ለአንድ አገር ኢኮኖሚያዊ እድገት የንግዱ ዘርፍ ትልቅ ድርሻ አለው። ከጉልት ጀምሮ እስከ ጅምላና ችርቻሮ እንዲሁም እስከ አስመጪና ላኪ ደረጃ ያለው የንግድ ሰንሰለት ለአገሪቷ ኢኮኖሚ መነቃቃትም ሆነ መቀዛቀዝ አበርክቶው ጉልህ ነው። የንግዱ ዘርፍ ከማህበረሰቡ የዕለት ተዕለት ኑሮ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ እንደመሆኑ በህግ፣ በፖሊሲና በመመሪያ ተደራጅቶ መመራት እንዳለበት ይታመናል። ከዚህ ጋር ተያይዞ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታትና ዘመናዊና ጤናማ ስርዓትን ለማስፈን ልዩ ልዩ ተግባራትን ማከናወን እንደቻለ የ2015 በጀት ዓመት የእቅድ ክንውን ሪፖርት ያመለክታል።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በሚዛን አማን ከተማ በተካሄደ መድረክ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚንስትር አቶ ገብረ መስቀል ጫላ በተገኙበት የ2015 በጀት ዓመት አፈጻጸም በተገመገመበት ወቅት ለንግድ ስርዓቱ ወሳኝ የሆነው ፖሊሲና የጥራት ፖሊሲን ማዘጋጀት በተመለከተ የተከናወኑ አበይት ተግባራት ቀርበው ነበር።
‹‹ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ የንግድ ሚኒስቴር ያላት ብትሆንም እራሱን የቻለ የንግድ ፖሊሲና የጥራት ፖሊሲ ያልነበራት አገር ናት›› ያሉት የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚንስትሩ አቶ ገብረመስቀል ጫላ፤ በበጀት ዓመቱ እነዚህንና ሌሎች ፖሊሲዎችን አጠናቅቆ ማዘጋጀት እንደተቻለና ለመንግሥት መቅረባቸውንም ተናግረዋል። በተለይም የንግድ ሥርዓትን ከማዘመን አሰራሮችን ህጎችን ከማሻሻልና ፖሊሲ ከማውጣት አንጻር በርካታ የተሰሩ ሥራዎች ተተግብረዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ዋነኛ ዓላማው የንግድ ስርዓቱን ግልጽ፣ ዘመናዊ፣ ፍትሃዊና ውድድርን ያማከለ የንግድ ስርዓትን ማስፈን፤ እንዲሁም የጥራት ደረጃውን የጠበቀ ንግድን በማስፋፋት ለአገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ለህዝብ ተጠቃሚነት ከዘርፉ የሚጠበቀውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሆነ ነው። በመሆኑም በበጀት ዓመቱ ተቋማዊ የማስፈጸም ብቃት ለማሻሻልና የዘመነ የንግድ ስርዓት ለመገንባት በተጀመረው የለውጥ (የሪፎርም) ሥራ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ጠቅሰዋል።
አገራዊና ዓለማቀፋዊ የሰላም ሁኔታው በጦርነትና በግጭት የታጀበ በመሆኑ በምርቶችና አገልግሎቶች ዝውውርና አቅርቦት ላይ እጥረት ስለመፈጠሩ የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ ይህንን ተከትሎም በአገር ውስጥ ከፍተኛ የዋጋ ንረት መከሰቱንና የኑሮ ውድነት ማሻቀቡን አንስተዋል። እነዚህ ችግሮች ተደራርበው የህብረተሰቡን የመግዛት አቅም ከመፈታተን ባለፈ መንግሥት ላይም የፈጠረው ጫና ፈታኝ ቢሆንም እነዚህን ተግዳሮቶች በመቋቋም በዚሁ ጊዜ ውጤት ማስመዝገብና የንግድ ሥርዓቱን ማስቀጠል መቻሉ በበጀት ዓመቱ የተመዘገበ ውጤት ስለመሆኑ ነው ያስረዱት።
ተቋማዊ የማስፈጸም አቅምን ከማሻሻል ባለፈ የንግድ ጥራት አሰራርን ለማሻሻል በነበረው ፍላጎትና የተሰጠው ትኩረት አስመልክቶ ገለፃ ያደረጉት ሚኒስትሩ፤ የኢትዮጵያ ደረጃዎች አዋጅ፣ ህጋዊ የሰነድ ህግ አዋጅ፣ የተስማሚነት ምዘና ደንብ ማሻሻያ፣ የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት ማሻሻያ ደንብ፣ የኢትዮጵያ ስነ ልክ ደንብ አዋጅ እንዲሁም የተለያዩ አዋጅ መመሪያዎችና ደንቦችን ተሻሽለው ቀርበዋል። አገራዊ ቀልጣፋ፣ ዘመናዊና ተደራሽ የንግድ አሰራርና የሸማቾች ጥበቃ ስርዓት በመዘርጋትና በመቆጣጠር ረገድ ፍትሀዊና ውድድርን ያማከለ የንግድ አሰራርና የግብይት ስርዓት ለማስፈን ትኩረት ተሰጥቶት የተሰራ ሥራ ስለመኖሩ ያነሱት ሚኒስትሩ፤ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ ኢንስፔክሽን ማሻሻያ ተደርጎባቸው ወደ ሥራ መግባት የተቻለ እንደሆነ ተናግረዋል።
በአገር ውስጥ ከሚገኙ 1 ሺህ 187 የንግድ ምዝገባና አገልግሎት ፈቃድ መስጫ ጣቢያዎች መካከል 1 ሺህ 92 ወይም 92 በመቶ የሚሆኑትን በወረዳ ማስተሳሰር የተቻለ ሲሆን፤ በይነ መረብን ተጠቅመው በኦን ላይን አገልግሎት ለሚሰጡ ጣቢያዎች የማሻሻል ሥራ ተሰርቷል። ይህም የንግዱን ማህበረሰብ የመረጃ ልውውጥ አሰራር ከማሳለጥ አኳያ የኦንላይን አገልግሎቱን በአንድ መስኮት አገልግሎት አሰራር ጋር ማስተሳሰር በመቻሉ አበረታች ውጤት ማስመዝገብ እንደተቻለ ነው የተናገሩት።
በበጀት ዓመቱ ሁለት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት ታቅዶ ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን በመፈጸም 94 በመቶ ማሳካት መቻሉን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን የኦንላይን አገልግሎት በመስጠትም የኦንላይን ሽፋን አገልግሎቱን ወደ 50 በመቶ ማሳደግ እንደተቻለ ነው ያስረዱት።
በአሁን ወቅት የኤሌክትሮኒክስ ንግድ አሠራር ትግበራ እየተጠናከረ መምጣቱን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ ይህም ለንግዱ ማህበረሰብ ውጣ ውረድን ወጪና የጊዜ ብክነትን የሚቀንስለት እንደሆነ ነው ያስረዱት። የኤሌክትሮኒክስ ንግድ በተለይም ከንክኪ የጸዳ አገልግሎትን ለመስጠትና ለብልሹ አሰራርና ለመልካም አስተዳደር ችግር ተጋላጭነትን በተጨባጭ በመቀነስ አይነተኛ ድርሻ ያለው እንደሆነ አመልክተዋል።
በአገሪቷ ለተከሰተው የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ችግር የፈጠረውን ጫና ከንግድ አሰራር አኳያ ለማቃለል የመፍትሔ እርምጃ መወሰዱን ያነሱት ሚኒስትሩ፤ የቅዳሜና እሁድ የግብይት ማዕከላትን ማስፋፋት እንዱና ዋነኛ መፍትሔ እንደሆነ ጠቅሰው፤ የገበያ ማዕከላቱን በማስፋፋት በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች በቀጥታ የሚገናኝባቸው ገበያዎች በአሁን ወቅት 650 የደረሱ ሲሆን እነዚህ ገበያዎች በየከተሞቹ መኖራቸውን ተናግረው በዚህም አምራቾችንና ሸማቾችን በቀጥታ ማገናኘት ተችሏል ነው ያሉት።
ሸማቹ በአቅራቢያው የሚያገኘውን ገበያ ተጠቅሞ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ የመሸመት ዕድል ያገኘ ሲሆን፤ በአንድ ከተማ ውስጥ በመደበኛ ገበያና በሰንበት ገበያ በሚቀርቡ የምርቶች ዋጋም ግልጽና ተጨባጭ የሆነ ልዩነት ማየት የሚቻል እንደሆነ ጠቅሰው ይህም ከአገር ውስጥ ንግድ አንጻር መሰረታዊና አበረታች ለውጥ የታየበት የንግድ ስርዓት እንደሆነ አመላክተዋል። በመሆኑም የተጠቃሚውን ማህበረሰብ ብዛትና ፍላጎት ያማከለ የግብይት ስርዓት እንዲፈጠርና የገበያ ትስስር እንዲጠናከር በማድረግ የኑሮ ውድነቱ ከቁጥጥር ውጭ እንዳይወጣ ጉልህ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን አስረድተዋል።
በተጨማሪም የነዳጅ ሪፎርም ተጠናክሮ እንዲቀጥል የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በርካታ ሥራዎችን እንደሠራ ያነሱት ሚኒስትሩ፤ በተለይም ድጎማን ከማስቀረትና ወደ ዋጋ ማረጋጊያ ፈንድ ከመመለስ እንዲሁም አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ከመደጎምና የነዳጅ ብክነትንና ህገ ወጥነትን ከመከላከል አንጻር ትርጉም ያለው ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ እስከ ግንቦት ወር መጨረሻ ድረስ 66 ነጥብ 81 ቢሊዮን ብር የታክስ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን እና በየወሩ የነበረውን የ10 ቢሊዮን ብር ተሰብሳቢ የዕዳ መጠን መቀነሱን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ በሰኔ ወር ከዕዳ ኪሳራ ነጻ መሆን እንደተቻለ ተናግረዋል። አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ከመደጎም አኳያ አፈጻጸሙ 15 ነጠብ 15 ቢሊዮን ብር መድረስ ተችሏል። በሌላ በኩል የዲጂታል ግብይትን ተግባራዊ ማድረግ በመቻሉ የተገኘ ውጤት ስለመኖሩ ሲናገሩ፤ የነዳጅ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ከጎረቤት አገራት ጋር ተቀራራቢ መሆኑን እና በዚሁ ምክንያትም በህገወጥ መንገድ ይወጣ የነበረውን የነዳጅ መጠን ትርጉም ባለው መንገድ መቀነሰ እንደተቻለ ነው ያብራሩት።
በበጀት ዓመቱ ከፍተኛ ርብርብ የተደረገበት የዕቅድ ግብ አገራዊ የወጪ ንግድን ማስፋትና ማሳደግ እንደነበር የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ በዚህ ረገድም በርካታ ሥራዎች የተሠሩ እንደሆነ ነው የገለጹት። እሳቸው እንዳሉት፤ የኤክስፖርት ምርቶችን በዓይነት፣ በመጠንና በጥራትና በገቢ የማሳደግ፤ የዕቃዎችንና የሸቀጣ ሸቀጦች የወጪ ገቢ ንግድ በማሳደግ የማኑፋክቸሪንግና የግብርና ምርቶች የወጪ ንግድ ገቢ አፈጻጸምን ለማሻሻል ጥረት ተደርጓል። በመሆኑም በዘመናዊ የምርት ግብይት ስርዓት የታቀፉ የምርት አይነቶችን ለማሳደግ በሚያስችሉ ሥራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል።
የግብርና ምርቶች የወጪ ንግድ የወልና የኢንቨስትመንት እርሻ አፈጻጸም መመሪያ ላይ የሪፎርም ሥራ ተሠርቷል። በዚህም ቀደም ሲል በዘርፉ የነበሩ ማነቆዎችን መፍታት የተቻለ ሲሆን፤ በተለይም ከቅባት እህልና ከጥራጥሬ ምርት ወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ እንዲጨምር አስተዋጽኦ ያደረገ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ ባለሃብቶች በእርሻ ስራቸው ሰሊጥ፣ ቦሎቄና የተለያዩ ጥራጥሬዎችን ያለማሉ። ነገር ግን ከዚህ ቀደም በነበረ የአሰራር ክፍተት እነዚህን ምርቶች ከገበያም ጭምር ገዝተው የሚያቀላቅሉና ምርቱ ወደ ውጭ ከወጣ በኋላ የሚመለስበት አጋጣሚ እንደነበር አስታውሰዋል።
ይሁንና በአሁን ወቅት ባለሃብቱ ትክክለኛ አምራች መሆኑ እየተረጋገጠ ምርቱ ወደ ውጭ ገበያ የሚወጣበት አሰራር ተዘርግቷል። በቅባት እህልና በጥራጥሬ ወጪ ንግድ ለለፉት ሶስት ዓመታት ከነበረው አፈጻጸም በመጠንም ሆነ በዋጋ በጣም ከፍተኛ ገቢ ማግኘት መቻሉንና ይህም በሌሎች ምርቶች ማለትም በወርቅና በጫት ማግኘት ያልተቻለውን ገቢ ከዚሁ ከቅባት እህልና ጥራጥሬ ማግኘት በመቻሉ ማካካስ እንደተቻለ ነው ያብራሩት።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የገበያ ማፈላለግና የትስስር ሥራዎችን ማሳደግ እንዲሁም የምርት መዳረሻ አገራትን ቁጥር በማስፋት የወጪ ንግድ ገበያን የማሳደግ ሥራዎች ተከናውነዋል። ከእነዚህ ተግባራት መካከልም ለወጪ ንግድ ትርዒት ዝግጅት ፈቃድ መስጠት፣ ኤግዚቢሽንና ኮንፈረንስ ማዘጋጀት፣ የበይነ መረብ ማስታወቂያ ንግድ መድረኮችን ማካሄድ ይጠቀሳሉ። እነዚህ ስራዎች ትምህርት የተወሰደባቸው ከመሆናቸው በላይ በቀጣይ መጠኑንና ተደራሽነቱን በማስፋት ለላቀ ውጤት መሥራት እንደሚገባ ማሳያዎች ናቸው ብለዋል።
አለማቀፋዊ፣ አህጉራዊና ቀጠናዊ ግንኙነትን በማጠናከር እንዲሁም ውህደትን በመፍጠር አገራዊ ተጠቀሚነትን ለማሳደግ ቀጠናዊ ትስስርን ማስፋት የግድ እንደሆነ ያነሱት ሚኒስትሩ፤ እንዲህ አይነት የገበያ ዕድሎችን ለማስፋት የተለያዩ ጥረቶች መደረጋቸውን እና የአፍሪካ ተገማች የገበያ ዕድል ለመፍጠር በበጀት ዓመቱ ከተሰሩ ሥራዎች መካከል ግንባር ቀደም እንደሆነ ነው ያስረዱት።
የዓለም ንግድ ድርጅትን በመቀላቀል እንዲሁም የኮሜሳ ነጻ ንግድ ቀጠና ሙሉ አባል ለመሆን ባይላተራል ንግድ ትስስር በመፍጠር፣ በማጠናከርና የገበያ ዕድልን በማስፋት ከጎረቤት አገራት ጋር የተቀላጠፈ የድንበር ንግድ ስምምነት በመፈራረም ህጋዊ የንግድ ስርዓት ማስፈን የሚያስችሉ ተግባራትም በበጀት ዓመቱ ተከናውኗል።
በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ አምስት ነጥብ 21 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ ሶስት ነጥብ 64 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በማግኘት የዕቅዱን 69 ነጥብ ስምንት በመቶ መፈጸም እንደተቻለ የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ ለዚህ ውጤት ግብርና 79 በመቶ ማኑፋክቸሪንግ ኢንደስትሪ 11 ነጥብ 79 በመቶ፣ ማዕድን ስድስት ነጥብ ዘጠኝ በመቶ፣ እንዲሁም ኤሌክትሮኒክስና ሌሎች የኤክስፖር ምርቶች ሶስት በመቶ ድርሻ ያላቸው መሆኑን ተናግረው፤ አፈጻጸሙ ካለፉት በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ቅናሽ ማሳየቱን ነው የተናገሩት።
እሳቸው እንደሚሉት፤ በበጀት ዓመቱ የተመዘገበው ውጤት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 487 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወይም 11 ነጥብ ስምንት በመቶ የገቢ ቅናሽ አሳይቷል። የወጪ ንግድ ገቢ አፈጻጸም ቅናሽ ካሳየባቸው ምክንያቶች መካከል በአንዳድ ምርቶች ላይ የዓለም ገበያ መቀዛቀዝ፣ የህገወጥ ንግድ እንቅስቃሴን መግታት አለመቻል፣ ምርትን በክምችት መያዝ፣ የጸጥታ መጓደል በአቅርቦት ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ እና በቅንጅት ያለመስራት ችግሮች በዋነናነት የሚጠቀሱ ናቸው።
የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ከመከላከልና ገበያን ከማረጋጋት አንጻር እንዲሁም ወጪ ንግድን ለማሳደግ በቀጣይ በ2016 ዓ.ም ትኩረት የሚደረግባቸው ተግባራትን አስመልክቶ በተለየ ሁኔታ የቅዳሜና እሁድ ገበያን ማጠናከር ዋነኛው ትኩረት የሚሰጠው እንደሆነ ሚኒስትሩ አንስተው፤ ለዚህም ባሉት ከተሞች ልክ የገበያ ማዕከላቱን ማስፋትና የአገር ውስጥ ንግድ በነጻ እንዲንቀሳቀስ የማድረግ ሥራ የሚሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከወጪ ንግድ ጋር በተያያዘ ትልቁ ችግር ህገወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ መሆኑን ጠቅሰው በጫት፣ በማዕድንና በቁም እንስሳት ንግድ ኮንትሮባንድ ትልቅ ማነቆ በመሆኑ እነዚህ ምርቶች በወጪ ንግዱ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ፈጥረዋል። ስለዚህ ክልሎችን ጨምሮ መላው ህዝብ ለአገር ኢኮኖሚ አለኝታ የሆነውን የወጪ ንግድን እንዲደግፍና በኮንትሮባንድ ንግድ ወጥ የሆነ አቋም እንዲያዝ የማድረግ ሥራ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ዋና ሥራ ይሆናል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 17/2015