መፍትሔ የሚያሻው የኤሌክትሪክ ኃይል በተደጋጋሚ መጥፋትና መቆራረጥ ፤

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ባስጠናው አንድ ጥናት በተደጋጋሚ በሚከሰት የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ሀገራችን በአንድ ዓመት ብቻ 95.5 ቢሊየን ብር ታጣለች ። በዓመት በአማካኝ ለ162 ሰዓታት መብራት ይጠፋል። ይቅርታ አድርጉልኝና እኔ ግን ከዚህ የባሰ ነው እላለሁ። ይሄን መጣጥፍ እያጠናቀርኩ እያለ እንኳ፣ ማክሰኞ ነሐሴ 16 ቀን 2015 ዓ.ም እንኳ 3 ጊዜ ጠፍቶ ከበራ በኋላ መልሶ እንደጠፋ ነው።

አዲስ አበባ መኖር ከጀመርኩ ከ15 ዓመታት በላይ ቢሆንም እንደ አለፉት አራትና አምስት ዓመታት ግን ሆኖ አላየሁትም። የዘንድሮው ደግሞ የተለየ ነው። እንዲህ ያለ ተደጋጋሚ የመብራት መጥፋትና ኃይል መቆራረጥ አይቼ አላውቅም። በዚህ አይነት ዘንድሮ ለ200 ሰዓታት ምን አልባትም ከዚያ በላይ መብራት ሳይጠፋ ይቀራል። በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ያስከተለውን ጉዳት ደግሞ አስቡት። አሁን አሁን የመልካም አስተዳደር ችግር እየሆነ፤ ደንበኛውን እያማረረ ይገኛል።

ለነገሩ ተደጋጋሚ የመብራት መጥፋት ከኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ የተሻገረ ነው። በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ዳፋው የእያንዳንዱን ግለሰብና ማህበረሰብ ኑሮ ያናጋል። በገጠመኝ የጤና እክል የተነሳ ቤት ሆኜ ለምሰራው ለእኔ ደግሞ መብራት ጠፋ ማለት ስራ ቆመ ማለት ነው። ዜጎች ከመቼውም ጊዜ በላይ በኤሌክትሪክ ኃይል ጥገኛ በሆኑበት በ21ኛው መክዘ መብራት ጠፋ ወይም በተደጋጋሚ ተቆራረጠ ማለት ህይወት ቀጥ አለ፣ ተስተጓጎለ ማለት ነው። ለዚህ ነው በመብራት መጥፋትና መብራት ሰዎች መስራት፣ ፋብሪካዎች ማምረት፣ ተማሪዎች መማር፣ ነጋዴዎች መነገድ፣ ምግብ ማብሰል፣ በበይነ መረብ መገናኘት፣ ወዘተረፈ አይቻልም። ከዚህ ባሻገር ግብዓት ይበላሻል።

በዚህ የኑሮ ውድነት በምኖርበት የጋራ መኖሪያ በተደጋጋሚ ሊጋገር የተቦካ ሊጥ ሲደፋ፣ ፍሪጅ ውስጥ የተቀመጠ የበሰለ ምግብ፣ አትክልትና ስጋ ተበላሽቶ ሲጣል ታዝቤአለሁ። መብራት ቴሌቪዥን፣ ምድጃ፣ የእጅ ስልክና ሌሎች የኤሌክትሪክ ቁሳቁሶችን አቃጠለብኝ የሚሉ ቅሬታዎችን መስማት እማ የተለመደ ነው። የኃይል ተደጋግሞ መቆራረጥ በንግዱ ከፍ ሲልም በኢኮኖሚው ላይ የሚያስከትለው ጉዳትና ኪሳራ ከፍተኛ ነው። የፋብሪካዎችን የምርት ሒደት ያስተጓጉላል ብሎም ያቆማል። ግብዓት ያበላሻል። በመጨረሻም ለኪሳራ ይዳርጋል።

በተለይ በቴክኖሎጂ፣ በጤና ዘርፍና በመረጃ ማዕከሎች ላይ ተደጋግሞ የሚከሰት የኃይል መቆራረጥና መጥፋት ምርታማነትን ከመቀነስ ባሻገር በማሽኖች፣ በመሳሪያዎችና በሰርቨሮች ብልሽት ብሎም መቃጠል ያስከትላል። ተደጋጋሚ የኤሌክትሪክ ኃይል መጥፋትና መቆራረጥ ቁልፍ በሆኑ መሠረተ ልማቶች ላይ ዘላቂ ጉዳት ያስከትላል። የንጹሕ መጠጥ ውሃ ማጣሪያ ተቋሞችን፣ መጓጓዣን፣ የቴሌኮሙኒኬሽን ኔትወርኮችን፣ ወዘተረፈ መሠረተ ልማቶችን ይጎዳል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በተደጋጋሚ የማሻሻያ ሥራ እየሠራ እንደሆነ ሲገልጽ ቢቆይም፣ ክረምት በገባ፣ ዳመን ባለ ቁጥር፣ ዝናብ ጠብ ሲል የመብራት መቆራረጡ ይጀምራል። ዝናብ በረከት ነው ብዬ ባምንም ገና መዝነብ ሲጀምር ደግሞ ሊጠፋ ነው ብዬ እሰጋለሁ። ለነገሩ የመብራት ነገር የማያሳስበው የማያስጨንቀው ማን አለ። ቢቸግረው ስለዚች ሀገር መብራት በተደጋጋሚ መጥፋት ላይ ያልተሳለቀ፣ ያልቀለደ ኮሜዲያን፣ ማህበራዊ ሚዲያና የቴሌቪዥን ሾው የለም።

የችግሩን ግዝፈት ተረድቶ ተከታታይ ዘገባ የሰራ፣ የጠየቀና የመረመረ መደበኛ ሚዲያ ግን የለም ብል አልተሳሳትኩም። አገልግሎቱ የሚሰጠውን መግለጫና መልስ ከማስተጋባት አልፎ የምርመራ ዘገባ ለመስራት ያሰበ የለም። በዚህ የተነሳ ችግሩ መፍትሔ ሳያገኝ ቀጥሏል። ተደጋጋሚው የኃይል መቆራረጥ ችግር እየፈጠረባቸው እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ አስተያየታቸውን የሰጡ በተለያየ ሥራ ላይ የተሠማሩ ግለሰቦች ይናገራሉ።

አገልግሎቱ የደንበኞችን ዕርካታ ካለማሟላቱ ጋር በተያያዘ ብዙ ጊዜ ስሙ በመጥፎ ይነሳል። ጊዜው የክረምት ወቅት ሲሆን ደግሞ ቅሬታው ይበረታል። የኢትዮጵያ አሌክትሪክ አገልግሎት ይህን የደንበኞች የዕርካታ መጠንን ለመለካት ይረዳው ዘንድ በ2013 ሕዳር ወር ላይ ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር ባስጠናው ጥናት፣ በአገራችን ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል በተለያየ ምክንያት እንደሚቋረጥ ተገልጿል።

ከዚህም አልፎ በተለይ በ2011 በአገር ዐቀፍ ደረጃ የፈረቃ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል። በ2012 በተቋም ደረጃ ያለውን ተደራሽነት ለማሳደግና የኃይል መቆራረጥን ለመቀነስ የተለያዩ የካፒታል ፕሮጀክት ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ የተቋሙ የ2012 ሪፖርት ያሳያል። በእነዚህ ስራዎች የፈረቃ አገልግሎቶችን ማስቀረት መቻሉ ተመልክቷል። ተቋሙ ዘርፈ ብዙ የሆኑ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ እያደረገ ቢሆንም፣ የጥናቱ ውጤት እንደሚያሳየው ከሆነ በኃይል መቆራረጥ ላይ የተገልጋዩ ሕብረተሰብ ቅሬታ በጣም ከፍተኛ እንደሆነ ነው። ከጥናቱ ተሳታፊዎች 75 በመቶ የሚሆኑት የሚቀርብላቸው የኤሌክትሪክ ኃይል የመቆራረጥ ድግግሞሽ እንዳለው ገልፀዋል። ይህ በጣም ከፍተኛ የሚባል አኃዝ ነው ተብሏል።

የዚህ መቆራረጥ መደጋገም ደግሞ በበርካታ ዘርፎች ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ የማይካድ ሐቅ ነው። ይህን የመቆራረጥ መደጋገም እና ተቋርጦ የሚቆይበትን የጊዜ ብዛት በተመለከተ በ2020 የወጣው The World Bank’s Enterprise Surveys (WBES) እንደሚያሳየው፣ ከሰሀራ በታች በሚገኙ አገራት በወር ውስጥ ከአስራ አንድ ጊዜ በላይ የመብራት መቋረጥ እንደሚኖር ይገልጻል። በነዚህም ጊዜያት ከስድስት ሰዓት ላላነሰ መብራት ጠፍቶ እንደሚቆይም ጽሑፉ ያሳያል።

ይህ ሁነት በኛም አገር በየጊዜው የሚከሰት ጉዳይ እንደመሆኑ መጠን፣ የመብራት መቆራረጥ እና ተቋርጦ የሚቆይበት ጊዜም መርዘም የሚያስከትለው የራሱ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር እንዳለ ይታመናል። እኔ በምኖርበት የየካአባዶ የጋራ መኖሪያ ቤት ግን በቀን ከ10 ጊዜ በላይ ሲጠፋ፤ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ለቀናት ሲጠፋ ታዝቤያለሁ።

አሁን ላይ ሁሉም ነገር በሚባል ደረጃ በኤሌክትሪክ ኃይል መንቀሳቀስ ከጀመረ ዋል አደር ብሏል። አቅርቦቱን ተማምነው ሥራቸውን በኤሌክትሪክ ኃይል ላይ በመሰረቱት ደግሞ ያለው ተጽዕኖ ቀላል የሚባል አይደለም። እንጀራና ዳቦ በመጋገር እና ማከፋፈል ሥራ ላይ እንደተሰማሩ የሚናገሩት ስማቸው እንዲጠቀስ የማይፈልጉ አስተያየት ሰጪ፣ ከክረምቱ መግባት ጀምሮ በመብራት መቆራረጥ ምክንያት ሥራ በአግባቡ መሥራት እንዳልቻሉ ይገልጻሉ። በዚህ ወቅት ያለው ተጽዕኖ የታወቀ ነው ሲሉ ይጀምራሉ አስተያየት ሰጪዎች፣ ሥራችንን በአግባቡ መከወን እንዳንችልና ውጤታማ እንዳንሆን ራሱን የቻለ ተጽዕኖም አለው ሲሉም ያክላሉ።

ደንበኞቻቸውንም በአግባቡ ማስተናገድ አለመቻ ላቸውንም ያነሳሉ። ትዕዛዝ ለሚሰጡን ደንበኞች ትዕዛዛቸውን በጊዜው እንዳናደርስ እክል ሆኖብናልም ሲሉ ይናገራሉ። መብራት ከጠፋ ያለን አማራጭ እስኪመጣ ሥራ ፈትቶ መቀመጥ መሆኑንና በዚህም ምክንያት ገቢያቸው እንዳሽቆለቆለ ያስረዳሉ። በመብራቱ የተነሳ ሥራ መሥራት እንዳልቻሉ የሚገልጹት አስተያየት ሰጪው፣ መብራት ይኖራል በሚል ምኞት ወደ ሥራ መሄድና ባለመኖሩም የትራንስፖርት ወጪ አውጥቶ መመለስ ብቻ ሥራቸው እንደሆነ ይገልጻሉ። ደንበኞችንም በመብራት ምክንያት እያጡ እንደሆነም ያክላሉ።

የመብራት መቆራረጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በተቋማት ላይ ተጽዕኖ ይፈጥራል። በመቆራረጡ ምክንያት የሠራተኛ ደመወዝን ጨምሮ የተለያዩ ወጪዎች በመኖራቸው ኪሳራም ሊያጋጥም እንደሚችልም ይታሰባል። በዚህ የመብራት መቆራረጥ ዙርያ አስተያየታቸውን የሰጡን የአዲስ አበባ ከተማ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ኮሚዩኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ በቀለ ክፍሌ ሲናገሩ፣ ኃይል በሁለት መንገድ የሚቋረጥ ሲሆን አንደኛው በብልሽት፣ ሌላኛው ደግሞ በዕቅድ እንደሆነ ያስረዳሉ። አብዛኛው አሁን ከተማው ውስጥ እየተከሰተ ያለው ግን በብልሽት ምክንያት የሚኖር የኃይል መቆራረጥ እንደሆነ ይገልጻሉ።

ብዙውን ጊዜ በዛፎች ምክንያት ሽቦዎች ሲነካኩ ኃይል እንደሚቋረጥና አልፎ አልፎም የሽቦዎች መናጋት የኃይል መቋረጥን እንደሚያስከትልም ያስረዳሉ። ከተማችን በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ የመልሶ ግንባታ እየተከናወነ ነው የሚሉት ሥራ አስኪያጁ፣ በዚህ ጊዜ ስናቋርጥ ግን በዕቅድ ነው ይላሉ። የኃይል ፍላጎት መሸከም ያልቻለ መስመር ክረምት ሲጨመርበት ለብልሽት የተጋለጠ ነው ይላሉ የኮሚዩኒኬሽን ሥራ አስኪያጁ። በአሁን ወቅት በምስሶዎች ላይ የሚያጋጥም የመኪና ግጭት፣ የዛፍ መውደቅ፣ በግንባታና መንገድ ሥራዎች ወቅት ከሚከሰት የኤሌክትሪክ ሽቦ መቆረጥ ጋር በተገናኘ የሚከሰቱ አደጋዎች መብራት ለረጅም ሰዓት እንዲቋረጥ ምክንያት መሆናቸውን ይገልጻሉ። እነዚህም ጉዳዮች የመልካም አስተዳደር ችግር ጥያቄዎች በመሥሪያ ቤታቸው ላይ እንዲነሳ እያደረጉ መሆኑን ያነሳሉ።

ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ አሌክትሪክ አገልግሎት የሚከሰተውን የኤሌክትሪክ መቆራረጥና መዋዠቅን ለመቀነስ፣ እንዲሁም ተደራሽነት ለማረጋገጥ እየሠራ መሆኑን መግለጹም ይታወሳል። ከነዚህም መካከል ቋሚ ንብረቶችን መቁጠር እና መመዝገብ ይገኝበታል። ከሚመዘገቡት መካከል የመካከለኛ እና ዝቅተኛ መስመር እና ትራንስፎርመሮችን መረጃ በመሰበሰብና መለያ በመስጠት፣ ዲጂታላይዝ በማድረግ የሚፈጠሩ ችግሮችን በአፋጣኝ ለመፍታት እየሠራሁ ነው ቢልም፣ አሁንም ችግሩ አልተፈታም።

ተቋሙ አሁንም የኃይል መቆራረጥ ማስተካካል እንዳልቻለ ሌላኛው ያነጋገርናቸው አስተያየት ሰጪ ይናገራሉ። በረከት ውብሸት ለደንበኞች ምግብ በማቅረብ ሥራ የሚተዳደሩ ሲሆን፣ በፊት ላይ ምንም የመብራት መቋራረጥ ችግር እንዳልነበረ ያስታውሳሉ። ከዚህ ቀደም ቢሄድ እንኳን ቶሎ ነበር የሚመጣው የሚሉት አስተያየት ሰጪው፣ አሁን ላይ ግን ቀኑን ሙሉ መብራት እንደሚጠፋ ይገልጻሉ። አክለውም በሥራችንም ላይ ኪሳራ እያመጣብን ነው ይላሉ።

መብራት በማይጠፋባቸው ቀናት ላይ ድርጅታቸው እስከ ስምንት ሺሕ ብር ድረስ እንደሚሰራ የሚገልጹት በረከት፣ አሁን ላይ መብራት መጥፋት ከጀመረ ወዲህ ግን ሦስት መቶ ሀምሳ ብር ተሰርቶ የሚያውቅባቸው ቀናትም እንዳሉ ያስታውሳሉ። አብዛኞቹ ደንበኞቼ የግል ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ናቸው የሚሉት በረከት፣ ተማሪዎቹ የሚጠቀሙበት ሰዓት ደግሞ ምሳ ላይ በመሆኑ ምሳ ማድረስ ስለማይቻል ለኪሳራ እየተጋለጡ እንደሆነ ያስረዳሉ። ሙሉ በሙሉ ሥራቸውን መብራት ላይ መሰረት እንዳደረጉ የሚገልጹት አስተያያት ሰጪው፣ መብራት መቆራረጡ በመደጋገሙ ደንበኞች የሚፈልጉትን ማቅረብ እንዳልቻሉና ደንበኞቻቸውም ወደ ሌላ ስፍራ እየሄዱባቸው እንደሆነ ገልጸዋል።

በያዝነው ነሐሴ ወር ላይ ችግሩ በጣም እየከፋ መሄዱን የሚያነሱት በረከት፣ “ካልሆነ በፈረቃ ቢሆን” ይላሉ። መብራት በተቋረጠ ቁጥር እንዲያስተካክሉልን ስንደውል ትንሽ ችግር እንደሆነና ቶሎ እንደሚመጣ ቢነግሩንም፣ ስለማይስተካከል ሥራ ፈትቶ ቁጭ ከማለት ውጪ መፍትሄ እንዳላገኙ ይገልጻሉ። መኖሪያቸው ኃይሌ ጋርመንት አካባቢ እንደሆነ የሚናገሩት እኚህ ተገልጋይ፣ የመብራት መቆራረጥ ጉዳይ በሁሉም አካባቢ የሚታይ ስለሆነ ይሻሻላል ብሎ ተስፋ ከማድረግ ውጪ ምንም ማድረግ እንደማይችሉ ተስፋ በመቁረጥ ስሜት ያስረዳሉ።

የክረምቱ መበርታት ዋነኛ ችግር እንደሆነ ቢነሳም፣ ሌላ ለመሥሪያ ቤቱ ትልቅ ችግር እየሆነ የመጣው የኃይል ስርቆት እንደሆነ ሥራ አስኪያጁ ያነሳሉ። እነዚህ ኃይል በመስረቅ የሚጠቀሙ ሰዎች መስመር በማጨናነቅ የኃይል መቆራረጥ እንዲከሰት እያደረጉ እና ትራንስፎርመርን ጨምሮ በውጭ ምንዛሬ የሚገቡ የተለያዩ መሳሪያዎችን ለብልሽት እየዳረጉ እንደሆነም ይገልጻሉ።

ለእንደዚህ አይነት ችግሮች መፍትሄ ይሆናል የተባለውን የቆጣሪ ምርመራ እያደረጉ እንደሆነ የሚናገሩት በቀለ ክፍሌ፣ የተሰረቀ ኃይል በመጠቀም እንጀራ የሚጋግሩ፣ ብረት በመበየድ ሥራ የተሰማሩ ግለሰቦች እና በጥቃቅንና አነስተኛ የተደራጁ ቡድኖች እንዳገኙ ገልጸዋል። በዚህ ሕገ-ወጥ ተግባር ላይ ተሰማርተው ያሉትንም ለሕግ የማቅረብ ሥራ እየተከናወነ እንደሆነም የአዲስ አበባ ከተማ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ኮሚዩኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ ያነሳሉ። በከተማው የሚስተዋለውን የመብራት መቆራረጥ ችግር መቼና እንዴት ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ መፍታት እንደሚቻል በውል ባይታወቅም፣ እንደ በረከት ውብሸት ይሻሻላል ብሎ በተስፋ ከመጠበቅ ውጭ ሌላ አማራጭ ያለ አይመስልም።

ሻሎም ለሀገረ ኢትዮጵያ !

አሜን።

 በቁምላቸው አበበ ይማም(ሞሼ ዳያን)

fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 18/2015

Recommended For You