ለሀገርም ለሕዝብም ፈውስ እንሁን!

ለዓመታት የተሰበኩ የልዩነት ትርክቶች ኢትዮጵያዊ ስሜታችንን እየጎዱ ቁልቁል አንደርድረውን ብሔራዊ ስሜታችን እያሽቆለቆለ መንደርተኝነት እንዲያገነግን አድርገው ቆይተዋል። ይህ ሁኔታ ዛሬ ዛሬ በሀገራችን እየታዩ ላሉት ግጭቶች ዋነኛ መንስዔ መሆኑም ከማንም አይሰወርም። የከፋፋዩ ትርክት ሰለባ የሆኑ ግለሰቦች መንደርተኝነታቸውን አብዝተን ከማፍቀራቸው የተነሳ እየፈጠሩ ያሉት ችግር አሁን ድረስ ብዙ ዋጋ እያስከፈለን ይገኛል።

መንደር ስል መቼም ይገባችኋል ብዬ እገምታለሁ፤በላያችን ላይ ያጠርነውን የክልል አጥር ለማለት ነው። ጉዳዩ መንደራችንን ለምን ወደድን አይደለም። ነገር ግን ሁሉም ነገር ጊዜና ቦታ አለው ከጋሪው ፈረሱ ከቀደመ ወደፊት እያሰብን የተገላቢጦሽ ወደኋላ መሄዳችን የማይቀር ነው።

አዎን እኛ በባህልና እምነቶቻችን የማንደራደር ዜጎች ነን። ልክ እንደዚሁ አባቶቻችን ያስተማሩን አንድ ሌላ ግዙፍ እምነት አለን። ይሄውም በየትኛውም ጊዜና ሁኔታ ውስጥ በሀገራችን የማንደራደር መሆንን ነው። ኢትዮጵያዊ በሀገርና በእርስቱ. የሚባለው ለዚህም ነው።እርስት ሲባል ዛሬ እንደምናስበው ይቺን ጠባብ የአፈር ክምር አይደለም።

የኢትዮጵያዊ እርስት ሀገሩ ናት። የእርሱ ሁሉም ነገር በሀገር ውስጥ ስለመሆኑ ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ሀገር ከሌለች ምንም ነገር እንደማይኖረውም ቀድሞ ተረድቶታል።ያለምንም ቅድመ ሁኔታ አባቶቻችን ለሀገራቸው ሲሉ ደማቸውን አፍስሰው አጥንታቸውን የከሰከሱላት ለዚህም ነው።

እነርሱ ከየመንደሩ ወደ አንድ እየተመሙ አንድነታቸውን አጠንክረው ያኖሩልንን ሀገር እኛ በየመንደሩ ገብተን በየመንደራችን የመመሸጋችን ነገር ምን ይባላል?አልገባንም እንጂ ሳናውቀው የአንድ ሴራ ሰለባ ሆነናል።

ዛሬ ላይ ጎጠኝነትን ሹመን መንደርተኝነትን በእኛ ላይ ለማንገስ የምንጓተትበት ሰንሰለት እንደምናስበው ቀላል አይደለም። የተወረወረው ከእሩቅ ማዶ በመሆኑ ሁላችንም ወደን አንገት ካስገባን ቁልፉንም እስከመጨረሻው አናገኘውም። አንድነታችን እዚህ ወጥመድ ውስጥ ከገባ እጣ ፈንታችን እየተጎተትን ወደ ገደሉ መግባት ነው።

ከኢትዮጵያ ሰማይ በታች ዓለም ኢትዮጵያን ካወቀበት ጊዜ ጀምሮ የተቆፈረ ስውር ገደል ጥልቀቱ መጨረሻ ያለው አይመስልም። ምን አለንና ካልጠፋ ስንት ሀገር እኛን?ሊባል ይችላል።በእጅ ያለ መዳብ ሆኖብን ዓይናችን ተጋረደና ኢትዮጵያን የምናውቀው እኛ ሳንሆን ሌሎች ናቸው።

‹‹ገነትን አግኝተናልና ኑ! በውስጧ ያሉትንም አራዊት አስወግደን ግዛታችን እናድርጋት›› ሲሉ ጸሐፍቶቻቸው ጥንቱን የገነት መግቢያን የጥሪ ካርድ በትነውላቸዋል።እንግዲህ ገነቷ ኢትዮጵያ አራዊቱም እኛ ዜጎችዋ መሆናችን ነው።ይሄው ከዚያን ጊዜ አንስቶ እኛን አጥፍቶ በላያችን ላይ የመስፈር አባዜ ተጸናውቷቸዋል።

የእኛ አባቶች የጻፏቸውን መጽሐፍት በቅጡ እንኳን መያዝ እየተሳነን እያደኑ የሚተረጉሟቸው እነርሱ ናቸው።ምክንያቱም ከመጽሐፍቱ በስተጀርባ ተቀርጻ ያለችውን ኢትዮጵያ ብዙዎች ይፈልጓታል።

ታዲያ ሀገራችንን ችላ ብለን በዘር፣በሃይማኖት፣ በብሔርና በጎሳ መርዞች እርስ በርስ የምንናደፈው የእውነትም ፈልገነው ነው? አይመስለኝም…ነገር ግን አለመፈለጋችን ብቻ ዋጋ የለውም። ምክንያቱም ከጀርባችን ቆሞ በለው በለው የሚለንን ስውር ኃይል ማየት ተስኖናል።

ፈተናውንም እየወደቅን ነው። ሁሉንም ነገር በእነርሱ እያሳበብን መቀጠልም አለብን ተብሎም መታመን የለበትም። ተጠያቂው እኛ የሆንባቸው በርካታ አጋጣሚዎችና ክስተቶችም መኖራቸው አይካድም።

እነርሱ የሚያደርጉት ለራሳቸው ጥቅም የሚገባቸውን ነው ። እኛስ? ተጠያቂ መሆን ያለብን እኛው እራሳችን ነን። ዛሬም ድረስ ራሳችንን ለመለወጥ የተሳነን ለጥፋቶቻችን መፍትሔ ሳይሆን ሰበብ አስባብ በመፈለግ ስለምንጠመድ ነው።

 ነገር ግን የጥፋቶቻችንን መርዝ አቀባይ ለይቶ ማወቁ ለመፍትሔው ይበጀናል። እነርሱን መለወጥ ስለማንችል ሰበዞቻችንን ተረድተን ራሳችንን እንለውጥ ከሚል እሳቤ ነው ይህን ሃሳብ ያነሳሁት።

እኛን እርስ በእርስ በመከፋፈል መንደርና ክልል የሚሏትን መደለያ አሻንጉሊት ሰጥተው ሀገር ያህሏን ወርቅ አልማዝ ሊነጥቁን ስለመሆኑ ጥርጥር አይግባን። ያልጠረጠረ ተመነጠረ አይደል ተረቱም የሚለን። ወገን እንቃ እንጂ በግድ አልሆን ቢላቸው ዛሬ ላይ አዛኝ ቅቤ አንጓች መስለው ጸጉራችንን እየዳበሱ እኛን እንቅልፍ አሲዘው ሊያልቡን ይሞክራሉ።

እርሱም ካልሆነ ስስ ብልታችንን በመርፌ ወግተው እርስ በርስ ማፋጀት ነው። ባህል፣ ሃይማኖት፣ ብሔርና ጎሳ ስስ ብልቶቻችን ስለመሆናቸው ከኛ በላይ ጠንቅቀው ያውቁታል። ከጉያችን ስር ሆነው ከቤተ ሙከራቸው ካስገቡን ዘመናት አልፈዋልና። ይሄው ከጥንት እስከዛሬ በትግል ላይ ናቸው። በግድ አልሆን ቢላቸው መልካም መስለው እያሻሹን በእንቅልፍ አስወስደው ይህችን የማትነጥፍ ሀገር ለማለብ በእጅጉ ቋምጠዋል።

እኛ መስማማት ተስኖን እርስ በእርስ መገፋፋታችን ለእነርሱ ሥራ ማቅለል ነው። ምኞት ዓይን የለውምና ለእነርሱ ምኞት እኛን እየማገዱን ስለመሆኑ አያጠራጥርም።የኢትዮጵያን አፈር ረግጦ በጊዮን ወንዝ ምንጭ ፊታቸውን መታጠብ ይፈልጋሉ፤ ለበረከት ሳይሆን ለስርቆት። አላማቸውም ኢትዮጵያን ማፍረስና የራሳቸውን መንግሥት መገንባት ነው።

አልገባችሁ አለና የአባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ አይነት ሆነብን። የውስጥ ጠላትን የሚወልደው የውጭው ጠላት ነው። ከእያንዳንዱ የውስጥ ጠላት በስተጀርባ እነዚህን ኃይሎች ታገኛለህ። ምክንያቱም ያላቸው ብቸኛ አማራጭ ይህ መንገድ ብቻ ስለሆነ ነው።

የነጻነት ግንባሮቻችንም በሰላማዊ መንገድ ዴሞክራሲን ለማስፈን ሲሳናቸው ነጻነትን ፍለጋ ወደ ጦር ግንባር ይወርዳሉ። ከሚያልፍ መንግሥት ጋር በያዙት የፖለቲካ ቁርሾ የማታልፈውን ሀገርና ሕዝብን ማደባየት የተለመደ ሆኗል። ያለ ደም ስርየት ስልጣን የለም የሚል ሕግጋት ያለ ይመስል በደም ካልተጥለቀለቅን በቀር ስልጣኑም ስልጣን ዙፋኑም ዙፋን አይመስለንም።

በስልጣኔ ከሁሉ ቀድማ ስንቱን ለዓለም ያሳየች ሀገር፣ ስንቶች ፈለግዋን ተከትለው መጥቀው በመሄድ በስንቱ ጥበብ ሲጠበቡ እኛ እዚህ አዕምሯችንን አጥበን በብሔር በጎሳ መዋቀጣችን ለጠላት የመስዋዕት ድልድይ ከመሆን በዘለለ አንዳችም አናተርፍበትም። እኛ መልካም ታሪክ መስራት ባንችል እንኳን ስለምን የአባቶቻችንን ያማረ ታሪክ እናፈርሳለን? እነርሱ የሰሩትን ጀብዱ ስንዘክር ኖረን ኖረን በአፋችን ላይ አጃጀነው መሰለኝ እርሷንም አውጥተን ለመትፋት ቃጣን።

ለሚያልፍ ብርድ ያለችህንም ደሳሳ ጎጆ አንዴ ማገሩን ሌላ ጊዜ ወራጁን እያነደድክ እሳት መሞቅ ከጀመርክ ከጊዜያዊ ምቾት ወደ ዘላለማዊ ስቃይ መግባትህ አይቀሬ ነው። ወገኔ ሆይ ንቃ!

ለችግራችን መፍትሔው አንድና አንድ ብቻ ነው። እሾህን በእሾህ ለማውጣት መታገላችን ማቆም አለብን። እያንዳንዳችን እራሳችንን ከዚህ ሰንሰለት እናላቅ። የዚህ አጀንዳ አስፈጻሚዎች በየጊዜው የውሸት ትርክታቸውን እየተረኩ ፍቅራችንን በጥላቻ ሀገራችንን በመንደር ሊለውጡ የሚሰናዱትን ጆሮ ዳባ ብለን ልናልፍ ይገባል።

በጆሮ አሰምተውን መጨረሻ ላይ ጆሮዎቻችንን የሚቆርጡት እነርሱ እራሳቸው ናቸው። “የእናት ሆድ ዥንጉርጉር” እንዲሉ በአብሮነትና በፍቅር መሃል ለምድ ለብሰው የሚኖሩ ጥቂቶች መኖራቸው ሊያስደንቀን አሊያም ሊያሸብረን አይገባም። ምክንያቱም ዛሬ ብቻ ሳይሆን ትናንት በደጉ ዘመንም ነበሩ። ወደፊትም ይኖራሉ።

እነዚህ ጥቂቶች ለሀገር በሽታ ሲሆኑ ብዙኃኑ መድኃኒት ሊሆን ይገባል። አሊያማ መሳ ለመሳ መሯሯጥ ከጀመርን በየጥሻው የቆፈሩት ጉድጓድ ለእነርሱ ሳይሆን ለኛው ይሆናል። “እሾህን በእሾህ እያልን ”ለበቀል ከተሰናዳን፣ ፍቅር ሳይሆን ስሜታዊነት ካሸነፈን፣ ያው ለእነርሱ የመስዋዕት በግ ሆንን ማለት አይደል… ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በኛ አልተጀመረምና በኛም የሚያከትም መስሎ እንዳይሰማን፤ ይልቅስ በቀጣዩ ትውልድ ትዝብትን ከማትረፍ ሁሉም እራሱን ያድን።

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ነሃሴ 17/2015

Recommended For You