ራሳችንን ከፅንፈኛ መገናኛ ብዙኃን እንጠበቅ!

 መገናኛ ብዙኃን በዋነኝነት አመሠራረታቸው ለህብረተሰቡ መረጃ ከማድረስ ባሻገር ለማስተማርና በአንድ ሀገር ውስጥ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር የበኩላቸውን ለመወጣት ጭምር ነው፡፡ ይህንንም ማድረግ የሚያስችል ኤዲቶሪያል ፖሊሲ አላቸው፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ መገናኛ ብዙኃን የሀገሮቻቸውን የውጪ ፖሊሲ መሠረት አድርገው ሥራዎችን ያከናውናሉ፡፡ ለአብነት መቀመጫቸውን አሜሪካ ያደረጉ መገናና ብዙኃን ትኩረታቸውን አድርገው የሚንቀሳቀሱት አሜሪካ የምትከተለው የውጪ ፖሊሲ ላይ ነው፡፡

ለምሳሌ አሜሪካ በጠላትነት የፈረጀቻቸውን ሀገራት በተመለከተ ብዙ ጊዜ የሚዘግቡት በተሳሳተ መንገድ መሆኑን መታዘብ ይቻላል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ መገናኛ ብዙኃን መሠረት የሚደርጉት የሀገሪቱን ሕግና የዲፕሎማሲ አቅጣጫ ሲሆን የአዘጋገብና ኢዲቶሪያላቸው በተመሳሳይ በአንድ አቅጣጫ ላይ ያተኩራል፡፡

በኢትዮጵያም የኤሌክትሮኒክስና የህትመት መገናኛ ብዙኃን ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ለህብረተሰቡ አስፈላጊ ናቸው የሚሏቸውን መረጃዎች ሲያደርሱ ቆይተዋል፡፤ እያደረሱም ናቸው፡፡ ከንጉሡ ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ መገናኛ ብዙኃን የሀገሪቱን የዲፕሎማሲ አቅጣጫና ሕግ ተከትለው እየዘገቡ ነው፡፡

በተለይ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን እና የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ታሪክ ሰንዶ ከማስቀመጥ አንፃር ራሳቸውን በመቃኘት ሥራቸውን ሲያከናውኑ ቆይተዋል፡፡ በእነዚህ መገናኛ ብዙኃን በኩል ሲተላለፉ የነበሩ ዘገባዎችን ብንመለከት በወቅቱ የነበረውን የመንግሥት አቋምና የአገዛዝ ሁኔታ ቁልጭ አድርጎ ማሳየት የሚችሉ ናቸው፡፡

ከኢህአዴግ የሥልጣን ዘመን ጀምሮ የግል መገናኛ ብዙኃን በተወሰነ መልኩ ወደ ሥራ የገቡ ሲሆን መንግሥትን በመንቀፍና አዳዲስ መረጃዎችን ለህብረተሰቡ በማድረስ ተቀባይነታቸውን አሳድገዋል፡፡

በተለይ ደግሞ በምርጫ ወቅቶች ላይ አስፈላጊ የሚሏቸው መረጃዎችን ማድረስ ቢጀምሩም በመንግሥት ምርጫው ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራሉ በብዙ ተግዳሮቶች ውስጥ ማለፋቸው ይታወሳል፡፡ ይህ ሁኔታ በሀገሪቱ የፕሬስ ነፃነት የሚል አሉታዊ እንድም ታ ፈጥሮም ነበር፡፡

ይህንንም ተከትሎ መቀመጫቸውን የተለያዩ የውጭ ሀገራት አድርገው በኢትዮጵያ ውስጥ ስለሚከናወኑ ሁነቶች የራሳቸውን ምልከታ በማስቀመጥ መረጃ የሚሰጡ የድረገፅ መገናኛ ብዙኃን እንዲፈጠሩ አድርጓል። ከተወሰኑት ውጪ አብዛኛዎቹ ወደ አንድ ቡድን ያደላ መረጃ በመስጠትና ህብረተሰቡን በማደናገር ሥራ ላይ ተጠምደው ይታያሉ፡፡

የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚው ሕዝብ መበራከት ለሀሰተኛና ፅንፈኛ መገናኛ ብዙኃን መፈጠር የራሱን አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ ፅንፈኛ መገናኛ ብዙኃን ትኩረታቸውን የሚያደርጉት በአብዛኛው መንግሥትን መቃወም፣ የብሄር ግጭትና ሌሎች የርስበርስ ግጭት ሊፈጥሩ የሚችሉ ጉዳዮች ላይ ነው፡፡

ለአብነት በ2007 ዓ.ም ከተካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ ጋር ተያይዞ በሁሉም ሀገሪቱ ክፍሎች ሕዝባዊ የሚመስሉ ተቃውሞዎች መነሳታቸው ይታወሳል፡፡ በዚህ ወቅት ጉዳዩ እንዲጋጋልና ከፍተኛ ወደ ሆነ ቀውስና የመንግሥት ለውጥ እንዲሻገር በውጭ የሚገኙ መገናኛ ብዙኃን የራሳቸውን ሚና ተጫውተዋል፡፡ ከለውጡ በኋላ እንደ አርበኛ የተሸለሙበት ሁኔታም እንደነበር ይታወሳል፡፡

እነዚህ መገናኛ ብዙኃን ለውጡ ቀናት እያስቆጠረ በሄደ ቁጥር ተመልሰው ወደ ጽንፈኛ መንገዳቸው በመመለስ ሕዝብን በሕዝብ ላይ፤ ሕዝብን በመንግሥት ላይ በማነሳሳት ላይ ያተኮሩ ዘገባዎችንና ጽንፈኛ ትርክቶችን በማቅረብ ሀገርና ሕዝብን ብዙ ዋጋ አስከፍለዋል አሁንም እያስከፈሉ ነው።

በ2013 ዓ.ም በሰሜኑ የሀገሪቷ ክፍል ተቀስቅሶ በነበረው ጦርነት በውጭ የሚገኙ ፅንፈኛ መገናኛ ብዙኃን በሚያገኙት ርዳታ በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ እልቂት እንዲኖር ጥረት አድርገዋል የሀገርን ህልውና ስጋት ውስጥ በሚከት ደረጃ ተንቀሳቅሰዋል፡፡ በሀሰተኛ ዘገባቸውና ጽንፈኛ ትርክታቸው የዓለምን ትኩረት ለመሳብ ጥረት አድርገዋል፡፡ ይህ ሁኔታ በወቅቱ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ተደጋጋሚ ስብሰባ መታዘብ ይቻላል፡፡

በጦርነቱ ወቅት በሀገር ውስጥ የነበሩ ፤በተለይ በዩቲዩብ ሲሰራጩ የነበሩና የርስበርስ ግጭትን የሚያስፋፉ መረጃዎች ምን ድረስ ተፅዕኖ ሲፈጥሩ እንደነበር ይታወሳል፡፡ አሁንም በተመሳሳይ በአማራ ክልል እየተካሄደ ባለው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ፅንፈኛ መገናኛ ብዙኃን ጉዳዩን ወደ ከፍተኛ ግጭት ለማድረስ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

መንግሥት እየወሰደ ያለውን ሰላምና መረጋጋት የመፍጠር ርምጃ ወደ ጎን በመተው መንግሥት ክልሉን ለማጥፋት ጦር እንዳዘመተና ሰው እየገደለ መሆኑን በማጉላት ህብረተሰቡን እያደናገሩ ነው፡፡ በዚህም ራሳቸውን ስኬታማ አድርገው እስከ መቁጠር የደረሰ ጀብደኝነት ውስጥ ስለመክተታቸውም እለት ተእለት የምናየውና የምንሰማው እውነታ ነው ።

አብዛኛው ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ለማህበራዊ ሚዲያ ቅርብ ከመሆኑ አንጻር ፤ በነዚህ ሀሰተኛ መረጃዎችና ጽንፈኛ ትርክቶች ሰለባ የመሆኑ እውነታ ላላስፈላጊ መስዋዕትነት እየተዳረገ ይገኛል፡፡ ለዚህ ደግሞ በትግራይ ክልል በነበረው ጦርነት በተሳሳተ መንገድ ተመርተው የአካል ጉዳት የደረሰባቸውን ወጣቶች መመልከቱ በቂ ነው፡፡ አሁን ላይ በተመሳሳይ መልኩ በአማራ ክልል ያለውም ከትናንት መማር ያለመቻላችን ማሳያ ሊሆን የሚችል ነው፡፡

መቀመጫቸውን ውጪ ያደረጉ እነዚህ ፅንፈኛ መገናኛ ብዙኃን የጥይት ድምጽ በማይሰማባቸው የአውሮፓና የአሜሪካ ከተሞች ወጣቱን በውሸት መረጃ እንዲሞት ከማድረግ ውጪ እነሱ ላይ የሚደርስ ምንም ጉዳት የለም፡፡ እነዚህ ሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳ የሚያሰራጩ ግለሰቦች በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ሲመጣ እንደ አስታራቂና ሕዝቡን እንወክላለን የሚል ታፔላ ለጥፈው ብቅ ማለታቸው ደግሞ የማይቀር ጉዳይ ነው፡፡

እዚህ ላይ የመንግሥትና የግል የኤሌክትሮኒክስም ሆነ የህትመት መገናኛ ብዙኃን ለህብረተሰቡ ትክክለኛ መረጃዎችን በማድረስና የፅንፈኛ መገናኛ ብዙኃንን ሀሰተኛ መረጃዎችን በማጋለጥ ረገድ ሚናቸውን ሊወጡም ይገባል፡፡ በሚሰሯቸው ፕሮግራሞችም ወጣቱን ሊያስተምሩና ስለ ሀገሩ ትክክለኛ እውቀት እንዲኖረው ማስቻል ይጠበቅባቸዋል፡፡

መንግሥትም በየወቅቱ ሀገሪቱ የምትገኝበትን ነባራዊ ሁኔታ ለህብረተሰቡ በበቂ ሁኔታ ማስረዳት ፤ በሀገሪቱ የሚገኙት መገናኛ ብዙኃን/የሕዝብ/ ትክክለኛ መረጃ ለሕዝቡ በወቅቱ እያደረሱ ስመሆናቸውም መከታተል ይኖርበታል፡፡ ከፅንፈኛ መገናኛ ብዙኃን በኩል የሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎችን ለማምከን የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ቡድኖችን ማቋቋም ይጠበቅበታል፡፡

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 20/2015

Recommended For You