በመኸሩ ወቅት የግብርናችን ፈተናዎች

ከሰማኒያ በመቶ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ኑሮው በግብርና ላይ የተመሰረተ መሆኑ ይነገራል። አርሶ አደሩ በልቶ የመኖር ሕልውናውን ከማረጋገጥ አልፎ በከተሞች አካባቢ በንግድ፣ በወር ደመወዝተኝነትና በሌሎች ሥራዎች የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የመመገብ ኃላፊነትም ትከሻው ላይ ወድቋል። እንደዛሬው የበጋ ግብርና ከመታወቁና ከበሬ ጫንቃ ውጪ ሌላ አማራጮችን የመጠቀም እድል ከማግኘቱ በፊት እንኳን ሃምሳ እና ሰማኒያ ሚሊዮን ሕዝቦችን እየቀለበ አሻግሯል። ዛሬም ከመቶ ሚሊዮን ሕዝብ በላይ የእርሱን እጅ ይጠብቃል።

ግብርናችን ኋላቀር አሠራሮችን የሚከተል ስለነበር የምርታማነት ችግር የነበሩበት ነው። በአንዳንድ አካባቢዎች ድርቅ ሲከሰት እንኳ በሌላው አካባቢ የተመረተውን ምርት ተቋድሶ የችግሩን ወቅት ለመሻገር የሚያስችል አቅም አልነበረውም። በዚህ የተነሳ በተለያየ ጊዜ ለምግብ እጥረት የተጋለጡ ወገኖቻችንን ነፍስ ለመታደግ እጃችንን ዘርግተናል፤ ከብራችንን ዝቅ አድርገን ስንዴና መሰል እርዳታዎችን ከለጋሽ ሀገራት ተመጽውተናል። ስንዴ የሚሰፍሩልን ለጋሽ ሀገራት የሚሰጡንን ድጋፍ እንደማስያዣ ተጠቅመው ለፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎታቸው ማስፈጸሚያነት እንዲያውሉት እኛው ራሳችን እድል ሰጥተናቸዋል።

በምግብ ራስን መቻል ከጥገኝነት መላቀቅ ነው፤ ከምግብ ጥገኝነት መላቀቅ ማለት ደግሞ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሀገርን ክብርና ሉዓላዊነት አለማስደፈር ማለት ነው። ስለዚህ ከላይ በተገለጸው አውድ መሰረት ግብርናችን የጉሮሯችንን ችግር የሚፈታ ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚያችን ፣ የክብራችን እና የሉዓላዊነታችንም ዋስትና ነው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መንግሥት ለግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በአንድ በኩል የምግብ ዋስትናችንን ለማረጋገጥ፤ እልፍ ሲልም ለውጭ ገበያ የሚተርፍ ምርት በማምረት ኢኮኖሚያችንን የመደጎም አቅጣጫ ይዞ እየሠራ ይገኛል።

ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግም በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል። ከነዚህም የኩታ ገጠም እርሻን ማስፋፋት፣ ምርጥ ዘር መጠቀም፣ በመስመር መዝራት፣ የአፈር ማዳበሪያ፣ ጸረ-አረምና ጸረ-ተባይ መድኃኒቶችን መጠቀም ተጠቃሽ ናቸው። እነዚህ የግብርና ፓኬጆች ምርታማነታችን እንዲያድግ ያደረጉና ግብርናችን ከመቶ ሚሊዮን በላይ ሕዝብን እየመገበ እንዲጓዝ ያስቻሉ አዳዲስ አቅሞቻችን ናቸው።

እንደሚታወቀው አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች የግብርና ሥራዎችን የሚያከናውኑትና ከፍተኛ ምርት የሚሰበስቡት በመኸር ወቅት ነው። የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዓመት ጉርሳቸውን እና ስንቃቸውን የሚቋጥሩትም በአመዛኙ ከመኸሩ ወቅት በሚያገኙት በረከት ነው። ‹‹ እጄን በእጄ›› እንዲሉ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን የመኸሩ ግብርናችን ራሳችን በምንፈጥረው ችግር ምክንያት ፈተናዎች እየገጠሙት ይገኛል።

የመኸሩ አዝመራ ችግር ሲገጥመው በሀገር እና በሕዝብ ላይ የሚያሳድረውን ከፍተኛ ጉዳት ካለመረዳት ወይም የግብርናውን ሥራ ሆን ብለው በማስተጓጎል መንግሥት ላይ ጉዳት የሚያደርሱ እየመሰላቸው የምግብ ዋስትናችንን የምናረጋግጥበትን ወርቃማ ጊዜ የሚያውኩ አካላት ተፈጥረዋል። ባለፈው የሰሜኑ ጦርነት ሁለት የመኸር ወቅቶች ጦርነት ተደርጎባቸዋል።

ይህ በተለይም በአካባቢው አርሶ አደሮች ላይ ጥሎ ያለፈው የሞራልና የኢኮኖሚ ውድቀት ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም፤ በአካባቢው ያሉ አርሶ አደሮች ማምረት አለመቻላቸው ብቻ ሳይሆን ለስደትና ለችግር እንዲጋለጡ ሆነዋል። ለብዙዎች ይተርፉ የነበሩት የአርሶ አደሩ እጆች ምጽዋት ለመጠየቅ ተዘርግተዋል። ዛሬም ድረስ ከገቡበት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ ወጥተው የቀደመ ሕይወታቸውን ለመምራት የተቸገሩ አርሶ አደር ወገኖቻችን በርካቶች ናቸው።

በመኸሩ ወቅት አብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል ዝናብ የሚያገኝ እንደመሆኑ እንደየ መልክዓ ምድሩ ፀባይ የተለያዩ አዝርዕቶች ይመረታሉ። ገበሬው በአካባቢው ካመረተው ምርት የሚተርፈውን እየሸጠ የጎደለውን እና ሌላ አካባቢ የሚመረተውን ምርት እየተለዋወጠ ሕይወትን መግፋት የኖረበት ባህሉ ነው። የጎጃም ጤፍ ፣ የአርሲ ስንዴ፣ የባሌ ገብስ ፣ የሲዳማ በቆሎ ወዘተ በተመረቱበት ቦታ ላሉ ሰዎች ብቻ የሚያገለግሉ ሳይሆን በግብይት ሥርዓት ውስጥ እያለፉ ለመላው ሕዝብ ጥቅም የሚውሉ ናቸው። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የዚህ በረከት ተቋዳሽ መሆን የሚችለው ሰብሎቹ ወቅታቸውን ጠብቀው ሲመረቱ ነው።

ቀደም ሲል የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ ወደ ሀገር ውስጥ አለመግባቱ ሥጋት ሆኖ እንደነበር ይታወሳል። ማዳበሪያው ሀገር ውስጥ ከገባ በኋላ ደግሞ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚገኙ የሥራ ኃላፊዎች በተገቢው መንገድ ለአርሶ አደሩ ማሰራጨት ሲገባቸው በመጋዘን ውስጥ ከዝነው የግል መጠቀሚያቸው ለማድረግ ሲሞክሩ እንደነበርም ታይቷል። እንዲህ አይነቱ ብልሹ አሠራር በምርታማነታችን ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ ቀላል አይደለም። ማዳበሪያና አስፈላጊ የሚባሉ የግብርና ግብዓቶች በወቅቱ ተደራሽ ከማድረግ ጀምሮ በተገቢው መንገድ እስከማሰራጨት ድረስ ያለው ሂደት በጥብቅ ዲሲፒሊን መመራት እንደሚገባው ጠቁሞ ማለፍ ያስፈልጋል።

በአንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት የገባውን ማዳበሪያ አርሶ አደሩ ጋር ለማድረስ አስቻይ ሁኔታዎች እንዳልነበሩም ተስተውሏል። ያም ብቻ ሳይሆን እንደምንም ብለው ቦታው የደረሱና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የወጣባቸው የአፈር ማዳበሪያዎች ነፍጥ ባነገቡ ግለሰቦች ቁጥጥር ስር ገብተው ለተለያየ ዓላማ ሲውሉ እንደነበር ታይቷል።

በተለይም በአማራ ክልል በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ታጣቂዎች የማዳበሪያ መጋዘኖችን እየሰበሩ ላሻቸው ሰጥተዋል፤ ላሻቸው ነስተዋል። በየወረዳው በህጋዊ መንገድ ወረፋ ይዘው ማዳበሪያ ይጠባበቁ የነበሩ አርሶ አደሮች ዛሬም ድረስ የማዳበሪያ ጥያቄያቸው በእንጥልጥል መሐል መንገድ ላይ እንደቀረ ነው። ይህም በዘንድሮው ምርታማነት ላይ የራሱን ተፅዕኖ የሚያሳድር መሆኑን መገመት አይከብድም።

በአንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠረው የጸጥታ ችግር አርሶ አደሩ የሥራ ጊዜውን በሚገባ እንዳይጠቀም አድርጎታል። የግብርና ሥራ የዕለት ተዕለት ክትትል የሚፈልግና ከእርሻ እስከ አውድማ ሥራ ድረስ የአርሶ አደሩን የዘወትር ትጋት የሚጠይቅ ነው። በአንዳንድ አካባቢዎች የተደራጁ ቡድኖች የአርሶ አደሩን መንደሮች የጦርነት ቀጣና ስላደረጓቸው የግብርና ሥራው እየተስተጓጎለ ይገኛል።

አርሶ አደሩ እንዳያመርት ማድረጋቸው ሳያንስ ያስቀመጠውን ቀለብ ሳይቀር እያራገፉ እንዲሰጣቸው የሚያስገድዱት ነጻ አውጪ ነን ባዮች ተበራክተዋል። በተለይም የመኸሩን ወቅት እየጠበቁ የአርሶ አደሩን መንደር ማወክና የግብርና ሥራዎችን ማስተጓጎል አዲስ ፋሽን ሆኗል። ነፍጥ ያነሳሁት የሕዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ ነው የሚል እንደ ቡድን የገበሬውን የእርሻ ቦታ የጦርነት ቀጣና ባላደረገ ነበር።

ቃለአብ ዘሰማይ

 አዲስ ዘመን ነሐሴ 21 ቀን 2015 ዓ.ም  

Recommended For You