ሥልጣኔ ራስን መተው፣ ራስን መርሳት… ማንነትን መቀየር አይደለም !

ወርሀ ነሀሴ የመስከረም መባቻ..የአዲስ ዓመት መዳረሻ ከመሆኑም በተጨማሪ በኢትዮጵያ አሁናዊና ትናንታዊ ታሪክ ውስጥ የራሱ የሆነ ሰፊ የታሪክ ዐሻራ ያለው ወር ነው።ዳግማዊ አጼ ምኒልክን ጨምሮ ባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱም ወደዚች ዓለም የመጡት በዚህ ወር ነው። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር ዐቢይ አሕመድም በዚህ ወር ልደታቸውን ከሚያከብሩ የኢትዮጵያ መሪዎች ውስጥ አንዱ ናቸው፡፡

ፈረንጆች አሁን ያለንበትን 21ኛውን ክፍለ ዘመን የሥልጣኔ ጥግ ይሉታል። አንዳንዶች ደግሞ የዓለም ፍጻሜ ዋዜማ ያደርጉታል። ሁለቱም እሳቤ አሁን ያለችውን ዥንጉርጉር ዓለም ይገልጻታል ብዬ አስባለሁ። የእኔና የእናተ አሁናዊ መልክ እንኳን ከዚህ የዘመን እድፍ ጋር የተለወሰ ነው። ዘመን የበረከቱን ያክል የሚነጥቀን ብዙ ነገር አለው። ጊዜ የእድሉን ያክል የሚቀማን፣ የሚወስድብን ብዙ ማንነት አለው፡፡

ሥልጣኔ ጌጥ ብቻ አይደለም ነውርም ነው.. ኩነኔም ነው።አረማመድ ካላወቅን፣ አያያዝ ካላወቅን ራሳችንን፣ ታሪካችንን ሊበርዝ የሚችል በርካታ ስውር ገጽ አለው። የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን እሳቤ በፈጠረውና ግሎባላይዜሽን በሚል ምንድርና የተፈበረከው ዓለምን ወደ አንድ መንደር የማምጣት እሳቤ በረከቱ እንዳለ ሆኖ እኛን ከራሳችንና ሌላውንም ከራሱ ነጥቆታል ብዬ አስባለሁ። ዓለምን አንድ ቦታ ላይ የማየት አባዜ በፈጠረው የሥልጣኔ ልክፍት ተያይዞ በመጣው የዘመን አብዮት ተጽዕኖ ስር የወደቀ በርካታ ማንነት አለ፡፡

ቴክኖሎጂና ወጣቱ በደንብ መተዋወቅ አለባቸው። ሰው ከዘመን ሲልቅ እንጂ ዘመን ከሰውነት ሲልቅ ውበት የለውም። ዘመን ከሰውነት ሲልቅ የሚነጥቀን ብዙ ነገር አለው። ዛሬ ላይ በሥልጣኔ ስም ያጣናቸውና እያጣናቸው ያሉ ታሪክና ማንነቶቻችን በዘመን መበለጣችን የፈጠረው ጣጣ ነው። አንዳንዶች ዘመንን በልጠው፣ ከጊዜ ቀድመው ራሳቸውን ሳያስነኩ፣ ታሪካቸውን ሳያጎድሉ በኩራት ይኖራሉ። ሰው በዘመን ሲበለጥና ዘመንን ሲበልጥ አንድ አይነት አይደለን፡፡

የጠፉ ማንነቶች፣ የተበረዙ ታሪኮች በዘመን የመበለጣችን ምልክቶች ናቸው። ሰው በጊዜ ሲበለጥ ምንም ነው.. የዘመን ባሪያ የጊዜ ሎሌ ከመሆን ባለፈ ጥቅም አይሰጥም። ይሄ ዘመን ራሳችንን በንቃት የምንጠብቅበት ዘመን ነው። ሁሉም ሥልጣኔ ሊባርከን ወደ እኛ አልመጣም። የዓለም ሥርዓት ሰጥቶ መቀበል ነው። አንድ ሥልጣኔ ወደ እኛ ሲመጣ የሆነ ነገራችንን ሊወስድብን ነው። በጥንቃቄና በማስተዋል ዘመኑን መዋጀት ይኖርብናል፡፡

የምንጠቀማቸው ስማርት ስልኮች፣ የምናያቸው ፊልሞች፣ የምንጫወታቸው ጌሞች፣ ባጠቃላይ ቀላልና ምቹ ሆነው አጠገባችን የምናገኛቸው ማህበራዊ ሚዲያዎች የሚሰጡን ተዝናኖት እንዳለ ሆኖ ከጊዜ አኳያ የሚቀሙን ብዙ ነገሮች አሏቸው። ከዚህ አኳያ ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው አይሎ በብዙ መልኩ አይተናቸዋል። ከሰሞኑ ይሄን እውነት የገለጸ አንድ ኩነት በኬንያ ተስተናግዷል፡፡

የማህበራዊ ሚዲያ አካል የሆነው ቲክቶክ በባህልና ሥርዓት እንዲሁም በትውልዱ ላይ እያደረሰ ባለው ተጽዕኖ በኬንያ የይታገድልን ሰልፍ ወጥቶበታል። በሌሎችም ሀገራት ተመሳሳይ ሕዝባዊ ጥየቃዎች እየተስተዋሉ ነው። የቲክቶክ ፈጣሪና መዲና የሆነችው ቻይና እንኳን ከዓላማው ውጪ ሰዎች እየተገለገሉበት ባለው ግኝቷ ላይ እገዳ ልትጥል ዛሬ ነገ በማለት ላይ ትገኛለች። በእኛም ሀገር ብዙ የጥላቻና መሰል ንግግሮች ሥርዓት ባጣ መልኩ በዚህ አውታር በኩል የሚፈበረኩ ናቸው፡፡

ጊዜ ሕይወት ነው.. ሕይወት ጊዜ ነው እንደሚለው አባባል እውነት የለኝም። ጊዜን በንቃትና በብልጠት መቅደም የዚህ ትውልድ ትልቁ ንቃት ሊሆን ይገባል። ብዙ ጊዜአችንን ስልካችን ላይ ስናሳልፍ በጊዜ እየተበለጥን ነው። ብዙ ጊዜአችንን ፌስ ቡክና ሌሎች ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ስናጠፋ በጊዜ እየተሸነፍን ነው። ጊዜን የምናሸንፈው የሰጠንን በረከት በእውቀትና በምክንያታዊነት ስንጠቀመው ነው።ለበጎ ነገር ስንገለገልበት ነው፡፡

ዘመን የሰጠንን በረከት እንዴትና ለምን፣ መቼና የት እንደምንጠቀመው ካላወቅን እየጠፋን ነው።ሰው ራሱን ካጣ ምንም ነው። በሕይወት ውስጥ እንዳናጣው ልንታገልለት የሚገባን አንድ እውነት ራሳችን ነው። ራሳችንን ያጣን ቀን ሁሉ ነገራችን ይቆማል። ያለን ነገር እንኳን አይጠቅመንም። ለዚህም ከዘመን መቅደም ፤ ከሥልጣኔ ፊተኛ መሆን የግድ ነው፡፡

ሰጥቶ የመቀበል መርህ ካልተረዳንው አደገኛ መርህ ነው። ሥልጣኔ ምናችንን እንደሚወስድብን አናውቅም። የሆነ ቀን ላይ ድንገት ነው ራሳችንን አንሰንና ጎለን የምናገኘው። “ውሃ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው” እንደሚባለው ፤ እያዝናና እያጫወተ የሆነ ጊዜ ላይ ልናስተካክለው ወደማንችለው የሕይወት ቀውስ ይከተናል፡፡

ሥልጣኔ ሕይወትን በብዙ መንገድ ያቀልልናል። በዚያው ልክ የሰውን ልጅ ከሕይወት ሙላት የማጉደል አቅምም አለው። ምናችንን እንደሚወስድብን አናውቅም። ካልነቃን ህልማችንን ሊወስድብን ይችላል። አስተዋይ ካልሆንን ታሪካችንን፣ ማንነታችንን፣ ባህልና ወጋችንን አንድ ሳይቀር ሊበርዝብን ይችላል፡፡

ዘመን የሰጠን የሆነ ነገር ላይ ብዙ ጊዜአችንን ስናሳልፍ ህልማችንን እያጣን ነው ማለት ነው። እቅዳችንን እየሳትን ነው ማለት ነው። ልንሰራው የሚገባንን እንዳንሰራ ጊዜአችንን በመሻማት ከእቅዳችን እንድንዘገይ በማድረግ ወደ ኋላ ያስቀረናል። ሁሉም ነገር ሥርዓት አለው። ሁሉም ነገር ልክና እውነት የሚሆነው በሥርዓት ውስጥ ሲከወን ነው።

ለዚህም ነው ጊዜ የሰጠንን በረከት በአግባቡ መጠቀም ከሕይወት ሙላት እንዳንጎድል ያደርገናል የሚለው የዚህ ጽሁፍ ትልቁ መልዕክቴ የሆነው። ሕይወት ዘልማድ አይደለችም እቅድና ተልዕኮ ናት። በእያንዳንዱ እንቅስቃሴያችን ውስጥ የምናደርገው ነገር፣ የምንሆነው መሆን የሕይወታችንን የወደፊት እጣ ፈንታ ይወስነዋል፡፡

በእቅድና በመላ መኖር የዘመናዊነት አንዱ መገለጫ ከመሆኑም በተጨማሪ ለሕይወት እሴት የሚጨምር ልምድ ነው። ከተፈጥሮ መጉደል መሸነፍ ነው። በዙሪያችን ያሉ ማናቸውም ነገሮች ከተፈጥሮ እንዳያጎሉን እድል ልንሰጣቸው አይገባም። አሁን ላይ ለወጣቱ አደገኛ ከሆኑ ሱሶች ውስጥ አንዱ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ነው።

እንዴት መጠቀም እንዳለብን ብቻ ሳይሆን ምን እየተጠቀምን እንደሆነ ካላወቅንም አደጋ ውስጥ ነን። አጠቃቀማችን ጊዜአችንን ይወስነዋል። ምን እየተጠቀምን እንደሆነ ማወቃችን ደግሞ ማንነታችንን ይታደገዋል። እንዴትና ምን እየተጠቀምን እንደሆነ በማወቅ ጊዜአችንን ከመባከን ራሳችንንም ከመጥፋት ልንታደገው እንችላለን፡፡

በዘመን ስጦታ ከራሳችንና ከታሪካችን ከእውነትና ከተፈጥሮ ጎለን ሌላ ሆነን እየኖርን ያለንበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው። ሀገር፣ ትውልድ፣ ማህበረሰብ መልካቸው እስኪጠፋን ድረስ ከማንነታችን ጎለን እየኖርን ነው። ባህል፣ ታሪክ ሥልጣኔ ውሃ ሳያነሱ ዘመን አመጣሽ በሆነው አውሮፓዊ ሥልጣኔ እየተወሰድን ማናችሁ ስንባል ማንነታችን እየጠፋን የተቸገርንበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡

እኔና እናተ በዚህ ዘመን ለሚፈበረኩ ማናቸውም የውሸት ፈጠራዎች የተጽዕኖ ማረፊያ እየሆንን ነው። ራሳችንን ከዘመን እድፍ ከሥልጣኔ ነውር መጠበቅ አለብን።ራሳችንን መከላከል ካልቻልንና የሰማነውን.. ያየንውን ሁሉ ልክ እንደሆነ የምንቀበል ከሆነ የሌሎች መጠቀሚያ ከመሆን ባለፈ ለራሳችንም ሆነ ለሀገራችን የምናመጣው ትርፍ የለም። ከሁሉ በፊት የሥልጣኔን ትርጉምና ምንነት ማወቅ ይኖርብናል።

ሥልጣኔ ራስን ከመውደድና ከመንከባከብ የሚጀምር ነው። ሥልጣኔ ራስን መተው፣ ራስን መርሳት.. ማንነትን መቀየር አይደለም። ሥልጣኔ ትናንትን መናቅ.. የኋላን መተው አይደለም። ሥልጣኔ አስተሳሰብን መቀየር ነው።ሥልጣኔ መሠረትና መረጃ ከሌለው የሕይወት ልማድ ተላቆ ወደ ላቀ እውነት መሸጋገር ነው።

አርነት የሚያወጣን እውነትና እውቀት እንጂ ሌላ ነገር አይደለም። በእውቀት መኖር ደግሞ የዚህ ዘመን አንዱ የሥልጣኔ መገለጫ ነው። ያየነውን ሁሉ ማመን፣ የሰማንውን እንዳለ መቀበል ሳይሆን እውነቱ የቱ ጋ እንዳለ መመርመር ያስፈልጋል። እንደነገርኳችሁ ይህ ዘመን ዓለም በእውቀት በሥልጣኔ በውሸትና በማስመሰል ጥግ የደረሰችበት ዘመን ነው።

በስልካችን እንኳን ብዙ ውሸቶችን የመቀበልና ብዙ ውሸቶችን የመላክ እድል አለን። ዘመኑ ዘመናዊ ውሸቶች እንደ አሸን የፈሉበት ዘመነ ፍዳ ልንለው እንችላለን። እውነቱ ውሸት.. ውሸቱ ደግሞ እውነት የሆነበት ግራ የሚያጋባ ሥልጣኔ ላይ ነን። እንደ ወጣት እንደ አንድ ምርጥ ዜጋ የሰጡንን ሁሉ መቀበል ሳይሆን ለምን ብለን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡

እስከዛሬ እውነት የሚመስሉ፣ ለእውነት የቀረቡ ፍጹም ውሸቶችን ስንሰማ ኖረናል። እኛም የፈጠርናቸው ሆኑ በሌሎች የተፈጠሩ ውሸቶች በማህበረሰቡ ላይ ይሄ ነው የማይባል ጥቁር ጠባሳዎችን አሳርፈው አልፈዋል። ዘመናዊነታችንን ከእውነት እንጀምር። ሥልጣኔን ሀገርን ከመውደድ ሀገርን ከመጠበቅ እንጀምር። ውሸት እውቀት አይጠይቅም.. ማንም ሊያደርገው የሚችል ነገር ነው። ይልቅ የላቀው እውቀት በእውነት መኖርና በእውነት ሌሎች እንዲኖሩ መፍቀድ ነው።

ሀገራችን ከመቼውም ጊዜ በላይ እውት ትሻለች በምንጠቀመው ማህበራዊ ሚዲያ ከቻልን ሕዝብ የሚጠቅም፣ ትውልድ የሚቀርጽ አስተማሪ መልዕክቶችን እንጻፍ.. እናብብ። ካልቻልን ደግሞ ዝም እንበል። ዝምታ ውበት ነው። ከክፉዎች ጋር አለመተባበር፣ የክፉዎችን ሃሳብ አለማስተጋባት አንዱ የዘመናዊነት መገለጫ ነው፡፡

እጆቻችንን፣ ኮምፒውተሮቻችንን ለክፋት አንንካ። እስከዛሬ በኮምፒውተር የታገዙ በርካታ ዘመናዊ ውሸቶችን ሰምተናል። እኚህ ውሸቶች እኛጋ ደርሰው የፈጠሩት ማህበራዊ ቀውስ አለ። ራስን በእውቀትና በጥበብ በማነጽ ለሀገር ባለውለታ መሆን ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል። እውቀት በምክንያት እንጂ በወሬ አይመራም። እውነት በተግባር እንጂ በይሆናል አይወሰንም።

ወሬኞች ሥራቸው ማውራት ብቻ ነው። ሌላ ነገር ስለማይችሉ የተሻለ ነገር መፍጠር አይሆንላቸውም። እኛ ደግሞ በእውነትና በእውቀት የውሸታሞችን ሴራ ተረት ማድረግ ይጠበቅብናል። ሥልጣኔ የሰው ልጅ የእውቀትና የማስተዋል ውጤት ነው። የሰው ልጅ እውቀቱን ላልተፈለገ አገልግሎት ሲጠቀምበት ግን ሥልጣኔ ስይጥንና ይሆናል። ከሥልጣኔ ወደ ስይጥንና መሸጋገር ይሄ ነው።

ዘመኑ የሥልጣኔና የስይጥንና ነው። በርካታ የተሳሳቱና ሀገር አፍራሽ የሆኑ መልዕክቶች የሚነገሩበት። ሥልጣኔው ተራቆ በኮምፒውተሩ ቁልፍ ማንም ቤቱ ሆኖ የፈለገውን የሚጽፍበት፣ የፈለገውን የሚዋሽበት ጊዜ ነው። በምክንያት የሚኖር፣ ስለሀገሩ የሚቆረቆር፣ እውነትን፣ እውቀትን በጎነትን የተላበሰ ትውልድ ሀገራችን ትሻለች። እኚህ የዘመናዊነት ጸዳሎች የዚህ ትውልድ መገለጫዎች እንዲሆኑ እፈልጋለሁ። ሌላው ሁሉ የሚጥለን ነው። ሌላው ሁሉ የሚያጎሳቁለን፣ ከክብራችን ዝቅ የሚያደርገን ነው፡፤

ሥልጣኔና ስይጥንና እውነትና ማስመሰል..የአሁኗ ዓለም አሁናዊ ስቃዮች ሆነው በየቤታችን አሉ።አንዳንዱ የዘመኑን ጥሩ ነገር ተጠቅሞ ሀገር ይለውጣል አንዳንዱ ደግሞ ሥልጣኔውን ባልተፈለገ መንገድ በመጠቀም በውሸት ወሬ የግል አጀንዳውን ያራምዳል። ማህበረሰባችን የወሬን አደገኝነት ሲገልጽ ‹ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው› ይላል.. ወሬ ምን ያክል አደገኛ እንደሆነ ይሄን ማየቱ ብቻ በቂ ነው፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያን ለወሬ ብርቅ አይደለንም ለበርካታ ዘመን በወሬና በአሉባልታ ፍቅራችንን፣ አንድነታችንን አጥተን እናውቃለን። በውሸት በማጭበርበር አብሮነታችንን፣ ኢትዮጵያዊነታችንን ተነጥቀን እናውቃለን። ለዚህም እኮ ነው ‹ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው› ብለን የተቀኘነው፡፡

አሁንም ከውሸትና ከአሉባልታ አልወጣንም። የሚጠቅመን ወሬ ሳይሆን ሥራ፣ አሉባልታ ሳይሆን በጠረጴዛ ዙሪያ መነጋገር ነው። እንደ ዜጋ እንደወጣት የጊዜ አጠቃቀማችንን ማስተካከል አለብን። በተለይ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ያለንን አቋም ማስተካከል አለብን። ጥሩ ነገር ምንና የት ጋ እንደተቀመጠ ማወቃችን ሀገራችን አሁን ካለችበት ፈተና እንድትወጣ ማገዝ ነው፡፡

ወጣትነታችን ለሀገር የምንሰራበት፣ ህልማችንን የምናሳካበት እንጂ የማንም መጠቀሚያ የሚሆንበት አይደለም።በወጣትነታችን ውስጥ ሀገራችንን እንፈ ልጋት። ሥልጣኔ ለሀገር ከመሥራት፣ ለሀገር ከማሰብ፣ ለሀገር ከመሞት የሚጀምር ነው። ለሀገር ስንሰራ ለራሳችንና ከእኛ በኋላ ለሚመጣውም ትውልድ እየሠራን ነው፡፡

ሥልጣኔያችንን ከሀገር እንጀምር።ሀገር በመውደድ፣ የራስን እውነት ከመቀበል እንጀምር። ባህል፣ ታሪክ በማክበር ወደምንፈልገው የሥልጣኔ ጥግ መሄድ እንችላለን። በጊዜ ከመበለጥ ይልቅ ጊዜን በመብለጥ ከፍ ማለት እንችላለን። የዚህ ዘመን አብዛኛው ሥልጣኔ ከራስ ሽሽት ነው። ሀገርና ሕዝብ፣ ታሪክና ባህል የሚለይ ነው። ከወግ ባህል የሚጣረስ ነው።

እውነተኛ ሥልጣኔ ደግሞ በትናንት እውነት ውስጥ ዛሬን መፈለግ እንጂ ትናንትን ትቶ ወደ ነገ መሄድ አይደለም። ከኋላው ውጪ የፊት የሚባል የለም ፤ እውነተኛ ሥልጣኔ በራስ እውነት ውስጥ መኖር.. በትናንት ዳና የዛሬን አብራክ መፈለግ ነው፡፡

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን ነሃሴ 19 / 2015

Recommended For You