በኢትዮጵያ የባንክ አመሰራረት ታሪክ ስሙ ቀድሞ ይጠቀሳል፤ ባንኮ ዲሮማ:: በባንኮ ዲሮማ አካባቢ እድሜ ጠገብ የንግድ እና የመኖሪ ቤቶች በስፋት ይገኛሉ:: አንዳንዶቹ የንግድ ቤቶች ስያሜዎቻቸው ጥንታዊነታቸውን የሚያሳዩ ናቸው:: ዘመናትን ያስቆጠሩት ህንጻዎቹና ሥያሜዎቻቸው ብቻ ሳይሆን፤ ትልቅ ዕድሜ ያስቆጠሩ ሰዎችንም በአካባቢው ማግኘት አዳጋች አይደለም::
በህንጻዎቹ አገልግሎት የፈለገ ሰው ወደ ውስጥ ሲዘልቅ፤ ቆየት ያሉ ፎቶግራፎችን በግድግዳዎች ላይ ተሰቅሎ ይመለከታል:: በእነዚህ ቤቶች ውስጥ ለደቂቃዎች መቆየት የተለያዩ ነገሮችን በአዕምሮዎ ለማመላለስ ያስገድዳል:: በተለይ በእርጅና ወይም በጉልምስና ዕድሜ ክልል ውስጥ ያለ ሰው በትዝታ ጭልጥ ብሎ ትካዜ ውስጥ እንዲገባ ያደርጋሉ:: ያኔ ላልነበረው ለወጣቱም ቢሆን፤ ፎቶግራፎቹ ታሪክን የሚያሳዩ በመሆናቸው ያለፈውን ከእነሱ ዘመን ጋር ለማነጻጸር እድል ይሰጣሉ:: ያለፈውን እና የአሁኑን እያዩ እንዲወያዩ፤ ይጋብዛሉ::
በአካባቢው እንዲህ ያሉ የፎቶግራፍ ማስታወሻዎችን ከያዙ እድሜ ጠገብ የንግድ ቤቶች መካከል ኤንሪኮ አንዱ ነው:: ኤንሪኮ (ENRICO) የሚታወቀው ኬክና ትኩስ ነገር ጥራቱን ጠብቆ በማቅረብ ሲሆን፤ በኬክ ቤቱ አፄ ኃይለሥላሴ 80ኛ የልደት በዓላቸውን ለማክበር የተዘጋጀላቸውን ኬክ ሊቆርሱ ሲሉ የሚያሳይ ፎቶግራፍ ይገኛል:: ፎቶግራፎቹ ከያዙት ታሪክ ባሻገር በወቅቱ የነበረው የፎቶግራፍ ጥራት ያስደንቃል::
ይህ ፎቶ ኬክ ቤቱ የራሱንም ታሪክ ጭምር በፎቶግራፍ ሰንዶ ትውልድ እንዲያውቀው እያደረገ መሆኑን የሚያመላክት ሲሆን፤ በወቅቱ ኬክ ቤቱም ለንጉሱ ልደት የሚሆን ኬክ ለማቅረብ መመረጡ፤ በዘመኑ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ካሉ ኬክ ቤቶች መካከል ተመራጭ መሆኑን የሚያሳይ ነው::
በዚህ ዘመን ተሻጋሪ በሆነ ኬክ ቤት ውስጥ ፎቶግራፎቹን ማየት፣ ኬክ ቤቱ የቆየበትን ዘመን በአእምሮ ለማሰላሰል የሚያስገድድ ሲሆን፤ በጠባቧ ኬክ ቤት ውስጥ ተጠቃሚዎችን ከሚያስተናግዱ መካከል አንዱ በእድሜ ገፋ ያሉ አስተናጋጅ ታዋቂነትን ያተረፉ ናቸው::
ቤቱ ጠባብ በመሆኑ አስተናጋጆቹ ውስን ናቸው:: ከአስተናጋጆች መካከል እይታ ውስጥ የሚገቡት አስተናጋጅ ከሌሎቹ በእድሜ ጠና ያሉት ቢሆኑም፤ ወጣት አስተናጋጆችም አሉ:: ነገር ግን ሻይ ቡና የሚያፈሉት (ባሬስታው)፣ ትእዛዞችን ተቀብለው ኬክ እያሸጉ ለደንበኞች የሚሰጡት አስተናጋጅ፤ በውስጥ ደግሞ ኬክ በመጋገር የተካኑት ባለሙያም በኬክቤቱ ውስጥ ረጅም ዓመት የሰሩና በእድሜም ጠና ያሉ ናቸው::
ከሌሎቹ በእድሜ ጠና ብለው የሚታዩት አስተናጋጅን ለማዘዝ የሚከብዳቸው ቢኖሩም፤ እርሳቸው ግን ውስጥ ተቀምጦ የሚስተናገደውን ‹‹ ምን ልታዘዝ ?›› ብለው ያቀርባሉ:: መኪና ይዞ በር ላይ ቆሞ የሚያዘውንም ትእዛዙን ተቀብለው ፈጠን ብለው በማድረስ ያስተናግዳሉ::
‹‹ ለእርሳቸው መታዘዝ ሲገባ ማዘዝ ይከብዳል::›› የሚባሉት እኝህ ሰው፤ ሥራ እያማረጡ አፍላ ጉልበታቸውን ለሚያባክኑ አንዳንድ ወጣቶች አርአያ መሆን የሚችሉ ናቸው:: ስለሥራቸው፣ የወጣትነት ጊዜያቸውንም፣ አሁን የሚሰሩበት አካባቢ ቀደም ሲል ስለነበሩበት ሁኔታና አሁን ላይ ስላለው ለውጥ ወደኋላ መለስ ብለው ታሪክ እንዲያስታውሱን፣ ሌሎችንም ጉዳዮች እንዲያጫውቱን ጠየቅናቸው::
‹‹እኔ በቃ አርጅቻለሁ›› ብለው ቢያንገራግሩም፤ በኋላም ተግባብተን ይጠቅማል ያሉትን ሀሳብ አጫውተውናል:: ‹‹ማን ይናገር የነበረ፤ ማን ያርዳ የቀበረ?›› እንዲሉ፤ እርሳቸው ኬክ ቤት ውስጥ በሰራተኝነት የተቀጠሩበትን አጋጣሚ ብቻ ሳይሆን፣ ስለ አካባቢውም ታሪክ ጭምር ተጫውተናል::
የትውልድ ስፍራና የእድገት ሁኔታ
75ኛ እድሜ ላይ እንደሆኑ የነገሩን እኝህ ሰው፤ ዓለማየሁ በድኦ ይባላሉ:: የተወለዱት በአዲስ አበባ ከተማ ፈረንሳይ ለጋሲዮን ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ነው:: እርሳቸው ተወልደው ያደጉበት ይህ አካባቢ፤ ያኔ የእርሻ ቦታ ነበር:: ‹‹ማን ይናገር የነበረ፤ ማን ያርዳ የቀበረ›› እንዲሉ እርሳቸው ስለአካባቢው እንዲህ ባይነግሩን ፈረንሳይ ለጋሲዮን ተብሎ የሚጠራው አካባቢ የእርሻ መሬት ነበር ብሎ በአይነህሊና እንኳን ለመሳል ሊያስቸግር ይችላል:: አሁን ጥቅጥቅ ብሎ ሙሉ ለሙሉ በቤት ግንባታ የተጨነቀው ይህ አካባቢ ጤፍ፣ ባቄላና የተለያዩ አዝርእቶችን ያበቅል ነበር:: የእርሳቸው ቤተሰብም የሚተዳደረው በሚያመርቱት ምርት ነበር::
አቶ ዓለማየሁ ከተማ ውስጥ ተወልደው ቢያድጉም፤ ለትምህርት ቦታ ሠጥተው አልተማሩም:: እርሳቸው እንዳጫወቱን ለትምህርት ፍላጎት አልነበራቸውም:: በወቅቱ ለትምህርት የነበረው ጉጉት በብዙዎች ዘንድ አናሳ መሆንም እርሳቸውንም እንዳይነሳሱ አድርጓቸዋል:: በጊዜው እናታቸው፣ እህት ወንድሞቻቸው ቢኖሩም ከነገ ዛሬ ሲሉ ወደ ትምህርት ቤት ሳይልኳቸው ቀሩ:: ፊደል መቁጠር የጀመሩት ጎልማሳ ከሆኑ በኋላ በሥራ ላይ ሆነው በማታ የትምህርት ክፍለ ጊዜ ተምረው ነው::
ዘግይተው የጀመሩትን ትምህርት ዳር ለማድረስ ጥረቱና ፍላጎቱ ቢኖራቸውም በተለያየ ምክንያት ከአምስተኛ ክፍል በላይ በትምህርታቸው መግፋት አልቻሉም:: ከእህት ወንድሞቻቸው በትምህርት ወደኋላ የቀሩት እርሳቸው ብቻ ነበሩ:: ልጅነታቸውን በጨዋታ፣ የታዳጊነትና የወጣትነት እድሜያቸውን ደግሞ ያሳለፉት በግብርና ሥራ ነበር::
ወደ ጉርምስናው ሲሸጋገሩ አካባቢያቸው ላይ አይውሉም:: ውሏቸው አሁን በሚሰሩበት ኬክ ቤት አካባቢ ነበር:: አሁን በከተማዋ እንደሚርመሰመሰው ያኔ መኪና የለም:: ትራንስፖርት ለመጠበቅ ጊዜ የሚያጠፋ ሰው የለም:: ሰው ወደየጉዳዩ የሚሄደው በእግሩ ነው:: እርሳቸውም ኳስ የሚጫወቱት ከሰፈር ጓደኞቻቸው ጋር አብረው በመሆን በእግራቸው በመመላለስ ነበር ::
ያኔ ኳስ የሚታወቀው በካልሲ ወይም በጨርቅ ተሰርቶ ነበር:: በወቅቱ በከተማዋ የሰው ብዛት አነስተኛ በመሆኑና መኪናም ባለመኖሩ፤ በመንገድ የሚመላለስ ሰውና መኪና ኳስ ሲጫወቱ አያስቸግራቸውም:: በአካባቢው ላይም መኖሪያም ሆነ የንግድ ቤቶች የነበሩት በቁጥር ነው:: ሜዳው የተመቸ ስለነበር እንደልባቸው ይጫወቱ ነበር:: ጨዋታቸውን ከጨረሱ በኋላም በምን እመለሳለሁ የሚለው አያሳስባቸውም:: ምሽት እንኳን ቢሆን ወደ ቤታቸው በእግራቸው ተጉዘው ይመለሳሉ::
እርሳቸው የሚሰሩበት አካባቢ በተለምዶ የሚጠራው ቸርችል ጎዳና ተብሎ ነው:: በየቀኑ ከዚህ አካባቢ በእግራቸው ተጉዘው መኖሪያቸው ወደ ሆነው ፈረንሳይ ለጋሲዮን ተብሎ ወደ ሚጠራው አካባቢ ይሔዳሉ:: ዛሬ እንኳን ከፒያሳ ወደ ፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ፤ አጭር ርቀት በትራንስፖርት ለመጓዝ አንድ ሰዓትና ከዚያ በላይ ሰልፍ የሚጠብቀውን ሰው ላየ ያኔ አማራጭ ባለመኖሩ ነው? ወይስ ሰው ብርቱ ነበር? የሚል ጥያቄ ወደ አእምሮዎ ያመጣል:: ለአቶ አለማየሁም ግን ከቸርችል ፈረንሳይ ለጋሲዮን ሩቅ እንደሆነ መንገር ቀልድ ነው:: መልሳቸውም ‹‹ምን እሩቅ ነው?›› በማለት ቀላል መሆኑን ይናገራሉ::
ይሄ የእለት ተእለት ተግባራቸው እንደሆነና ከአካባቢያቸው ይልቅ አሁን የሚሰሩበትን አካባቢ እንደሚመርጡም ይገልፃሉ:: ‹‹የዚህ ሰፈር ዱርዬ ነበርኩ›› ሲሉም ወጣትነታቸውን ያስታውሳሉ:: ዱርዬ ብለው እራሳቸውን የገለጹት፤ ባህሪያቸው ኃይለኛ ስለነበረ ሲሆን፤ ሲነኳቸው እንደማይወዱና በክፉ የመጣባቸውንም ጠንካራ ቡጢያቸውን ከማቅመስ ወደኋላ እንደማይሉ ይናገራሉ:: ይህ የአትንኩኝ ባይነት ባህሪያቸው አሁንም በእርጅናቸው ዘመንም እንዳለቀቃቸው ይገልጻሉ::
አቶ ዓለማየሁ ለአጭር ጊዜ ከአዲስ አበባ ከተማ ኑሯቸውን ኦሮሚያ ክልል በቾ ተብሎ የሚጠራው አካባቢ አድርገው ነበር:: በቾ የወሰዷቸው እህቶቻቸው ነበሩ :: በኋላም ሰንዳፋ የሚኖሩ አያታቸው ጋር ሄደው ለጥቂት ጊዜ ተቀምጠዋል:: እህቶቻቸው ጋርም ሆነ አያታቸው ጋር ከብቶች እያገዱ፣ እርሻም እያረሱ እየረዷቸው የተወሰኑ ጊዜያትን አሳለፉ:: በእርሻ ሥራም የተዋጣላቸው ገበሬ እንደሆኑ አንዳንድ ሰዎች ይነግሯቸው ነበር:: የወጣትነት ጉልበቱም ስለነበር ለጉልበታቸው ሳይሳሱ ያለረፍት ይሰሩ እንደነበር ይነገርላቸዋል::
አቶ ዓለማየሁ እንዳጫወቱን፤ የአካባቢው ወጣቶች ተሰብስበው በመንደራቸው በመዟዟር የመንደሩን ነዋሪዎች መሬት በማረስ ሰብል ሲደርስ በህብረት ሰብስበው በወቅቱ እህሉን ጎተራ ያስገቡ ነበር:: በጤፍ አጨዳ ወቅት ካልሆነ በሌላው የግብርና ሥራ አዋቂዎችን አያስገቡም:: ወጣቶቹ የጤፍ አጨዳ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል ተብለው ስለሚከለከሉ እንጂ ጤፉንም ለማጨድ ወደኋላ አይሉም ነበር::
በቆይታቸው የገጠሩን ኑሮ ወደውት ነበር:: በተለይም ምሽት ላይ ተሰብስቦ ቆሎና ዳቦ እየበሉና የሚጠጣው ጠላ ቀርቦ እየተጠጣ እስከ መኝታ ሰዓት ድረስ መጫወቱን አልጠሉትም:: ቆይታቸውን ቢወዱትም ተወልደው ያደጉበት መንደራቸውን መርሳት ግን አልቻሉም:: ወደ አዲስ አበባ ከተማ ለመምጣት ዋና ምክንያታቸው ግን ሌላ ነው:: እንደለመዱት በአንዱ ቀን ጠዋት ተነስተው ለእርሻ ሥራ በሬ ጠምደው ማሳውን እያረሱ አዳልጧቸው ሲወድቁ፤ ያልጠበቁት ነገር ይገጥማቸዋል:: በወደቁበት መሬት ላይ እንደተኙ እባብ በአንገታቸው ላይ ተጠመጠመ::
ድንጋጤው አሁን ድረስ ይታወሳቸዋል:: እባቡን ከላያቸው ላይ እንዴት እንደጣሉት አያውቁም:: የሚያስታውሱት ብድግ ብለው ከአካባቢው በሩጫ ማምለጣቸውን ነው:: ወደቤታቸው አልተመለሱም፤ ለእርሻ የጠመዱትን በሬ እና ከቤት ይዘዋቸው የወጡትን በግና ፍየሎች ሜዳ ላይ ጥለው፤ ከእርሻ መሬቱ በሩጫ ወጥተው ወደ አዲስ አበባ ከተማ ለመምጣት ወሰኑ::
ከነበሩበት ወደ አዲስ አበባ ከተማ በትራንስፖርት ተሳፍረው ለመምጣት ክፍያው 50 ሣንቲም ብቻ ነበር:: ተሳፍረው የመጠቡት መኪናም ያወረዳቸው መርካቶ ነበር:: ከትራንስፖርት ከወረዱ በኋላ ሌላ ትራንስፖርት አላስፈለጋቸውም:: ፈረንሳይ ለጋሲዮን ድረስ የሄዱት በእግራቸው ነበር:: ድንጋጤውም ስለነበር ሰውነታቸውን አላስተዋሉም:: ልብሳቸው ሁሉ ጭቃ ብቻ ነበር:: ቤተሰቦቻቸው እንኳን አላወቋቸውም ነበር:: በኋላ ማንነታቸውን ነግረው እናታቸው ተቀበሏቸው::
እናታቸው ወዲያው አቅራቢያቸው በሚገኘው ቀበና ወንዝ ወስደው ገላቸውን እና ልብሳቸውን አጥበው የራሳቸውን ቀሚስ አልብሰው ወደቤት አስገቧቸው:: ይሄ አጋጣሚ ባይፈጠር ኖሮ አቶ ዓለማየሁ ገበሬ ሆነው ይቀጥሉ ነበር? ወደ አዲስ አበባ ከተማ ከተመለሱ በኋላ ወደየትም አካባቢ አልሄዱም:: ኢንሪኮ በሚባል ኬክ ቤት ተቀጥረው ከግማሽ በላይ የሚሆነውን እድሜያቸውን በዚህ ኬክ ቤት ውስጥ በሥራ አሳለፉት::
ኤንሪኮ ኬክ ቤት የተቀጠሩበት አጋጣሚ
አቶ ዓለማየሁ ለመዋያና ለጨዋታ የመረጡት አካባቢ፤ በዚያው አስቀርቷቸዋል:: ሥራ ያገኙት እዚሁ አካባቢ ነው:: አሁን የሚሰሩበት ኬክ ቤት ያኔ እርሳቸው ሲጫወቱ አልነበረም:: የኬክ ቤቱ ባለቤት በዚያው አቅራቢያ ሌላ ቦታ ከፍቶ ይሰራ ነበር:: የአሁኑን ኬክ ቤት ሲገነባም የአይን እማኝ ናቸው:: ግንባታው የተካሄደበትንም ጊዜ እንደምልክት ያነሱት መንግሥቱ ነዋይን ከሥልጣን ለማውረድ የታህሳስ ግርግር እየተባለ የሚታወቀውን ወቅት ነበር:: ህንፃው አልቆ የነበረበትን አጠናቅቆ ሲዘዋወርም እርሳቸው በቦታው ነበሩ:: በወቅቱም የኬክ ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ አባተ በኬክ ቤቱ ሥራ እንዲጀምሩ ጥያቄ ያቀርቡላቸዋል:: ከጓደኞቻቸው መካከል ተመርጠው ለሥራ ሲጠየቁ መሥፍረቱ ቀልጣፋና ጥሩ ባህሪ በመሆናቸው ጥያቄው ቢቀርብላቸውም፤ አቶ ዓለማየሁ ግን ‹‹ ዱሩዬ ስለሆንኩ ነበር::›› ይላሉ::
መጀመሪያ ሥራቸው ብርጭቆ ማጠብ ነበር:: የቀረበላቸውን የሥራ ጥያቄ ተቀብለው በ80 ብር የወር ደመወዝ ሥራ ጀምሩ:: ይሄ ሁሉ በ1950ዎቹ ውስጥ የሆነ ታሪክ ነው:: እርሳቸውም በኬክ ቤቱ ሥራ ሲጀምሩ ወጣት ነበሩ:: በኬክ ቤቱ በግድግዳ ላይ ከተሰቀሉት ፎቶግራፎች መካከል የእርሳቸውም ይገኝበታል:: የተቀጠሩበት ወርሃዊ የወር ደመወዝ በዚያን ጊዜ ብዙ ነበር::
ምንም እንኳን የሥራ ድርሻቸው ብርጭቆ ማጠብ ቢሆንም፤ በኬክ ቤቱ የእከሌ ሥራ ነው የሚባል ነገር የለም:: ሰው በጎደለበት ሥራ ቦታ ሁሉ ክፍተቱን መሙላት የቤቱ መገለጫ ነው:: አንድ ሰራተኛ በተለያየ ምክንያት ሲቀር፤ ሥራን ተባብሮ በመሸፈን አንዱ ሌላውን ያግዛል:: ተባብሮና ተጋግዞ ሥራን ማሸነፍ እንጂ አንዱ ሌላውን ለማሳጣት የሚደረግ ተግባር በቤቱ ነውር ነው:: የሁሉም ሩጫ በቤቱ ውስጥ የሚስተናገደውን፣ ከውጭ ሆኖ የሚያዘውን ደንበኛ አስደስቶ መሸኘት ነው::
‹‹ለሀሜትና ለማሳጣት ጊዜ የለም›› የሚሉት አቶ ዓለማየሁ፤ የሥራ ሰው እንደሆኑ አንደበታቸው ብቻ ሳይሆን ተግባራቸውም ይመሰክራል:: ጊዜ ሰጥተው እርሳቸውን ለማነጋገር የሚፈልገውን ሰው እያነጋገሩ፤ በስልክ የመጣላቸውን ትእዛዝ ተቀብለው ደንበኛቸውን አስቀድመው ያነጋግራሉ:: ወንበር ይዞ የተቀመጠ ደንበኛ የሚታዘዘው ካጣ ሀሳባቸው እርሱ ጋር ነው:: ከቻሉ ሁሉንም ራሳቸው ያስተናግዱ ወይም ሌሎችን እየጠሩ ወደ ደንበኛው ያመለክታሉ:: ‹‹ደንበኛ ክቡር ነው ››የሚባለውን በተግባር ያሳያሉ::
አቶ ዓለማየሁ አገልገሎት ሰጪ ሆደ ሰፊ መሆን አለበት የሚል አቋምም አላቸው:: አንዳንዴ በሥነምግባርም ወጣ ያለ፤ በተለያየ ነገርም ተበሳጭቶ የሚመጣ ደንበኛ ሲያጋጥም የእርሳቸው ማምለጫ ዝምታ ነው:: ከተቻለም ሌላ ሥራ እንደያዘ አስመስለው ወደ ሌላ ዞር ማለት እንጂ፤ የደንበኛውን ባህሪ አያባብሱም:: ለደንበኛ መሸነፍ ያለብኝ እኔ ነኝ የሚል አቋም አላቸው::
እርሳቸው ሥራ በጀመሩበት ጊዜ የነበሩ ተስተናጋጅ ደንበኞችና በዚህ ወቅት ያሉት ፍጹም የተለያዩ እንደሆኑ ይገልጻሉ:: ቀደም ባለው ጊዜ በኬክ ቤቱ ይጠቀሙ የነበሩ ደንበኞች በእድሜም በሥራ ኃላፊነታቸውም ከፍ ያሉ ናቸው:: የሚያስተናግዷቸው እነርሱን በሚመጥን መልኩ ነው:: ኬክ ቤቱ በጣም ጠባብ ቢሆንም፤ ያኔ ተስተናጋጆቹም ቢሆኑ ለአስተናጋጆች ክብር ይሰጡ ነበር:: በአስተናጋጅና በተስተናጋጅ መካከል ያለው መከባበር ሥራውንም እንዲወዱት አድርጓቸው እንደነበር አጫወቱን::
ዛሬ የሚስተናገደው በቁጥር የበዛ ነው:: በእድሜም የተለያየ ነው:: ባህሪውም እንዲሁ የተለያየ ነው:: አቶ ዓለማየሁ በተቻላቸው መጠን ይዘውት በመጡት በአክብሮት የማስተናገድ ባህል ለመጠቀም ጥረት ያደርጋሉ:: የልጅ ልጆቻቸው የሚሆኑ አንዳንድ ደንበኞች ያልተገባ ባህሪ ሊያሳዩዋቸው ሲሞክሩ እንኳን ‹‹እኔ ቅድመ አያት ሆኛለሁ ምን ከነርሱ ጋር አጨቃጨቀኝ›› በማለት ደንበኛው ቢያበሳጫቸው እንኳን አላስፈላጊ ምልልስ ውስጥ ላለመግባት ዞር ማለትን ይመርጣሉ:: እራስን ማስተናገድ የኬክ ቤቱ አሰራር በመሆኑም በአክብሮት መስተናገድ ያልፈለገ በዚህኛው መንገድ እንዲጠቀም ዞር ይላሉ::
በዚህ ዘመን እንዲህ ያለውን የመስተንግዶ ባህል እያየን ይሆን? ለእናንተ ለአንባብያን ትተን ወደ አቶ ዓለማየሁ እንመለስ:: በዚህ ኬክ ቤት ውስጥ ያገለገሉት ለ52 ዓመት ነው:: ከአምስት አስርት ዓመታት በላይ የገነቡትን የመስተንግዶ ሥነምግባር አሁንም ይዘው እያስቀጠሉ ይገኛሉ:: የመሥተንግዶ ሥነምግባሩ፣ ከሌሎች ሰራተኞች ጋር ተባብሮና ተሳስቦ መሥራቱ ለእርሳቸው ትልቅ የሥራ እርካታ እንደሆነ ነው የሚናገሩት:: ደስተኛም ናቸው:: ልጆቻቸውም ሆኑ አንዳንድ ወዳጆቻቸው ሥራቸው እንደሚበቃቸው ሲነግሯቸው እንኳን ጨክነው ለማቆም አልቻሉም:: የሥራ ባልደረቦቻቸውም ሊያጧቸው ስላልፈለጉ ይመስላል ቤት ቢውሉ የበለጠ እንደሚደክማቸው እየነገሯቸው በሥራ ላይ እንዲቆዩ ያበረታቷቸዋል::
አቶ ዓለማየሁ ከዚህ በኋላ በሥራ ላይ ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆዩ እርግጠኛ ባይሆኑም ውሳኔ ላይ አልደረሱም:: ቀኑን በሥራ አሳልፈው ምሽት ላይ ደግሞ ለፀሎት ወደቤተእምነት ይሄዳሉ::
52 ዓመት በአንድ የሥራ ቦታና አካባቢ ለምን?
አቶ ዓለማየሁ ከግብርና ሥራ ቀጥሎ አብዛኛውን ሥራ የሰሩት ኤንሪኮ ኬክ ቤት ውስጥ በአስተናጋጅነት ነው:: አንዳንዶች እንደሚያደርጉት እዛው የሚጋገረውን ኬክ ሙያ ተምረው የራሳቸውን ኬክ ቤት ለመክፈት እንኳን ጥረት አለማድረጋቸው ጥያቄ ይፈጥራል:: ለምን እንዳልሞከሩ ጠየቅናቸው:: በአጭሩ እኔ የተመደብኩበት ሥራ ማስተናገድ ስለሆነ በዚሁ ሥራ ነው የቀጠልኩት ነው አሉ:: ወደፊት ለመኖር ያሰቡት ጫንጮ በሚባል አካባቢ በመሆኑ በዚያ አካባቢ ከብት እርባታ መጀመራቸውንና ቤትም መሥራታቸውን አጫወቱን::
መስተንግዶ አዋቂው አቶ አለማየሁ
ከብዙ ደንበኞቻቸው መካከል በሥራ ቦታቸው አካባቢ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ይማሩ የነበሩና ያኔ ከአባቶቻቸው ጋር የኬክ ቤታቸው ደንበኞች ትላልቅ ሰዎች ሆነው አንዳንዶችም ኑሯቸውን ውጭ ሀገር አድርገው ወደ ሀገር ቤት ሲመጡ፤ መኖራቸውን ለማረጋገጥ ወደ ኬክ ቤቱ ይመጣሉ:: ትውስታቸውንም ተጨዋውተው እንደሚለያዩ ነግረውናል:: ህፃን ሆነው የሚያውቋቸው አንዳንዶቹም በእድሜ ከፍ ብለው ሲያዩዋቸው ይገረማሉ::
የሥራቸው ባህሪ በትህትና ትእዛዝን ተቀብሎ ማስተናገድን ይጠይቃል:: ደንበኛው ሲደስት ደግሞ ጉርሻ ይሰጣል:: በስልክ ትእዛዝ ይኖራል:: ኬክ ቤቱ ውስጥም የሚስተናገደው በመስተንግዶው ሲደሰት ለጫማ ማስጠረጊያ ይሁንህ፣ አንድ ሁለት ድራፍት ጠጣ ብሎ ጉርሻ ይሰጣል:: ታዲያ ጉርሻውም መስተንግዶውም በጨዋታ ነው::
የቤተሰብና የመኖሪያ ቤት ሁኔታ
ትዳር የመሰረቱት በ1961 ዓ.ም ነው:: ከባለቤታቸውም ሁለት ሴቶችና ሶስት ወንዶች ልጆች አፍርተዋል:: አቶ ዓለማየሁ የአብራካቸውን ክፋይ ብቻ ሳይሆን ባለቤታቸው ከእርሳቸው በፊት የወለዷቸውን ሁለት ልጆች ጨምረው ሰባት ልጆች አሳድገዋል:: ይህ ሁሉ ቤተሰብ የሚኖረው አቶ ዓለማየሁ በአስተናጋጅነት በሚያገኙት ገቢ ነው:: ደመወዛቸው አሁን ላይ ወደ አምስት ሺ ብር ከፍ ይበል እንጂ፤ ቤታቸውን የሚመሩት ከዚህ በታች በነበረበት ጊዜ ነው :: ባለቤታቸው የቤት እመቤት በመሆናቸው በገቢ አያግዟቸውም:: በሚያገኙትም ገቢ ‹‹ተመስገን›› ይላሉ:: ቤተሰባቸውን ይዘው የሚኖሩት ፒያሳ አካባቢ በኪራይ ባገኙት የቀበሌ ቤት ውስጥ ነው::
ያኔ ሜዳ ከነበረው የሥራ አካባቢያቸውም ሆነ ተወልወደው ካደጉበት ፈረንሳይ ለጋሲዮን የቤት መሥሪያ የሚሆን ቦታ እንዴት እንዳላገኙና እንዳልሰሩ ጠየቅናቸው:: እርሳቸውም እንደነገሩን ፈረንሳይ ለጋሲዮን የነበራቸውን የእርሻ መሬት ወታደራዊ የደርግ መንግሥት መሬት ላራሹ ብሎ በማወጅ አምስት ሺ ካሬ ስፋት ያለው መሬት በውርስ ተወሰደባቸው:: ለውጥ ሲመጣ ደግሞ የተተካው መንግሥት መሬታቸውን መልሶ ሰጣቸው:: ልጆቻቸው በመሬቱ ላይ ቤት ሰርተው ይኖሩ ነበር::
ግብር በመክፈል ግዴታቸውን የሚወጡበት መኖሪያ ቤታቸው በቅርቡ ደግሞ ሳያስቡት ‹‹ህገወጥ ነው›› ተብሎ ፈረሰባቸው:: አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የግል ቤት ሳይኖራቸው የቀረው በዚህ ሁኔታ ነው:: ወደፊት ጫንጮ በሚባል አካባቢ የመኖር እቅድ እንዳላቸውና ለመተዳደሪያቸው እንዲሆን ከብቶች ገዝተው እርባታ መጀመራቸውንና መኖሪያ ቤትም መሥራታቸውን አጫውተውናል::
የኤንሪኮ ኬክ ቤት አመሰራረትና የያኔው የኬክ ዋጋ
አቶ ዓለማየሁ እንዳጫወቱን፤ የኤንሪኮ ባለቤቶች ጣልያንያውያን ባልና ሚስት ነበሩ:: ቤቱ ውስጡ ዙሪያውን በመስታወት በመሰራቱ ዙሪያውን ማን ምን እንደሚሰራ ይታያል:: ስርቆት ለመፈጸም ወደ ኬክ ቤቱ የሚመጣ እንኳን ቢኖር በእይታ ውስጥ ስለሚሆን አያመልጥም:: ቤቱም የተሰየመው በባለቤቱ በወንድየው ስም ነው:: ጣሊያንኛ ቋንቋ መስማት እንጂ በቋንቋው መናገር አይችሉም:: የኬክ ቤቱ ባለቤት ይጋግሩ ነበር:: ሴቷ ደግሞ ከገንዘብ ተቀባይ ጎን ተቀምጠው ይውላሉ:: የሚወጡትና የሚገቡት ሁለቱም የሥራ ሰዓታቸውን አክብረው ነው:: አስተናጋጆቹና ኃላፊው ኢትዮጵያውያን ናቸው::
ጣሊያኑ ባልና ሚስት አሁን በህይወት የሉም:: ቀድመው የሞቱት ወንድየው ነበሩ:: በወቅቱ ኃይለኛ የአስም ህመም ነበረባቸው:: ሙቀት ፍለጋ ከአዲስ አበባ ከተማ ወጣ የሚሉባቸው አጋጣሚዎች እንደነበሩ አቶ ዓለማየሁ ያስታውሳሉ:: ለሙቀት ሶደሬ መዝናኛ ያሳልፉ ነበር:: እርሳቸው እንዳሉት ባለቤታቸውም በህይወት ብዙ አልቆዩም:: ከጥቂት ወራት በኋላ አረፉ:: የሁለቱም የቀብር ሥነሥርአት በአዲስ አበባ ከተማ ጉለሌ ተፈጸመ:: ባልና ሚስቱ አንድ ሴት ልጅ አፍርተዋል::
ከኬክ ቤቱ ባለቤት ኤንሪኮ የሥራ ባህልን መማራቸውን የሚናገሩት አቶ ዓለማየሁ፤ ባልና ሚስቱን በጥሩ ባህሪያቸውም ይገልጿቸዋል:: ሰራተኞቻቸውን በጥሩ ሁኔታ በማስተዳደርም የሚመሰገኑ መሆናቸውን መስክረውላቸዋል:: ሰራተኛው የጤና ችግር ቢያጋጥመው የህክምና ወጭም እንደሚችሉ ገለፁሉን:: በኬክ ቤቱ ያለው የሥራ ሥነሥርዓት በመስተንግዶውም ሆነ ለገበያ የሚያቀርቡት ኬክ እንደቀድሞ ይዞታው እንደሆነና በደንበኞች ያለው ተፈላጊነትም አለመቀነሱን ነገሩን::
ኬኩን የሚጋግረው እርሳቸውን ለብርጭቆ አጣቢነት ሥራ የጠየቃቸው አባተ የሚባለው የኬክ ቤቱ ሥራ አስኪያጅ ልጅ ነው:: በህጻንነቱ ኬክ ቤት እየመጣ አደገ:: እርሳቸውም እንደልጃቸው የሚያዩት ልጅ ነው:: እዛው ሥራ ጀምሮ ኬክ የመጋገሩን ሙያ ከሥር ቀስሞ ያደገ ሰው መሆኑንና ሙያውን እንደተካነበት ገለፀልን:: የኬክ ዋጋ በዚያን ጊዜ አንድ ሰው የሚመገበው በ15 ሣንቲም የሚሸጥ ነበር:: አሁን ላይ ዋጋው 30 ብር ደርሷል:: ኬክ ቤቱ በአሁኑ ጊዜ የሚተዳደረው በኤንሪኮ የልጅ ልጅ ጁሊያ በምትባል ነው:: ኑሮዋ በውጭ ሀገር ቢሆንም አልፎ አልፎ እየመጣች ትጎበኛቸዋለች::
የሥራ ቆይታ ገጠመኝና ስላካባቢው ያላቸው ትዝታ
አቶ ዓለማየሁ በመጥፎም ይሁን በጥሩ ጎልቶ የሚወጣ ትውስታ እንደሌላቸው ቢነግሩንም፤ በኬክ ቤቱ ግድግዳ ላይ ስለተሰቀሉት ፎቶግራፎች በጠየቅናቸው ጊዜ ከፎቶግራፎቹ መካከል ስለነበረው አፄ ኃይለሥላሴ ነገሩን:: እርሳቸው እንዳሉት፤ ለ80ኛ የልደት በዓላቸው ኬኩ የተዘጋጀው ኤንሪኮ ነው:: ኬኩ እንዲዘጋጅ የተፈለገው በኢትዮጵያ ካርታ ቅርፅ ነበር :: ኬኩን የሚጋግረው ባለሙያም በወረቀት ላይ ነድፎ ካዘጋጀ በኋላ ነው:: ኬኩ ተጭኖ ወደ ማዘጋጃ ቤት እንዲሄድ ተደረገ:: የኬክ ቤቱን ሥራ አስኪያጅ አቶ አባተን ጨምሮ አቶ ዓለማየሁ ኬኩ ከተቆረሰ በኋላ ለእንግዶች ለማስተናገድ አምረውና ተውበው የማስተናገጃም ሳህን ይዘው ማዘጋጃ ቤት ተገኙ:: በወቅቱ ግን መስተንግዶውን ያደረጉት እነርሱ ሳይሆኑ ከቤተመንግሥት የመጡ አስተናጋጆች ነበሩ:: እነ አቶ ዓለማየሁ የተቀመጡት እንደ እንግዳ ነበር::
ስለአካባቢውም እንዳጫወቱን፤ ኬክ ቤቱ ከሚገኝበት ፊትለፊት ያለው ህንፃ የልዑል ኃይለሥላሴ ነው:: አካባቢው ላይም ላውንደሪቤቶችን ጨምሮ የተለያዩ የንግድ ቤቶች ነበሩ:: ጊዜውንም የሞኝ ጊዜ ብለው ይገልጹታል:: አሁን ላይ በመኪናና በእግረኛ የመንገድ መጨናነቁ ከቀደመው ጋር ሲያነጻጽሩት ልዩነቱ የምድርና የሰማይ ያህል እንደሆነባቸው ይናገራሉ:: ኪስ አውላቂም የዚያኑ ያህል በዝቷል ይላሉ::
አቶ ዓለማየሁ በተለያየ የ ሥርአት ለውጥ ያለፉ ሰው በመሆናቸው በሥራቸው ላይ የገጠማቸው እንቅፋት ይኖር እንደሆን ጠየቅናቸው:: ሥራቸውን የሚያስተጓጉል ነገር እንዳልገጠማቸው ምላሽ የሰጡን:: በወታደራዊ የደርግ አገዛዝ ወቅት ኢትዮጵያ ከሶማሌ ጋር በነበራት ጦርነት ስንቅ ለማዘጋጀት ታጠቅ ጥሪ ይደረግ ነበር:: ኬክ ቤታቸውም ዳቦ ጋግሮ እንዲያቀርብ ተጠይቆ የተወሰኑ ሰራተኞች ሄደው እንደነበር አስታውሰው፤ በኬክ ቤቱ እንቅስቃሴ ላይ ያሳደረው ተጽእኖና እርሳቸውም በሥራቸው ላይ የገጠማቸው እንቅፋት አለመኖሩን ነገሩን::
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 14/2015