ሀገራዊ ፈተና ሆኖ የቀጠለው ሕገ ወጥ ስደት ፤

 ፍልሰት እንበለው ስደት ሰፊና ውስብስብ የሰው ልጆች ታሪክ ነው። በብዙ ሺዎች የሚቆጠር ዓመታትን ያስቆጠረ ሰብዓዊ ክስተትም ነው። ሰዎች ከቅድመ ታሪክ አንስቶ በተለያዩ ገፊ ምክንያቶች ማለትም በአየር ንብረት ለውጥ፣ በሕዝብ ብዛት፣ በኢኮኖሚያዊ ዕድሎች፣ በፖለቲካዊ አለመረጋጋት፣ በባህላዊና ማህበራዊ ተጽዕኖዎች የተነሳ ከቦታ ወደ ቦታ ይፈልሳሉ፣ ከሀገር ወደ ሀገር ይሰደዳሉ።

በአምላክነት ምኞት ወይም ጥንተ ዓብሶ /Origi­nal sin/ የተነሳ አደም ኃጢያተኛ ሆኖ ልጅነቱን አጥቶ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ፍጹም ጸብ ተጣልቶና መርገም መጥቶበት ከገነት ከተባረረበት ከዛ ሩቅ ዘመን አንስቶ ዘረ አዳም ፍልሰተኛና ስደተኛ ነው። ሳይንሱ ደግሞ የሰው ዘር ወይም ሆሞ ሳፒንስ ከአፍሪካ ተነስቶ ወደ ሌሎች አህጉራት እንደተስፋፋ ይነግረናል። የዕለት ጉርሱን ለማግኘት፣ በአየር ንብረት ለውጥ የተነሳና አዳዲስ አካባቢዎችን ከማግኘትና ከማወቅ ጉጉቱ የተነሳ እግሩ በመራው ሲሰደድ ኖሯል።

በጥንታዊው የታሪክ ሂደት በስልጣኔዎች መካከል ሳይቀር ስደት መከሰቱን የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ። ሜሶፓታሚያንስ፣ ግብጻውያን፣ ግሪኮችና ሮማንስ በግዛታቸው ውስጥም ሆነ ውጭ በጦርነት፣ በንግድ፣ በቅኝ ግዛትና ሀብት ለመፈለግ ሲሉ ይሰደዱ ነበር። በመካከለኛው ዘመን ደግሞ በሮማን ግዛት ወይም ኢምፓየር መንኮታኮት የተነሳ፣ በቪኪንግ መስፋፋት፣ በሞንጎሎች ወረራና በመስቀል ጦርነቶች የተነሳ ሕዝብ በስፋት ተሰዷል።

ከ15ኛው መክዘ እስከ 18ኛው መክዘ የነበረው የአሰሳ ዘመን በሰው ልጆች ታሪክ አሻራውን ትቶ ያለፈ ከፍተኛ ስደት ተከናውኗል። አውሮፓውያኑ ክርስቶፈር ኮለምበስ፣ ቫስኮ ዳ ጋማና ፈርዲናንድ ማጅላን አዳዲስ የንግድ መስመሮችንና ስፍራዎችን ለማሰስ ባደረጉት ጉዞ አሜሪካን፣ አፍሪካን፣ እስያንና የሰላማዊ ውቅያኖስ ደሴቶችን በማግኘታቸው በአውሮፓውያን ቅኝ እንዲገዙ ፈር ቀድዷል። ይሄን ተከትሎ በተስፋፋው የባሪያ ንግድ ደግሞ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ከቀዬአቸው ተፈንግለው ወደ ሰሜንና ደቡብ አሜሪካ ተግዘዋል።

በ19ኛውና በ20ኛው መክዘ ደግሞ በኢንዱስትሪው አብዮት፣ በፖለቲካዊ አለመረጋጋት በተሻለ ኑሮ ፍለጋ የሰው ልጅ በገፍ ተሰዷል። የአይርላንድ የድንች ርሀብ፣ የካሊፎርኒያ የወርቅ ፍለጋና የኢንዱስትሪ አብዮቱ ታላቅ የሕዝብ ስደትን አስከትለዋል። በዚህም የአይሪሽና የጂዊሽ ዲያስፓራዎች ተፈጥረዋል። ሁለቱ የዓለም ጦርነቶችም ከፍተኛ የሕዝብ ስደት ቀስቅሰዋል። በአፍሪካና በእስያ ቅኝ ግዛት ከተንኮታኮተ፣ ሶቭየት ሕብረት ከፈራረሰች በኋላና ሉዓላዊነትን ተከትሎ ከፍተኛ የሕዝብ ስደትና ፍልሰት ተከስቷል።

ኢትዮጵያውያንም ይህን የሰው ልጅ ታሪክ በራሳቸው አውድ ተጋርተውታል። የሰሜኑ ወደ ደቡብ፣ የደቡቡ ወደ ሰሜን ፤ የምዕራቡ ወደ ምስራቅ፣ የምስራቁ ወደ ምዕራቡ የሀገራችን ክፍል ፈልሷል። ቀይና ነጭ ጤፍ ሲቀላቀል ለመለየት እንደሚቸግረው ኢትዮጵያውያን በጋብቻ፣ በሃይማኖት፣ የሀገር ሉዓላዊነትን ለማስከበር በተደረገ ተጋድሎ፣ ወዘተረፈ እርስ በርስ በአጥንትና በደም ተጋምደዋል። ምንም እንኳ ጽንፈ በረገጠ ጽንፈኝነት እየተፈተኑ ቢሆንም።

በተለይ ባለፉት 50ና ከዚያ በላይ አመታት መንገድና መጓጓዣ በመስፋፋቱና በመዘመኑ፤ የሀገሪቱ ፖለቲካም መጠፋፋት ላይ መጎንቆሉ፤ የተሻለ ኑሮና ኢኮኖሚያዊ ዕድል የሚሻው ትውልድ እየተበራከተ መምጣቱ፤ በሀገራችን የተንሰራፋው ሥራ አጥነትና ድህነት፣ ሀገራዊ አለመረጋጋት፣ የገነገነ ሙስና፣ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ፣ ድርቅና ርሀብ በሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎች ታግዞ በተለይ ሕገ ወጥ ስደቱ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። ዜጎች በሀገራቸው ሰርተውና ጥረው ግረው ከመለወጥ ይልቅ ስደትን መምረጣቸው ለተለያዩ ችግሮች እያጋለጣቸው ነው። የሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎችንና ደላላዎችን የማይጨበጥና ሀሰተኛ ማማለያ እየሰሙ የባሕር፣ የበርሀ፣ የአውሬ፣ የአሸባሪና የአረመኔ የድንበር ጠባቂ ሰለባ እያደረጋቸው ይገኛል።

ለአካላታቸው ማለትም ለኩላሊትና ጉበታቸው ሲባል በሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎች እየተገደሉ፤ አካላቸው እየጎደለ ነው። ሴቶች አልፎ አልፎም ወንዶች ሳይቀሩ እየተደፈሩ፤ ኅልቆ መሳፍርት የሌለው ግፍ፣ ሰቆቃና ስቃይ እየተፈጸመባቸው ይገኛል። ይሄን ሁሉ ፈተና አልፈው ሳውዲ፣ ባህሬን፣ ኩየት፣ ዩናይትድ ኤሚሬት፣ ሶሪያና ሊባኖስ ከደረሱ በኋላ በሕገ ወጥ መንገድ ስለሚቀጠሩ ሌት ተቀን የሰሩበት የደላላና የአሰሪ ሲሳይ ሆኖ ይቀራል። በዚህ ብስጭት ለአእምሮ ሕመም ይዳረጋሉ። በአሰሪዎቻቸው አሰቃቂ ግፍና በደል ይፈጸምባቸዋል። እንደ ደቡብ አፍሪካ ባሉ ሀገራትም ሰርተው በበሉ በተለወጡ በሀገሬው ይገደላሉ። ይዘርፋሉ።

በሕገ ወጥ መንገድ በሱዳን፣ በሞያሌና በጅቡቲ የሚወጡ ዜጎች መንገድ ላይ በውሃ ጥም፣ በርሀብ፣ በአውሬ፣ በሰው አካላት Human organs ነጋዴዎች እየተገደሉና እየሞቱ፣ ባሕር ላይ የአሳ ነባሪ ሲሳይ እየሆኑ፣ በሊቢያና በየመን በአጋቾች እየተሰቃዩ፣ በድንበር ጠባቂዎች በግፍ በጥይት እየተደበደቡ እንደሚገደሉ እያዩና እየሰሙ፤ ሕገ ወጥ ስደተኞች ግን ከዓይናቸውና ከጆሯቸው ይልቅ አዘዋዋሪዎችንና ደላላዎችን ማመን በመምረጣቸው ዛሬም ለማየት የሚዘገንን ለመስማት የሚሰቀጥጥ ሰቆቃ እየተፈጸመባቸው ይገኛል።

ሕገ ወጥ እየተባሉ በአረብ ሀገራት ማጎሪያዎች እየተሰቃዩ ነው። ኢትዮጵያ ነብዩ መሐመድ የሚወዷት፣ መልካም ምድር፣ የታማኞችና የደጎች፣ ፍትሕ የሚያውቁ ሕዝቦች ሀገር እንደኾነች የተናገሩላት፣ አምነው መልእክተኞችን የላኩባት፣ እርሷን አትንኳት ያሉባት የቃል ኪዳን ሀገር ብትሆንም ሳውዲ አረቢያ በዜጎቻችን ላይ የምትፈጽመው ኅልቆ መሳፍርት የሌለው ግፍ ግን ከዚህ ፍጹም የሚቃረን ነው፡፡

በተለይ በሳውዲ አረቢያ ዜጎቻችን በተለየ መንገድ በደልና ስቃይ ይፈጸምባቸዋል። ዓለም አቀፉ የስደተኞች ማህበር እንዳስታወቀው የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ከኅዳር 2009 ዓ.ም አንስቶ ስደተኞችን በግዳጅ ወደ ሀገራቸው መመለስ ከመጀመሩ በፊት በሀገሪቱ 500 ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ይኖሩ ነበር። በዚህም ከግንቦት 2009 እስከ መጋቢት 2011 ዓ.ም ባለው ጊዜ 260 ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን በአማካይ በየወሩ 10 ሺህ ሰዎች በግዳጅ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ተደርገዋል።

ዓለም አቀፉ የስደተኞች ማህበር እንዳስታወቀው በግዳጅ ወደ ሀገራቸው የመመለሱ ሂደት አሁንም ቀጥሏል። የሳዑዲ አረቢያ የሀገር ውስጥ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ከተለያየ ዓለም በመምጣት በሳዑዲ እየኖሩ ሕግ የጣሱ 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሰዎች በፖሊስ ታስረዋል። ከነዚህ ውስጥ 51 በመቶ የሚጠጉት ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ በአጠቃላይ 895 ሺህ የሚጠጉት ኢትዮጵያውያን ደግሞ በግዳጅ ወደ ሀገራቸው የሚመለሱ መሆናቸውን ሪፖርቱ አመላክቷል። ሰሞኑን ደግሞ ሒውማን ራይትስ ዋች ባወጣው ሰፊ ሪፖርት ኢትዮጵያውያን በሳውዲ ድንበር ጠባቂዎች በግፍ እንደተገደሉ፤ ከፍ ሲልም በሰብዓዊ ፍጡር ላይ የሚፈጸም ወንጀል እንደሆነ እየተዘገበ ይገኛል።

የሳውዲ ድንበር ጠባቂዎች ከመጋቢት 2022 እስከ ሰኔ 2023 ባለው ጊዜ ውስጥ የየመን-ሳውዲን ድንበር ለመሻገር በሞከሩት በትንሹ በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችንና ጥገኝነት ፈላጊ ኢትዮጵያውያንን ገድለዋል። የሳውዲ ባለሥልጣናትም በአንድ በኩል የራሳቸውን ገፅታ ለመገንባት በስፖርታዊ ውድድር ላይ በቢሊዮኖች ወጪ ሲያደርጉ በሌላ መልኩ ደግሞ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሴቶችና ሕፃናትን ከቀረው ዓለም እይታ በተሰወረ መንገድ ይገድላሉ። ሳውዲ አረቢያ በስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ላይ የምትከተለውን ገዳይ ፖሊሲ ጊዜ ሳትሰጥ በአስቸኳይ መሻር አለባት። ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሀገሮች በበኩላቸው ተጠያቂነት እንዲኖር ግፊት ማድረግ ያለባቸው ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም በጉዳዩ ዙሪያ ምርመራ ማካሄድ አለበት ሲል ሒውማን ራይትስ ዎች ያሳስባል።

ሒዩማን ራይትስ ዎች ዛሬ ያወጣው ሪፖርት፣ የሳውዲ ድንበር ጠባቂዎች ከመጋቢት 2022 እስከ ሰኔ 2023 ባለው ጊዜ ውስጥ የየመን–ሳዑዲን ድንበር ለመሻገር የሞከሩትን በትንሹ በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችንና ጥገኝነት ፈላጊ ኢትዮጵያውያንን ገድለዋል። ስደተኞችን የመግደል ርምጃ የሳውዲ አረቢያ መንግሥት ፖሊሲ አካል ሆኖ ከተፈፀመ፣ እነዚህ ግድያዎች ቀጣይነት ያላቸውና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ይሆናሉ ይላል።

ባለ 73 ገጹ የሒውማን ራይትስ ዎች ሪፖርት ሰሞኑን ይፋ እንዳደረገውና ዓለም አቀፍ ብዙኃን መገናኛዎችም እንደተቀባበሉት፤ ተኩስ በእኛ ላይ እንደ ዝናብ አወረዱብን ሲሉ ስደተኞች ይናገራሉ። የሳውዲ ድንበር ጠባቂዎች ብዙ ስደተኞችን ለመግደል ፈንጂ እንደተጠቀሙ፣ በስደተኞች ላይ በቅርብ ርቀት ሆነው እንደተኮሱባቸው እና ብዙ ሴቶችንና ሕጻናትን ጨምሮ፣ ሰፊ እና ስልታዊ በሆኑ ጥቃቶች መግደላቸውን አረጋግጧል። በአንዳንድ አጋጣሚዎች፣ የሳዑዲ ጠረፍ ጠባቂዎች ስደተኞቹን በየትኛው አካላቸው ላይ እንደሚተኩሱባቸው እየጠየቁ በቅርብ ርቀት ተኩሰው ገለዋቸዋል።

በተጨማሪም እነዚህ የሳውዲ ድንበር ጠባቂዎች ወደ የመን ለመመለስ የሞከሩ ስደተኞች ላይም ፈንጂ እንደተኮሱባቸው ከጥቃቱ የተረፉ ስደተኞች ለተቋሙ ገልጸዋል። በሒዩማን ራይትስ ዎች ድርጅት የስደተኞችና ፍልሰተኞች መብቶች ተመራማሪ የሆኑት ናዲያ ሃርድማን እንደሚሉት” የሳዑዲ ባለሥልጣናት በነዚህ ሩቅ በሆኑ ድንበር አካባቢዎች ከቀረው ዓለም እይታ በተሰወረ መልኩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችና ጥገኝነት ፈላጊዎችን ይገድላሉ። የሳውዲን ገፅታ ለመገንባት ለጎልፍ ፕሮፌሽናል፣ ለእግር ኳስ ክለብ እና ለዋና ዋና መዝናኛ ዝግጅቶች ግዥ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ሀብት ወጪ ማድረጋቸው በእነዚህ ዘግናኝ ወንጀሎች ላይ ያለውን ትኩረት ማዛባት የለበትም። “

ሒውማን ራይትስ ዎች ከመጋቢት 2022 እስከ ሰኔ 2023 ባለው ጊዜ ውስጥ የየመን-ሳዑዲን ድንበር ለመሻገር የሞከሩትን 38 ኢትዮጵያውያን ስደተኞችና ጥገኝነት ፈላጊዎችንና 4 ዘመድና ጓደኞቻቸውን ጨምሮ ለ42 ሰዎች ቃለ መጠይቅ አድርጓል። የሒውማን ራይትስ ዎች ማህበራዊ ድረ-ገፆች ላይ የተለጠፉ፣ ከሌሎች ምንጮች የተገኙና በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ስኩዌር ኪሎ ሜትሮችን ካካለሉ የሳተላይት ምስሎች የተገኙ ከ350 በላይ ቪዲዮዎችን እና ፎቶግራፎችን መርም ሯል።

በግምት 750,000 ኢትዮጵያውያን በሳውዲ አረቢያ ውስጥ እየሠሩ ይኖራሉ። ብዙ ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች ቢኖሩአቸውም በቅርቡ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል እንደነበረው በጦር መሣሪያ የታገዘ አሰቃቂ ግጭት፣ አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ በሚደርስባቸው ሰብዓዊ መብት ጥሰት ምክንያት ሀገራቸውን ጥለው ይሰደዳሉ። ሒዩማን ራይትስ ዎች በየመንና ሳውድ ድንበር አካባቢ የተፈፀሙ የስደተኞችን ግድያ ከ2014 ጀምሮ በሰነድ ያዘጋጀ ሲሆን፣ ግድያዎቹም ሆን ተብለው የተፈፀሙና የሟቾችም ቁጥር የበዛና የአገዳደላቸው ሁኔታም የከፋ ነው።

ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች በባህር ላይ ለመጓዝ ምቹ ባልሆኑ መርከቦች የኤደንን ባህረ–ሰላጤ እንዳቋረጡ ተናግረዋል። ከዚያም የየመን ሕገ ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች በሳውዲ ድንበር በሁቲ ታጣቂ ቡድን ቁጥጥር ሥር ወደሚገኘው ሰዓዳ ግዛት ወስደዋቸዋል። ብዙዎች የሁቲ ኃይሎች ከሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች ጋር እንደሚሠሩና እንደሚዘርፏቸው ወይም ስደተኞችን ወደ ማቆያ ማዕከላት እንደሚያስተላልፉ እና ሰዎች “የመውጫ ክፍያ” እስኪከፍሉ ድረስ በዚያ እንግልት ይደርስባቸዋል ብለዋል።

እስከ 200 የሚደርሱ ስደተኞች በቡድን ሆነው ወደ ሳውዲ አረቢያ ድንበር ለመሻገር በየጊዜው ይሞክራሉ። ብዙ ጊዜ የሳዑዲ ድንበር ጠባቂዎች ወደ ኋላ ከገፏቸው በኋላ ብዙ ሙከራ ያደርጋሉ። ስደተኞች ቡድኖቻቸው ከወንዶች የበለጠ ሴቶች እንደሚበዙ ተናግረዋል። ሒውማን ራይትስ ዎች ከእነዚህ መረጃዎች ጋር የሚጣጣሙ የሳውዲ ድንበር ጥበቃ ቦታዎችን ከሳተላይት ምስሎች ለይቷል። በተጨማሪም ሒውማን ራይትስ ዎች ከጥቅምት 11/2021 እስከ ጥር 1/2023 በአንዱ የሳውዲ የድንበር ጥበቃ ጣቢያ አካባቢ ከደፈጣ የተጠበቀና ፈንጂን መቋቋም የሚችል የሚመስል ተሽከርካሪ መታየቱን ለይቷል።

ተሽከርካሪው በጣራው ላይ የተገጠመ ከባድ መትረየስ ያለው ይመስላል። ከሳውዲ ድንበር ጠባቂዎች አቅጣጫ በሞርታር ፕሮጄክታይሎች እና በሌሎች ፈንጂ መሳሪያዎች ድንበሩን እንዳቋረጡ ጥቃት እንደደረሰባቸው በቡድን የሚጓዙት ሰዎች ገልጸዋል። የሳውዲ ድንበር ጠባቂዎች ፈንጂ መሳሪያዎችን ስለመጠቀማቸው ቃለ- መጠይቅ የተደረገላቸው ሰዎች 28 ክስተቶችን በመግለፅ አስረድተዋል። በሕይወት የተረፉ ሰዎችም ሳውዲዎች አንዳንድ ጊዜ በማቆያ ቦታዎች እንደሚያግቷቸውና ለወራት እንደሚያቆዩአቸው ገልጸዋል።

ሳውዲ አረቢያ በስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ላይ በፈንጂና በቅርብ ርቀት በመተኮስ ማጥቃትን ጨምሮ ገዳይ ኃይልን ለመጠቀም የተቀመጠ ማንኛውንም ፖሊሲ በአስቸኳይ መሻር አለበት። መንግሥት በየመን ድንበር ላይ ሕገወጥ ግድያ፣ ማቁሰል እና ሰቆቃ የሚፈፅሙትን የደህንነት አባላትን መርምሮ በተገቢው መቅጣት ወይም መክሰስ ይገባል። ጉዳዩ የሚመለከታቸው መንግሥታት ሳውዲ አረቢያ የዚህን አይነት ገዳይ ፖሊሲ እንድታቆምና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ግፊት ማድረግ አለባቸው።

ከዚህ ጋር በተገናኘ የሚመለከታቸው መንግሥታት በድንበር ላይ እየተፈጸሙ ያሉ ጥሰቶች ላይ ታማኝ በሆነ መልኩ በሳዑዲ እና የሁቲ ባለስልጣናት ላይ ማዕቀብ መጣል አለባቸው። በተባበሩት መንግሥታት የሚደገፍ ምርመራ በማቋቋም በስደተኞች ላይ የሚደርሰው በደል ግድያዎችም በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች ስለመሆናቸው መመርመር አለበት። ሃርድማን “የሳውዲ ድንበር ጠባቂዎች ባልታጠቁ ሰላማዊ ዜጎች ላይ እንደሚተኩሱ ያውቃሉ ወይም ማወቅ ነበረባቸው” ብላለች። “በኢትዮጵያውያን ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ላይ ለሚፈፀሙ ወንጀሎች ፍትህ ካልተገኘ ተጨማሪ ግድያዎችንና እንግልቶችን ያባብሳል። “ስትል ታስጠነቅቃለች።

ሻሎም ለሀገረ ኢትዮጵያ !

አሜን ።

አዲስ ዘመን ነሐሴ 21 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You