ሰላምን በማጽናት ፤ የተረጋጋ ኢኮኖሚን ማዋለድ !!

ከሰሞኑ ወደ በረሃዋ ንግስት ድሬዳዋ ከተማ አቅንቼ ነበር። ድሬ ከስድስት ዓመት በፊት ከማውቃት በላይ በእጅጉ ተነቃቅታለች። በ1890ዎች መጨረሻ አካባቢ የተመሰረተችው ድሬዳዋ ከተማ በ1902 ደግሞ የራሷ ማዘጋጃ ቤት እንደነበራት ታሪካዊ መዛግብት ያስረዳሉ።

ይህች ታሪካዊ ከተማ ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ የተለያዩ ሕዝቦች በአንድነት የሚኖሩባት ሲሆን ቀደምት ሥልጣኔን ከተላበሱ የኢትዮጵያ ከተሞች መካከል ትጠቀሳለች፡፡ ቀድሞ የምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል የንግድ ማዕከል ከመሆን ባለፈ የዓለም አቀፍ ትስስር እምብርት በመሆን አገልግላለች። ዛሬም ወደ ቀድሞ ገናናነቷ ለመመለስና ለነዋሪዎቿ የተመቸች ከተማ ለመሆን በትጋት እየሠራች ትገኛለች ።

ዘመን የተሻገረ ህብረ- ብሔራዊ ፍቅርና አንድነትን ያነገበ ሕዝብ ባለቤት የሆነችው ድሬዳዋ ከተማ ፣ በጊዜ ወረት ፣ በዘመን ለውጥ ፣ ልዩነትን ጌጡና ፋሽን ላደረገው ጆሮ ሳትሰጥ ፊቷን ወደልማት ካዞረች ውላ አድራለች ።

በዚህም እስከ አሁን ድረስ ካስመዘገበቻቸው ተጨባጭ ስኬቶች በተጨማሪ ውብና ምቹ ፤ መልካም አስተዳደር የሰፈነባት፤ በንግድ፣ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፍ ላይ ያተኮረ፤ የዳበረ ዘላቂ ኢኮኖሚ ያላትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት በዕድገት ጎዳና እየገሰገሰች ነው ፡፡

የውጭ ንግድና የሀገር ውስጥ ፍላጎትን የሚያሟሉ እና እርስ በእርሳቸው ተደጋጋፊ የሆኑ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች በብዛትና በጥራት መገንባትና የሥራ እድል መፍጠርን ቀዳሚ አጀንዳዋ አድርጋ እየተጋች ነው። የከተማዋን ኢኮኖሚ በማሳደግ ራዕዬን ያሳኩልኛል ያለቻቸውን አቅጣጫዎች ነድፋ የዕድገት ጉዞዋን እያፋጠነች ትገኛለች ።

ከከተማው ነዋሪዎች አንደበትም ያረጋገጥኩት በሀገራችን የለውጡ መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ ጀምሮ በአስተዳደሩ በገጠርና ከተማ በርካታ ግዙፍ የልማት ሥራዎች እያከናወነ መሆኑን ነው። ይህም በከተማዋ በሁሉም ዘርፍ መነቃቃት ፈጥሯል። በርግጥም በድሬ የሚታየው የልማት እንቅስቃሴ በአጭር ጊዜ ወደቀድሞ ክብሯ መመለስ የሚያስችል እንደሆነ አያጠራጥርም ።

በዚህች ታሪካዊ ከተማ የሚታየው የአንድነት መንፈስ፣ የልማት እንቅስቃሴና የተነቃቃ ኢኮኖሚ መሠረቱ ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ መቻል ነው። ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት ነው። በአንድ ሀገር ሕዝብን የልማት ተጠቃሚ ማድረግ የሚቻለው ዘላቂ ሰላም መፍጠር ከተቻለ ብቻ ነው።

ይህ ባልሆነበት ስለ ቀጣይ የልማትና የዕድገት ጉዞ ለማቀድ እና የዜጎቿን የልማት ተጠቃሚነት ማሰብ “ላም አለኝ በሰማይ” ይሆናል። ምክንያቱም ዘላቂ ሰላም ባልተረጋገጠበት ሀገር የልማት ፣ የእድገት ጉዳይን አጀንዳ አድርጎ በሙሉ አቅም መንቀሳቀስ ያዳግታል።

ከክልል ክልልና ከአካባቢ አካባቢ ፣ ከከተማ ከተማ ጤናማ የሆነ የንግድ ዕቃዎችና አገልግሎቶች የሚንቀሳቀሱትና የተረጋጋ ገበያ የሚኖረው የሁሉም ነገር ቁንጮ የሆነውን ሰላም ማጽናትና መንከባከብ ከተቻለ ብቻ ነው። የድሬዳዋ ከተማ የተነቃቃ ኢኮኖሚ እና የልማት እንቅስቃሴ ይሄንኑ ያረጋግጥልናል።

እዚህ ጋር የድሬዳዋን የሰላም አየር አወድሰን ፤ የሱማሌ ክልልን ሳያደንቁ ማለፍ አይታሰብም ። በሁለቱ አካባቢዎች ከፍ ብሎ የሚነፍሰው የሰላም አየር ሁሉንም የሀገራችን ክፍሎች ማዳረስ አለበት የሚል ቁጭት ያሳድራል። ዛሬ አድናቆት የቸርነው ሰላም መምጣት የቻለው እንዲያው ዝም ብሎ አይደለም ።

በኢትዮጵያ ከአምስት ዓመት በፊት የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ሁከት ፣ ግጭት ቀድመው ካስተናገዱት የሀገራችን ክፍሎች መካከል ነበሩ (ኧረ እንዲያውም የሱማሌ ክልል ቀድሞ ነበር ያስተናገደው) ። በወቅቱ በሀገራችን ለየት ባለ ሁኔታ አዲስ የለውጥ ንፋስ መንፈስን ተከትሎ ፣ አንዳንድ ያኮረፉ ኃይሎች ሀገራዊ ለውጡን ለመቀልበስ እይታ ከነበሩት መካከል የፍቅር ተምሳሌቷ ድሬዳዋ ከተማ አንዷ ነበረች ።

በወቅቱ የድሬን ሕዝብ ሰላም ፈላጊነት ፣ ሰው ወዳድነት ከስር ከመሠረቱ ያልተረዱ የፖለቲካ ነጋዴዎች ከሃዲዱ ለማውጣት ሞክረው ነበር። ይህን እኩይ ሃሳብ በማወቅም ፤ ባለማወቅም ጥቂቶች በመቀበል ተንቀሳቅሰው ነበር። ይሁን እንጂ የሰፊው ሕዝብ ልብ “የሰው ልጅ ፣ ሚዛኑ ሰው ከመሆኑ በላይ የሚበልጥም፣ የሚቀድምም የለም ” ብሎ የሚያምን ነውና ፤ የፍቅር ባቡሩ ሃዲዱን ሳይስት እንዲጓዝ አድርገውታል ።

በድሬዳዋ ከተማ ሰላምን ማጽናት በመቻሉ ፤ ህብረተሰቡ ንጋትም ሆነ ምሽት ከስጋት የፀዳ ሕይወትን ይመራል ። ዛሬም እንደ ትናንቱ ድሬ ላይ የነበረው የፍቅር ባቡር ሃዲዱን ሳይለቅ በአንድነት በእርጋታ መጓዙን እንደቀጠለ ይገኛል ።

በተመሳሳይ በሱማሌ ክልል ሐምሌ 27 ቀን 2010 ዓ. ም. ጅግጅጋ ከተማ ላይ የነበረውን ጭንቅ ከብዙዎቻችን አዕምሮ የሚጠፋ አይደለም። በወቅቱ በሱማሌ ክልል ዋና ከተማ ከጅግጅጋን ጨምሮ በክልሉ የተለያዩ ከተሞች የነበረው እንቅስቃሴ ክልሉ ዳግም ወደ ሰላም ይመለሳል ለማለት የሚያስደፍር አልነበረም። ነገር ግን አዲሱ የክልሉ አመራር በአጭር ጊዜ ክልሉን ከስጋት ቀጣናነት ወደ ሰላም እንዲሸጋገር ማድረግ ችሏል።

በአጠቃላይ ምስራቃዊ የሀገራችን ክፍል ደፍርሶ የነበረውን ሰላም ፤ ወደነበረበት ለመመለሱ ሁለት ምክንያቶችን ተጠቃሽ ማድረግ የሚቻል ይመስለኛል። አንደኛው የሕዝቡ ሰላምን ከመሻት ተሻግሮ ሰላምን ለማጽናት መሥራት በመቻሉ ፤ ሁለተኛውና ዋነኛው የአመራሩ ቁርጠኝነትና የሕዝብን ጥቅም አስቀድሞ መሥራት በመቻሉ ነው ።

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከምንም በፊት ሰላም ይቅደም ከሚል አፋዊ ንግግር ባሻገር ተጨባጭ ሥራዎችን ማከናወን ችሏል። በተለያዩ ጊዜያት የሚፈጥራቸው የውይይት መድረኮች የማህበረሰቡን ችግር በቅርበት መረዳትና መስማት እንዲችል አግዞታል። ከዚህ በተጓዳኝ ችግርን በጋራ ለማስወገድና የጋራ መግባባት ለመፍጠር እንዳገዙት ነው ለመረዳት የቻልኩት ።

በተለይ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ተገልጋዩን ለብሶት የሚዳርጉና ለሀገር ሰላም መናጋት ምክንያት የሚሆኑ አመራሮችና ባለሙያዎችን በሕግ ተጠያቂ በማድረግ ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ ተሞክሯል ። በዚህም ለሰላም ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው ሕዝብም በተግባር ተክሷል ።

በአሁኑ ወቅት በሁለቱ አካባቢዎች ዜጎች በሃይማኖታቸውም ሆነ በብሄራቸው ሳይሸማቀቁ በነጻነት የእለት ተለት እንቅስቃሴያቸውን ከመተግበርም በላይ በነጻነት ሃሳባቸውን መግለጽ እንዲችሉ ተደርጓል። ይህም ድሬንም ሆነ ጅግጅጋን ሁሉም ዜጋ በአንድ መነጽር የሚታዩበት ፣ በሰላም የሚኖሩበትን አውድ በመፍጠር ተጨባጭ ለውጥ አስገኝቷል።

የመንግሥት ተቀዳሚ ኃላፊነት ዘላቂ ሰላም መፍጠር እንዲሁም ፣ የተገኘን ሰላም በማጽናት የሕዝቡን ደህንነት መጠበቅ ፣ መሠረተ ልማት መዘርጋት ነው። የተገኘን ሰላም በማጽናት ረገድ ከምስራቁ የሀገራችን ክፍል ብዙ መማር ይገባል። በተለይ በአማራ ክልል እና ኦሮሚያ ክልል ያለው ወቅታዊ ሁኔታ ይሄንን እንድል ያስደፍረኛል።

በክልሉ ያለው የጸጥታ ችግር የመንግሥት ሠራተኛው ተረጋግቶ መደበኛው ሥራውን እንዳይሠራ፣ ነጋዴው ለሸማቹ አገልግሎት እንዳይሰጥ ማጉላላት፣ አርሶ አደሩ በክረምት የእርሻ ሥራው ላይ እንዳያተኩር እንቅፋት መሆን፣ ህብረተሰቡ በሰላም ወጥቶ እንዳይገባ እክል ፈጥሯል።

ይህም በመሆኑ ህብረተሰቡ ስለተሰማራበት ሥራ ሳይሆን ስለ ሰላም እጦትና ወጥቶ ስለመግባት እንዲያስብ ተገዷል። በየጫካው የፈላው የጎበዝ አለቃ ፣ የሕዝብ ነጻ አውጪ የሚል የዳቦ ስም ተሸክሞ ሕዝብን የሚያሸብር ዘራፊ እየተሰቃየ ይገኛል። በትራንስፖርት ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ የሚደረግ ጉዞ ስጋት ከሆነ ውሎ አድሯል።

በየጫካው የሚሽሎኮሎኩ ‘ነጻ አውጪ ሽፍቶች’ ሕዝብን በጠራራ ፀሃይ በማገት ገንዘብ መሰብሰብን ፋሽን እስኪመስል ድረስ አጠናክረው ቀጥለውበታል። ይህም ሕዝቡን ከመቼውም ጊዜ በላይ ሰላምን እንዲጠማ አድርገውታል ።

ዘላቂ ሰላም ባልተረጋገጠ ሀገር ልማት ፣ ዕድገት ቀዳሚ አጀንዳ ሆኖ በሙሉ አቅም መንቀሳቀስ ያዳግታል። ስለዚህ የክልል መንግሥታት ዘላቂ ሰላም የመፍጠር እንዲሁም የተገኘን ሰላም ማጽናት ቀዳሚ ሥራ መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል። ይህንንም በዘርፉ ውጤታማ ከሆኑ ክልሎች ሊማሩ ይገባል።

 ዳንኤል ዘነበ

አዲስ ዘመን ነሃሴ 19 / 2015

Recommended For You