዘመን፡- ከትግራይ ክልል ጋር በተያያዘ በአካል ተገኝታችሁ ተወያይታችሁ ነበር፤ ይህ ምን ላይ ደረሰ?
ፕ/ሮ መስፍን፡- በእርግጥ እኔ በወቅቱ አልነበርኩም። ከየሕብረተሰብ ክፍሉ ከተውጣጡ ሰዎች ጋር የምክክር ኮሚሽኑ አባላት ተዋውቀዋል። ነገር ግን የሔዱበት ሁኔታ ስለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለብቻው በሀገራዊ ሁኔታ የተወያዩበት ወይም የተፈጠረላቸው መድረክ አልነበረም። ከዛ ወዲህ ግን በጎ ፍላጎት እንዲኖር፤ ሌላ ቦታ የሠራነውን መሥራት እንድንችል ጥያቄ ጠይቀናል። ደብዳቤ ፅፈንላቸዋል። መልሳቸውን እየተጠባበቅን ነው። መምጣት ትችላላችሁ በሚባልበት ጊዜ ሁሉ፤ ሕዝቡን ለማግኘት እንሠራለን። በዛ ሒደት ደግሞ ሌላ አካባቢ እንዳደረግነው ሁሉ የጋራ ሥራ እንጀምራለን።
አዲስ ዘመን፡- ከምክክሩ ጋር በተያያዘ ከማን ምን ይጠበቃል? ሕዝቡ ምን ያድርግ?
ፕ/ሮ መስፍን፡– ከሕዝቡ የሚጠበቀው ለሰላም ተግቶ መሥራት እና መፀለይ ነው። ሁሉም መሣሪያ ያነሱ ወገኖች መሣሪያቸውን አስቀምጠው ወደ ሰላም መምጣት አለባቸው። በቀጥታ ወደ ውይይቱ እንዲመጡ ለታጣቂዎች ጥሪ አቀርባለሁ። ለመንግሥትም መልክት ማስተላለፍ የሚፈልግ ሲሆን፤ መንግሥት ለሁሉም እጁን ዘርግቶ ምሕረት እንዲያደርግ እና ከሁሉም ጋር እንዲደራደር እጠይቃለሁ።
ደም መፍሰስ ምን እንዳመጣ እናውቃለን። በኪሳራ ላይ ኪሳራ ጨምሮልን ሄዷል። ገና ከኀዘናችን አልወጣንም። በዚህ ላይ የኑሮ ውድነቱ እና ሌሎች ነገሮችም ተጨምረው በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ በመሆኑ ለሁላችንም የምለው ሰላሙ ላይ ትኩረት እንስጥ።
በተለይ ዋና ዋናዎቹ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት እና ማህበራዊ ሚዲያውም ከምን ጊዜውም በላይ ያለፉት ሶስት ዓመታት ተመልሰው እንዳይደገሙ በሰላሙ ዙሪያ ጠንክረው እንዲሠሩ እጠይቃለሁ።
በሌላ በኩል በትግራይ በኩል መንግሽት ያደረገው ድርድር ጥይት እንዳይጮህ አድርጓል። አሁንም እልህ መጋባት እንዲቀር እጠይቃለሁ። በመሃል ኢትዮጵያ፣ በሰሜን ኢትዮጵያም ላሉ ወገኖች የሰላም ጥሪ ቢቀርብ የተሻለ ነው እላለሁ። ሁላቸውም ቁጭ ብለው ቢነጋገሩ እና ከንግግሩ ቀጥሎ ግን ሁሉም ወደ ውይይት እና ወደ ምክክር እንዲመጡ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ።
የሀገር ሽማግሌዎች፣ በተለይም የሃይማኖት አባቶች፣ ከአሁን በፊት እንዳደረጉት እናቶችም በተቻላቸው መጠን ልጆቻችንን መሣሪያ እንዲያስቀምጡ፤ መንግሥትም ቀርቦ እንዲነጋገሩ ግፊት እንዲያደርጉ እጠይቃለሁ። በመጨረሻም የሀገር ሽማግሌዎች በሽምግልና፣ የሃይማኖት አባቶችም በፀሎታቸው እንዲያግዙን እጠይቃለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም እጅግ አመሰግናለሁ።
ፕ/ሮ መስፍን፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 22/2015