ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት ፈተና ሆነው ከሚጠቀሱ ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል ሙስና ተጠቃሽ ነው። በተለይም በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ሕዝቦች ያሉባቸውን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ተሻግረው ነገዎቻቸውን ብሩህ ለማድረግ በሚያደርጓቸው የእለት ተእለት እንቅስቃሴያቸው ውስጥ ትልቁ ተግዳሮታቸው ሙስና እንደሆነ ብዙ ጥናቶች ያመላክታሉ።
በአንድ ሀገር ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ሊከሰት የሚችለው ይህ የሙስና ችግር በቂ ትኩረት ተሰጥቶት በጥንቃቄ ሊያዝ ካልቻለ ከመልካም አስተዳደር ባለፈ መልኩ ሁለንተናዊ በሆነ መንገድ የሀገርን ህልውና ስጋት ውስጥ እስከ መክተት ሊደርስ የሚችል አቅም ሊላበስ እንደሚችል ይታመናል።
ለልማት የሚውል ከፍተኛ ሀገራዊ ሀብት እንዲባክን ከማድረግ ጀምሮ፤ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንዳይኖር በማድረግ ለሀገራዊ አለመረጋጋት እና ግጭት ምንጭ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም ሙስና አብዛኛውን የማኅበረሰብ ክፍል በማደህየት ዜጎች ስለነጋቸው ብሩህ ተስፋ እንዲያጡ በማድረግ፤ ሀገርን ጽልመት ማልበስ የሚችል ሁለንተናዊ ጥፋት ነውና።
ሙስና እንደየሀገራቱ ተጨባጭ ሁኔታ የተለያየ መልክና መገለጫ ቢኖረውም፤ ችግሩ ዓለም አቀፋዊ ገጽታ እየተላበሰ ከመጣ ውሎ አድሯል። እንደ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ፎረም መረጃ ከሆነ ደግሞ፤ በየዓመቱ በጉቦና በስርቆት ብቻ በሚፈፀም ሙስና ከ3 ነጥብ 6 ትሪሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ የዓለም ኢኮኖሚ ላይ ጉዳት ይደርሳል።
ከዚህ ውስጥ 50 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የሚሆነው ከአፍሪካ በሕገ ወጥ መንገድ የሚወጣ ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ በዚህ መልኩ በሙስና የባከነ ሀብት ለመሠረተ ልማት አውታሮች፣ ለትምህርት ቤት ግንባታ፣ ለጤና ተቋማት፣ ለንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት፣ በጥቅሉ ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ቢውል 43 በመቶ የሚሆኑ የዓለም ደሃ ሕዝቦች ህይወት ይቀየር እንደነበር ጥናቶች ያመላክታሉ።
ይህንን ሀገራዊ ብሎም ዓለም አቀፋዊ ችግር ለመከላከል የኢትዮጵያ መንግሥት የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል። በተለይም ከለውጡ ማግስት የለውጡ አመራር ወደ ስልጣን ከመጣ ጀምሮ ችግሩን ለመቅረፍ ሰፊ ጥረቶችን አድርጓል። «ሙስና የሀገር ደኅንነት ሥጋት ሆኗል» በሚል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሚመራ ሰባት አባላት ያሉት የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ አቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል።
ቀደም ባለው ጊዜ በተለያዩ የፌዴራል መንግሥት ተቋማት በሙስና የተጠረጠሩ ባለስልጣናትንና ባለሙያዎችን ለሕግ ከማቅረብ ጀምሮ፤ ለሙስና በር የሚከፍቱ አሠራሮችን በማዘመን ችግሩን ለመከላከል የተለያዩ ሥራዎች ተሠርተዋል። ከዚህም ባለፈ ለሙስና ተጋላጭነት ያላቸውን የመንግሥት ሕግጋት፣ ደንቦች፣ መመሪያዎችና አሠራሮች ለማስተካከል ረጅም ርቀት ተሂዷል።
አዲስ አበባ መስተዳድርን ጨምሮ በክልል መንግሥታት አካባቢም ችግሩን ለመከላከል በተደረጉ ጥረቶች በችግሩ እጃቸው ያለባቸውን የክልል ቢሮ አመራሮች እና ባለሙያዎች ላይ ርምጃዎች ሲወስዱ ቆይተዋል።በዚህም ችግሩ ገዝፎ የተጀመረውን ሀገራዊ የልማት እንቅስቃሴ እንዳያደበዝዘው ሰፊ ጥረት ተደርጓል።
ሰሞኑን በ2015 ዓ.ም አጠቃላይ ግምገማ ተከትሎ በሲዳማ ክልል በመልካም አስተዳደር ችግርና በሙስና የተጠረጠሩ አመራሮችን በመለየት ፣ የክልሉ መንግሥት በችግሩ ዙሪያ እጃቸው ያለበትን ከ50 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ ማከናወን ጀምሯል። ይሄም እንደ ሀገር መንግሥት ችግሩን ለመከላከል እያደረገ ያለው ጥረት አንድ አካል ነው።
በክልሉ ደረጃ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም በሕዝብና በመንግሥት ሀብት ላይ የተፈጸመ ሙስና ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ሊበረታታና ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባ ነው። ርምጃው በታችኛው የመንግሥት አስተዳደር እርከን ላይ ያሉ ተጠርጣሪዎችን ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ምዝበራ እየተፈጸመ ዝምታን የመረጡ ኃላፊዎችን ጭምር ተጠያቂ ያደረገ መሆኑ በብዙ መልኩ ለሌሎች አስተማሪ እንደሆነ ይታመናል። ይሄው ተግባር በሁሉም አከባቢዎች እንደ ልምድ ተወስዶም ሊተገበር ይገባዋል!
አዲስ ዘመን ነሐሴ 21 ቀን 2015 ዓ.ም