እንደ ሀገር በትብብር፣ እንደ ወንድም በወዳጅነት የተገለጠው የኢትዮ-ኤሜሬትስ ግንኙነት!

ወዳጅነት በክፉ ቀን ይፈተናል፡፡ ምክንያቱም ወዳጅ ያሉት አንድም ችግርን አብሮ ተጋፍጦ ያሻግራል፤ ካልሆነም በችግር ወቅት ከወዳጅነቱ ሰገነት ፈቀቅ ይላል፡፡ ይሄ ሰውኛ ባህሪ በሀገራት መካከልም የሚገለጥ ሃቅ ነው፡፡ ሀገር እንደ ሀገር በተለያየ መልኩ ትፈተናለች፤ ሕዝቦቿም ይቸገራሉ፡፡ ይሄ ወቅት ደግሞ እንደ ሀገርም እንደ ሕዝብም ከፍ ያለ የወዳጅ ሀገራትንና ሕዝቦችን ድጋፍና አለሁ ባይነትን አብዝቶ የሚፈለግበት ነው፡፡

ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያንም በዘመን ጅረት ውስጥ በሚገጥሟቸው አያሌ ፈተናዎች መካከል የልብ ወዳጅ ሀገራትን እና ሕዝቦችን ማግኘት ችለዋል፡፡ በዚያው ልክ ወዳጅነታቸው ለክፉ ቀን የማይሆን የፌሽታ ጊዜ ወዳጆች ስለመኖራቸውም ታዝበዋል፡፡ ከእነዚህ ክስተቶች መካከል ደግሞ ከ2010ሩ ሀገራዊ ለውጥ ማግስት ያለውን የኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያውያንን ፈታኝ ዓመታት መመልከቱ ብቻ በቂ ነው፡፡

በእነዚህ ከአምስት ያልበለጡ የለውጥ ዓመታት ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን በብዙ ተፈትነዋል፡፡ በብዙም የአጋርና ወዳጅ ሀገርና ሕዝቦችን ወዳጅነት ለመፈለግ ተገድደዋል፡፡ በዚህ ወቅት ብዙዎች ፊታቸውን ሲያዞሩባቸው፤ ጥቂት ግን ወዳጅነታቸው ከልብ የሆነ ታላቅ ነገርን ማድረግ የቻሉ ሀገራትና ሕዝቦች ተገኝተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ካዝናዋ ሲራቆት የሞሉላት፤ በጦርነት ስትታመስ ለሰላሟ የተጉላት፤ ዓለምአቀፍ ክስና ጫና ሲገጥማት ሸክሟን ያቀለሉላት የክፉ ቀን የልብ ወዳጆች መኖራቸው በግልጽ ታይቷል፡፡ እነዚህ ሀገራት ስለ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ይሄን ማድረጋቸው ደግሞ በመርህ ላይ የተመሠረተ የአብሮነት መንገድ ስለያዙ ነው፡፡ እኛ ብቻ ሳይሉ ለጋራ ተጠቃሚነት ስለሚሠሩ ነው፡፡ እናም እነዚህ ሀገራት በእሳት የተፈተኑ የልብ ወዳጆችና አጋሮች ናቸውና ሊመሰገኑም ይገባል፡፡

ከእነዚህ ሀገራትና ሕዝቦች መካከል ደግሞ የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች ተጠቃሽ ነው፡፡ ታዲያ ከትናንት በስቲያ የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች ፕሬዚዳንት ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ነበር፡፡ ፕሬዚዳንቱ ቦሌ ዓለምአቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የወዳጅ አቀባበል ያደረጉላቸው ሲሆን፤ በቆይታቸውም ይሄንኑ ወዳጅነታቸውን የሚገልጽ እና በሀገራቱ መካከል ያለውን ሁለንተናው ትብብር ከፍ ወዳለ ደረጃ የሚያሳድጉ 17 የትብብር ማዕቀፎች ስምምነት እንዲፈረሙ ሆኗል፡፡

የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች እና ኢትዮጵያ ወዳጅነታቸው ከፍ ብሎ ከተገለጸባቸው ወቅቶች መካከል፣ ከ2010ሩ ሀገራዊ ለውጥ ማግስት ኢትዮጵያ በገጠማት የበጀት ቀውስ ምክንያት የተገለጸው አጋርነት ነበር፡፡ እንደ ሀገር መንግሥት ካዝናው ባዶ ቀርቶ በነበረበት ወቅት ይህች ሀገር የኢትዮጵያን የበጀት ጉድለት ብቻ ሳይሆን የውጭ ምንዛሬ ችግር ማስታገስ ያስቻለ ድጋፍ ነበር ያደረገችው፡፡ ይሄ ድጋፍ ደግሞ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ብቻ ሳይሆን መንግሥትም እንደ መንግሥት ከፍ ካለ አጣብቂኝ ወጥቶ እፎይ እንዲል ያደረገ ነበር፡፡

በሁለቱ መካከል ያለው አጋርነት ታዲያ በዚህ ብቻ የሚገለጽ አልነበረም፤ በግዙፍ ፕሮጀክቶች ግንባታ፣ በሕዝቦች ግንኙነት፣ በትምህርትና ቴክኖሎጂም ጭምር እንጂ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ለፕሬዚዳንቱ አቀባበል ባደረጉበት ወቅት በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው «ውድ ወንድሜ እና ጓደኛዬ ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ወደ ኢትዮጵያ እንኳን ደህና መጣህ። እያደገ የመጣው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በመከባበር እና ለጋራ እድገት የጋራ ራዕይ ላይ የተመሠረተ ነው። ዘላቂ ልማትን ለማስቀጠል ትብብራችንን እንቀጥላለን፤» ሲሉ መግለጻቸውም ከዚሁ ከፍ ያለ የወዳጅነት ገጽ የመነጨ ነው፡፡

እርግጥ ነው ፕሬዚዳንቱ በቆይታቸው በአየር ንብረት ለውጥ፣ በሰላምና ደህንነት፣ በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በግብርና፣ በትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ፣ በንግድና ኢንዱስትሪ፣ በጉምሩክ እና ሌሎችም ዘርፎች ላይ በአብሮነት መሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ እነዚህ ስምምነቶች ደግሞ ቀድሞ የነበረውን የሁለቱን ሀገራት ትብብር ከፍ የሚያደርገው ብቻ ሳይሆን፤ በመሪዎቹ የታየው ወንድማማቻዊ ግንኙነትም በሕዝቦች መካከል ለሚኖረው ከፍ ያለ ትብብርና አብሮነት የሚኖረው ፋይዳ እጅጉን የላቀ ነው፡፡

በመሆኑም እንደ ሀገር በሀገራቱ መካከል፤ እንደ ሕዝብም በሕዝቦች መካከል ያለው ይሄ ትብብርና ወዳጅነት፤ ከትናንት ዛሬ ከፍ ያለ እምርታ የታየበት ነው፡፡ ከዛሬ ደግሞ ነገ የበለጠ ልቆና ጎልብቶ መዝለቅ ያለበት ነው፡፡ በመሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹትም፣ እያደገ የመጣው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በመከባበር እና ለጋራ እድገት የጋራ ራዕይ ላይ ተመስርቶ፤ ዘላቂ ልማትን ማስቀጠል ላይ አተኩሮ፤ እንደ ሀገር በትብብር፣ እንደ ሕዝብም በወንድማማችነት ከፍ ያለ አርአያነት ወዳለው ከፍታ ማደግ ይኖርበታል!

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 14/2015

Recommended For You