‹‹የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የሚያሳየው ማንሰራራት ጠንካራውን የብሪክስ ኅብረት ለመቀላቀል እድል ይሰጣል››ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ በሻህ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር

‹‹ብሪክስ›› በሚል ምህጻረ ቃል የሚጠራው ኅብረት የብራዚል፣ የሩሲያ፣ የህንድ፣ የቻይና እና የደቡብ አፍሪካ ሀገራት ጥምረት ነው። ኅብረቱ የመጀመሪያዎቹን አራት ሀገራት አቅፎ እኤአ በ2009 የተመሰረተ ሲሆን፤ 2010 ላይ ደግሞ አፍሪካዊቷን ሀገር ደቡብ አፍሪካን ማካተት የቻለ ነው። ዋና ዓላማ አድርጎ የተመሰረተውም በዓለም የአስተዳደር ሥርዓት ውስጥ ሚናውን ጉልህ ለማድረግ እና ለታዳጊ ሀገራት ኢኮኖሚ ድምጽ እና ውክልና ለመፍጠር ጭምር እንደሆነ ይነገራል።

ይህ ኅብረት የራሱ የሆነ ጠንካራ ጎን እንዳለው በብዙዎቹ ሀገራት ዘንድ የታመነበት በመሆኑ 40 ያህል ሀገራት መካከል ገሚሱ ጥምረቱን የመቀላቀል ፍላጎት ያሳዩ ሲሆን፤ ገሚሱ ደግሞ የ‹‹ቀላቅሉን›› ጥያቄያቸውን በማመልከቻቸው ማስገባታቸው ሲነገር ሰንብቷል። ከፍላጎት አልፈው የ‹‹ቀላቅሉኝ››ን ጥያቄ በማመልከቻቸው ካስገቡ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ ሰኔ 22 ቀን 2015 ዓ.ም በግልጽ ጥያቄ ያቀረበች ሀገር መሆኗም ይታወቃል።

ታዲያ በአፍሪካዊቷ ምድር ደቡብ አፍሪካ ላይ እየተካሄደ ያለው የብሪክስ መሪዎች ጉባኤ ከትናንት በስቲያ እና ትናንት በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ሲመክር የቆየ ሲሆን፤ ጉባኤው ዛሬ ይጠናቀቃል ተብሎም ይጠበቃል። ኢትዮጵያ ያቀረበችው የአባልነት ጥያቄ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ አዲስ ዘመን ከፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ በሻህ ጋር ያደረገው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል። መልካም ንባብ።

 አዲስ ዘመን፡- ብሪክስ በሚል ምህጻረ ቃል የሚጠራው የብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ ጥምረት አደረጃጀቱ ምን ይመስላል?

ፕሮፌሰር ብሩክ፡- ብሪክስ አዲስ የሆነ ታዳጊ ሀገራት ስብስብ ነው። የብሪክስ ተቋም የተቋቋመው እኤአ በ2009 ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ሲቋቋሙ አባል የነበሩት አራት ሀገራት ብቻ ነበሩ። ከአንድ ዓመት በኋላ ማለትም እኤአ በ2010 ላይ ደቡብ አፍሪካ አራቱን ሀገራት ተቀላቀለች። እነዚህ የተቀላቀለቻቸው አራቱ ሀገራት ብራዚል ከላቲን አሜሪካ፣ ራሽያ ከአውሮፓ እና ኤዥያ፣ ቻይና እና ሕንድ ከኤዥያ ናቸው።

የእነዚህ ሀገራት ጥምረት ዋና ዓላማው የተለየ አማራጭ የሆነ የዓለም የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ኅብረት ለመፍጠር ነው። እንደሚታወቀው በአሜሪካ የሚመራው ጂ-7 ተጽዕኖ ፈጣሪ ነው። ይህ ቡድን ጃፓን እና ካናዳን ያካተተ ሲሆን፤ አራቱ ደግሞ ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ጣሊያንና እንግሊዝን ከአውሮፓ የያዘ ነው። የዚህ አማራጭ የሆነ በተለይ ቀዝቃዛው ጦርነት ካለፈ በኋላ አዲስ አይነት የኃይል አሰላለፍ በዓለም ላይ መታየት ጀመረ። በተለይ ቻይና እና ህንድ በጣም እያደጉ ስለመጡ ያንን የሚያንጸባርቅ አዲስ አይነት የኃይል አሰላለፍ በማስፈለጉ አዲስ አይነት ማህበር ያስፈልገናል በሚል እኤአ 2009 ላይ ይህ ኅብረት ሊቋቋም ቻለ።

አዲስ ዘመን፡- ይህ ብሪክስ የተባለው ጥምረት ምን ያህል ጠንካራ ነው ማለት ይችላል?

ፕሮፌሰር ብሩክ፡– ብሪክስ የዛሬ 14 ዓመት ከተቋቋመ ወዲህ በርካታ ሀገራት ለቡድኑ ያላቸው ፍላጎት እየጨመረ መጥቷል። ፍላጎት ማሳየት ብቻ ሳይሆን ብዙዎቹም ቡድኑን ለመቀላቀል ጥያቄ አቅርበዋል። ከእነዚህ ጥያቄ ካቀረቡት በርካታ ሀገራት መካከል ደግሞ አንዷ ሀገራችን ኢትዮጵያ ናት።

እውነቱን ለመናገር ብሪክስን ለመቀላቀል ፍላጎት ያሳዩ ወደ 40 ሀገራት ያህል ናቸው። ይህ የሚያሳየን ደግሞ ብሪክስ ምን ያህል የተሳካ ተቋም እና ጠንካራ ኅብረት ያለው እንደሆነ ነው። ይህን የሀገራቱን ተነሳሽነት የምንመድበው በሁለት ፈርጅ ነው። ይኸውም ፍላጎት ያሳዩ ሀገራት በሚልና ተቋሙን ለመቀላቀል ማመልከቻ ያስገቡ ሀገራት በሚል ነው።

ለምሳሌ የመጀመሪያው እንደ ቱርክ እና ናይጄሪያ የመሳሰሉ ሀገራት ተቋሙ ትኩረታቸውን በመሳቡ ለመቀላቀል ፍላጎት ያሳዩ ናቸው። ሁለተኛው ፈርጅ ላይ የሚገኙት ደግሞ ልክ እንደ ሀገራችን ኢትዮጵያ የመሳሰሉ ሀገራት የተቋሙን አስፈላጊነት በአግባቡ አስበውበት ለመቀላቀል ማመልከቻ ጽፈው ያስገቡ ናቸው። ኢትዮጵያ እንዳልኩሽ የተቋሙ ዓላማና ራዕይ ለእኔ የሚበጅ ነውና ልቀላቀላችሁ ወድጃለሁ ስትል ያስገባችው ማመልከቻ ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ተቋሙ ጥያቄዋን ተቀብሎ መቀላቀል ብትችል ሕዝቤ ተጠቃሚ ይሆናል በሚል አስባ ነው።

አዲስ ዘመን፡- የኅብረቱ ዋና ዓላማ ምንድን ነው? የኢትዮጵያስ ጥምረቱን የመቀላቀል ጥያቄ ከዚህ አኳያ የሚቃኘው እንዴት ነው?

ፕሮፌሰር ብሩክ፡- ብሪክስ የያዛቸው ሶስት ዋና ዋና የሚባሉ ዓላማዎችን ነው። የመጀመሪያ የኢኮኖሚ ትብብርን ለማሳለጥ ነው። በዚህ ውስጥ ንግድ እና የንግድ ለውውጥ አለ። ሁለተኛው ዓላማ ደግሞ ተከታታይነት እና ቀጣይነት ያለውን እድገት ለማበረታታት ያለመ ነው። ይህም ማለት የተመጣጠነ እና የሚያዛልቅ ማኅበራዊ-ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማምጣት ያለመ እና ያቀደ ነው። ይህ አካታች እድገት የሚሉት ነው። እንዲህም ሲባል እጅ ለእጅ ተያይዞ የዓለም ሀገራት በተለይም እንደ እኛ ኢትዮጵያን የመሰሉ ሀገራት ማደግ አለባቸው የሚል ሲሆን፣ አቃፊ እንጂ አግላይ መሆን የለበትም የሚል እሳቤን የያዘ ነው። የማኅበራዊ-ኢኮኖሚ ልማት እድገቱ የሚያገልል ሳይሆን የሚያካትት መሆን አለበት ከሚል ጽኑ ዓላማ የተነሳ ነው።

ሦስተኛው ትልቁ ዓላማቸው ደግሞ ፖለቲካዊ ትብብርን ለማሳለጥ የሚያስችል ነው። የፖለቲካ ትብብርንና አንድነትን ማሳለጥ የሚፈለገው የት ላይ ቢባል ለምሳሌ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስብሰባ ላይና ድርጅቱ ባሉት የተለያዩ ተቋማት ላይ፣ በዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ኮንፍረንሶች ላይ፣ በዩኒስኮ፣ በሜትሪዮሎጂ እና በመሳሰሉ ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ የሶስተኛው ዓለም አዳጊ ሀገራትን በሚመለከት የተቀነባበረ ፖለቲካዊ አካሄድ እና ስልትን ለመከተል ነው።

እንደሚታወቀው እኛ ኢትዮጵያውያንም የአምስት ዓመት፤ የአስር ዓመት በሚል የራሳችን እቅድ አለን፤ ይህ የለውጡ መንግስት ከመጣ በኋላ ደግሞ አምስት ዓመት ሆኖታል። ይህ እቅዳችን ደግሞ ከተያዘው ዋና ዓላማ ጋር የተጣጣመ በመሆኑ በእኔ እይታ ኢትዮጵያም በዚህ ተስባለች ለማለት እችላለሁ።

በአፍሪካ ካሉ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ ትልቅ ኢኮኖሚ እና ትልቅ ሕዝብ ያላት ሀገር ናት። ይህ ብቻ አይደለም፤ ኢትዮጵያ ጠንካራ ወታደራዊ ኃይል ያላት ሀገር ናትና በዚህ በአዲሱ በዓለም ኃይል አሰላለፍ ውስጥ ኢትዮጵያ ልካተት ብላ ጥያቄ ብታቀርብ የሚደንቅ አይሆንም፤ በሌላ በኩል ደግሞ የወደፊቱ ሃያ እና ሰላሳ ዓመታት በእዝነ ልቦናችን ስናስተውል ደግሞ በአዲሱ ምዕተ ዓለም በሳል እና ተገቢ የሆነ አካሄድ ነው ብዬ አስባለሁ።

ስለዚህም የኢትዮጵያ ጥያቄ የተጠየቀው ወቅቱን ጠብቆ ነው። ምክንያቱም ከሌሎቹ ሀገራት በተለይም ከእነ ቻይና እና ሕንድን ከመሳሰሉ ሀገራት ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ ለማደግ እድሉን የሚሰጥ ተቋም ነው። እንዲሁም ከአፍሪካዊቷ ሀገር ከደቡብ አፍሪካ፣ ከብራዚል ብሎም ከሩሲያ ጋር እርስ በእርስ የንግድ ልውውጡን እንዲሁም የቴክኖሎጂ ሽግግሩንም በመለዋወጥ የሚካሄድ እድገት ነው፤ አንዱ ማዕድኑን ሌላው ደግሞ ዘይቱን ሌላው ደግሞ የግብርና ግብዓቱን የሚለዋወጥበትም ጭምር ተቋም ነው። በዚህም አብሮ ለማደግ እና አብሮ ለመስራት እድሉን የሚያመቻች ነው ።

ከዚህ በተጨማሪ ኅብረቱ የራሱን የፋይናንስ ተቋም ማቋቋም ችሏል። ያቋቋመው የፋይናንስ ተቋም ‹‹ኒው ዲቨሎፕመንት ባንክ (NDB) የሚባል ነው። ይህም ባንክ በአባል ሀገራቱ ውስጥ ያለውን ከፍተኛ የመሰረተ ልማት ብሎም የገንዘብ አቅርቦት ክፍተት ለመሙላት ያለመ ነው። በእነዚህ ተቋም ውስጥ ኢትዮጵያ በአባልነት ስትካተት ከዚህ የፋይናንስ ተቋም ማለትም ከአዲሱ ባንክ የሚገኘውን የአጭር እና ረጅም ጊዜ ብድሮች ያለወለድም ሆነ በእርዳታ መልክ ማግኘት ስለሚያስችላት ኢትዮጵያ ትጠቀምበታለች። ይህ ለአባል ሀገራቱም ሆነ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ጥቅም ስለሆነ ነው ኢትዮጵያ ለማመልከት የበቃችው።

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ተሳክቶላት ተቋሙን የምትቀላቀል ከሆነ እርስዎ ከጠቃቀሷቸው ዋና ዋና ዓላማዎች መካከል በተለይ የንግድ ልውውጡን በማሳለጡ በኩል ትኩረቷ የትኛው ዘርፍ ላይ ቢሆን ወሳኝ ነው ይላሉ?

ፕሮፌሰር ብሩክ፡- ኢትዮጵያ ሀብታም ሀገር ናት፤ ነገር ግን ይህ ሀብቷ በማህጸኗ ውስጥ ያለ እንደመሆኑ ገና አልወጣም ባይ ነኝ። በሌላ በኩል ለምሳሌ ጋዝ እና ዘይትን የተመለከተ ኢትዮጵያ በተመጣጣን ዋጋ ማግኘት ትችላለች። ይህንን ምርት ከእነ ብራዚልም ሆነ ከሌሎች ሀገራት ማግኘት ያስችላታል።

ንግድ እና ኢንቨስትመንትን በተመለከተ ደግሞ ቻይና በጣም ቀዳሚ ሀገር ሆናለች። እንደሚታወቀውም ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር በጣም ከፍተኛ የሆነ ቁርኝት ያላት እንደመሆኗ የቻይና ባለሀብቶች የበለጠ ወደ ኢትዮጵያ እየመጡ እንዲሰሩ በማድረግ በኩል ሚናው ከፍተኛ ነው። እንዲሁም የደቡብ አፍሪካም ባለሀብቶች የጋራ በሆነ እና ንግድ እና ኢንቨስትመንትን በሚያሳለጥ መልኩ እንዲሰሩ የሚያደርግ በመሆኑ የኢትዮጵያ ተጠቃሚነት ከፍ ያለ የሚሆን ነው።

አዲስ ዘመን፡- ይህ ሁሉ ተጠቃሚነት የሚኖር ከሆነ ኢትዮጵያ ኅብረቱን የመቀላቀሉ እድሏ ምን ያህል ነው ማለት ይቻላል?

ፕሮፌሰር ብሩክ፡- አስቀድሜ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት በርካታ ሀገራት ማለትም 40 ያህል ሀገራት ፍላጎት ያሳዩ ሲሆኑ፣ ብዙዎች ደግሞ የ‹‹እንቀላቀላችሁ›› ማመልከቻቸውን አስገብተዋል። ኢትዮጵያም አንዷ ስትሆን ከዚህ አኳያ ላመለከቱ ሀገራት ሁሉ አዎንታዊ ምላሽ ሊኖርም ላይኖርም ይችላል የሚለውን መያዙ ጥሩ ነው። ለዚህ ምክንያቴ ደግሞ የብሪክስ ተቋም የራሱ የሆኑ ዓላማ እና የራሱ የሆነ መተዳደሪያ ደንብ ያለው መሆኑ ነው።

ከዚህ የተነሳ ኅብረቱ ያመለከቱ ሀገራት ሁሉ ይግቡ ብሎ ውሳኔ የሚያሳልፍ አይመስለኝም። በዚህ ውስጥ ለመለየት በመስፈርትነት ይጠቀማሉ ብዬ የምለው ጠንካራ ኢኮኖሚ ያላቸውን ሀገራት ስለሆነ የኢኮኖሚ ደረጃ አንደኛው መለኪያቸው ነው ብዬ አምናለሁ። ሁለተኛ መለኪያቸው ደግሞ ውክልና የሚባለው ነው። እንደዚህም ሲባል አፍሪካውያን፣ ኢዥያውያንና ላቲን አሜሪካውያን ሁሉም እኩል መወከል አለባቸው።

 ስለዚህ እነዚህን ሁለት ነጥቦችን አይተው የሚወስኑ ይመስለኛል። ይህን ስል ከምን ተነስተህ ነው የሚባል ከሆነ ከእኛ ከኢትዮጵያ የበለጡ ጠንካራ ሀገራት ቡድኑን ለመቀላቀል አመልክተዋል።

ለምሳሌ ከአፍሪካ ሀገራት ብንወስድ ግብጽ ተቋሙን ለመቀላቀል ማመልከቻ አስገብታለች። ከዚህ የተነሳ የእኔ ግምት ከእኛ ይልቅ ግብጽ በፈጠነ ሁኔታ ተቋሙን ትቀላቀላለች ብዬ አስባለሁ። በተመሳሳይ አልጄሪያም ወደዚሁ ቡድን ለመቀላቀል ካመለከቱ ሀገራት መካከል አንዷ ናት፤ ስለዚህም በዚህ ዓመት አልጄሪያም የመግባት እድል አላት የሚል ግምት አለኝ። በተመሳሳይ ሞሮኮም ካመለከቱ ሀገራት ውስጥ የምትጠቀስ እንደመሆኗ ትገባለች ብዬ አስባለሁ።

በእርግጥ ናይጄሪያ በተቋሙ ከተሳቡ ሀገራት መካከል አንዷ ብትሆንም ፍላጎት አሳየች እንጂ ማመልከቻ አላስገባችም። ይሁንና በቀጣዩ ዓመት ከፍላጎት ሻገር ብላ ጥያቄዋን በማመልከቻ ብታቀርብ ትገባለች የሚል አተያይ አለኝ።

ብሪክስ በአሁኑ ወቅት ጥምረቱን ለመቀላቀል ጥያቄያቸውን ያመለከቱ ሀገራትን በተመለከተ ያለው ቀመር ‹‹ቱ ፕላስ ቱ ፕላስ ቱ›› የሚል ነው። ጥምረቱ በዚህ ቀመር መሰረት በጥያቄዎች ዙሪያ እየተወያየበት ነው። በቀመሩ መሰረት ጥያቄ ካቀረቡ ሀገራት መካከል ከየአህጉሩ መስፈርቱን የሚያሟሉ ሁለት ሁለት ሀገራት አዎንታዊ ምላሽ እንደሚሰጣቸው ይጠበቃል።

ይህም ማለት በ ‹‹ቱ ፕላስ ቱ ፕላስ ቱ›› ቀመር መሰረት ከአፍሪካ፣ ከላቲን አሜሪካ ሆነ ከኤዥያ ለአሁኑ ሁለት ሁለት ሀገር ይግቡ የሚል ነው፤ አሁን በተያዘው ቀመር መሰረት ስድስቱ ሀገራት የሚገቡ ከሆነ የኅብረቱ አባል ሀገራቱ ቁጥር ወደ 11 ከፍ የሚል ይሆናል። ምናልባትም ጥምረቱ ከዚህ ሰፋ አድርጎ የሚያስብ ከሆነ፤ ‹‹ስሪ ፕላስ ስሪ ፕላስ ስሪ›› የሚለውን ቀመር ሊከተል ይችላል። በዚህም አካሄዱ ከእያዳንዱ አህጉር ሦስት ሦስት ሀገራትን ስለሚወስድ የኅብረቱ አባል ሀገራት ቁጥር ወደ 14 ከፍ ይላል። ከዚህም የተነሳ ኢትዮጵያም የኅብረቱ አባል የመሆን እድሏ ሰፊ ይሆናል። እድሉ በጠበበ ቁጥር የመግባት ተስፋዋ የዚያን ያህል ይጠባል።

እንዲያም ሆኖ አስቀድሜ ለመጠቆም እንደሞከርኩት ዘንድሮ ካለው ሁኔታ አንጻር ሲታይ ኢትዮጵያ ጥምረቱን ትቀላቀላለች የሚል ግምት የለኝም። ምክንያቱ ደግሞ ከኢትዮጵያ በበለጠ ኢኮኖሚያቸው ላቅ ያሉ ሀገራት ልክ እንደ እርሷ ሁሉ ያመለከቱ በመሆኑ ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት እድሉን ታገኛለች ብዬ ለመናገር ይከብደኛል። እርግጥ ነው የብዙ ሕዝብ ባለቤትና በአፍሪካ ቀንድ በጂኦ ፖለቲካው ቁልፍ ቦታ ያላት ሀገር ብትሆንም ከእርሷ በኢኮኖሚያቸው የላቁ ሀገራት ደግሞ ስላሉ አሁን ትገባለች ብዬ አልደመድምም።

ከአፍሪካ ሀገራት እንኳ ያመለከቱትን ስናስተውል ግብጽ፣ አልጄሪያ እና ሞሮኮ ናቸው። ከላቲን አሜሪካ ደግሞ ሜክሲኮና አርጀንቲና ተጠቃሽ ናቸው። እድሉ ሰፋ ተደርጎ እንኳ ቢታሰብ ቬንዚዌላ ካመለከቱ ሀገራት መካከል ተጠቃሽ በመሆኗ ትገባለች። ከኤዥያ ደግሞ በርካታ ሀገራት አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ሳዑዲ አረቢያም ኢንዶኔዥያም ካመለከቱ ሀገራት መካከል የሚጠቀሱ ሲሆን፤ ኢንዶኔዥያ ከሳዑዲም የበለጠ ለመግባት ተስፋ ያላት ሀገር ናት። ይህ ግን የእኔ ትንበያ ነው።

በሌላ በኩል ባንግላዲሽ፣ ፓኪስታን እና የተባበሩት አረብ ኢምሬቶችም ለመግባት ፍላጎት ያላቸው ሀገራት ናቸው። ቱርክ ደግሞ ፍላጎት ነው ያሳየችው እንጂ ገና እንደእነርሱ ሁሉ አላመለከተችም። ከዚህ የተነሳ ዘንድሮ የሚገቡ ሀገራት አይደሉም። ኢራን ደግሞ መግባት ከሚፈልጉ ሀገራት መካከል አንዷ ናት።

ስለዚህ ጥምረቱ ከእየአህጉራቱ ቢበዛ ሦስት ሦስት ቢያንስ ደግሞ ሁለት ሁለት ሀገራትን መውሰድ ይፈልጋል። ያለበለዚያ ጥምረቱ በሩን በአንድ ጊዜ ከመስፈርቱ አልፎ በሰፊው ከከፈተ ትልቅ ድርጅት መሆኑ ጥያቄ ውስጥ ሊገባ ይችላል። የሀገራቱ መብዛት ጠቀሜታ እንዳለው ሁሉ ጉዳትንም ሊያመጣ ይችላል ባይ ነኝ። በእርግጥ ጥምረቱ የሚንቀሳቀሰው አስቦና መርህንም ተከትሎ በመሆኑ ያንን ያደርጋል የሚል ግምት የለኝም።

ስለዚህም ባስቀመጡት መርህ እና መስፈርት ተከትለው የሚሄዱ ከሆነ በ‹‹ቱ ፕላስ ቱ ፕላስ›› ቀመር ከላቲን አሜሪካ ሜክሲኮና አርጀንቲና ቀዳሚውን ያገኛሉ የሚል እምነት አለኝ። በ‹‹ስሪ ፕላስ ስሪ ፕላስ ስሪ›› ቀመር የሚከተሉ ከሆነ ደግሞ በሦስተኛ ደረጃ የሚጨምሩት ቬኒዜዌላን ነው የሚል እምነት አለኝ። ከአፍሪካም ደግሞ አስቀድሜ የጠቀስኳቸው ሀገራት እድሉን ያገኛሉ ብዬ አስባለሁ።

ውሳኔያቸውን በተመለከተ ሊሆን የሚችለው 40ውንም ሀገራት በቅን ልቦና ላሳዩት ጉልህ ትኩረታቸው እና ፍላጎታቸው አመስግነው በአሁኑ ዙር በተቀመጠው አካሄድ መሰረት የሚገቡ ሀገራትን ይፋ ያደርጋሉ የሚል አተያይ አለኝ።

የኢትዮጵያ የመግባት ጥያቄ ዘንድሮ ካልተሳካ በቀጣዩ እንደሚሳካ ማሰቡ መልካም ነው። ኢትዮጵያ በታሪኳም ሆነ በታላቅነቷ ስፍራዋ ከፍ ያለ ቢሆንም በኢኮኖሚ ደግሞ ያለባትን ክፍተት አስተካክላ በቀጣይ ጥምረቱን መቀላቀል የምትችል ስለመሆኗ ጥርጥር አይኖረውም።

አዲስ ዘመን፡- እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ በሕዝብ ብዛትም ስትታይ ደረጃዋ ቀላል የሚባል አይደለም፤ ይህ ደግሞ ገበያን ለመያዝ አንዱ ምክንያት ነውና ከጥምረቱ አባል ሀገራት የኢትዮጵያን የአባልነት ጥያቄ የሚደግፉ ሀገራት ይኖሩ ይሆን?

ፕሮፌሰር ብሩክ፡- የሕዝብ ብዛት በራሱ ብቻውን ጥምረቱን ለመቀላቀል አያስችልም። በእርግጥ የሕዝብ ብዛት ከኢኮኖሚ እድገት ጋር ይሄዳል። ይሁንና በመጀመሪያ ኢኮኖሚው ማደግ መቻል አለበት። ለምሳሌ እኛ እና ባንግላዲሽ አንወዳደርም። ምንም እንኳ ባንግላዲሾች ከኤዥያ አህጉር ቢሆኑም ጥምረቱን ለመቀላቀል ሰፊ እድል ያላቸው ናቸው። በተመሳሳይ ኢንዶኔዥያም ማሊዤያም ሰፊ እድል ያላቸው ሀገራት ናቸው። ስለዚህ ኢትዮጵያም የሚታየው በዚህ ዓይን ነው።

በአሁኑ ወቅት ኤንዶኔዥያን ስንወስድ በሕዝብ ብዛቷ ከዓለም የአራተኛን ደረጃ የያዘች ናት። ይሁንና ኤንዶኔዥያ የምትመረጠው ባላት የሕዝብ ብዛት ብቻ አይደለም፤ ኢኮኖሚያዋም የዚያኑ ያህል ያደገ በመሆኑ ነው። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ደግሞ እያደገ ያለ ቢሆንም የሌሎቹን ስንመለከት ከእኛ ከፍ ያለ ነው። ስለዚህ ምንም እንኳ የሕዝብ ብዛት ጥምረቱን ለመቀላቀል አንዱ መስፈርት ቢሆንም ወሳኙ ግን እሱ ብቻ አይደለምና ከኢኮኖሚውም ጋር ተያይዞ መኬድ ያለበት ያህል ርቀት መጓዝን የሚጠይቅ ነው።

ከጥምረቱ ሀገራት ውስጥ ኢትዮጵያ እንድትገባ የሚደግፉ ሀገራት አሉ ወይ ላልሽው በደንብ አሉ የሚል ምላሽ ነው ያለኝ። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ታዋቂ ሀገር ናት። ከጥምረቱ ሀገራት መካከል አፍሪካዊቷ ደብቡ አፍሪካ የእኛን መግባት የምትፈልግ ሀገር ናት። ከሩሲያም ጋር በጣም ጠንካራ ግንኙነት ስላለን የእኛን መግባት ከሚደግፉት መካከል ናቸው። በተመሳሳይ ቻይናም እንዲሁ ልትደግፈን የምትችል ሀገር ናት። በሁለተኛ ደረጃ ከማያቸው መካከል ደግሞ ብራዚልም ትደግፈናለች ብዬ አስባለሁ። የብራዚልን በሁለተኛ ደረጃ የማስቀመጤ ምስጢር ከእኛ ይልቅ እነ ሜክሲኮ፣ አርጀንቲና እና ቬኔዚዌላን የመሳሰሉ ሀገራት እንዲገቡ የምትመርጥ ስለሚመስለኝ ነው።

በእርግጥ ኢትዮጵያ ከሁሉም ጋር ጥሩ የሚባል ግንኙነት ያላት ሀገር ነች። ነገር ግን ሁሉም በየመስኩ የራሱ የሆነ ወዳጅ አለውና ቀዳሚው መስፈርት የሚሆነው ጥምረቱ ያስቀመጠው መንገድ በመሆኑ ከዚህ አንግል የሚታይ ይመስለኛል።

አዲሱን የዓለም ኃይል አሰላለፍ ሚዛን በአጭር ጊዜ ምን ያህል ሊለውጥ ይችላል በሚል በጣም ግዙፍ የሆኑትን ሀገራት ወደኅብረቱ ሊቀላቅሏቸው ይችላሉ። ለምሳሌ እንደ ኢንዶኔዥያ፣ ሜክሲኮ እንዲሁም አርጀንቲናን ብሎም ግብጽን ሊወስዱ ይችላሉ የሚል እምነት አለኝ። ይህ ጥምረቱን የመቀላቀሉ ጉዳይ ደግሞ በተቀመጠው መስፈርት ሊሔድ ስለሚችል እኛም ኢኮኖሚያችንን ስናጎለብት በተራችን ጥምረቱን በአጭር ጊዜ ውስጥ እንቀላቀላለን የሚል እምነት አለኝ። እንዲያም ሆኖ በአሁኑ ዙር የመግባታችን ሁኔታ ጥምረቱ በሩን በርግዶ የሚቀበል ከሆነ ብቻ ነው ሊሳካልን የሚችለው።

በእርግጥ ጥምረቱ መስፈርትን የሚያስቀምጠው በሩን ለመከርቸም አስቦ አይደለም። ዓላማው አንድ ተመራጭ የሆነ የኢኮኖሚክ ፖለቲካ ኃይል እና ሥርዓት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያስፈልግ መሆኑን ስለተስማማበት ነው። ስለዚህ እንኳን እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታላላቅ ሀገራት ቀርተው እንደ ሁንድራስ ያሉ አነስተኛ ሀገራት እንኳ ጥምረቱን ለመቀላቀል ፍላጎት አሳይተዋል።

በአፍሪካም ያሉ በብዙ መስፈርት ከእኛ በታች የሆኑ ትንንሽ ሀገራት የመግባት ፍላጎት አሳይተዋል። ነገር ግን መጥነው መሄድ ተመራጭ በመሆኑ ነው። እስካሁኑ ጥምረቱ ከተመሰረተ እስከ 14 ዓመቱ ድረስ ያሉት አምስት ሀገራት ብቻ ናቸው። በአሁኑ ስብሰባቸው ወደ ዘጠኝ አሊያም ከፍ ካለ ወደ 11 ሀገራት ሊያድግ ይችላል። ከዚያ ደግሞ የዛሬ ዓመት 20 እንዲሁም 25 እያለ ሲያድግና በአግባቡ እየታሰበበት ሲሄድ መዝረክረክን ስለሚያስቀር እየመጠኑ መሄዱ ተመራጭ ነው። ሁሉም ነገር የራሱ አካሄድ ስላለው ነው እንጂ ጥምረቱ ‹‹አትምጡብን›› አሊያ ‹‹አትግቡብን›› የሚል መርህን አይከተልም።

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ በዚህ ዙር እድሉን ባታገኝ በቀጣይ በምን በምን ላይ ዝግጅት ማድረግ አለባት ይላሉ?

ፕሮፌሰር ብሩክ፡- በእርግጥ በአሁኑ ዙር ጥምረቱን ለመቀላቀል የሚያስችላትን እድል የማታገኝ ከሆነ በቀጣዩ አንድ እና ሁለት ዓመት ውስጥ እድሉን ታገኛለች የሚል እምነት አለኝ። በእርግጥ እነርሱ የሚጠብቁት ነገር አለ። ለምሳሌ አንድ ከፍ ያለ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ ደግሞ ያንን ፖሊሲ እየቀረጸች ነው። ተዓማኒነት ያለው እና የተረጋጋ ኢኮኖሚ እንዲኖረን ይፈልጋሉ። በተመሳሳይ ደግሞ ጸጥታ እና ደህንነትም የሚፈለግ ጉዳይ ነው።

ወደ ጥምረቱ ሲገባ በኢኮኖሚውም ሆነ በፖለቲካውም ጉልህ የሆነ አስተዋጽኦ ያለውን ሀገር ይፈልጋሉ። ምክንያቱም ጥምረቱ ዓላማ ያለው ድርጅት ነው። ስለሆነም መታየት ያለበት በዛ መልክ ነው። በዚህ አይነት አካሄድ ስለሆነ የእኛ መግባት ምናልባት የአንድ እና የሁለት ዓመት ጉዳይ መሆኑ እንጂ የሚቀር ነገር ባለመሆኑ ብዙም የሚያሳስበን አይሆንም።

እኛ ተፈላጊነት ያለን ሀገር ነን። በአፍሪካም ደረጃ ጉልህ አስተዋጽኦ ያለን ነን። ኢኮኖሚያችንም ከዓመት ዓመት እድገት እያሳየ ነው። የዛሬ ሁለት ዓመት አንጎላን፤ የዛሬ ዓመት ኬንያን፣ በቀጣዩ አንድ ዓመት ተኩል ደግሞ ሞሮኮን በኢኮኖሚ ልንቀድም እንችላን። ባልተረጋጋ ሀገራዊ እውነታ ውስጥ እያስመዘገብን ያለነው የኢኮኖሚ እድገት ለቀጣይ የኢኮኖሚ እድታችን ተስፋ ሰጪ ነው።

በቀጣዮቹ ዓመታት ግብጽ፣ ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ ከፍ ያለ የኢኮኖሚ ባለቤት ሆነው ይቀጥላሉ የሚል እምነት አለኝ። በተለይ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በቀጣዩ አንድ እና ሁለት ዓመታት ውስጥ በሚያሳየው ማንሰራራት ጠንካራውን የብሪክስ ጥምረት ለመቀላቀል እድል ይሰጣል።

በኢኮኖሚ ፖሊሲውና በፊሲካል ፖሊሲው ላይ በርትቶ እና ጠንክሮ መስራት ይጠበቃል። ምክንያቱም በጥምረቱ አማካይነት የተቋቋመ ባንክ አለ፤ እዚህ ባንክ ውስጥ እንደ አባልነት ስንገባ ለዛ የሚሆን ድርሻ ማበርከት የምንችል እና ሕጉን የምናከብር ሀገር መሆን ይጠበቅብናል።

ዓለማችን አዲስ ህልውና ውስጥ ነች። ብሪክስ በኢኮኖሚውም ሆነ በፖለቲካው የጂ7 ተጽዕኖ የሚመክት አማራጭ ድምጽ የሆነ ጥምረት ነው። አዲስ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ እና የማህበራዊ ኅብረት ተፈጥሯል። አሁን ያ ኅብረት የራሱን በር ከፍቶ ወደማስፋቱ እየሄደ ነው። ይህንን ጥምረት ኢትዮጵያ ሀገሬ መቀላቀል እንድትችል መልካም እድልን እመኝላታለሁ። ኢትዮጵያም ጥምረቱንም ሆነ የዓለምን ሕዝብ የሚመጥን አስተዋጽኦ በሰላሙም ሆነ በኢኮኖሚውም የምታበረክት ይሆናል።

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ።

ፕሮፌሰር ብሩክ፡- እኔም አመሰግናለሁ።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 18/2015

Recommended For You