መቋጫ ያላገኘው የኒጀር ጉዳይ፤

 በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን የተቆጣጠረው የኒጀር ወታደራዊ ቡድን የሩሲያው ዋግነር ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን እንዲረዳው መጠየቁ ፤ የኒጀር ጉዳይ ቀጣናውንና አኅጉሩን ብቻ ሳይሆን ኃያላን ሀገራትን ስቦ ወደ ጦርነት እንዳያስገባ እና እንደ ዩክሬን ኒጀርም የውክልና ጦርነት አዲሷ ግንባር እንዳትሆን ስጋት ፈጥሯል። ይህ በእንዲህ እያለ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ወይም ኤኮዋስ ወደ ኒጀር ወታደሮቻቸውን ለማዝመት የሚያስችላቸውን እቅድ አጠናቀቅን ካሉ ሳምንታት ቢያልፉም የተወሰደ እርምጃ የለም ። የሀገራቱ የጦር አመራሮች በናይጀሪያ አቡጃ ባደረጉት ምክክር ነው ከስምምነት ላይ የደረሱት። ኤኮዋስ ፕሬዚዳንት መሐመድ ባዙም እንዲለቀቁ ያስቀመጠው ቀነ ገደብ ባለፈው እሁድ ሀምሌ 30 ቀን 2015 ዓ.ም ተጠናቋል ይለናል የአሜሪካው ዜና አገልግሎት አሶሼቲድ ፕሬስ AP።

በዚህ ምክክር ላይ መፈንቅለ መንግስት አድራጊ ጁንታዎች እነ ማሊ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ጊኒ እና ኒጀር የመከላከያ ሚኒስትሮች አልተሳተፉም ። በአቡጃ በተደረገው የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ አባል ሀገራት የጦር አመራሮች ውይይት በቀጣይ በኒጀር ስለሚካሄድ ዘመቻ ስምምነት ላይ ተደርሷል ይለናል። የኤኮዋስ የፖለቲካ፣ የሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ኮሚሽነር አብደል ፋቱ ሙሳህ፥ በኒጀር ለሚደረገው ዘመቻ የሚያስፈልገው ወታደራዊ ኃይል እና ግብአት እንዲሁም ጊዜው ላይ ስምምነት ላይ መደረሱን ይናገራሉ። ወታደራዊ አመራሮቹ የተስማሙበት የወታደራዊ ጣልቃ ገብነት እቅድ ተግባራዊ የሚሆነው የሀገራቱ መሪዎች ፊርማቸውን ሲያኖሩበት ነው። ኮሚሽነሩ የኤኮዋስ ጥምር ኃይል መቼ ወደ ኒያሚ እንደሚዘልቅ ባይጠቅሱም የመንግስት ግልበጣውን ያደረገው ጁንታ ስልጣኑን ለፕሬዚዳንት ባዙም እንዲመልስ የተቀመጠው ጊዜ ገደብ ከተጠናቀቀ ከሳምንት ባላይ ሆነው።

በጀነራል አብዱርሃማን ቺያኒ የሚመራው ወታደራዊ ኃይል ግን የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ ከመግባት ሊቆጠቡ ይገባል ሲል አስጠንቅቋል። በኒጀር ላይ ለሚታወጅ ወረራ ፈጣን አፀፋዊ እርምጃ እንወስዳለን ያሉት የወታደራዊ ኃይሉ ቃል አቀባይ ኮሎኔል አማዱ አብድራማን ፤ ወታደር በሚልኩት የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ዜጎች ላይ ሳይቀር እርምጃ እንደሚወሰድም ዝተዋል። በማሊ እና ቡርኪናፋሶ የተደረጉ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራዎችን ማክሸፍ ያልቻለው ኤኮዋስ በኒጀር ይሳካለት ይሆን የሚለው ጥያቄ እያነጋገረ ነው። የኒጀር አጎራባች አገራት ቡርኪናፋሶ እና ማሊ በኒጀር የተከሰተውን መፈንቅለ መንግሥት ለማኮላሸት የሚደረግ ጣልቃ ገብነትን እጃችንን አጣጥፈን አንመለከትም ሲሉ አስጠንቅቀዋል። በኒጀር ውስጥ ሊደረግ የሚችል ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት በአጎራባች አገራቱ ላይ ጦርነት ማወጅ ነው ሲሉም የጋራ መግለጫ አውጥተዋል። የጊኒውን መፈንቅለ መንግሥት ያቀነባበረው ወታደራዊ ጁንታም ነገ በእኔ በሚል ስጋት የእነ ማሊን ጥሪ ተቀላቅሏል።

ኤኮዋስ በመፈንቅለ መንግሥት ከስልጣን የተወገዱትን የኒጀር ተመራጩን ፕሬዚዳንት መሐመድ ባዙምን ወደ ስልጣን ለመመለስ ኃይል እንደሚጠቀም መዛቱንም ተከትሎ ነው የአገራቱ መግለጫ የተሰማው ይለናል ቢቢሲ። ቡርኪናፋሶ እና ማሊ ኤኮዋስ አደርገዋለሁ ካለው ኃይል መጠቀምን ዝም ብለው እንደማያዩና ጎረቤታቸውንም ደግፈው እንደሚከላከሉ ተናግረዋል። በተጨማሪም ከኤኮዋስ አባልነታችን እንወጣለን ሲሉም አስጠንቅቀዋል። የአገሪቱ ፕሬዚዳንት መሐመድ ባዙም በክቡር ዘብ መሪያቸው ጄነራል አብዱራህማኔ ቺያኒ ወይም በተለምዶ ኦማር ቺያኒ በተመራ መፈንቅለ መንግሥት ከስልጣናቸው ተነስተዋል። የቀድሞው የፕሬዚዳንቱ ክቡር ዘብ መሪ የኒጀር አዲሱ መሪ መሆናቸውን አውጀዋል።

የቀድሞው ፕሬዚዳንት መሐመድ ባዙም ኒጀር ከፈረንሳይ ቅኝ ግዛት በጎርጎሮሳውያኑ 1960 ዓ.ም ነጻ ከወጣች በኋላ የአገሪቷን መሪ እንዲተኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመረጡ መሪ ናቸው። መፈንቅለ መንግሥቱን የአፍሪካ ህብረት፣ ኤኮዋስ፣ የአውሮፓ ህብረት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ እያወገዙት ነው። በተቃራኒው ቡርኪናፋሶና ማሊ በተደጋጋሚ ከኒጀር ጎን መቆማቸውን እየገለጹ ሲሆን ከምዕራቡ ዓለም ጋር ያላቸውን ግንኙነት አቋርጠው ከሩሲያ ጋር እልል በቅምጤ እያሉ ስለሆነ ኒጀርም የእነሱን መንገድ ትከተላለች እየተባለ ነው። እንደ ኒጀር በፈረንሳይ ቅኝ ግዛት የማቀቁት ቡርኪናፋሶ እና ማሊ በሳህል ውስጥ ያሉ ጽንፈኞችን እየተዋጉ መቆየታቸው ሌላው የትብብራቸው መነሻ ነው ይለናል ቢቢሲ።

በቡርኪናፋሶ እና ማሊ ተመሳሳይ መፈንቅለ መንግሥት መደረጉ የሚታወስ ሲሆን በኒጀር መሰለሱ የሳህልን ቀጠና የበለጠ አደጋ ውስጥ ከቶታል። የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የኒጀር ፕሬዚዳንት መሐመድ ባዙም እና ቤተሰቦቻቸውን በፍጥነት እንዲለቀቁ ፤ ባለፈው ሳምንት መፈንቅለ መንግስት ያካሄደው ወታደራዊ ኃይል ኒጀር በብዙ ዋጋ ያገኘችውን ዴሞክራሲ ሊጠብቅ እንጂ ወደኋላ ሊመልስ አይገባም ሲሉ አሳስበዋል። ባይደን አሜሪካ 63ኛ ዓመት የነጻነት በዓሏን ለምታከብረው ኒጀር የምታደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል፤ በሌላ በኩል የፕሬዚዳንት ባዙም ዋነኛ አጋር ዋሽንግተን በወታደራዊ ኃይሉ ላይ ማዕቀቦችን እንደምትጥል ያስጠነቀቀች ሲሆን፤ አሜሪካ በኒያሚ የሚገኙ የዲፕሎማቶቿን ቁጥርም ቀንሳለች።

ኤኩዋስም ሆነ የአፍሪካ ሕብረት አልያም አሜሪካም ሆነች የአውሮፓ ሀገራት ያሻቸውን ማዕቀብ ቢያዥጎደጉዱ ወደኋላ እንደማይመለሱ መፈንቅለ መንግስት አድራጊዎች ገልጸዋል። የኒጀር አዲሱ መሪም ከስልጣን የተባረሩትን ፕሬዚዳንት መሀመድ ባዙምን ወደ ስልጣን ለመመለስ ለሚደረገው ጫና እንደማይንበረከኩ ደጋግመው እየተናገሩ ነው። ከመፈንቅለ መንግስቱ በኋላ ጣልቃ እገባለሁ ካለው የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ጋር ፍጥጫው ተባብሶ የቀጠለ ሲሆን፤ ኤኮዋስም በኒጀር ላይ ማዕቀብ ከመጣሉ ባሻገር የመፈንቅለ መንግስቱ መሪዎች ፕሬዚዳንት ባዙምን ወደ ስልጣን ካልመለሱ የኃይል እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል ነጋ ጠባ ይዝታል።

ወዲህ ኤኮዋስህ ከወታደራዊ ጣልቃ ገብነት በፊት ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ ለማምጣት ስልጣን ከያዙት የጦር መኮንኖች ጋር ለመደራደር ወደ ኒጀር የልዑካን ቡድን ልኳል። የመፈንቅለ መንግስቱ መሪ አብዱራሃማኔ ቺያኒ ጦሩ ማዕቀቦችን ሙሉ በሙሉ እንደማይቀበልና ማስፈራሪያውንም ከየትም ቢመጣ ከየት ወደ ኋላ እንደማይሉ በድጋሚ አስጠንቅቀዋል፡፡ ከቀናት ድንግርግርና ድንግዝግዝ በኋላ ባለፈው ሀምሌ 19 ፣ 2015 ዓ.ም ለኒውክሌር ግንባታ የሚውለው ዩራኒየም በስፋት የሚገኝባትና የሚመረትባት የምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ኒጀር ፕሬዚዳንት መሐመድ ባዙማ በቤተ መንግስት ዘቦቻቸው መፈንቅለ መንግስት እንደተደረገባቸው ዓለማቀፍ ብዙኃን መገናኛዎች ቢቀባበሉትም አሜሪካ ግን አፏን ሞልታ መፈንቅለ መንግስት ለማለት አልደፈረችም ። አንዳንድ ባለስልጣናቷም እገታ ነው እያሉት ይገኛል።

ጄነራል አብዱራህማን ቺያኒ ወይም ኦማር በሀገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ቀርበው ፤ የሀገሪቱን ህልውና ለማረጋገጥና ኃላፊነታችንን ለመወጣት ስንል ጣልቃ ለመግባት ወስነናል ማለታቸውን የ”The New York Times” ዘጋቢ አሮን ቦክሰርማን ያወሳል። ነገሩ እንዲህ ነው ይለናል ጋዜጣው፤ ከመፈንቅለ መንግስቱ ሁለት ቀን ቀደም ብሎ እሮብ ዕለት ጧት በዋና ከተማዋ ኒያሚ የሚገኘውን ቤተመንግስት የፕሬዚዳንቱ ዘቦች ከብበው ባዙምን አገቷቸው። አመሻሽ ላይ በቴሌቪዥን ብቅ ብለው አገዛዙ መገርሰሱን አወጁ።

የመፈንቅለ መንግስቱ ጠንሳሾች ቃል አቀባይ ኮሎኔል አማዱ አብድራማኔ፤ አገዛዙን በኃይል ያወረድነው ከዕለት ወደ ዕለት የሀገሪቱ ጸጥታና ደህንነት ጉዳይ እያሳሰበ ስለመጣና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታው እያሽቆለቆለ ስለሆነ የሀገሪቱን ህልውና አደጋ ላይ እንዳይጥለው ስላሰጋን ነው ብለዋል። አይሲስ፣ አልቃይዳና ቦኮ ሀራም ሀገሪቱ ላይ የጸጥታና የደህንነት ስጋት መደቀናቸው ሳያንስ እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነት ወደለየለት አጠቃላይ ቀውስ እንዳይከታት እርምጃ ወስደናል ይላሉ ኮሎኔል አማዱ።

በበነጋው ሀሙስ ዕለት የሀገሪቱ ጦር፤ በጸጥታ መዋቅሩ የተለያዩ ክፍሎች መካከል ደም መፋሰስ እንዳይኖርና ለሀገሪቱ አንድነት ሲል መንግስት ግልበጣውን በመደገፍ መግለጫ አወጣ ። ለምዕራብ አፍሪካዊት ኒጀር መፈንቅለ መንግስት ድንቋም ብርቋም አይደለም ። የአሁኑ ፕሬዚዳንት በ2021 በምርጫ አሸንፈው በዓለ ሲመታቸው ሊካሄድ ሁለት ቀን ሲቀረው ያልተሳካ መፈንቅለ መንግስት ተደርጎባቸው ነበር። በ1960 ከፈረንሳይ ከቅኝ ግዛት ነጻ ከወጣች በኋላ አራት መፈንቅለ መንግስቶችን አስተናግዳለች። ፕሬዚዳንቱ በጦሩ አመራሮች ላይ ሹም ሽር ማድረጋቸውና የተወሰኑትን በጡረታ ገለል ማድረጋቸው ስልጣናቸውን ሳያሳጣቸው አልቀረም ይለናል የሳህል ቀጣና ተንታኙ ያሀያ ኢብራሂም ።

ጦሩ የዋጋ ግሽበቱ ፣ የኑሮ ውድነቱና ስራ አጥነቱ በሕዝብ ዘንድ የፈጠረውን ቁጣና ተስፋ መቁረጥ እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅሞበታል ። ፕሬዚዳንት ባዙማ ስልጣን ላይ እያሉ በርካታ ስኬቶችን ያስመዘገቡ ቢሆንም ሀገሬው ግን ጠብቆት የነበረው ከዚያ በላይ ነው። የኒጀር መፈንቅለ መንግስት በአሸባሪዎች ፣ በጃጁ አምባገነኖችና የመንግስት ግልበጣዎች መናኸሪያ የሆነውን የሳህል ቀጣና ከድጡ ወደ ማጡ እንዳይከተው ይሰጋል።

በአሜሪካ የሚደገፈው የኒጀር መንግስት በሳህል በርሀ የሚንቀሳቀሱ አሸባሪዎችን ለመደምሰስ በሚደረገው ጥረት ታማኝ አጋር ከመሆኑ ባሻገር 1100 የአሜሪካ ወታደሮች በሀገሪቱ እንዲሰፍሩ ፈቅዷል ። ፕሬዚዳንት ባዙም ከፈረንሳይ ጋር የነበራቸውን ጥብቅ ወዳጅነት ለምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት በር ይከፍታል በሚል ጦሩ ደስተኛ አልነበረም ይሉናል የሳህል ቀጣና ተንታኙ ያሀያ ኢብራሂም ። ከ2020 ወዲህ እንኳ በምዕራብ አፍሪካዎቹ ቡርኪና ፋሶ፣ ጊኒና ማሊ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ተካሂዷል። እነዚህ ሀገራት ከራሽያ በተለይ ከዋግነር ቅጥረኛ ወታደር ጋር የጠበቀ ግንኙነት እየፈጠሩ፤ ቅኝ ገዥዎቻቸውን ግን አይናችሁን ለአፈር ማለታቸው ስጋት ፈጥሯል።

15 የምዕራብ አፍሪካ መንግስታት የኢኮኖሚ ማህበረሰብ መፈንቅለ መንግስቱን አውግዞ ማዕቀብ የጣለ ሲሆን፤ ጦሩ በምርጫ ወደ ስልጣን የመጡትን መሪ እስከ ሀሙስ ወደ ስልጣን እንዲመልስ ቀነ ገደብ ያስቀመጠ ቢሆንም ወታደራዊ ጁንታው ከቁብ አልቆጠረውም ።

በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ፕሬዚዳንቱ ወደ ስልጣናቸው ካልተመለሱ፤ ኤኩዋስ ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለማስመለስ ጦሩን እንደሚልክ ያስጠነቀቀ ቢሆንም እስካሁን ግን ያደረገው ነገር የለም። ሴኔጋልም ጦሯን ልታዘምት እንደምትችል እየዛተች ነው። ቡርኪና ፋሶና ማሊ ደግሞ ኤኩዋስ በኒጀር ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት ከተንቀሳቀሰች ከኒጀር መንግስት ጎን እንደሚሰለፉ አስጠንቅቀዋል። ፈረንሳይና አሜሪካም ለፕሬዚዳንት ባዙም ያላቸውን ድጋፍ ገልጸዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንቶኒ ብሊንከን ደግሞ መፈንቅለ መንግስቱ እየተካሄደ ሳለ ለሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ባዞም ደውለው አሜሪካ ከጎናቸው መሆኗን የገለጹ ቢሆንም ከግልበጣው አላዳኗቸውም ። የሲቪል አስተዳደሩ ወደ ስልጣን ካልተመለሰ አሜሪካ ለኒጀር የምታደርገውን ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ እንደምታቋርጥ ብሊንከን ማስጠንቀቃቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ ያስታውሳል። ፈረንሳይ ቦኮ ሀራምን ጨምሮ አሸባሪዎችን ለመዋጋት ወታደሮቿን በሀገሪቱ አሰማርታ የቆየች ቢሆንም አሁን ግን ይሄ ተልዕኮዋ አደጋ ላይ የወደቀ ይመስላል ይለናል The New York Times ፤ የኒጀር መፈንቅለ መንግሥት ደጋፊዎች፤ ከሥልጣን የተወገዱትን ፕሬዚደንት ፓርቲ ዋና ጽሕፈት ቤት ያቃጠሉ ሲሆን፤ በጽ/ቤቱ አቅራቢያ የነበሩ መኪናዎችንም ከጥቅም ውጭ አድርገዋል።

የመፈንቅለ መንግሥቱ ደጋፊዎች ፓርላማው አካባቢ ሠልፍ ወጥተው የሩሲያን ባንዲራ ሲያውለበልቡ ታይተዋል። በምትኩ የፈረንሳይን ባንዲራ ሲያቃጥሉ፤ ኤምባሲውን ሲያጠቁ በቴሌቪዥን መስኮት ታይቷል። ሩሲያን ጨምሮ ምዕራባውያን እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት ፕሬዚደንቱና ቤተሰቦቻቸው እንዲለቀቁ ጥሪ አቅርበዋል። አርብ ዕለት የፈረንሳይ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካትሪን ኮሎና፤ ፕሬዚደንቱ በመልካም ጤንነት ላይ ናቸው ብለዋል። ለፈረንሳዩ ዜና አገልግሎት ኤኤፍፒ የዜና ወኪል የተናገሩት ሚኒስትሯ የመፈንቅለ መንግሥቱ ጉዳይ ያበቃለት ጉዳይ አይደለም ።

መፈንቅለ መንግሥቱን ያቀናበሩት ሰዎች ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ የሚሰሙ ከሆነ መውጫ መንገድ አለ ብለዋል። የ64 ዓመቱ ፕሬዚዳንት መሐመድ ባዙም ከሁለት ዓመታት በፊት ምርጫ አሸንፈው ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በምዕራብ አፍሪካ አሸባሪዎችን ለማጥፋት በሚያደርጉት ጥረት የምዕራባውያን አጋር ሆነው ቆይተዋል። መፈንቅለ መንግሥቱን ያወገዙት ዩናይትድ ስቴትስ እና የኒጀር የቀድሞም የአዲሱም ቅኝ ገዥዋ ፈረንሳይ ፤ በኒጀር ወታደራዊ ካምፕ አላቸው። የተባበሩት መንግሥታት በኒጀር ያካሂድ የነበረውን ሰብዓዊ እርዳታ ማቋረጡን ይፋ አድርጓል። እርዳታው የተቋረጠው በመፈንቅለ መንግሥቱ ምክንያት ይሁን አይሁን አልተጠቀሰም ።

የመንግሥታቱ ድርጅት ከዚህ ቀደም በኒጀር 4 ሚሊዮን ሰዎች ሰብዓዊ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ማለቱ ይታወሳል። ከሳምንታት በፊት የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ፕሬዚደንት ባዙም “ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በፍጥነት እንዲለቀቁ” ጥሪ አቅርበው ነበር ሰሚ አላገኙም እንጂ። ከስልጣን የወረዱት ፕሬዚዳንት በቲዊተር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ፤ በብዙ መስዋዕትነት ያገኘናቸው ድሎች ይጠበቃሉ። ይሄን ደግሞ ዴሞክራሲ እና ነፃነት ወዳድ ኒጀራውያን ያዩታል” ብለዋል። ወታደራዊው ጁንታ መሪውን ባለማሳወቁ ምክንያት በኒጀር መፈንቅለ መንግሥቱን ማን እየመራው እንዳለ ግልፅ አልነበረም ይለናል ቢቢሲ።

ነገር ግን ወዲያው በዋና ከተማዋ ኒያሚ ሱቆች ተከፍተው ሰዎች የዕለተ ከዕለት ኑሯቸውን ቀጥለዋል። ለድጋፍ ወደ አደባባይ የወጡ ሰልፈኞች የሩሲያን ባንዲራ፣ “ፈረንሳይ ትውደም”፣ እንዲሁም “የውጭ ኃይሎች ይውጡ” የሚሉ መልዕክቶችን ይዘው ታይተዋል። ፖሊስ መፈንቅለ መንግሥቱን ደግፈው ወደ ገዢው ፓርቲ ያመሩ ሰዎችን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ ተኩሷል። የኒጀር ጎረቤት አገራት የሆኑት ማሊና ቡርኪና ፋሶ በተመሳሳይ በቅርብ ዓመታት መፈንቅለ መንግሥት እንደተካሄደባቸው ይታወሳል ።

ሻሎም ለሀገረ ኢትዮጵያ !

አሜን ።

 በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)

fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 14/2015

Recommended For You