ለሰላም ዋጋ መክፈል ለሀገርና ለሕዝብ ተቆርቋሪነት ዋነኛ መገለጫ ነው

ለአንድ ሀገር ህልውና ሆነ ሁለንተናዊ እድገት፤ ሰላም መሠረታዊ ጉዳይ ስለመሆኑ ብዙ ነጋሪ የሚያስፈልገው ጉዳይ አይደለም። ይህንን ተጨባጭ እውነታ ታሳቢ በማድረግም ሀገራት ለሰላም ከፍያለ ትኩረት ሰጥተው ይንቀሳቀሳሉ። ለሰላም ቀናኢ ትውልድ ከማፍራት ጀምሮ፤ሰላምን አጽንተው መሄድ የሚያስችሉ ጠንካራ ተቋማትን ለመገንባት ብዙ ርቀት ይጓዛሉ።

በዚህም ሂደት/ጥረት የተሳካላቸው የዓለም ሀገራት ሕዝቦች እያንዳንዷን ቀን በሰላም፤ ከሰላም በሚመነጭ መንፈሳዊ እና አእምሯዊ መረጋጋት መምራት የሚያስችል ማኅበረሰባዊ/ ሀገራዊ ሥነልቦና መፍጠር የሚያስችል አቅም ፈጥሮላቸዋል፤ የጠንካራ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ሕይወት ባለቤት መሆን የሚያስችላቸውን ቁመናም አላብሷቸዋል።

እነዚህ ሀገራት ዜጎቻቸው ስለ ሰላም ተገቢውን ግንዛቤ እንዲጨብጡ፤ በእያንዳንዱ ዜጋ የሕይወት ትርክቱ ውስጥ የሰላም ጉዳይ ተገቢውን ስፍራ እንዲያገኝ፤ መንፈሳዊ ፣ ማኅበራዊ እና ባህላዊ መስተጋብሮቹ ለሰላም ሁለንተናዊ አቅም ሊሆኑ የሚችሉበትን የማኅበረሰብ መስተጋብር ፈጥረው ከትውልድ ትውልድ ማስቀጠል የሚችል ሥርዓት ገንብተዋል።

በየዘመኑ ያለው ትውልድ የዛሬ ማንነቱ ሆነ አሁን ላይ እንደሀገር /ማኅበረሰብ የደረሱበት ኢኮኖሚያዊ ፣ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ስኬት የሰላማቸው ትሩፋት መሆኑን በአግባቡ እንዲረዳ በማድረግ፤ ሰላሙን አጥብቆ እንዲጠብቅ የሚያስችል ጠንካራ የአዕምሮ መዋቅር መፍጠር ችለዋል። ለዚህም በየደረጃው ያሉ የትምህርት ሥርዓቶችን አቅም መገንቢያ ስትራቴጂክ መሣሪያ አድርገው ተጠቅመውበታል።

በእነዚህ ሀገራት የሚገኙ የጸጥታና የፍትሕ አካላትም ቢሆኑ ገና ከጅምሩ በዚህ እውነታ በተገነባ የአስተሳሰብ መሠረት ላይ የተዋቀሩ በመሆናቸው ውጤታማ መሆን ችለዋል። እራሳቸውን ከዘመኑ ጋር ተለዋዋጭ ከሆነው ዓለም አቀፋዊና ሀገራዊ እውነታ ጋር አስተሳስረው በመሄዳቸውም ጥንካሬያቸው ሳይሸረሸር ከትውልድ ትውልድ መሻገር ችለዋል።

በኛም ሀገር ድህነትን ታሪክ እናደርጋለን በሚል በለውጡ ማግስት የተጀመረው ሀገራዊ ንቅናቄ ስኬታማ እንዲሆን የለውጡ ኃይል ከሁሉም በላይ ለሰላም ከፍያለ ትኩረት ሰጥቶ ተንቀሳቅሷል። ችግሮችን በይቅርታ ከማለፍ ጀምሮ፤ አለመግባባቶችን በሃሳብ የበላይነት በውይይት ለመፍታት የሚያስችሉ አማራጮችን ይዞ በመምጣት ሀገሪቱን ከግጭት አዙሪት ለማውጣት ሞክሯል።

በታሪክ ካለፍንባቸው የኃይል እና የሴራ ፖለቲካ አንጻር ጥረቶቹ የተፈለገውን ያህል ውጤት ማምጣት አልቻሉም። ከሁሉም ይልቅ የሰላም እጦት በየዘመኑ ካስከፈለን አስከፊ ዋጋ አለመማራችን እንደ ሀገር ተፈጥሮ የነበረውን መልካም አጋጣሚ መጠቀም እንዳንችል በፍጥነት ውጤታማ እንዳናደርገው አድርጎናል።

በዚህም ከድህነታች ፣ ከኋላ ቀርነታችን ከዚህም ባለፈ ዛሬ ላይ ዋጋ እያስከፈሉን ካሉ ችግሮቻችን በስተጀርባ ያለው ስለ ሰላም ያለን የተዛባ አመለካከታችን መሆኑን በፖለቲካችን ውስጥ ያለው ፉከራና ቀረርቷችን ፣ ከዚህ የሚመነጨው ጀብደኝነታችን እንደ ሀገር ዛሬያችንን ብቻ ሳይሆን ነገዎቻችንን ጭምር እየገደሉብን ስለመሆናቸው ማስተዋል አልቻልንም።

አሁን ላይ በየዘመኑ የነበሩ ትውልዶች ተስፋ ያደረጉት ድህነትን ታሪክ የማድረግ ህልም እውን ማድረግ የሚችለው ከሁሉም በላይ ስለ ሰላም ያለን የተዛባ አመለካከት ሲለወጥና በተለወጠው አመለካከት የተገነባ ሀገራዊ ሥነልቦና መፍጠር ስንችል ነው። ከዛ ውጪ “ውረድ እንውረድ” በሚለው ዘመን ያለፈበት ሀገርን በጎዳ ዜማ ድህነትን ታሪክ ማድረግ አንችልም።

ለሀገርና ለሕዝብ ተቆርቋሪ ነኝ የሚል የትኛውም ግለሰብ ሆነ ቡድን ስለ ሰላም ያለውን የተዛባ አመለካከት ሊያርም ይገባል። እንደ ሀገር የሰላም ማጣት ያስከፈለንን ያልተገባ ዋጋ ቆሞ በማጤን፤ ስለ ሰላም ሊከፈል የሚገባውን ዋጋ ሁሉ ለመክፈል ዝግጁነትን መፍጠር ይጠበቅበታል፤ ለሀገርና ለሕዝብ ተቆርቋሪነት ዋነኛ መገለጫውም ይኸው ነው!

አዲስ ዘመን ነሃሴ 22/2015

Recommended For You