መንግሥት የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ፤ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ እድገትን የማፋጠን ከፍተኛ ሃላፊነት አለበት። ሄን ኃላፊነት ለመወጣት ደግሞ የራሱ ገቢ ምንጭ ያስፈልገዋል። ለአንድ ሀገር አስተማማኝ የገቢ ምንጮች ውስጥ ዋነኛው ደግሞ ግብር ነው።
በአግባቡ ግብር መሰብሰብ የቻለ ሀገር የተፋጠነ ልማት ማከናወን ይችላል፤ የተረጋጋች ሀገርንም ይፈጥራል። አስተማማኝ ሰላምና ጸጥታንም ያረጋግጣል። የተረጋጋና ቀጣይነት ያለውን ብልጽግናንም ያመጣል።
ግብር የዜጎች ሁሉ መብትም ግዴታም ነው። በአንድ ሀገር የተረጋጋ መንግሥታዊ ሥርዓት እንዲኖር፣ ዜጎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተግባሮቻቸውን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማከናወን እንዲችሉና በግለሰብ ደረጃ ሊሟሉ የማይችሉና የጋራ መገልገያ የሆኑ እንደ መንገድ፤ ጸጥታና ደህንነት፤ ትምህርትና ጤና የመሳሰሉ አገልግሎቶችን ማስፋፋት የሚቻለው አስተማማኝ ግብር ሲኖር ነው።
በአጠቃላይ ግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ያሉት እና የመንግሥታት ሀገር የመምራት አቅም እና ብቃት የሚመዘንበት ብቻ ሳይሆን የአንድ ሀገር የኢኮኖሚ ግስጋሴ የሚለካበትም ቁልፍ ተግባር ነው። በመሆኑም፣ ያለ ግብር መንግሥት ሊንቀሳቀስ፣ ሀገርም ልትለማ አትችልም።
ስለዚህ ግብር መክፈል ለሀገር ዕድገትና ለዜጎች ሁለንተናዊ መብቶች መረጋገጥ ካለው ፋይዳ አንጻር አስፈላጊ ከመሆኑም ባሻገር በአንዲት ሉዓላዊ ሀገር ውስጥ ግብር መክፈል ግዴታም ጭምር ነው። ይህንንም ተግባራዊ አለማድረግ ደግሞ የወንጀልና አስተዳደራዊ ቅጣቶችንም ያስከትላል።
በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ስለ ግብር አስፈላጊነትና ግዴታ ከተደነገገው በተጨማሪ በፌዴራል ታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 አንቀጽ 116 እና በተመሳሳይ ድንጋጌዎች ግብርን አለመክፈል፤ ማጭበርበር፣ ግብር መሰወር፣ ቫት ማጭበርበር እና በጠቅላላው ከታክስ ጋር ተያይዘው የሚፈጸሙ ወንጀሎች በእስር እና እንደየወንጀሉ ክብደት በብርም የሚያስቀጡ ናቸው።
ግብር ማጭበርበርና መሰወር ሕጋዊ ተጠያቂነትን የሚያስከትል ቢሆንም በሀገራችን ከግብር ጋር ተያይዞ በርካታ ወንጀሎች ይፈጸማሉ።
ለአብነትም የሽያጭ መጠንን ዝቅ በማድረግ የሚፈጸም ግብር መሰወር፤ ግዢን ዝቅ በማድረግ የሽያጭ መጠን እንዲቀንስ እየተደረገ የሚፈጸም የግብር ስወራ፤ የተጨማሪ እሴት ታክስ የተለያዩ የማስከፈያ ምጣኔዎች ያለአግባብ በማቀያየር የሚፈጸም የግብር ስወራ፤ የተሰበሰበን ታክስ (VAT) ለመንግሥት አለመክፈል፤ ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ዕቃዎች በሕገወጥ መንገድ በማስገባት ሊሰበሰብ የሚገባ የተጨማሪ እሴት ታክስ ማስቀረት፤ ሐሰተኛ የታክስ ተመላሽ መጠየቅ፤ በሀሰተኛ ደረሰኝ ገቢ መሰብሰብ እና የመሳሰሉት የግብር ሥራዎችና ማጭበርበሮች ይከናወናሉ።
ይህንኑ መሠረት በማድረግም ሰሞኑን የገቢዎች ሚኒስቴር ሀሰተኛ ደረሰኝ ሲጠቀሙ በተገኙ 12 ድርጅቶች ላይ ሕጋዊ ርምጃ ወስዷል። ሚኒስቴሩ ይፋ እንዳደረገውም በ2015 በጀት ዓመት የታክስ ማጭበርበር ምርመራ ከተደረገባቸው 528 ድርጅቶች ውስጥ 322 የሚሆኑት ሀሰተኛ ደረሰኝ ተገኝቶባቸዋል። እነዚህ ድርጅቶችም 12 ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ብር እንዲከፍሉም ተደርጓል።
በተጨማሪ ሁለት ማተሚያ ቤቶችና 10 ድርጅቶች ሀሰተኛ ደረሰኝ እያተሙ ሲያሰራጩ እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል። ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ 14 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል :: ከወንጀሉ ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ 864 ግለሰቦችም በምርመራ ላይ ይገኛሉ።
የገቢዎች ሚኒስቴር ያከናወነው ሕግ የማስከበር ተግባር የሚበረታታና ሀገርን ከበርካታ ቀውሶች የሚታደግ ነው። በተለይም ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ነባራዊ ሁኔታ ለዘርፈ ብዙ የልማት ጥያቄዎች በርካታ መዋዕለ ንዋይ የሚያስፈልጋት ከመሆኑ አንጻር በሕገ ወጦች የሚሰወረውን የሕዝብ ሀብት መታደግ ማለት ሀገርን የመታደግ ያህል ትርጉም የሚሰጠው ነው።
ስለዚህም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የጀመራቸው ሕገ ወጦችን አድኖ የመያዝና ብሎም የሕግ ተጠያቂነት እንዲሰፍን እያከናወነ ያለው ተግባር ልማትን ማፋጠን፤ ሰላምን ማረጋገጥና ብሎም የሀገርን ህልውና ማጽናት ነውና ርምጃው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።
አዲስ ዘመን ነሃሴ 17/2015