የሰብል ጥበቃውን በጋራ ርብርብ

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ 2011 ዓ.ም ለኢትዮጵያ፣ ሶማሊያና ኬንያ እንዲሁም አጎራባቻቸው እጅግ ፈታኝ ጊዜ ነበር። ያ ዓመት የበረሃ አንበጣ መንጋ በሀገሮቹ በከፍተኛ ሁኔታ ጉዳት ያደረሰበት ነበር። ከኬንያ ውጭ ባሉ ሀገራት መሰል የአንበጣ መንጋ ሲከሰት ከ25 ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ያ ወቅት በተለይ በኬንያ ከ70 ዓመታት በኋላ አስከፊ የአንበጣ መንጋ የተከሰተበት ወቅት ሆኖ ተመዝግቧል። የአንበጣ መንጋ ወረርሽኙ ግዙፍ ሲሆን፤ የአፍሪካ ቀንድንና ደቡብ እስያን እያካለለ ያገኘውን ሰብል በማውደም የአካባቢውን ሕዝብ የምግብ አቅርቦትና ሕይወት አደጋ ላይ ጥሏል።

በወቅቱ መንጋውን ለመከላከል መንግሥት ብቻ ሳይሆን ዓለምአቀፍ ተቋማትም ርብርብ አድርገዋል። አርሶ አደሩም ሴት፣ ወንድ፣ ሕፃን ሽማግሌ ሳይል ድምፅ እያወጣ፣ ጢስ እያጤሰ መንጋውን ለመከላከል ርብርብ አድርጓል። ሥራው ግን ከባድ እንደነበር መረጃዎች ያስታውሳሉ። አብዛኛው ጉዳት የደረሰው በደን ላይ ቢሆንም በአዝእርት ላይም እንዲሁ ጉዳት ደርሷል፤ የአርሶ አደሮች ሰብል ወድሟል። የተለያዩ የዜና አውታሮች እንደዘገቡት ደግሞ 2014 ዓ.ም በአፍሪካ ቀንድ ሀገራት የአንበጣ መንጋ አስጊነቱ ቀንሷል።

የምሥራቅ አፍሪካ የበረሃ አንበጣ መከላከል ድርጅቱ ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው፤ በተጠቀሰው ዓመት ኢትዮጵያና ኬንያን ጨምሮ በቀጣናው ሀገራት ዝቅተኛ ዝናብ መኖሩ እንዲሁም በአካባቢው የተከሰተው ድርቅ የአንበጣ መንጋውን እንዳይፈለፈል አድርጎታል። አንበጣ ዋና መፈልፈያው እርጥበት ማግኘት ስለሆነም በቂ እርጥበት አለመኖሩ፣ አንበጣው እንዲዳከምና የመቀነስ አዝማሚያ እንዲያሳይ አድርጎታል።

መረጃው እንዳመለከተው፤ የአንበጣ መንጋው ከፍተኛ መጠን ያለው ነው። ቁጥሩም እስከ 10 ቢሊዮን ሊሆን ይችላል። የሚሸፍነውም ቦታ በመቶዎች ኪሎ ሜትር ሲሆን፤ በቀን እስከ 200 ኪሎ ሜትር በመሸፈን ያገኘውን እየበላ በመራባት የአርሶ አደሮችን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥል ነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብና የእርሻ ድርጅት እንደገለፀውም የአንበጣ መንጋው በአማካይ 2500 ሰዎችን ለአንድ ዓመት የሚመግብ ምርትን ሊያወድም ይችላል። እናም ከጅምሩ እርሱን መከላከል የውዴታ ግዴታ ሆኖ ካልቀጠለ አደጋው ይከፋል። ስለዚህም ሁሉም በተቻለው መጠን ሳይከሰት ለመከላከል፤ ከተከሰተ ደግሞ በተለያዩ አማራጮች መፍትሄ ለማፈላለግ መስራት ይኖርበታል።

የአንበጣ መንጋውን በቋሚነት ለመከላከል ሥራዎች ቢከወኑም እርሱን በቋሚነት ማጥፋት ያዳግታል። በመሆኑም ትንበያዎችን እየተከታተሉ ቅድመ ጥንቃቄዎችን ማድረግ ያስፈልጋል። ለዚህም ማሳያው ከሰሞኑ አንበጣው በስፋት የታየባቸው ክልሎች ሲሆኑ፤ እንደየክልሉ ሁኔታና የአንበጣ መከሰት አቅም ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን የክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊዎች ይገልጻሉ። አንበጣው በድጋሚ እየተራባ እንደመጣና ለመከላከል ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን የትግራይ፣ አማራና አፋር ክልሎች እየገለጹ ይገኛሉ። ግብርና ሚኒስቴርም እያገዛቸው መሆኑን ያስረዳሉ።

የምሥራቅ አፍሪካ የበረሃ አንበጣ መከላከል ድርጅት በበኩሉ የአንበጣ መንጋውን አስቀድሞ ለመከላከል እና ከተከሰተም በቶሎ ለመቆጣጠር እንዲያስችል የመሠረተ ልማቶች ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን ያመለክታል፤ በኢትዮጵያም በተለያዩ አካባቢዎች ላይ ተዛማጅ ተባዮችን የመከላከያ ማዕከላት እየተቋቋሙ እንደሆነም ይገልጻል። ይህ ሁሉ ተግባር ምን መልክ ይዟል፤ ክልሎች የት ላይ ናቸው፤ ግብርና ሚኒስቴርስ ምን ያህል ዝግጁነት አለው የሚሉና መሰል ጥያቄዎችን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ለሚመለከታቸው አካላት አንስቷል።

በአፋር ክልል ከሰብል ጥበቃ ጋር በተያያዘ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን የክልሉ የእንስሳት፣ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ አስታውቋል። የቢሮው የዕጽዋት ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ሀቢብ አብደላ እንዳሉት፤ የሰብል ጥበቃ ሥራው በተለያየ መልኩ እየተከናወነ ይገኛል። አንዱ በክልሉ የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ የመከላከል ተግባር ሲሆን፤ ክልሉ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመሆን የተለያዩ ሥራዎች እያከናወነ ነው።

መንጋው በአረንጓዴ ዐሻራ በተተከሉ ችግኞችና ለእንስሳት ምግብ በሚሆኑ ተክሎች ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፣ መነሻው ደግሞ ከቀይ ባህር አካባቢ መሆኑን ይናገራሉ፤ የአንበጣ መንጋው መታየት የጀመረው ከሰኔ 15 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ነው። የመከላከል ሥራው ወዲያው የተጀመረ ባለመሆኑም ከአፋር ክልል አልፎ የትግራይ አጎራባች ዞኖች ላይም እንዲከሰት አስችሎታል ሲሉ አቶ ሀቢብ ይጠቁማሉ።

የአንበጣ መንጋው በክልሉ በሚገኙ 15 ወረዳዎች ላይ ጉዳት እያደረሰ የሚገኝ እንደሆነ ያነሱት አቶ ሀቢብ፤ አንበጣው በተለይ ግመሎችና ፍየሎች የሚመገቧቸው ተክሎች ላይ እንዲሁም በቅርቡ በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብሮች የተተከሉ ችግኞች ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው ብለዋል። መንጋው የተከሰተበት ወቅት የደረሱ ሰብሎች በሚሰበሰቡበትና የእርሻ ስራ በሚከናወንበት ወቅት በመሆኑ በከፊል አርብቶ አደር አካባቢ የሚገኙ አርሶ አደሮች ላይ ጉዳት ያስከትላል የሚል ስጋት እንዳለም ነው የገለጹት።

የአንበጣ መንጋው እስካሁን በተክሎች ላይ ያደረሰው ጉዳት ምን ያህል እንደሆነ ክልሉ መረጃ በማሰባሰብ ላይ እንደሚገኝ የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፤ ክልሉ ከመረጃ ማሰባሰብ ጎን ለጎን የመከላከል ሥራውን ማጠናከር ላይ እየሠራ ነው። የክልሉ መንግሥት ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበርም ከሐምሌ 18 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ መንጋውን የመከላከል ሥራ እያከናወነ ነው ሲሉ ያብራራሉ።

በዚህ ደግሞ ከትግራይ ክልል ተነስቶ ወደአፋር ክልል በመጓዝ ጉዳት ሲያደርስ የነበረውን የአንበጣ መንጋ ከመነሻው መቆጣጠር መቻሉን ጠቅሰው፤ ግብርና ሚኒስቴር የባለሙያ፣ የበጀትና የኬሚካል እንዲሁም ሌሎች ድጋፎችን ያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፤ ችግሩን ለመቆጣጠር የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ያስገነዝባሉ። የአንበጣ መንጋውን ሙሉ በሙሉ ማጥፋት እስከሚቻልበት ጊዜ ድረስ ከትግራይ ክልልና ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በጋራ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።

እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ለማህበረሰቡ ግንዛቤ የመፍጠርና መንጋውን ለመከላከል የሚረዱ የግብዓትና የበጀት ድጋፎችን ከአጋር ድርጅቶች ማሰባሰብም ይገባል። ለዚህ ደግሞ ክልሉ ቁርጠኛ ሆኖ ይሠራል፤ አሁን ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር አንበጣ የት፣ እንዴትና መቼ እንደሚራባ ለባለሙያዎች ሥልጠና በመስጠት አስፈላጊውን የመከላከል ሥራ ለማከናወን ጥረት እየተደረገ ነው።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮም እንደ አፋር ሁሉ ክልሉ ተለይቶ የተሰጠውን ተግባርና ኃላፊነት ለመወጣት የምርት ዘመኑን ግብና ዕቅድ አዘጋጅቶ በርካታ ሥራዎችን እንዳከናወነ የቢሮ ኃላፊ ዶክተር ኃይለማርያም ከፍያለው ይናገራሉ። በተለይም ከሰብል ጥበቃ አንጻር የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ይገልጻሉ።

‹‹እንደ ክልል አሁን ያለንበት የክረምት ወቅት ዝናብ ወጣ ገባ የሆነበት ነው። ይህ ደግሞ ለተባይ መፈጠር ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። እናም እንደ ክልል የሰብል ጥበቃን በተመለከተ ብዙ ሥራዎች ማከናወን እንዳለብን ተገንዝበናል›› ያሉት ዶክተር ኃይለማርያም፤ በምስራቅ አማራ በኩል ያሉ አካባቢዎች ለዚህ ተጋላጭ ሆነዋል። የተምች ወረርሽኙና የአንበጣ ወረርሽኝ በተከታታይ አጋጥሟቸዋል። የፌዴራል መንግሥት የኬሚካል አቅርቦቱን ትኩረት አድርጎ ሲከታተለው ስለነበር እንደ ወረዳና ክልል ከፍተኛ ርብርብ ተደርጎ የተምች ወረርሽኙን ጉዳት ሳያደርስ መከላከል ተችሏል ይላሉ።

በአካባቢው የተከሰተውን የአንበጣ ወረርሽኝ ግን ገና ለመቆጣጠር እየተሠራ እንደሆነ የጠቀሱት ኃላፊው፤ አሁን ባለው ሁኔታ ወረርሽኙ ሦስተኛ ዙር ጭምር ሊከሰት እንደሚችል ስጋት መኖሩንም አመልክተዋል። ስለሆነም ትኩረት ሰጥተን በእኛ በኩል ለመስራት እንሞክራለን። ሕዝቡና የሚመለከታቸው አካላትም በዚህ ጉዳይ ላይ ርብርብ ሊያደርጉ ይገባል ይላሉ።

የትግራይ ክልል የእርሻ ተፈጥሮ ሀብትና የአፈር ልማት ማሻሻል ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ገብረስላሴ ከአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ጋር የሚስማማ ሃሳብ አላቸው። ሃላፊው መንጋው እንዲጠፋና ጉዳት እንዳያደርስ ማድረግ የሚቻለው ተቀናጅቶ መሥራት ሲቻል እንደሆነም ያምናሉ። የበርሃ አንበጣ መንጋው የክልሎችን ድንበር የሚሻገር መሆኑን ጠቅሰው፣ በመከላከሉ ላይ የፌዴራል መንግሥት ሥራ እንዳለ ሆኖ ክልሎችም ተጋግዘው መሥራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

እሳቸው እንዳብራሩት፤ የትግራይ ክልል በዚህ የመኸር ወቅት ችግር ሊሆን ይችላል ተብሎ ከሚያስበው ውስጥ አንዱና ዋነኛው የሰብል ጥበቃ ጉዳይ ነው። ምክንያቱም በክልሉ የአንበጣ መንጋ በምስራቃዊና ደቡብ ምስራቅ አካባቢ እየታየ ነው። አስቀድሞ በነበረ ትንበያ መሠረት ግን ከወዲሁ ግብረ ኃይል በማዘጋጀት አሁን ላይ በፍጥነት ወደ መከላከል ሥራ ተገብቷል። ሥራው የአንድ ወቅት ብቻ አይደለምና ዝግጁ ሆኖ መጠበቅ እንዲሁም ሁሉም አመራርና ህዝብ በትኩረት መሥራት ይኖርበታል ሲሉ አስገንዝበዋል።

የግብርና ሚኒስቴር የዕፅዋት ጥበቃ መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ በላይነህ ንጉሤ እንዳሉት፤ በክልሎች የተከሰተው የአንበጣ ወረርሽኝ ብዙ አደጋ እንዳያደርስ ቀደም ብሎ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል። ከተከሰተም በኋላም ቢሆን ለመከላከል የሚያስችሉ ዝግጅቶች ተደርገዋል። ለአብነት በክልሎች ላይ ለተከሰተው የአንበጣ ወረርሽኝ መከላከል የሚውል 41 ሺህ 500 ሊትር የተለያዩ የኬሚካል አይነቶች ተሰራጭተዋል።

አቶ በላይነህ እንዳመለከቱት፤ ችግሩን ለመከላከል ስድስት አውሮፕላኖች ተዘጋጅተዋል፤ የተሰራጨውን ኬሚካል የሚረጩ ስምንት መኪናዎች ከ11 ባለሙያዎች ጋር ወደ አካባቢዎቹ ተልከዋል።

መሪ ሥራ አስፈጻሚው አሁን የተከሰተው ወረርሽኝ የከፋ አይደለም ሲሉ ጠቅሰው፣ ይሁንና እያደር የመበራከታቸው ነገር ሊመጣ ይችላልና ሁለቱ አውሮፕላኖች የኬሚካል ርጭት ሥራ እንዲጀምሩ ሆነዋል ብለዋል። የአንበጣ መንጋ ወረርሽኝ በክልሎች ተከስቶ በሰብል ላይ ጉዳት ከማድረሱ በፊት ለመከላከል የተለያዩ ኬሚካሎች ክልሎች ተደራሽ መደረጋቸውን ጠቅሰዋል፤ ለኦሮሚያ ክልል 12 ሺህ፣ ለአማራ 10 ሺህ 500፣ ለትግራይ ሰባት ሺህ ፣ለአፋር አንድ ሺህ፣ ለደቡብ ሦስት ሺህ፣ ለደቡብ ምዕራብ ሁለት ሺህ ሊትርና ለሌሎች ክልሎችም ተደራሽ የማድረግ ሥራ እንደተሠራም ያነሳሉ።

በክልሎች የተከሰተው የአንበጣ መንጋ ወረርሽኝ በሰብል ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ በሚደረገው የመከላከል ሥራ በቂ የኬሚካል ክምችት ባይኖርም ያለውን ችግር ሊቋቋም የሚችል የኬሚካል ክምችት አለ ሲሉ ጠቅሰው፣ የመከላከል ትግበራውም በትኩረት እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ የአንበጣው ወርርሽኝ የማጥቃት ደረጃው እየተጠና ኬሚካል መርጨት፤ የሚያስፈልገውን የመለየት ሥራ እየተሠራ ነው። በትግራይ ክልል በባህላዊ መንገድ የመከላል ሥራ እየተሠራ ሲሆን፣ የተላኩት ባለሙያዎችና መኪናዎች በክልሉ ካሉት የግብርና ባለሙያዎች ጋር በቅንጅት እየሠሩ ይገኛሉ።

በክልሎች የተከሰተው ወረርሽኝ እያደረሰ ያለው ጉዳት የከፋ ባለመሆኑ ተራራማ ቦታዎችን ኬሚካል ለመርጨት አንድ አውሮፕላን በቂ ነው ያሉት መሪ ሥራ አስፈጻሚው፣ አንድ አውሮፕላን ሁለት ሺህ ሊትር ኬሚካል የመርጨት አቅም አለው። አንድ ሊትር ኬሚካል ደግሞ አንድ ሄክታር መሬት መሸፈን ይችላል ብለዋል። ተቋሙ የአንበጣ ወረርሽኝና ፀረ ሰብል ተባዮችን ለመከላከል በቀጣዮቹ ጊዜያትም ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት የሚሠራበት እንደሚሆን አስታውቀዋል።

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን ነሃሴ 22/2015

Recommended For You