ሁለተኛው ምዕራፍ የመካከለኛ ጊዜ ዕቅድ የኢኮኖሚ ዕድገቱን ለማስቀጠል ተጨባጭ አቅም ነው!

 የለውጡ ኃይል በምርጫ ወደ ሥልጣን መምጣቱን ተከትሎ ለሀገሪቱ ብልጽግና መሰረት ይጥላል ያለውን የ10 ዓመት ሀገራዊ የልማት ዕቅድ ወደ ስራ ማስገባቱ ይታወሳል። ባለፉት አምስት ዓመታትም ይህንን እቅድ ተግባራዊ በማድረግ ውጤታማ አፈጻጻም እያስመዘገበ ስለመሆኑ በየዓመቱ የሚታዩ የኢኮኖሚ ዕድገቶች ተጨባጭ ማሳያ ናቸው።

እቅዱ በሀገራዊ አለመረጋጋቶች ፤ በጦርነትና በግጭቶች በብዙ ተግዳሮት ውስጥ ያለውን የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በመታደግ፤ ሀገሪቱን አጋጥሟት በነበረውና አሁንም እየተፈታተናት ባለው የኑሮ ውድነት ዜጎች ለከፋ አደጋ እንዳይጋለጡ ትልቅ አቅም ሆኗል። በግጭቶችና በጦርነት ምክንያት ሊፈጠሩ የሚችሉ ሀገራዊ ምስቅልቅሎችን መሸከም አስችሏል።

በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የተቃኘው ይህ የ10 ዓመት የልማት እቅድ፤ ዓላማ አድርጎ የተነሳው የግሉን ዘርፍ ማነቃቃት፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራቶችን ማሻሻል እንዲሁም የብዝሃ ዘርፍ ምርታማነትን ማሳደግና ማስቀጠል እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይህንንን እውን በማድረግ በአሁን ወቅት ሀገሪቱ በዓለም ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ ሀገራት አንዷ እንድትሆን አድርጓታል፡፡

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለፉት ዓመታት በአማካይ 6.1 በመቶ ዕድገት አስመዝግቧል። ለውጡ ሲጀመር ከአጠቃላይ የሀገሪቱ ገቢ 59 በመቶ በላይ የነበረውን ከፍተኛ የዕዳ ጫና ወደ 38 በመቶ ዝቅ ብሏል፡፡ ይህንን የእዳ ጫና በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት ከ30 በታች ለማድረስ እየተሠራ ነው፡፡ ከዚህም ጎን ለጎን ኢትዮጵያ ከለውጡ በፊት የነበራትን አጠቃላይ ሀገራዊ የምርት መጠን ከ2 ነጥብ 2 ትሪሊዮን ብር ባለፈው ዓመት ወደ 6 ነጥብ 2 ትሪሊዮን ማድረስ ተችሏል፡፡

በ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት በሀገር አቀፍ ደረጃ የ 7 ነጥብ 5 የኢኮኖሚ እድገት ይመዘገባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከዚህ ውስጥ ከግብርና 6 ነጥብ 3 በመቶ ፤ የኢንዱስትሪው ዘርፍ 8 ነጥብ 2 በመቶ፤ ከአገልግሎት ዘርፍ ደግሞ 7 ነጥብ 5 በመቶ ዕድገት እንደሚመዘገብ የተተነበየ መሆኑ ይታወሳል።

ሀገራዊ የውጭ ምንዛሪ ገቢያችን ከ50 ፐርሰንት በላይ ጨምሯል፤ የነፍስ ወከፍ ገቢም ቢሆን ቀደም ሲል ከነበረበት ከአንድ ሺህ በታች ወደ ከአንድ ሺህ በላይ አድጓል። በሀገሪቱ የሚታየውንም የገቢና የወጪ ከፍተት /ደፊሲት/ ለማጥበብ በተሰራው ሥራም የገቢያችንን ዕድገት 26 በመቶ፣ የወጪያችን 13 በመቶ ማድረስ ተችሏል።

ይህ የዕቅድ አፈጻጸም ሀገሪቱ ላለፉት አምስት ዓመታት ካሳለፈቻቸው አስቸጋሪ ሁኔታዎች አንጻር ሲሰላ፤ ሀገሪቱ ድህነትን ታሪክ ለማድረግ የጀመረችው ሀገራዊ ጥረት ተስፋ ሰጭ መሆኑን የሚያመላክት ነው፤ በተለይም ሀገራዊ ሰላሙን ዘላቂ አድርጎ ማስቀጠል ከተቻለ ጅማሮው ለበለጠ ስኬት አቅም እንደሚሆን ይታመናል።

በተለይም መንግስት ሙሉ ትኩረቱን ወደ ልማት የሚያዞርበትን አማራጭ ሕዝቡ በራሱ መፍጠር ከቻለ፤ እያንዳንዱ ዜጋ ከግጭትና ከጦርነት እንደ ሀገር ልናተርፍ የምንችለው አንዳች ነገር እንደማይኖር በመረዳት ለሀገራዊ ሰላሙ ዘብ መቆም ከቻለ፤ ተስፋ ያደረግነው ድህነትን ተሻግረን ለራሳችን ሆነ ለመጪው ትውልዶች የተሻለች ሀገር መፍጠር የሚያስችል የመሰረት ድንጋይ መትከል በምንችልበት የታሪክ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን።

በቀጣይ ከ2016 እስከ 2018 ዓ.ም በሚተገበረው ሁለተኛው ምዕራፍ የመካከለኛ ጊዜ ዕቅድ ለ9 ሚሊዮን ዜጎች አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር መታቀዱ በዕቅድ ዘመኑ በመጀመሪያው ምዕራፍ ዝቅተኛ አፈጻጸም የነበራቸው ዘርፎች የማካካሻ ዕቅድ እንዲያቅዱ፣ የተሻለ አፈጻጸም የነበራቸው ደግሞ ተጨማሪ ግብ እንዲኖራቸው ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ስኬቱን ለማስቀጠል እንደሚያስችል ይታመናል።

የቱሪዝም፣ ማዕድንና አምራች ዘርፎች የማካካሻ ዕቅድ እንዲኖራቸው፤ በዚህም የወርቅ የገበያ ድርሻ ከአራት ቶን ወደ 13 ቶን፣ የሀገር ውስጥ ምርቶችን የገበያ ድርሻ ወደ 46 በመቶ ለማሳደግ መታቀዱ፤ በጤና፣ በትምህርት፣ በውሃ፣ በኤሌክትሪክ አገልግሎት የዜጎችን ተጠቃሚነት ማሳደግ እንዲሁም የዋጋ ንረትን መቆጣጠር የቀጣይ ሦስት ዓመታት ትኩረቶች ሆነው መቀመጣቸው አሁነኛ ሀገራዊ ችግሮችን ተሻግሮ ለሀገርና ለሕዝብ የተሻሉ ነገዎችን ለመፍጠር የሚያስችል ተጨባጭ አቅም ነው !

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 18/2015

Recommended For You