እየተባባሰ የመጣው የአየር ንብረት ለውጥ

ከአላርም (አጣዳፊ የድረሱልኝ ጥሪ) በስተቀር በዚህ ጽሑፍ ምንም አዲስ ነገር ይዘን አልመጣንም። ጉዳዩ የዝሆን ጆሮ ይሰጠኝ ሆነና ነው እንጂ፣ በችግሩ ዙሪያ ያልተባለ ነገር የለም።

በዓለማችን የችግሩ መኖር ከታወቀበት ጊዜ ጀምሮ በአየር ጸባይ ለውጥ ዙሪያ ያልተካሄደ ስብሰባ፤ ያልመከረ ጉባዔ፣ ያልተፈረመ ስምምንት አለ ለማለት በማይቻል ደረጃ ሀገራት በመሪዎቻቸው አማካኝነት መክረዋል፤ ዘክረዋል፤ ምለው ተገዝተዋል።

በዘርፉ ያልተካሄዱ የጥናትና ምርምር ሥራዎች እንደሌሉ ሁሉ ያልተረቀቁ ፖሊሲዎችና ያልወጡ ሕጎችም የሉም። ይህ ሁሉ ይሁን እንጂ፣ የችግሩ ቀስት ዛሬም ወደ ላይ እንጂ ወደ ታች ሲያመለክት አይታይም።

የግላስኮው ኮፕ26 የአየር ንብረት ጉባኤ፣ የፓሪስ ስምምነት ወዘተ ሁሉ ይህንኑ የአየር ንብረት ለውጥን ለመታደግ የተደረጉ ውይይቶችና ስምምነቶች ናቸው፤ ከራሱ ከተባበሩት መንግሥታት ጀምሮ፣ ግሪን ፒስንና የመሳሰሉትን ይዞ በርካታ ድርጅቶች በዚሁ ችግር ዙሪያ በሥራ ተጠምደናል የሚሉ አካላት ናቸው። እነሱ ይህንን ይበሉ እንጂ ዓለም በየቀኑ እየነፈረች ከመሄድ ወደ ኋላ ያለችበት ደቂቃ የለም።

ያደጉት ሀገራት በአውሮፓውያኑ 2009 ደሃ ሀገራትን ለመደገፍና አማራጭ የኃይል መንገዶችን ለመደገፍ እስከ 100 ቢሊዮን ዶላር ድረስ ፈሰስ ለማድረግ ቃል ገብተው እንደነበር ይታወሳል። ቃል ይግቡ እንጂ እስካሁን ምንም የለም።

የዘርፉ ተመራማሪዎች በተደጋጋሚ እንደሚሉት፣ ያደጉት ሀገራት የገቡትን ቃል ለመፈጸም ቸልተኝነት ባሳዩ ቁጥር ከባድና ተደጋጋሚ ጎርፎች፣ በረሃማነት እንዲሁም ያልተለመደ ቅዝቃዜ እየጨመረ ይሄዳል። ይህም ለዓለማችን እጅግ አስጊና አጥፊ ነው። በመሆኑም ቃል የተገባው መፈፀም አለበት።

ወዳለንበት፣ ወደ ወቅታዊው የዓለማችን ሁኔታ እንምጣ፤ “የአየር ንብረት” ማለት በአንድ ሥፍራ ያለው የአየር ፀባይ በዓመታት የሚያሳየው አማካይ ውጤት፤ “የአየር ንብረት ለውጥ” ደግሞ የዚህ አማካይ አየር ፀባይ መቀየር ማለት መሆኑን ልብ ይሏል።

የቻይናን እና የሩሲያ መሪዎች ያልተገኙበት፤ በዓለማችን ከፍተኛውን የካርቦንዳይኦክሳይድ ልቀት የሚያደርጉት አሜሪካ እና ቻይና በሚቀጥሉት አስር ዓመታት በአየር ጸባይ ለውጥ ዙሪያ (ለግሪንሃውስ መሸንቆር ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርገውን የሚቴን ልቀት፣ ወደ ንጹህ ኃይል መሸጋገር እና ካርቦንን ማጥፋትን ጨምሮ) ተባብረው ለመሥራት መስማማታቸውን ይፋ አድርገዋል።

የቻይና ከፍተኛ የአየር ንብረት ተደራዳሪ የሆኑት ዢ ዤንሁዋ “በቻይና እና አሜሪካ መካከል ካለው ልዩነት በበለጠ ስምምነት አለ” በማለት የተናገሩበት የግላስጎው የአየር ጸባይ ስምምነት የከሰል ምርትን ከመቀነስም ባለፈ ሙሉ ለሙሉ ለማስቀረት የሚያስች የውሳኝ ሃሳብ የቀረበበት ነበር ።

በወቅቱ የከሰል ምርትን ሙሉ ለሙሉ ለማስቀረት የቀረበውን ሃሳብ የሕንዱ የአየር ንብረት ሚኒስትር ብሁፔንደር ያዳቭ በስብሰባው ወቅት “ድሃ ሀገራት ድህነትን ለመቀነስና የእድገት ጎዳናቸውን ለማሳለጥ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ውስጥ እንዴት አድርገው ከከሰል ሌላ አማራጭ ኃይል መጠቀም ይችላሉ?” በሚል ተቃውሞ አሰምተው ፤ በኋላም ሃሳባቸው ተቀባይነት አግኝቶ ውሳኔው ወደ “ቀስ በቀስ መቀነስ…” መሻሻሉ ይታወሳል።

በወቅቱ የተደረሰበት ስምምነት በአይነቱ የመጀመሪያ የተባለለት መባሉም ይታወሳል። ስምምነቱ ጎጂ ጋዞችን መልቀቅ በፍጥነት እንዲቆም ወስኖ የነበረ መሆኑም እንደዛው። ግን፣ “ምን ለውጥ መጣ?” እንደ ባለሙያዎቹ እይታ ከሆነ “ምንም”።

ፖላንድ፣ ቬትናም እና ቺሊን ጨምሮ ዋና ዋና የከሰል ተጠቃሚዎች እንደ ከሰል፣ ፔትሮሊየምና የተፈጥሮ ጋዝ የኃይል ምንጮችን ላለመጠቀም ቃል የገቡበት፤ ፖላንድ፣ ቬትናም እና ቺሊ ለመጀመሪያ ጊዜ የድንጋይ ከሰል ኃይል ላለመገንባት እና በዘርፉ መዋለ ንዋይ ላለማፍሰስ ከተስማሙ 18 ሀገራት መካከል መሆናቸው በደስታ የተገለፀበት ነበር ።

የቀድሞው የዩኤስ አሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ወጣቶችን ለአየር ንብረት ለውጥ “ተነሱ!!!” በማለት ጥሪ ያስተላለፉበት … የግላስጎው ኮፕ26 የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ምን ላይ ደረሰ??? ብለን ብንጠይቅ የምናገኘው መልስ ወደ ኋላ የሚወስድ እንጂ ወደ ፊት የሚያራምድ አይደለም፤

ችግሩ “የሰዎችንና የተፈጥሮ ሀብትን ህልውና እየተገዳደረው ይገኛል” ከሚለው ማእቀፍ ውስጥ አልወጣም። ወይም፣ ወፎች ሳይቀሩ ከሀገር ሀገር እየተሰደዱ ከመጥፋት የታደጋቸው አካል የለምና በጉዳዩ ላይ ተሰርቷል ለማለት አይቻልም።

ተመራማሪዎቹ እንደሚናገሩት ከሆነ፣ የዓለም ሙቀት ከ 1.5 ሴልሺየስ በላይ ከፍ የሚል ከሆነ ምድራችን አይታው የማታውቀው አይነት ቀውስን ታስተናግዳለች። በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ሰዎችም ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ይወድቃሉ። በኮፕ26 ጉባኤ ላይ እንደተገለፀው፤

• የሙቀት መጠን 1.5 ሴልሺዬስ ላይ መቆየት ካልቻለ ምድረ አውሮፓ በጎርፍ ልትጥለቀለቅ ትችላለች፤

• የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ከፍተኛ ሙቀት ያስተናግዳሉ፤ የእርሻ ቦታዎች ወደ በረሃማነት ይቀየራሉ፤

• የውቅያኖስ መጠን ሲጨምር በፓሲፊክ ክፍል ያሉ ደሴቶች የሚዋጡበት እድል ይኖራል፤

• በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ድርቅ ያጠቃቸዋል፤ የምግብ እጥረት ያጋጥማቸዋል፤

• ምዕራባዊ የአሜሪካ ክፍል በድርቅ ሲጠቃ፤ የተቀረው ክፍል ደግሞ በነጎድጓድ ዝናብ የመጥለቅለቅ አደጋ ይገጥመዋል፤

• አውስትራሊያ በከባድ ድርቅና ሙቀት ልትጠቃ የምትችልበት እድል ሰፊ ነው።

ተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በኮፕ26 የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ላይ “በአየር ንብረት ለውጥ የሚመጣ ትልቅ ቀውስ እንዲከሰት እያደረግን ነው። በፍጥነት ውሳኔ ላይ ደርሰን ምድራችንን የምንታደግበት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሰናል” በማለት እንዲናገሩ፤ የችግሩንም ጣራ መንካት እንዲገልፁ አስገድዷቸዋል።

ያ እንዳለ ሆኖ፣ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በቅርቡ የዓለም ሳይንቲስቶች አጥንተው ያቀረቡላቸውን የአየር ንብረት ለውጥ ሪፖርት መነሻ አድርገው የዓለማችን መልካም ጊዜ እያለፈ፤ የዓለማችን መጥፊያ ወቅት በፍጥነት እየመጣ ነው። በመሆኑም ያለ ምንም ጊዜ ማጥፋት መሪዎች በዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ላይ ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩ ይገባል በማለት ገልፀዋል።

እርግጥ ነው፣ የአየር ንብረት ለውጥ በከፍተኛ ደረጃ እየታየ ነው። ለዚህ ምክንያቶቹ ቢለያዩም በአብዛኛው የሰው ልጅ ራሱ የሚያደርሰው ጥፋት ስለ መሆኑ ሁሌም በማስረጃ ተደግፎ እየቀረበ ይገኛል። በተለይ ባለሀብት ተብዬ ግዙፍ ኩባንያዎች ማእድን አለ፣ ነዳጅ እናወጣለን … በማለት ደን ምንጠራውን ሊያቆሙ ይገባል።

የዓለም ሳይንቲስቶች “የምድራችንን ሳንባዎች ጠብቁ” ምክር ካልተሰማ፤ በካይ ጋዞችን የመቀነስ ሥራዎች ካልተሰሩና ሌሎች ችግሮችም ካልተወገዱ (ከፍተኛ ሙቀት እና ሰደድ እሳት ጉዳት ሲያደርስ ከባድ ዝናብ ባመጣው ጎርፍም የሰዎች ሕይወት እና ንብረት ሲጠፋ እየተመለከትን መሆኑን ልብ ይሏል) ዓለማችን የሚጠብቃት አደጋ ግልፅ ነው።

ከላይ ለደንቡ ያህል የገለፅናቸው እንዳሉ ሆነው፣ እጅግ አሳሳቢው የሰሞኑ የሳይንቲስቶቹ ሪፖርት ሙሉ ተቀባይነትን አግኝቶ ሁሉም በችግሩ ላይ እጁን ሊያነሳ ይገባል።

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ነሃሴ 22/2015

Recommended For You