ኢትዮጵያ የነጻነትና አልደፈር ባይነት ሰገነት ናት፤ ኢትዮጵያ የተገፉና ፍትሕ የተነፈጉ የዓለም ሕዝቦች ፍትሕን እንዲፈልጉ፣ ጭቆናን በቃኝ እንዲሉ መንገድ ያሳየች፤ የአሸናፊነትን ድል ብስራት ችቦ ለኩሳ ያቀበለች ታላቅም፣ ባለታሪክም ሀገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ የባህል እና የጥበብ ብቻ ሳይሆ ን፤ የሰው ልጆች ጥንተ መሠ ረት መገኛ ምድር ናት፡፡
እነዚህ ለኢትዮጵያ የተሰጡ ከፍ ያሉ ማንነቶችና መገለጫዎች ደግሞ እንዲሁ ከሌላ አካል የተቸሯት አይደሉም፡፡ ይልቁንም ኢትዮጵያ በምትባል ምድርና ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የሚል የወል መጠሪያ ያላቸው ሕዝቦች የጋራ የሥራ ውጤቶችና የምግባር መገለጫዎች እንጂ፡፡
እናም ስለ ኢትዮጵያ ነጻነት፣ ስለ ኢትዮጵያ አይደፈሬነት፣ ስለ ኢትዮጵያ የባህልና የጥበብ ማዕከልነት ሲወሳና ሲነገር፤ የእነዚህን የኢትዮጵያውያንን የወል ጀግንነት፣ የወል አልደፈር ባይነት፤ የወል የባህልና የጥበብ ባለቤትነት መግለጥ መሆኑ ለሁሉም ግልጽ ሊሆን ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም የሀገር መልኳ፤ የሀገር ልኳ በዜጎቿ አቅምና ምግባር ልክ የሚሰፋ ነው፡፡
በዚህ ረገድ የጥንቶቹ ለቅርቦቹ፤ የቅርቦቹም ለአሁኖቹ፤ የአሁኖቹ ደግሞ ለቀጣዮቹ የምትሆን ኢትዮጵያን በእሳቤና ተግባራቸው ልክ እየሠሩ አሸጋግረዋል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ ስሟም ግብሯም ሳይደበዝዝ በትውልዶች ቅብብሎሽ እዚህ ደርሳለች፡፡ በልጆቿ ሥራ ልክ ሀገራዊ ከፍታዋን፤ አሕጉራዊ መቀመጫነቷን፤ ዓለምአቀፋዊ የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን ተጎናጽፋለች፡፡
ቀደምቶቿ በዓለም መድረክ ያላትን ከፍታ ለመግለጥ የሊግ ኦፍ ኔሽን መስራች ሀገር አደረጓት፤ በኋላም አፍሪካ የተጣባትን የቅኝ ግዛት በሽታ ለማከም የሚያስችል አንድነት እንዲኖራት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እውን እንዲሆን የአንበሳውን ድርሻ ወስዳ በመሥራቷ የታሰበው ኅብረት ተመሠረተ፤ መቀመጫውንም አዲስ አበባ ሆነ፡፡
ከዚህ በተጓዳኝ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መቀመጫውን አዲስ አበባ እንዲያደርግ ከፍ ያለ የዲፕሎማሲ ሥራ ተሠርቶ ይሄም እውን ሆነ፡፡ በኋላም በተለያዩ ዓለምአቀፍና አሕጉራዊ ጉዳዮች ላይ ከፍ ያለ ሚና መጫወት ጀመረች። ዓለምአቀፍ ስምምነቶችን (ከሕግም ከዲፕሎማሲና ፖለቲካም ጋር የሚጎዳኙ) በመፈረም የሕገ መንግሥቷ አካል በማድረግ ከፍታዋን ጨመረች፡፡
ይሄ ከፍታዋ ደግሞ ዛሬም ሳይደበዝዝ ቀጥሏል፡፡ በተለይ ከ2010ሩ ሀገራዊ ለውጥ ማግስት በኅብር የደመቀ ኢትዮጵያዊነትን እውን በማድረግ በትርክት የታገዘው መንገዷ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ነገር ግን በደማማቅ ስኬቶች ታጅቦ ቀጥሏል፡፡ የኢትዮጵያ መላቅ የሚያምማቸው፣ ክፋት እየደገሱ ሲፈትኗት፤ የኢትዮጵያ መላቅ የሚያስደስታቸው ለከፍታዋ ዋጋ እየከፈሉላት ከፍ አድርገው ሲያስጉዟት ታይተዋል፡፡
ሆኖም የክፋት ጠማቂዎቿ እየደከሙ፤ የከፍታዋ ታጋዮች እያየሉ ኢትዮጵያ ዛሬም በከፍታዋ ላይ ተገልጣለች፡፡ በምግብ ራሷን የመቻል ግስጋሴዋ በማይቀለበስበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ የኢኮኖሚ እድገቷም በማንኛውም ፈታኝ ሁኔታ እንደማይደነቃቀፍ ታይቷል። የዐረንጓዴ ዐሻራ ሥራዋም በመሪዎቿም በሕዝቦቿም የተባበረና የተናበበ ሥራ ዓለምአቀፍ እውቅናንና ትሩፋትን እንዲሁም አሕጉራዊ ውክልናን አስገኝቷል፡፡
የዲፕሎማሲ መንገዷም ጠላትን እየቀነሱ ወዳጅን በማብዛት ቅኝት ውስጥ፣ በትብብርና ፉክክር መርህ ታጅቦ፤ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ በተመሠረተ የባለ ብዙና የሁለትዮሽ ትብብር ታግዞ ዛሬም ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ አሸናፊ ማድረግ መገለጫው ሆኗል፡፡
ኢትዮጵያ ዛሬ በሁሉም ቦታ ተፈላጊ መሆኗ፤ ተጽዕኖዋም እየጎላ መምጣቱ፤ የመልማት አቅም እንዳላት፤ ሕዝቦቿም የልማት አቅም ብቻ ሳይሆኑ የገበያ መዳረሻ ዕድል መሆናቸው፤ በብዙ መልኩ መልማት የሚያስችል እምቅ ሀብት እንዳላት፤ በጥቅሉ ከፍ ያለ ሁለንተናዊ ብልጽግናዋ እውን መሆኑ አይቀሬነት በእጅጉ እየተገለጠ መጥቷል፡፡
ይሄንን የተገነዘቡ ሀገራት ወዳጅነታቸውን እያሳዩ፤ አጋርነታቸውን እየገለጹ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያን ከመግፋት ይልቅ ማቀፍ፤ ከመጫን ይልቅ ማገዝ፤ ከመክሰስ ይልቅ ቀርቦ መነጋገርን ምርጫቸው እያደረጉ ይገኛል፡፡ ሀገራችንም ይሄንኑ አጋጣሚ በአግባቡ እየተጠቀመች ትገኛለች፡፡
ከሰሞኑም የዓለምን ትኩረት ይዞ የነበረው የብሪክስ ሀገራት ስብሰባ ውሳኔም የዚሁ አንድ ማሳያ ነው። ይሄ ኅብረት የዓለምን ሚዛን የማስጠበቅን ዓላማ ሰንቆ የተነሳ ይሁን እንጂ፤ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ከፍ ያለ ተስፋ ያላቸው ሀገራት በዚህ ኅብረት መታቀፍ ፋይዳው ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ ኢትዮጵያም የዚህ ኅብረት አባል ሆና ከብዙዎች መካከል መመረጧ ይሄንኑ ተጠቃሚነቷን የሚያረጋግጥ፤ የዲፕሎማሲ ከፍታዋንም የሚመሰክር ነው።
ይሄ የዲፕሎማሲ ከፍታም ሆነ በዚህ መልኩ ጥቅሟን የማስጠበቅ ግስጋሴዋ ቅቡልነት ታዲያ እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬም ኢትዮጵያውያን ምን እየሰሩ ነው የሚለውን ሃቅ የሚያሳይ ነው፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያውያን በአንድ ሆነው ሲተባበሩና በጋራ ሲሰሩ ተጽዕኗቸው ለሀገራቸው ከፍታ አቅም ይ ጨምራል፡፡
ይሄ ስኬት ግን ችግር አልባ ጉዞ ነው ማለት አይደለም፡፡ ሀገርን የሚፈትኑ፣ ሕዝቦችን ከአብሮነት መንገድ የሚያስተጓጉሉ እሳቤዎችና ተግባራት እዚህም እዚያም፣ በውስጥም በውጪም አሉ፡፡ ይሁንና እነዚህ ተግዳሮቶች ከኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት በላይ አይደሉም፡፡
ኢትዮጵያን ከከፍታዋ የማውረድ አቅም ያላቸውም አይደሉም፡፡ ከከፍታ ይልቅ ወደ ቁልቁል የሚወስዱ መንገዶችና እሳቤዎች እንደመሆናቸውም ኢትዮጵያንም፤ ኢትዮጵያዊነትንም አይመጥኑም፡፡
ስለዚህ ስለኢትዮጵያ መሰባሰብ፤ ስለኢትዮጵያ መነጋገርና መወያየት፣ ስለኢትዮጵያ ይቅር መባባልና በፍቅር መተቃቀፍ፣ ስለኢትዮጵያ በኅብር አንድ ላይ ቆሞ ለከፍታዋ የሚመጥን ተግባርን መፈጽም ይገባናል፡፡
ይሄ የቀደምቶቻችን ተግባር፤ የቅርቦቹም መገለጫ እንደነበረ እንገንዘብ፡፡ ከትናንቶቹም ላለመውረድ እንትጋ፡፡ ከፍ ያለችዋን ኢትዮጵያን በከፍታዋ ላይ ከፍታ ጨምረን እናልቃት፡፡ ሁለንተናዊ ብልጽግናዋ እውን የመሆኑን አይቀሬነት አብስረንም ለነገዎቹ እናስረክብ፡፡
አዲስ ዘመን ነሐሴ 20/2015