የተለየ አማራጭ የሆነ የዓለም የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ኅብረት ለመፍጠር እኤአ በ2009 የተቋቋመው (ብሪክስ) የብራዚል፣ የሩሲያ፣ የሕንድ፣ የቻይና እና የደቡብ አፍሪካ አዲስ የታዳጊ ሀገራት ስብስብ ፤ አሁን ላይ በርግጥም የተለየ አማራጭ የመሆኑ እውነታ ተጨባጭ እየሆነ በመምጣት ላይ ነው።
የቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃትን ተከትሎ አዲስ የኃይል አሰላለፍ በዓለም ላይ መታየቱ፤ በተለይ ቻይና እና ህንድ በጣም እያደጉ የመምጣታቸው እውነታ ፤ ይህንን አዲስ ዓለምአቀፋዊ ክስተት መሸከም የሚያስችል የኃይል አሰላለፍን መፍጠርን ጠይቋል።
ለዚህ ወቅታዊ ዓለም አቀፍ እውነታ ምላሽ ለመስጠት የተቋቋመው ብሪክስ ሦስት ዋና ዋና የሚባሉ ዓላማዎች ያሉት ሲሆን ፤ የመጀመሪያ የኢኮኖሚ ትብብርን መፍጠር ነው ። ይህም በአባል ሀገራት መካከል ሊኖር የሚችለውን ንግድ እና የንግድ ልውውጦችን የሚመለከት ነው።
ሌላው በአባል ሀገራት መካከል ተከታታይነት እና ቀጣይነት ያለውን ዕድገት ማበረታታትን ታሳቢ ያደረገው ዓላማ ነው። ይህ በአባል ሀገራት መካከል የተመጣጠነ እና የሚያዛልቅ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማምጣት ያለመ ነው።
አካታች ዕድገትን ታሳቢ ያደረገው ይህ ዓላማ ፤ እጅ ለእጅ ተያይዞ ማደግን የሚያበረታታ ነው። በሀገራት መካከል ሊኖር የሚገባው የማኅበራዊ-ኢኮኖሚ ልማት ዕድገት አግላይ ሳይሆን አካታች መሆን አለበት የሚል ጽኑ ዓላማን ያካተተም ነው።
ሦስተኛው እና ትልቁ ዓላማ ፖለቲካዊ ትብብርን ማጠናከር የሚያስችል ነው። ትኩረት የሚደርገው በዓለምአቀፍ መድረኮች ላይ ሊኖር በሚችለው ትብብር ላይ ነው ። ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ የሦስተኛው ዓለም አዳጊ ሀገራትን በሚመለከት የተቀነባበረ ፖለቲካዊ አካሄድ እና ስልትን መከተል የሚያስችል ነው።
ግልጽ የሆነውን የኅብረቱን ዓላማዎች ተከትሎ በርካታ ሀገራት የቡድኑ አባል የመሆን ፍላጎት እየጨመረ መጥቷል። ፍላጎት ማሳየት ብቻ ሳይሆን ብዙዎቹም ቡድኑን ለመቀላቀል ጥያቄ አቅርበዋል። ጥያቄ ካቀረቡት በርካታ ሀገራት መካከል አንዷ ሀገራችን ኢትዮጵያ ነበረች ።
ኅብረቱ ትናንት በደቡብ አፍሪካ ጆሀንስበርግ እያካሄደ ባለው ስብሰባ ፤ ሀገራችን ለተቋሙ አባል ለመሆን ያቀረበችውን ጥያቄ ተቀብሏል። በዚህም እንደሀገር ታላቅ የዲፕሎማሲ ስኬት ተመዝግቧል።
ሀገራችን የብሪክስ አባል የመሆኗ እውነታ ፤ ከአፍሪካ ሀገራት መካከል የትልቅ ኢኮኖሚ ፣ የትልቅ ሕዝብ እና ጠንካራ ወታደራዊ ኃይል ባለቤት ከመሆኗ አንጻር በቀጣይ በአዲሱ ዓለም ኃይል አሰላለፍ ውስጥ የራሷን ጥቅም እንድታስጠብቅ መልካም አጋጣሚ ሊፈጥር የሚችል ነው።
ከዚህም በላይ እንደ ሀገር ለጀመረችው ድህነትን ታሪክ የማድረግ አዲስ የታሪክ ጉዞ ትልቅ አቅም ሊሆናት እንደሚችል ይታመናል። በተለይም ከኅብረቱ የፋይናንስ ተቋም ኒው ዲቨሎፕመንት ያለ ብዙ አሳሪ እና አስገዳጅ ሁኔታዎች የአጭር እና ረጅም ጊዜ ብድሮች ያለወለድ ሆነ በርዳታ መልክ ለማግኘት የሚያስችል የተሻለ ዕድል የሚፈጥርላት ይሆናል።
ሀገራችን ከብሪክስ አባል ሀገራት ፣ በተለይም ከቻይና እና ከህንድ ጋር ቀደም ባለው ጊዜ ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ግንኙነት ያላት መሆኑ ፤ የኅብረቱ አባል መሆኗ የእነዚህ ሀገራት ባለሀብቶች በስፋት ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ በማድረግ በኩል ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሚሆን ይታመናል።
በቀጣይም አካታች ዕድገትን ታሳቢ ካደረገው የህብረቱ ዓላማ አንጻር ፤ ቀደም ሲል ከነበሩት ሆነ አሁን የህብረቱ አባል ከሆኑ ሀገራት ጋር ተቀራርቦ በመሥራት እንደ ሀገር የጀመርነውን የልማት ጉዞ ስኬታማ በማድረግ ሕዝባችንን ሁለንተናዊ ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል የተሻለ ዕድል ያዞ የመጣ ነው።
መንግሥት ኅብረቱ አባል መሆን ያለውን ስትራቴጂክ ተጠቃሚነት ቀድሞ በመገንዘብ፣ የአባልነት ጥያቄ ከማቅረብ ጀምሮ ጥያቄው ተቀባይነት እንዲያገኝ የሄደበት በሳል ፤ የተጠና የዲፕሎማሲ መንገድ ከፍ ያለ ዕውቅና ሊሰጠው የሚገባ ነው፤ እንደ ሀገርም ታላቅ ዲፕሎማሲያዊ ድል ነው!
አዲስ ዘመን ነሃሴ 19 / 2015