የሕዝብንና የሀገርን አደራ በኃላፊነት መንፈስ እንወጣ!

ዊልያም አርተር ዎርድ የተባለ ምሁር እንደሚገልጸው፤ የተማሩ ሰዎች ግልጽ በሆነ እና አመክንዮን መሠረት ባደረገ መልኩ ያስባሉ፤ ክብሩን የጠበቀ ኑሮን ይኖራሉ፤ድፍረትን ያንፀባርቃሉ፤ በሙሉ ፈቃደኝነት እና በለጋስነት ይሰጣሉ፤ ፍቅር እና ፀጋ በተሞላበት መንገድ ምህረትን ያደርጋሉ:: በመልካም አጋጣሚዎቻቸው ላይ ያተኩራሉ። ከቀሪው የሰው ዘር ጋር ያላቸውን አንድነት ያከብሩታል::

ኢትዮጵያም ይህን በመሰል ዕውቀት፣ብቃትና ስነ ምግባር የታነጹ በርካታ ምሁራንን ያፈራች ሀገር ነች። ጊዜ እና ሁኔታ በፈቀደላቸው መጠን ለሀገራቸው እና ለወገናቸው የሚያስቡ፤ከራሳቸው አልፎ ስለነገው ትውልድ አበክረው የሚጨነቁ እርቅዬ ምሁራን ያሏት ሀገር ነች።

በውስን አቋሟ አስተምራ ለሀገርና ለወገን የሚጠቅሙ ምሁራንን እንዳፈራች ሁሉ በዚያው መጠን ፊደል ከመቁጠር ውጪ አንዳች ቁም ነገር የማይገኝባቸውና ላስተማረቻቸው ሀገርና ከሌለው ላይ ቀንሶ ፊደል ላስቆጠራቸው ወገናቸው ጠብ የሚል ነገር የመስራት ሃሞቱ የሌላቸው በርካቶች ናቸው ።

እነዚህ ሰዎች ከእኛነት ይለቅ እኔነትን፤ከሀገር ይልቅ የራስ ጥቅምን፤ከአብሮነት ይልቅ መለያየትን፤ከፍቅር ይልቅ ጥላቻን ሲሰብኩ ይደመጣሉ።ሀገር ከመገንባት ይልቅ ማፍረስን ስራዬ ብለው የያዙት ይመስላሉ። ተደጋግሞ እንደተነገረውም ያልተማሩ ኢትዮጵያውን ያጸኗትን ሀገር ተማርን የሚሉ ሰዎች ለማፍረስ ሲጣጣሩ እየተመለከትን ነው።

ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝም ሰሞኑን በአንድ ዩቱብ ላይ ያየሁት ተንቀሳቃሽ ምስል(ቪዲዮ) ነው። በዚሁ ቪዲዮ ላይ ያየሁትንና የሰማሁትን ማመን አቃተኝ። ዓይኔንና ጆሮዬን ማመን አቃተኝ።እራሴን ተጠራጠርኩት። ግን ትክክል ነበርኩ።

በዚህ ምስል ላይ የማያቸው ምሁር ያስተማሩኝና የዕውቀት አባቴ ናቸው ብዬ የምመካባቸው ሰው ነበሩ። ከሀገር አልፈው ለዓለም የሚጠቅሙና በሰው ልጆች እኩልነት የሚያምኑ፤ከብሔርና ከሃይማኖት ጎጠኝነት የጸዱ ሰው እንደሆኑ ሳምን ቆይቻለሁ። ክፍል ውስጥ ሲያስተምሩንም የጎጠኝነትን አደገኛነትና ሀገር አጥፊነት ደጋግመው ሲያስተምሩን ቆይተዋል። እኝሁ መምህሬ ምሁር ማለት ዓለም አቀፍ አስተሳሰብ ያለው ሰው መሆኑን ደጋግመው አስተምረውናል።

እኒህን ጉምቱ ምሁር በመንደርተኝነትና በጠባብነት፤ብሎም ለራስ ብሔር በመወገን ግፋ በለው፣ ቁረጥው ፣ግደለው የሚል መልዕክት ያስተላልፋሉ ብሎ ለአፍታም የሚጠብቅ ሰው አልነበረም። የሆነው ግን አንድ ምሁር ነኝ ከሚል ግለሰብ ቀርቶ ከተራ ሰው የሚጠበቅ አይደለም።

እኒሁ ‹‹ምሁር›› ያለምንም ሀፍረት ወጣቱ ለብሔሩ እንዲታገል፤መንግሥትን እንዲያስጨንቅ፤ መብቱን በጉልበቱ እንዲያስከብር የሚያነሳሳ መልዕክት አስተላልፈዋል። ይባስ ብሎም አንዱን ወገን በሌላው ላይ የሚያነሳሳ እና ወጣቱ በስሜት እንዲነድ የሚያደርግ መልዕክት በላይ በላዩ እያስተላለፉ በእሳት ላይ ቤንዚን ሲጨምሩ አስተውያለሁ።

እኒሁ ‹‹ምሁር›› ስለሀገር ፍቅርና አንድት በቃለ ነቢብ የነገሩንና በገሃድ እየፈጸሙት ያለው ተግባር ሌሎችንም የሀገራችንን ምሁር ተብዬዎች በትዝብት እንድቃኛቸው አነሳስቶኛል። አብዛኞቹ ምሁሮች ወይም በዘመኑ አጠራር ኤሊቶች በድሃው ገንዘው ተምረው ወገናቸውን ከድህነት ያላቅቃሉ ተብሎ ሲታሰብ ጭራሽ ድህነቱን የሚያባብሱ ተግባራት ሲከውኑ ይታያሉ።

በቀዬው ድህነቱን ይዞ በሰላም እንዳይኖር አብሮ ከኖረው ጎረቤቱና ሀገሬው ጋር ያለፈ ታሪክ እያወሱ፤ሙት እየወቀሱ ያጣሉታል።የኢትዮጵያ ታሪክ ዛሬ የተፈጠረ ይመስል ታሪክን መነታረኪያ፤መለያያና ሀገር ማፍረሻ ሊያደርጉት ይሞክራሉ። እኒህ ምሁር ተብዬዎች አርሶ አደሩን በበሬ ከማረስ ሳያወጡ በምላሳቸው ጤፍ ሲቆሉ ይገኛሉ።

ሰርክ ከሥራ ይልቅ አንደበታቸውን እያስረዘሙ ጀግና መስለው ለድሃው አርሶ አደር በተቆርቋሪነት ይቀርባሉ። ዘወትር በሚረጩት መርዘኛ መልዕክትም ወገን በወገኑ ላይ እንዲነሳ አንደበታቸውን አሹለው በየማህበራዊ ሚዲያው ይጣዳሉ። በአጠቃላይ ተማርን የሚሉ የዘመኑ ኤሊቶች ከምሁርነት መስፈርት ባፈነገጠ መልኩ በሚከተሉት ጉዳዮች ላይ ተጠምደው ይታያሉ።

ኤሊቶቻችን ከመርህ ይልቅ ተወለድንበት ለሚሉት አካባቢ ወይም ብሔር ይወግናሉ። ምሁራን ከሀገር አልፈው ለዓለም መድህን እንደሆኑ ይታሰባል።ሆኖም የእኛዎቹ ኤሊቶች ከዓለም አቀፍ መድረክ ወርደው፤ ከሀገርም አንሰው መንደር ውስጥ ሲሸጎጡ ይታያሉ። የተወለዱበት አካባቢ የሚፈጠርን መጥፎ ክስተት ወይም ሀገርና ወገንን የሚጎዳ ድርጊት ከማውገዝ ይልቅ እውነትን ጥሰው በሀሰት ለትውልድ መንደራቸው ወግነው ይታያሉ።

እውነትን በመንደር ቅንብበው ፤ለሀሰተኛው ጉዳይ እውነተኛ ካባ አልብሰው ፤እሬቱን ማር ቀብተው ለትውልድ መንደራቸው የሀሰት ጠበቃ ሆነው ይቀርባሉ።ጭራሽ ማዶ ለማዶ ሆነው ከአቻቸው ጋር መርዘኛ ቃላትን ሲወራወሩ ይታያሉ።የትም ሆነ የትም ሊጣሱ የማይገባቸው የወንድማማችነት፤የአብሮነትና የአንድነት መርሆች በጎጠኛ አስተሳሰባቸው ምክንያት በጥላቻ፣በልዩነትና በክፋት ተለውጠው እናገኛቸዋለን።

ሌላኛው የኤሊቶቻችን ባህሪ ደግሞ ከአቀራራቢ ትርክት ይልቅ በሚያለያዩ ትርክቶች ላይ ማተኮራቸው ነው። እኒህ ‹‹ምሁራን›› ያላቸውን የካበተ ዕውቀትና ልምድ ተጠቅመው ሕዝብን ከሕዝብ የሚያስማሙ ትርክቶችን፤ሀገርን ወደ ፊት የሚያራምዱ ሃሳቦችን ማምጣት ሲጠበቅባቸው የጥላቻና የልዩነትን ትርክቶችን እየፈበረኩ ለዘመናት አብሮ በኖረው ሕዝብ መካከል ጥርጣሬንና ፍራቻን ሲፈጥሩ ይታያሉ።

በታሪክ አጋጣሚ የተፈጠሩ ክስተቶችን እየመዘዙ ‹‹ተበድለሃል፤ተጨቁነሃል፤ተጎድተሃል፤ ወ.ዘ.ተ›› የሚሉ ብሶቶችን እያራገቡ በየማህበራዊ ሚዲያው ጥላቻን ሲዘሩ ይውላሉ። ከአንደበታቸው የሚያጣላ እንጂ የሚያስማማ ነገር ጠፍቷል።

ከታሪኮቻችን መካከል አብሮነትን የሚያሳዩ የጋራ ታሪኮችን እየመዘዙ ትውልድ እንዲቀጥልና የነገዋ ኢትዮጵያ ብሩህ እንደትሆን ከመስራት ይልቅ ሀገሪቷን አኬልዳማ ለማድረግ ሲሯሯጡ ይታያሉ። ከእነዚህ ሰዎች ሀገር ተስፋ የምታደርገው ዕውቀትና ልምዳቸውን ተጠቅመው ኢትዮጵያን ለከበቧት ችግሮች መፍትሄ እንዲያመጡ እንጂ ችግር፤ግጭት፤ጦርነት እንዲቀፈቅፉ አልነበረም። ሆኖም እነዚህ ሰዎች እንደጥጥ ቀለው ከተስፋ ይልቅ ስጋት ሆነዋል።

እነዚህ ሰዎች ተማሩ ይባሉ እንጂ እውቀት አጠር ናቸው። ብዙ ጊዜ ከአንደበታቸው የሚደመጠው ስሜት እንጂ እውቀት አይደለም። ምሁር ደግሞ የሚለካው በእውቀቱ እንጂ በስሜቱ አይደለም። እውቀት ያለው ሰው ስሜቱን ይገራል። ስሜት ውስጥ የገቡትን ይመልሳል፤ ወደ ስሜት የገቡ ወጣቶችንም አብርዶ ወደ ተረጋጋ ሁኔታ እንዲገቡ ያደርጋል።

በወቅታዊ ስሜት ሀገር እንደሚፈርስ ስለሚያውቁ እውቀታቸውን ተጠቅመው ስሜቶቻቸውን ይቆጣጠራሉ የትውልድና የሀገር ጉዳይ ስለሚያስጨንቃቸው በወቅታዊ ወላፈን ትኩረትን ማግኘትና መወደስን አይሹም። አላፊ ስለሆነው ወቅታዊ ጉዳይ ሳይሆን ቋሚ ስለሆነው መጪው ጊዜ ይጨነቃሉ። የእኛዎቹ ጉዶች ግን ለዛሬ ብቻ የሚኖሩ ናቸው።ዛሬ እነሱ ከተጠቀሙና ጊዜያዊ ሙገሳ ካገኙ ስለመጪው ትውልድ የሚገዳቸው ነገር የለም።

ሌላኛው የእነዚህ ወገኖች ባህሪ ደግሞ ሕዝብ ሳይሾማቸው የሕዝብ ጠበቃና ተከራካሪ ሆነው ራሳቸውን መሾማቸው ነው። ሕዝብ ሳይሾማቸው ለሕዝብ ቆመናል የሚሉ ቡድኖችና ፖለቲከኞች ችግርን በሰላማዊ መንገድ ከመፍታት ይልቅ ነውጠኛ ደጋፊዎችን የማሰባሰብ ሴራ ውስጥ ስለሚገቡ፣ በኢትዮጵያ እዚህም እዚያም ግጭቶች በርክተው ይታያሉ።

እነዚሁ ኃይላት ኃላፊነት የጎደላቸው ስለሆኑም ግጭትና መገዳደልን ጨምሮ የሀገርን ተስፋ የሚያጨልሙ ድርጊቶች እንዲበራከቱ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ለሀገርና ለሕዝብ ከማሰብ ይልቅ ከመጠን ያለፈ ራስ ወዳድነት ስለተጠናወታቸውም ቆመንለታል ለሚሉት ሕዝብ የአዞ እንባ ከማንባት የዘለለ ተግባር ሲፈጽሙ አልታዩም።

እነዚህ የግጭት ነጋዴዎች ከመተማመን ይልቅ ጥርጣሬ፣ ከትብብር ይልቅ መገፋፋት፣ በግልጽ ከመነጋገር ይልቅ መተማማት ስለሚቀናቸው የማህበራዊ ሚዲያዎች እና ሌሎች የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም ሕዝቡን አላስፈላጊ ወደ ሆነ ጥርጣሬ ውስጥ በመክተት አንዴ በብሔር ሌላ ጊዜ በሃይማኖት እየከፋፈሉ የዘመናት አብሮነቱን ሊነጥቁት ሲሯሯጡ ይታያሉ። በእነዚህ ስግብግቦች የተነሳ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከባድ ጊዜን ለማሳለፍ ተገዷል።

‹‹ምሁሮቻችን›› ወይም ኤሊቶቻችን እንደብሂል ከያዟቸው ዘመን አመጣሽ መገለጫዎቻቸው ውስጥ በመንግሥትና በሌሎች አካላት የሚከናወኑ ተግባራትን ማጣጣልና ማጥላት አንዱ ነው።በማጥላላትና ማንቋሸሽ ዕውቅናን ለማግኘትና እውቀታቸውንም ለመግለጥ ሲጣጣሩ ይታያሉ። ማንቋሸሽን እና ማጥላላትን እንጂ ስለሚያንቋሽሹት ነገር እንኳን በቂ ዕውቀት የላቸውም። ወይንም ደግሞ ያንቋሸሹት ነገር እንዴት እንደሚሻሻል እንኳን የመፍትሔ ሃሳብ ወይም አማራጭ አያቀርቡም።

እነዚህ ሰዎች ችግኝ ተከላን ያንቋሽሻሉ፤ የድሃ ቤት ማደስን ያጥላላሉ፤ለድሆች ማዕድ ማጋራትን ይቃወማሉ፤የግብርና ሥራን ያጣጥላሉ፤ የቱሪዝም መዳረሻዎች ሲስፋፉ ይኮንናሉ። ብቻ የተሰሩ ነገሮችን በሙሉ ይቃወማሉ።ያጥላላሉ፤ ያንቋሽሻሉ።ይህም እንደሙያ ተቆጥሮላቸው ምሁራን ይባላሉ።

ሌላኛው ጎናቸው ደግሞ ከተማሩበትና ከሰለጠኑበት ውጭ በሁሉም ዘርፍ ውስጥ በመግባት መተንተን ይፈልጋሉ። አላውቀውም ወይም አይመለከተኝም የሚሉት ነገር የለም።ጋዜጠኛ ወይም ዩቱዩበር ነኝ የሚል ሁሉ በጠየቃቸው ቁጥር ለማብራራት ወይም ለመተንተን አያመነቱም። ዋነኛ አላማቸውም የተናገሩትን ተናግረው የማህበራዊ ሚዲያዎች አጀንዳ መሆን ብቻ ነው። ስለዚህም ስለተጠየቁት ነገር አወቁትም፤ አላወቁትም አንደበታቸው ያመጣላቸውን ነገር ከመናገር አይመለሱም።

ሌላኛው ገጽታቸው ደግሞ የመንግሥት ባለስልጣናትም ሆኑ ሌሎች ታዋቂ ሰዎች የሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች በቁንጽል በመውሰድ የመነጋገሪያ አጀንዳ ለመፍጠር መሞከራቸው ነው። መልዕክቶችን ከተነገሩበት አውድ ውጪ ቀንጭቦ በመውሰድ ተናጋሪዎችን ለማብጠልጠልና ለማሳነስ ይሞክራሉ። ባልዋሉበት የስብሰባ አዳራሽ ወይም የውይይት ቦታ ተንታኝና ምስጢር አዋቂ ሆነው ቁጭ ይላሉ።

ቅንጭብ ሃሳብ ላይ ተመስርተውም ሴራ ተንታኝና አዋቂ መስለው ይቀርባሉ። እነዚሁ ኤሊቶች ከኢትዮጵያ ጀምሮ እስከ ዓለም ጫፍ ያሉ ሴራዎችን ያለምን ሀፍረት ለመተንተን ይተጋሉ። በአጠቃላይ በአሁኒቷ ኢትዮጵያ በየማህበራዊ ሚዲያው ቀን ከሌሊት ተጥደው የሚታዩት ‹‹ምሁራን›› እና ኤሊቶች ሁኔታ ደስ የሚል አይደለም።

በእያንዳንዱ የዕለት ተዕለት ጉዳይ ሳይቀር ከመተማመን ይልቅ ጥርጣሬ፣ ከትብብር ይልቅ መገፋፋት፣ በግልጽ ከመነጋገር ይልቅ መተማማት፣ በማስረጃ ላይ ተመሥርቶ ውሳኔ ላይ ከመድረስ ይልቅ ባልተጣራ መረጃ መፈራረጅና የመሳሰሉት ከንቱ ነገሮች ጎልተው ይታያሉ። በማኅበራዊ የትስስር ገጾችና በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች በሚስተዋሉ ሽኩቻዎች ከሀገር አንድነት ይልቅ፣ ሀገርን ለመበተን የሚጎሻሸሙ ተቃርኖዎች ከመጠን በላይ በርክተው ይስተዋላሉ።

ነፍጥ ካነገቡ ጦር ሰባቂዎች ባልተናነሰ ሁኔታ አሁን በኢትዮጵያ ለሚታዩት ግጭቶች፤አለመረጋጋቶች፤ስደትና መፈናቀል ጥራዝ ነጠቅ ምሁሮቻችንና ኤሊቶቻችን የራሳቸውን ድርሻ ይወስዳሉ። ባሉት ችግሮች ላይ ተጨማሪ ችግሮች በመቀፍቀፍ ላይ የተጠመዱት እነዚሁ ወገኖችም፣ አንድ ጉዳይ ላይ አጽንኦት ቢሰጡ መልካም ነው።

የሚፈልጉትን ዓላማ ለማሳካት ሲነሱ፣ የሕዝብን ሕይወትና የሀገርን ህልውና አደጋ ውስጥ ከሚከት ድርጊት መታቀብ አለባቸው። በእነሱ ምክንያት ንጹሐን ሲገደሉ፣ ንብረታቸው ሲዘረፍና ሲወድም፣ ሲፈናቀሉና የሀገር ሰላም ሲታወክ ለጊዜው ከሕግ ተጠያቂነት ቢያመልጡም፣ ከታሪክ ተጠያቂነት የሚታደጋቸው ግን አይኖርም።

አዲስ ዘመን ነሃሴ 17/2015

Recommended For You