ለሰላም ቅድሚያ እንስጥ!

 በሰው ልጆች የዕለት ተዕለት ተግባር ውስጥ ከምንተነፍሰው አየር ያልተናነሰ ዋጋ ያለው ነገር ቢኖር ሰላም ነው፡፡ ሰላም ከሌለ ስለ መጪው ማሰብም ማቀድም አይቻልም፡፡ ሰላም የሁሉም ነገር ዋስትና ከመሆኑም በላይ እንደ ሰው ሠርቶ ለመለወጥ፣ ወልዶ ለማሳደግ፣ ወጥቶ ለመግባት፣ እጅግ ወሳኝ ነገር ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን ደግሞ ዓለም የሚያውቀን በሰላም ወዳድነታችን ችግሮችን ተቋቁሞ ለማለፍ ባለን ጥንካሬ ከሁሉ በላይ ደግሞ ከእኔ ችግር የወንድሜ ይበልጣል እሱ ያግኝ ቀጥሎ እኔ አገኛለሁ፤ በሚለው ፈሪሃ እግዚአብሔር በተላበሰው አስተሳሰባችን ነው::

ይህ ሁኔታ ግን ዛሬ ዛሬ ባልተገባ መልኩ እየተሸረሸረ ሰላም ወዳድ ሀገሩን ከጠላት ለመጠበቅ ተኝቶ የማያድረው ዜጋችን እርስ በእርሱ ችግር ውስጥ እየገባ እያየን ነው:: ለዚህ ደግሞ ትልቁ ምክንያት ያ በመልካም አስተሳሰብ ፈጣሪን በመፍራትና በማክበር ታንጾ የነበረው ስብዕናችን ከዕለት ዕለት እየተሸረሸረ በመምጣቱ ይመስለኛል::

በሀገር ደረጃ ባለፉት ዓመታት ሰላማችን በተለያዩ ምክንያቶች ጥላሸት ሲለብስ እዚህም እዚያም በአባባሽ ችግሮች ስንወጠር ወገን ባልተገባ መንገድ ሕይወቱን ሲያጣ እየተመለከትን ልባችንም እየተሰበረ አሁን እኛ የድሮዎቹ ኢትዮጵያውያን ነን እያልን ቆዝመናል:: ከዚህ ቁዘማችን ወጥተንም መፍትሔ ቢሆን በማለት የሰላም ሚኒስቴር እስከ ማቋቋም የደረሰ ጥረት አድርገናል።

በተለይም ሰላም ያሰፍናል ተብሎ በተቋቋመው ሰላም ሚኒስቴር አማካይነት ማኅበረሰቡን ያሳተፈ የዳበረ ዴሞክራሲን የማጽናት፣ የላቀ ብሔራዊ መግባባትን የመፍጠር፣ የሰላም ግንዛቤና ሁለንተናዊ ተሳትፎን የሚሳደግ የውይይት መድረኮች ስናካሂድም ቆይተናል።

በተጨማሪም ማኅበራዊ ሀብቶቻችንንና ባህላዊ እሴቶቻችንን በመገንባት ሂደት በተለይም የሰላም እናቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት ተቋማት በባለቤትነት እንዲሳተፉና እንዲያግዙ በማድረግ ለዘላቂ ሰላም ምቹ ምህዳር ለመፍጠርም ብዙ ርቀት ተሂዷል።

ከሲቪክ ማኅበረሰቡ ጋር በመሆን ሰላምን በማስፋፋት፣ ግጭትን በመከላከልና ዴሞክራሲን በማስፈን ላይ በቅንጅት ለመሥራትም ተሞክሯል። ነገር ግን እነዚህ ሁሉ ጥረቶች ፍሬ እያፈሩ አይደለም:: አሁን አሁን የቱ ጋ ነው ችግራችን? ፍላጎታችንስ ምንድን ነው? የሚለው ነገር ግራ የሚያጋባ እስከመሆን ደርሷል::

ከጥንት ጀምሮ ማለት ይቻላል ኢትዮጵያ ውስጥ ጦርነት ባልነበረባቸው ዘመናት ሁሉ፣ ለግጭት የሚዳርጉ ቅራኔዎች በሕዝቡ ውስጥ መብላላታቸው የተለመደ ከመሆኑም በላይ አንዳንዶቹ ጊዜ ጠብቀው ለግጭት መንስኤ ሲሆኑም አይተናል፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ ቅራኔን በመነጋገርና በውይይት ከመፍታት ይልቅ በኃይል መፍትሔ መፈለጉ እንዲለመድ ያደረገውም ይመስለኛል፡፡

ግን እኮ አባባሉም እራሱ «እንኳን ሰውና ሰው ዕቃ ከዕቃ ይጋጫል» አይደል የሚለው፤ በመኖር ሂደት ውስጥ ግጭት ተፈጥሯዊም ተለምዷዊም ነው:: ግን ሰው ተብለን እስከተፈጠርን ድረስ ማገናዘቢያችንን በማሠራት የቱ ግጭት ነው ሊያጋጨኝ የሚችለው እንዴትስ ባልፈው ነው ለትውልዴ ቁርሾን የማላስቀምጠው ብሎ ማሰብ ከምንም በላይ አስፈላጊ ይመስለኛል::

በኢትዮጵያ ታሪክ ግጭቶች ሌላ ግጭት እየወለዱ የግጭት አዙሪት ውስጥ ተነክረን ሰላም አልባ ዘመናትን እንድናሳልፍ የተፈረደብን እንመስላለን፡፡ በተለይ የእርስ በእርስ ግጭቱ እየተራዘመ በመጣ ቁጥር ከግጭቱ የሚያተርፉ አካላት እየበረከቱ ስለሚመጡ ለቀጣዩ ግጭት መፈጠር በር እየከፈቱ ስለመሄዳቸውም ቆም ብለን ማሰብ ያስፈልገናል፡፡

ለዘመናት ሲዘሩ የቆዩ የጥላቻና የመከፋፈል ዘሮች ፍሬ አፍርተው ኅብረተሰባችንን ያስተሳሰሩት ክሮች እየላሉና እየተበጣጠሱ የመጡበትና ተስፋ መቁረጥ የተንሰራፉበት ጊዜ ተከስቷል፤ ይህ ሁኔታ ደግሞ ከበድ ያሉ መንገራገጮችን ልንቋቋም የማንችልበት ደረጃ ላይ አድርሶናል ማለት ይቻላል፡፡ ይህም ሁኔታ በራሱ «ምክንያታዊ» ሆነን ሰላምና የሰላም መንገድ አማራጭ የሌለው መሆኑን ያሳየናል፡፡

በዚህ ረገድ መንግሥት ፍትሃዊነትን በማስፈን፣ ዴሞክራሲን በማስረፅ፣ የፍትሕ ተቋማትንም ገለልተኛ እንዲሆኑ በማድረግ ለዜጎች ሰላም ትኩረት መስጠቱ እንደተጠበቀ ሆኖ በሰላም ዙሪያ የሚሠሩ አካላት የሃይማኖት ተቋማት፣ የሀገር ሽማግሌዎች ሰላምን ለማስፈን ከእኛ ምን ይጠበቃል? ብለው ራሳቸውን በመጠየቅ ተግተው መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡

በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ስለ ሰላም የተሠሩ ሥራዎችን የተመለከትን እንደሆነ ለሰላም የተከፈለውን ዋጋ በእጅጉ እንድናይ ያደርገናል። የሕንድ የነፃነት አባት የሆኑትን ማህተመ ጋንዲን ስናነሳ ፀረ-ቅኝ አገዛዝ ትግሉን በድል የተወጡት በሰላማዊ መንገድ ነው፡፡ ሰላማዊ ትግል ዋጋ እንደሚያስከፍል የታወቀ ቢሆንም ምናልባት ጦርነት ከሚያስከፍለው ግን የሚበልጥ አይመስለኝም፡፡

ዋናው ነገር ግን በሰላማዊ መንገድ የተገኘ ድል ዘላቂነት እንዳለው ጠንቅቆ መረዳቱ ላይ ነው፡፡ ይህ ብቻም አይደለም ሰላማዊ ትግል የማካሄድ እንቅስቃሴ የሚመሠረትበት መርህ ከሰው ልጅ የኑሮ ግብና ዓላማ፣ ከሕይወት ምንነት፣ ከሰላምና ጦርነት በተቃራኒው ሲታይ የሰላም መንገድ ሚዛን ስለሚደፋ ነው፡፡

በጉልበት የተገኘ ድል ጊዜያዊ ስለሆነ ከሽንፈት እኩል የሚወሰድ ነው ለእኔ፡፡ «ጨለማ ጨለማን አያስወግድም፤ ጨለማን የሚያስወግድ ብርሃን ብቻ ነው» ይባላል፡፡ ይህ ማለት ለእኔ ጥላቻ ጥላቻን አያጠፋም፤ ፍቅር ጥላቻን ያጠፋል፤ እንደማለት ነው::

ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ምን ያህል ሰላም ወዳድ እንደሆኑ መናገር ለቀባሪው እንደማርዳት ነው፡፡ ለአብነትም ባለፉት ዓመታት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ገብተንበት በነበረው ጦርነት ወቅት ሲሰጡ የነበሩ የሰላም አማራጮችን መመልከት ይቻላል፡፡ አራት አምስት ጊዜ የሰላም አማራጮች ሲቀርቡም ስለመስማታችን እማኞች ነን፤ ይህ የሚያሳየው ኢትዮጵያውያን በየትኛውም ጊዜና አጋጣሚ እጃቸውን ለሰላም ከመዘርጋት ተቆጥበው የማያውቁ ሕዝቦች መሆናቸውን ነው።

አሁንም ልናስብ የሚገባን ነገር ከጦርነት አንዳችም እንደማናተርፍ ነው:: ይልቁንም ጦርነት ውስጥ በገባን ልክ አምራች የሆነውን ወጣት ኃይላችንን እያረገፍን߹ ኢኮኖሚያችንን እያደቀቅን ከመሄድ ያለፈ ትርፍ ለእኔ አይታየኝም፡፡ ሰላምን ለማምጣት ከታሪካዊ ቅራኔዎቻችን ይልቅ ለታሪካዊ መግባባታችን ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል፡፡

በእርግጥ ኢትዮጵያ ሰላም፣ ፍቅርና ብልፅግና ትመኛለች፡፡ ለዚህ ምኞት ተግባራዊነትም ኢትዮጵያዊ በሙሉ እንደ እህትና እንደ ወንድም በአንድነት ለመነጋገር፣ ለመሥራት እንዲሁም በጋራ ለመጠቀም በንጹህ ልቦና መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ በመሆኑም የጋራ አሸናፊነት መሣሪያ የሆነውን ሰላም ማንገብ ጠቀሜታው የጎላ በመሆኑ የግጭት ነጋዴዎች ቆም ብለው ሊያስቡ ይገባል። አበቃሁ !

በእምነት

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 14/2015

Recommended For You