“ሕጉን በሕግ አምላክ!”

 የመነሻችን ትዝብት፤

ከተወሰኑ ዓመታት በፊት የሀገራችንን የፍትሕ ሥርዓት አስመልክቶ ሰፋ ያለና በርካታ ታዳሚያን የተጋበዙበት አንድ ውይይት ተደርጎ ነበር፡፡ በዕለቱም ይህ ጸሐፊ በስብሰባው ላይ ለመገኘት ዕድል አጋጥሞት ነበር፡፡ በመርሃ ግብሩ መሠረት በተጠቀሰው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ሦስት ያህል “የጥናት ወረቀቶች” ከቀረቡ በኋላ መድረኩ ለጋራ ውይይት ክፍት እንደተደረገ የሀገሪቱን የፍትሕ ሥርዓት አተገባበር በተመለከተ የዘነበውንና የፈሰሰውን የተሳታፊያን ብሶትና እሮሮ “እንዲህ ነበር” ብሎ ለመደምደም በእጅጉ ያዳግታል። የታዳሚያኑ የስሜት ማዕበልና የቁጣ ወጀብ በእውነቱ እንዴት እንደነበር በቃላት መግለጽ ስለማይቻል እንዲሁ ብቻ “ነበር” ብሎ አስታውሶ ማለፉ ሳይቀል የሚቀር አይመስለንም፡፡

በተለየ ሁኔታ ግን ከተሳታፊያኑ መካከል አንድ ግለሰብ ምፀት በተላበሰ አገላለጽና አካላዊ ገለጻ የሰጡት አስተያየት ለዚህ ጽሑፍ መንደርደሪያት በእጅጉ ሊጠቅም ስለሚችል እንደሚከተለው ሃሳባቸውን ለማስታወስ እንሞክራለን፡፡ “የሀገራችን የሕግ አውጭ አካላት ማመስገን ካለባቸውና ደመቅ ተደርጎ ሊጨበጨብላቸው ከተፈለገ ሳይሰለቹና ሳይታክቱ ቀን ከሌት እየተጉ አናት በአናቱ መሥራት ያለመሥራቱን ሳይፈትኑ ሕጎችን እያመነጩ ስለሚደራርቡልን ሊሆን ይገባል፡፡ በዚህ ትጋታቸው ከፍ ያለ ምሥጋና ቢቀርብላቸው ተገቢ ይሆናል፡፡”

“ተደራርበው የሚመነጩት ሕጎች ገና መተግበር ሳይጀምሩ በሌላ ሕግ እየተሻሩ ዋጋ ሲያጡም እንመለከታለን፡፡ አዲስ መጤው ሕግም ገና በአግባቡ ለሕዝብ ሳይተዋወቅ እየመከነ ተገልጋዩ ሕዝብ ግራ ሲጋባ መመልከት የተለመደ ሆኗል፡፡ እንኳን ተራ ዜጎች ቀርተው የሕግ አርቃቂዎቹና አመንጭ አካላቱ ራሳቸው የሚያመነጩትን ሕግ በሚገባ ስለማወቃቸው ያጠራጥራል፡፡”

“ሕግን በብዛት ማመንጨትን በተመለከተ እኛን የሚተካከል ሌላ ሀገር ስለመኖሩ እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ ስለዚህ ፍትሕ ጠፋ የማለቱን ጩኸት ለጊዜው ገታ አድርገን ‹ሕጉን ራሱን በሕግ አምላክ› በማለት ብንሞግት ሳይሻል አይቀርም፡፡” ድንቅ አስተውሎት ነው፡፡ ይህ አገላለጽ የዘመነ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን የተማሪዎች ትግልም ያስታውሳል፡፡

በወቅቱ የተፋፋመው የኮሌጅ ተማሪዎች አብዮታዊ እንቅስቃሴ ፋታ የነሳቸው የንጉሡ ባለሟሎችና ተቋማት መፍትሔ ያገኙ መስሏቸው በተከታታይ ተማሪዎቹ የሚቀጡበትን ደንብና ሕግ በመደንገግ ይተጉ ነበር። ይህንን መሰሉን መንግሥታዊ ትጋት ያስተዋሉ ነውጠኞቹ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች “አዋጁን በአዋጅ” የሚል ጽሑፍ መበተናቸውን ታሪካቸው ዘክሮታል። እኛ ያስታወስናቸው የጉባዔ ሃሳብ ሰጪም ለማሳየት የሞከሩት “አዋጅን በአዋጅ” የመሻርን ሀገራዊ ነባር ትጋት ለማስታወስ ይመስላል፡፡

“የጉድ ሀገር ገንፎ እያደር ይፋጃል”፤

“እስከ 1993 ዓ.ም ድረስ በሀገራችን የሙስና ወንጀልን ሊተረጉም የሚችል ግልጽ ድንጋጌ ባይኖርም የሙስና ወንጀል ሊባሉ የሚችሉ እንደ ጉቦና በሥልጣን አላግባብ መገልገል የመሳሰሉት በ1949 የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ውስጥ ተደንግገው ነበር፡፡ በደርግ ሥርዓተ መንግሥትም እንዲሁ (አዋጅ ቁጥር 8/67 እና 214/74) የሙስና መገለጫ የተሰኙ ጥቂት ወንጀሎች ተደንግገው ሥራ ላይ ለማዋል ተሞክሮ ነበር፡፡”

የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገራችን የተቋቋመው በ1993 ዓ.ም በአዋጅ ቁጥር 235 መሠረት ነበር፡፡ አዋጁ ገና ሥራ ላይ ውሎ በበቂ ሁኔታ ሳይፈተንና የሁለት ዓመት ዕድሜውን ሻማ ሳይለኩስ በ1997 ዓ.ም “የተሻሻለው የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን መቋቋሚያ አዋጅ በቁጥር 433 ተደንግጎ ሥራ ላይ ዋለ፡፡

የማሻሻያው ግስጋሴ ሊገታ ስላልቻለ እንደገና በአዋጅ ቁጥር 883 በ2007 ዓ.ም የማሻሻያ “ለውጥ” ተደርጎበታል ተብሎ ይፋ ተደረገ፡፡ “ያልታደልሽ እንዴት አደርሽ” እንዲል ሀገራዊ ብሂላችን፤ ተንከራታቹ አዋጅ እንደገና በቁጥር 1236 የካቲት 12 ቀን 2013 ዓ.ም “የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን በሚል ስያሜ ለሦስተኛ ጊዜ በአዲስ ስም ተሸልሞ ብቅ አለ፡፡

ለሦስት ያህል ጊዜያት ልክ እንደ ቢራቢሮ የአፈጣጠር ዑደት ዕንቁላል፣ ዕጭ፣ ፑፓ እየተባለ ወደ አቅመ ቢራቢሮ የህልውና ደረጃ ላይ እንደሚደረሰው ሁሉ የፀረ ሙስናው አዋጅም እንዲሁ በአዙሪትና በእንፉቅቅ እየዳኸ ለሦስት ያህል ጊዜያት “እንደ ተሻሻለ” ቢገለጽም “ከስም ውበቱ” በስተቀር ሙስናን ለመሰለው ሀገራዊ ክፉ ደዌያችን “መሲህ” ሆኖ “ከብሔራዊ የውርስ ኃጢያት” ነፃ ሊያወጣን አልቻለም፡፡ ለምን ቢሉ ከዕጩና ከፑፓው ውስጥ አቅሙን አፈርጥሞ መውጣት ስላልቻለ፡፡ ለዚህ ተቋም ምሬት ባንገሸገሸው ስሜት የቅጽል መታወቂያ መስጠት ካስፈለገ “ስሙ እኩል፤ ሥራው ስንኩል” ብሂልን ማስታወስ ይቻላል፡፡

ከሁለት አሠርት ዓመት በላይ ዕድሜ ላስቆጠረውና “የስም ጥብቆ” ከመቀየር ውጭ ገና በወጉ “ጉተናው ጠንቶ” ለአቅመ ወግ ላልደረሰው ለዚህ ተቋም፤ “ብሔራዊ የፀረ ሙስና ኮሚቴ” የሚባል ስመ ሞክሼ መንትያ የተፈጠረለት በኅዳር ወር 2015 ዓ.ም ነበር። ሰባት ጎምቱ የሀገሪቱ ባለሥልጣናትን ያካተተው ይህ ኮሚቴ ከተቋቋመ ገና ዓመት ስላልሞላው እንዲህ ነው ብሎ በአግባቡ ለመተቸት ስለማይቻል እስካሁን ሠራሁ ላለው ተግባር ዕውቅና ሰጥተን መጨረሻውን ማየቱ የተሻለ ይሆናል፡፡

እንዲህ ዓይነት ተቋም ባለበት ሀገር “የጉድ ሀገር ገንፎ እያደር ይፋጃል” ያሰኘን የሀገራዊ ገመናችን ሽታ ይበልጥ ያስነጠሰንና እጃችንን አፋችን ላይ ያስጫነው ዜና የተለቀቀው ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ነበር፡፡ “ሀሰተኛ የሽያጭ ደረሰኝ አዘጋጅቶ ለተለያዩ ነጋዴዎች እና ድርጅቶች ከ30 ቢሊዮን ብር በላይ በመሸጥ በከፍተኛ የማጭበርበር ወንጀል የተጠረጠረ ግለሰብ በአዲስ አበባ ከተማ በቁጥጥር ሥር ውሎ ምርመራ እየተጣራበት እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ” ይላል፡፡

ዜናውን የሰሙ ብዙ ሰዎች “ተሳስተው ሚሊዮን ማለታቸው ነው? ወይንስ እውነትም ቢሊዮን ብር ነው?” በማለት እስከ መከራከር መድረሳቸው የሰሞኑ ዐቢይ ወሬ ነበር፡፡ ይበልጥ “ጉድ! ጉድ!” ያሰኘው ደግሞ የቢሊዮን ብሩን “ቁማር” ሲዘውር የነበረው ጎረምሳ ምናልባትም ወጣት የሚባል ዕድሜ ላይ መገኘቱ ነው፡፡

ይህን መሰሉ ዘረፋ ይፋ በወጣበት ተቀራራቢ ቀን (ምናልባትም በተመሳሳይ ቀን) በዚሁ አንጋፋ ጋዜጣ ላይ የወጣው ሌላው ዜና “በኢትዮጵያ በመሠረታዊ ህክምና ከአምስት የጤና ተቋማት መካከል የተሟላ አገልግሎት የሚሰጠው አንዱ ብቻ መሆኑን የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።… መሠረታዊ ህክምና የሚባሉት የሕጻናት ህክምና፣ የቤተሰብ ምጣኔ፣ የእርግዝና ክትትል፣ ተላላፊ የሆኑ በሽታዎች ወዘተ.” መሆናቸውን ዜናው አብራርቶ ገልጾልናል፡፡ ቢሊዮን የሀገር ሀብት ሲዘረፍ ሚሊዮኖች ህክምና አጥተው ለሞት መዳረጋቸውን በዓይነ ህሊናችን ስንመረምር “የሀገራችን ዕንቆቅልሽ፤ በምን አውቅልሽ” የብረት በር ተከርችሞ እንደቆመ መረዳት አይከብድም።

መቼም አንዴ ደንዝዘን ከአቅላችን ጋር ስላልሆንን ብዙውን “የሀገር ገመና” እንዳላየን ስለምናልፍ ወይንም አይተንም “ቁብ ባለመስጠት” ተረጋግተን የምንታይ መምሰሉ የኋላ ኋላ የሚያስከትልብንን ብሔራዊ ቀውስ ስናስብ “ኢትዮጵያም እጆቿን ወደ ፀባዖት ዘርግታ ‹ኤሎሄ! ኤሎሄ!›” እያለች በመቃተት የክርስቶስን የጣር ጩኸት” መድገሟ የሚቀር አይሆንም፡፡

ከሦስት ቀናት በፊት “በሲዳማ ክልል በሙስናና በብልሹ አሠራር ላይ ተሳትፈዋል የተባሉ 25 አመራሮች በሕግ ቁጥጥር ስር ሲውሉ 10 ከፍተኛ አመራሮች ደግሞ ከኃላፊነታቸው መነሳታቸውን ክልሉ አስታውቋል” ተብሎ የተለቀቀብን ዜና “መች መጣሽ ሙሽራ፤ መች ቆረጠምሽ ሽምብራ” በማለት እንደ ባሕር ማሽላ እያረርን ልንስቅ ግድ ሆኗል፡፡

ትናንት “የክልል ማዕረግ” የተጎናጸፈውና ገና ጎጆ ወጥቶ ያልተረጋጋው የሲዳማ ክልል እንዲህ በሙስና ከተጨማለቀ ለሽበትና ለጉልምስና ወግ የበቁት አንቱ ተብዬ ክልሎች ቢፈተሹማ ስንት ጉድ ይፍረጠረጥ ይሆን? አቅም ካላቸው የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽንና የብሔራዊ የፀረ ሙስና ኮሚቴውን “አፊኔ” (እዩልን ስሙልን) በማለት በሙስና የቆሰለችውን ሀገር እንዲታደጉልን “አቤት! አቤት!” እያልን አቤቱታ ከማቅረብ እንታቀብም፡፡

እንዲህም አለ!

ከቀናት በፊት ይህ ጸሐፊ የረጅም ዘመን ወዳጁ በሆኑት በዶ/ር ቤተ መንግሥቱ ቢሮ ተገኝቶ ነበር። እኒህ አንጋፋ ምሁርና አባት ከረጅም ዓመታት የውጭ ኑሮ በኋላ የኢትዮጵያን ፈውስ ናፍቀው ወደ ሀገር የተመለሱ ቅን፣ የኢትዮጵያ ፍቅር በአጥንታቸው ውስጥ ዘልቆ የገባና ለእድገቷና ለለውጧ የሚቃትቱ የወንጌል አማኝ ቤተ እምነቶች የተሰባሰቡበት ብሔራዊ ካውንስል አንዱ መሪ ናቸው፡፡

ከቢሯቸው እንደ ገባሁ “የምትፈርመው አንድ ሰነድ አለ” በማለት የቢሮ ጠረጴዛቸውን መሳቢያ በመክፈት በአማርኛና በእንግሊዝኛ የተጻፉ ሁለት ገጽ ወረቀት ከፊቴ አቀረቡልኝ፡፡ የሰነዱ ርዕስ “የቤዛ ባለሙያዎች የሥነ-ምግባር ቻርተር” የሚል ሲሆን፤ ዓላማው የተገለጸው እንዲህ ተብሎ ነው፡፡

“ይህ ሰነድ ለቤዛ ዓለም አቀፍ ቤተ ክርስቲያን አባላት፣ በግል፣ በመንግሥት ወይንም ለትርፍ ባልተቋቋሙ ተቋማት ውስጥ ለሚሰሩ ባለሙያዎች የተዘጋጀ ነው፡፡ ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ግዴታዎች መተግበር እና በእግዚአብሔር ፊት ተጠያቂ መሆን የፈራሚው ኃላፊነት ነው፡፡” በማለት የቃል ኪዳኑ ዓላማ ከተብራራ በኋላ በማስከተልም “በሥራ ቦታዬ እና በግል ሕይወቴ እግዚአብሔርን ለማክበር ከዚህ በታች ለተዘረዘሩት የሥነ-ምግባር መለኪያዎች ራሴን አስገዛለሁ፡፡” በሚል ቃል ኪዳን ፀንቶ ዝርዝሮቹ እንዲሚከተለው ተብራርተዋል፡፡

“የንግድ ልውውጥን በእውነተኛነት ስለመተግበር- ጉቦ ላለመቀበል፣ ጉቦ ላለመስጠት፣ ለጥሩ ምርቶች ተመጣጣኝ ዋጋ ለማስከፈል ቃል እገባለሁ፡፡ በመልካም አርአያነት ስለመኖር፡- ሠራተኞችን በሙሉ ለማክበር እና ተመጣጣኝ ደመወዝ ለመክፈል፣ ክብራቸውን እንዲጠበቅ ለማድረግ፤ ለደንበኞች፣ ለአቅራቢዎች፣ ለሥራ አጋሮች እና ለሸሪኮች ያለብኝን ግዴታ ሁሉ በታማኝነት ለመወጣት፣ የድርጅቴን ወይንም የኩባንያዬን ገንዘብ በእውነተኛነት ለማስተዳደር እና በሕግ የሚጠበቅብኝን ግብር ለመክፈል ቃል እገባለሁ።”

“ፈጣሪን በሥራ ፍሬ ስለማክበር፡- ንግዴን ወይንም ሥራዬን በጥንቃቄ ለማስተዳደር፣ በአምልኮ አጥቢያዬ በታማኝነት ለማገልገል እና ለታመሙና ለተቸገሩ ደግ እና ርሁሩህ ለመሆን ቃል እገባለሁ። የመንግሥት ሥራዬን በተመለከተ፡- ሀገሬንና ሕዝቧን ለማገልገል የተሰጠኝን ኃላፊነት በትጋትና በእውነተኛነት ለመወጣት፣ የተሰጠኝን መንግሥታዊ ሥልጣን ሕዝብን ለማገልገል እና ፈጣሪ አምላክን በትጋትና በታማኝነት ለማክበርና ለማስቀደም እንጂ ለራሴ ጥቅም ብቻ ላለማዋል ቃል እገባለሁ፡፡”

“ጽድቅ ሕዝብን ከፍ ታደርጋለች ኃጢአት ግን ሕዝብን ታስነውራለች” በሚል ቅዱስ ቃል የተደመደመው ከፍ ያለ ዋጋ ያለው ይህ የሥነ ምግባር መመሪያ ለብዙ ተቋማት በአርአያነት ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡ እጅግ የሚያስመሰግነው ተከታዩ ተግባር ደግሞ በመቶዎች የሚቆጠሩ የቃል ኪዳኑ ሰነድ ፈራሚዎች ፊርማቸውን ማኖር ብቻ ሳይሆን ቃል ኪዳናቸውን በተግባር ስለመተርጎማቸው በየሥራ ቦታቸው እየተገኙ ክትትል ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ይበልጥ የሚያበረታታ ነው፡፡

ከኢትዮጵያ ወቅታዊ ጽኑ ሕመሞች መካከል አንዱ ሕዝብ እያስለቀሰ ያለው ሙስና በተቀዳሚ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ በየትኞቹም የመንግሥት ተቋማት ውስጥ ጉዳይ ለማስፈጸም ያለ እጅ መንሻ እንደማይሞከር ከኡኡታ ባልተናነሰ ቋንቋ ደጋግመን “አቤት” ማለታችን አይዘነጋም፡፡ እጅ እጅ የሚያዩትን ሠራተኞችና ኃላፊዎች አልፎ ጉዳይ ለማስፈጸም ያለውን ትልቅ መሰናክልም ደጋግመን በማስረጃ ጭምር ለማሳየት መሞከራችን አልቀረም፡፡ እጅግ የሚደንቀውና ለሰሚውም ግራ የሚሆነው የብሔራዊ ፈተናችን ክብደት ሙስና እየተፈጸመ ያለው በድብቅና በአዩኝ አላዩኝ መገላመጥ ሳይሆን በግልጽ ድርድርና ክርክር መሆኑ ነው፡፡

የተለያዩ ሀገር በቀልና ዓለም አቀፍ ተቋማት በየጊዜው የሚያወጡትን ሪፖርት በመጥቀስ የሙስና ደዌ ምን ያህል ሀገራችንን እንዳሽመደመደ በማስረጃነት ማቅረብ አይገድም፡፡ ግን እስከ መቼ? የአዲስ አበባ ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች የሙስና ቫይረስ ተጠቂዎች ብቻ ሳይሆኑ የሥርጭት ማዕከላት ደረጃ ላይ ደርሰዋል መባሉን የሚክድ ያለ አይመስለንም፡፡ አንድ አነስተኛ ጉዳይ እንኳን ለማስፈጸም የግድ በድርድር እጅ መንሳትን ግድ ይላል፡፡

በቅርቡ በምኖርበት የወረዳ ቢሮ ደጃፍ ገና ከመድረሴ “ጋሼ የትኛውን ኃላፊ ለማናገር ይፈልጋሉ? እኛ ልናገናኝዎት እንችላለን፡፡ ጉዳይዎንም እኛ እናስፈጽምልዎታለን ” የሚሉ ወራሪዎች ግራ እስከ ማጋባት አድርሰውኝ ነበር፡፡ ጉዳዬን እንድትፈጽምልኝ የተመደበችው አንዲት ወጣት ሴት እጅ እጄን ብታይ ምንም ምላሽ ልሰጣት ስላልቻልኩ አገልግሎት የጠየቅሁበትን ዶኪዩመንት እንዴት እንዳበላሸች ይመለከተኛል የሚል አካል ካለ ከነማስረጃው ለማቅረብ ዝግጁ ነኝ፡፡

ነገሩ እንዲህ እየከፋ የሚሄድ ከሆነ የሚሞገተው ማነው? ሙሰኞቹ ግለሰቦች ወይንስ ተቋማቱ? “ሕጉን ራሱ በሕግ አምላክ!” በማለት በፍትሕ ፊት ማቆም ይቻል ከሆነም “እምባችን ፈሶ ሳያልቅ” ምላሽ የሚሰጠን መንግሥታዊ ተቋም “አለሁ!” ቢለን የጽድቅ ያህል ቆጥረን ለፈጣሪ ምስጋና ለአገልጋይ ተቋማቱም ክብር እንሰጣለን፡፡ አለበለዚያ ግን የሚንዠቀዠቀው የመከረኛው ሕዝብ እምባ ካልተገደበ በስተቀር ሀገርን የሚመራው የፖለቲካ ድርጅትም ቢሆን ከጦሱ መትረፉን እንጠራጠራለን፡፡ “ልብ ያለው ልብ ያድርግ!” ይላል ሆድ የባሰው ባለሀገር፡፡

 (በጌታቸው በለጠ/ዳግላስ ጴጥሮስ)

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 20/2015

Recommended For You