አዕምሯችን የጥላቻ ንግግርና የሐሠት መረጃ ሸቀጥ ማራገፊያ እንዲሆን አንፍቀድ

አሁን አሁን መቀያየሙ፣ መገፋፋቱና መራራቁ እየበረታ የመጣ ይመስላል። አለመተማመኑም የዚያኑ ያህል ላቅ ብሎ ይስተዋላል። ጠዋት አካባቢ አግኝታችሁት ሰላምታ የተለዋወጣችሁት ጎረቤታችሁ አሊያም የስራ ባልደረባችሁ ረፋድ ላይ ከለበሰው አልባስ ውጪ ባህሪው ሲቀያየር ታስተውላላችሁ።

አንዳንዴም እርሱ ከማኅበራዊ ትስስር ገጽ የቀራረማቸው የጥላቻ ንግግሮች እና ሐሰተኛ መረጃዎች ውስጡን ርብሽብሽ አድርጎት ሲንቆራጠጥ ታዩታላችሁ። ያነበባቸው አሊያም የተመለከታቸው ትክክለኛ መረጃ ሳይሆኑ ‹‹ማረጃ›› እንደሆኑ እንኳ ቆም ብሎ ማጤንን ስለሚዘነጋ በቀን ውስጥ አስር አይነት ማንነትን ሲላበስ ታስተውሉታላችሁ። እናንተም ግራ ግብት ቢላችሁ ‹‹እውን ይህ ሰው ማለዳ ላይ አግኝቼ ሰላም ያልኩት ጎረቤቴ አሊያም የስራ ባልደረባዬ ነውን›› ብላችሁ ራሳችሁን ትጠይቁታላችሁ።

የጥላቻ ንግግርንና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣ አዋጅ መግቢያ ላይ ‹‹የጥላቻ ንግግር ማለት በአንድ ሰው ወይም በተወሰነ ቡድን ማንነት ላይ ያነጣጠረ፣ ብሔርን ብሔረሰብንና ሕዝብን፣ ሃይማኖትን፣ ዘርን፣ ጾታን ወይንም አካል ጉዳተኝነትን መሰረት በማድረግ ሆን ተብሎ ጥላቻን፣ መድልዎን ወይም ጥቃትን የሚያነሳሳ ንግግር ነው›› የሚል ብያኔ አስቀምጧል።

በተለያየ ማንነት የተለያየ የጥላቻ ንግግርን ሲፈበርኩ የሚውሉ አካላት ደግሞ በፈበረኩት መርዛማ መልዕክት የመጣው ውጤት ምንም ይሁን ምን እነርሱን ግድ አይሰጣቸውም። አንዱ ግለሰብ አሊያም ቡድን በተነዛው የጥላቻ ንግግር መገፋፋትና ቂም መያያዝ ቢመጣ ባይመጣ አንዳች አያሳስባቸውም።

በጥላቻ ንግግር ምክንያት ወገን በወገኑ ላይ እጁን አንስቷል። በርካቶች ራሳቸውን ለአደጋ አጋልጠዋል። ጥቂት የማይባሉትም አካላቸውን አጎድለዋል። ብዙዎችም ቅስማቸው ተሰብሯል። እርስ በእርስ መከባበሩ ጠፍቶ በክፉ ተመኛኝተዋል። ከዚህ ባለፈ የብዙዎችን የውስጥ ቁስል ቤቱ ይቆጥረዋል።

የጥላቻ ንግግርንና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣ አዋጅ አንቀጽ 7 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ ‹‹የጥላቻ ንግግር ያደረገ ሰው ለሁለት ዓመት እስራት ወይም የመቶ ሺ ብር ቅጣት ይቀጣል። በጥላቻ ንግግር ምክንያት በግለሰቡ ላይ ወይም በቡድኑ ላይ ጥቃት ከተፈጸመ ከአንድ እስከ አምስት ዓመት የሚደርስ ቀላል እስራት ይጠብቀዋል›› ይላል።

በእርግጥ ሰው የጥላቻ ንግግርን ከመናገር መቆጠብ ያለበት የተደነገገውን ቅጣት ስለሚፈራ ብቻ መሆን የለበትም። ተገቢ ያልሆነ ንግግር ተናግሮ ወገኑን ወዳልተገባ ድርጊት መገፋፋት እና አንዱን በአንዱ ላይ እንዲነሳሳ ማድረግ ጨዋነት የጎደለው አካሄድ በመሆኑ አዕምሮውን ሊገዛ ይገባል።

ልክ የጥላቻ ንግግርን ያህል የሐሠት መረጃን ማሰራጨትም አደጋው የከፋ ነው፤ በግለሰብም ሆነ በቡድን ደረጃ ከሚሰማው ሐሠተኛ መረጃ የተነሳ ወደአስከፊ ውሳኔዎች ሊያንደረድሩ የማይችሉበት ምንም ምክንያት አይኖርም። እንደ አገርም የሚደቅነው ስጋት በቀላሉ የሚታለፍ አይደለም።

የጥላቻ ንግግርንና የሐሠተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣ አዋጅ ላይ ለሐሠተኛ መረጃ ብያኔ ሲሰጥ ‹‹መረጃው ሐሠት የሆነና የመረጃውን ሐሠተኝነት በሚያውቅ ወይም መረጃው የሚያሰራጨው ሰው ካለበት አጠቃላይ ሁኔታ አንጻር የመረጃውን እውነተኝነት ለማጣራት በቂ ጥረት ሳያደርግ የሚያሰራጭ ኹከት ወይም ግጭት የማስነሳት ወይም ጥቃት እንዲደርስ የማድረግ እድሉ ከፍ ያለ ንግግር ነው›› ይላል።

የሐሠት መረጃን ሆን ብለው በሚያሰራጩ አካላት የተነሳ የብዙዎች ኑሮ ተናግቷል። አንዳንዱን ሰው ፊት ለፊት ስታገኙት ቅልስልስና ጨዋ መስሎ ይታያል፤ በማኅበራዊ ትስስር ገጽ ላይ ደግሞ ሌላ ገጸ ባህሪን ተላብሶ የሐሠት መረጃን በማሰራጨት ሲተውን ይስተዋላል።

ስሙም ፎቶውም በአካል ከምታውቁት ጋር ስለማይገጥም እሱ ነው ለማለት ትቸገራላችሁ። ራሱን ሌላ ሰው አስመስሎ በሚያፈልቃቸው የሐሠት መረጃዎች አንዱን በሌላው ላይ ጥርሱን እንዲነክስ ይገፋፋል። የግለሰብ ብሎም የቡድን ሕይወት ምስቅልቅሉ መውጣት በአገር ደረጃ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ደግሞ ተንቆ የሚተው አይሆንምና ሃይ ባይን ይሻል።

በእርግጥ በዚህም ጉዳይ የጥላቻ ንግግርንና የሐሠተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣ አዋጅ ላይ የተደነገገ ቅጣት አለ። ይኸውም ‹‹የጥላቻ ወይም የሐሠተኛ መረጃ ስርጭት ወንጀሉ የተፈጸመው ከአምስት ሺ በላይ ተከታይ ባለው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ ከሆነ ወይም በብሮድካስት አገልግሎት ወይም በየጊዜው በሚወጣ የሕትመት ውጤት ከሆነ ቅጣቱ እስከ ሶስት ዓመት ይሆናል›› ይላል።

ከቅጣቱም በፊት ሆነ ከእውነት የራቀ መረጃ በማሰራጨታችን ምክንያት በአዕምሯችን ላይ ከሚፈጠርብን ውጥረት በፊት ለአፍታ ያህል ረጋ ብሎ ማሰቡ ውጤቱ ያማረ ነው። በቀን ውስጥ ሶስትና አራት አይነት ሰው አንሁን። በአደባባይ ሌላ፤ በጓዳ ደግሞ ሌላ ሰው አንሁን። የጥላቻ ንግግሩን ወይም ሐሠተኛውን መረጃ ተቀብለን ከማሰራጨት እንቆጠብ።

ከዚህ ሰፈር እንውጣ፤ አዕምሯችን የጥላቻ ንግግርና የሐሠት መረጃ ሸቀጥ ማራገፊያ እንዲሆን አንፍቀድለት። ተቀያያሪ ማንነታችንን ትተን ከፍ አድርገንም ለማሰብ እንጣር። አንዳችን ሌላኛችንን የምናይበት መነጽር የተቃረነ አይሁንብን።

ትርፋማ መሆን የሚያስችለንን መስክ ትተን በጠባቧ ሜዳ አንራኮት። ሰው እንደ ሰው፣ ቡድንም እንደ ቡድን የየራሱ የሆኑ ችግር ያጋጥመዋል። በዚያን ጊዜ ታድያ ለጋራ ችግራችን የጋራ መፍትሔ ለማበጀት እንትጋ።

ለሰላም ያለንንን አቋም ሁሉ አሟጠን እንጠቀም። በጥላቻ ከመተብተብ ይልቅ በሚያግባቡን የጋራ ጉዳዮቻችን ላይ እናተኩር። በሕዝብ መካከል የመወያየት፣ የመቀራረብና የአብሮነትን መንፈስ ለመፍጠር እንጣር። ያደፍነውን ለማንጻት፤ የተዋረደውን በክብር ለማከም የየራሳችንን እርምጃ እንውሰድ።

በተለይ አገራችን ኢትዮጵያ እንዳትረጋጋ ሁሌ የቤት ስራ ከሚሰጡን አካላት መዳፍ ለመላቀቅ እንሞክር። መታረም ያለበትን በአግባቡና በግዜ እንዲታረም ብናደርግ ኢትዮጵያ እንኳን ለዜጎቿ ለሌሎችም የሚተርፍ ሀብት ባለቤት ናትና ክምንም በላይ ለሰላም ቅድሚያ እንስጥ።

እንዲያ ካልሆነ ተለዋዋጭ በሆነ ማንነት ሰላማዊ ኑሮ መኖር አይቻልም። ሰፈር አካባቢ ስንሆን ሌላ ሰው መምሰል፤ ተንቀሳቃሽ ስልካችንን ስንይዝ በማኅራዊ ትስስር ገጽ ላይ ደግሞ የሚያጣላ ሐሳብ በመፍጠርም ሆነ የሐሰት መረጃ በምንሰጠው አስተያየት በማበረታታት ሰላምን ማግኘት በፍጹም አንችልም። የራሱን አግዝፎ የሌላውን አኮስሶ ከመግለጽ አባዜ እንላቀቅ። እኔነትን ትተን ስለእኛ እንድከም። የእኔ ጎሳ፣ የእኔ ብሔር፣ የእኔ ክልል፣ ዞን እያልን በቀለበት ውስጥ ስንመላለስ ዘመናችን አይጠናቀቅ።

ልዩነታችን ውበታችን ነው፤ እንከባከበው። ችግሮች ሲያጋጥሙን በግልጽ መነጋገርን ባህል እናድርግ፤ ለከንቱ ዓላማ አንዱን ከሌላው ጋር ለማጣላት አንሯሯጥ። ድብቅ ዓላማና ተልዕኮ አንግበን መንቀሳቀስ ለራስ፣ ለአገር ሆነ ‹‹ለእኔ›› ለምንለው በጭራሽ አይጠቅምምና በጋራ ጥቅማችን ላይ እናተኩር እላለሁ።

ወጋሶ

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 18/2015

Recommended For You