ድል ለኢትዮጵያውያን ጀግኖች አትሌቶች!

 ከዛሬ ጀምሮ በቀጣይ አስር ቀናት አውሮፓዊቷ ሃንጋሪ የዓለም ሕዝብ ትኩረት ሆና ትከርማለች። ምክንያቱ ደግሞ እጅግ ተወዳጅ ከሆኑ ስፖርቶች መካከል አንዱ የሆነውን የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮናን በመዲናዋ ቡዳፔስት አዘጋጅታለች። በቻምፒዮናው ከሚካፈሉ ሃገራት መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያም ለጀግኖች አትሌቶቸ የአደራ ሰንደቋ በአደራ አስረክባ በዓለም ህዝብ ፊት ሲያውለበልቡት ለመመልከት በጉጉት ትጠብቃለች።

አትሌቲክስ የኢትዮጵያ ውበት መገለጫ ነው። ለዘመናትም መልካም ገጽታዋን ለዓለም ሕዝብ አጉልቶ ያሳየ ራሱን የቻለ ትልቅ ዲፕሎማሲ ስለመሆኑ መናገር ለቀባሪ የማርዳት ያህል ነው። ዓለም በድህነትና ኋላቀርነት ስማቸውን ከሚያነሳ ሀገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ብትሆንም በአትሌቲክስ ስፖርት ሁሌም በክብር መነሳቷ እውነት ነው። አትሌቶቿ በሚካፈሉባቸው የውድድር መድረኮች ሁሉ የአሸናፊነት ቅድመ ግምቱን የማግኘታቸው እንዲሁም ተፈሪ የመሆናቸው ምክንያትም ያንን የጎደፈ ገፅታ የመቀየር ጉልበት ሰጥቶታል።

በስፖርቱ ከሚካሄዱ ውድድሮች ሁሉ ትልቁ በሆነው በዚህ መድረክም በየሁለት ዓመቱ ኢትዮጵያና ባንዲራዋ በጀግኖች አትሌቶቿ ገድል የክብር አክሊል ሲደፉ ኖረዋል። ከብቸኛው የማራቶን ጀግና አትሌት ከበደ ባልቻ የብር ሜዳሊያ አንስቶ እስካለፈው ዓመቱ የላቀ ድል፤ የዓለም ህዝብ ቆሞ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ጀግንነት አጨብጭቧል። ይህ የአትሌቲክስ ቤተሰቡ ልማድ እንዳይቀር፣ ኢትዮጵያም ከምትጠብቀው ድል እንዳትጎድል ባህር አቋርጠው ሃገራቸውን ሲሉ በባዕድ ሃገር የተሰለፉት የአትሌቲክስ ወታደሮቿ አደራ አለባቸው።

አምና በኦሪጎን ከተመዘገቡት 44 ቻምፒዮኖች መካከል 38 የሚሆኑት ዳግም በ19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ተካፋይ ሆነዋል። ከእነዚህ መካከል ለኢትዮጵያ አራቱን የወርቅ ሜዳሊያ ያስቆጠሩት ቻምፒዮኖችም ዘንድሮም ሃገራቸውን ሊወክሉ ተዘጋጅተዋል። በመሆኑም ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳንሆን መላው የዓለም አትሌቲክስ ወዳድ ህዝብ ከእነሱ ውጤት ይጠብቃል። ለዚህ ደግሞ 120 ሚሊየን ህዝብን ወክለው በቡዳፔስት የተገኙት አትሌቶች እንደቀደሙት ጀግና አትሌቶች ሃገራቸውን ያስቀደሙ፣ ቆራጥ፣ ጽኑ እና ጠንካራ ሊሆኑ ይገባል።

የዓለም አትሌቲክስ ከሰሞኑ በድረገጹ ያስነበበው ተከታዮቹ አስተያየት እንዲሰጡበት የሚጋብዝ አጭር ጽሁፍ ‹‹በእርግጥም ኢትዮጵያ ካለፈው ዓመት 10 ሜዳሊያዎች በላይ ዘንድሮ ታገኝ ይሆን?›› የሚል ነበር። ይህ አንድም ዓለም ስለ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ያለውን አስተያየት ለመመልከት የሚያስችል ነው። በአንጻሩ ያለፈው ዓመት ውጤት ዘንድሮ ስለመደገሙ ጥርጣሬ የሚያንጸባርቅም ይመስላል።

አምና አሜሪካ ባሰናዳችው ቻምፒዮና ኦሪጎን ላይ ከዓለም ሁለተኛውን ደረጃ በመያዝ በድል የተመለሰው ቡድን ያገኘው የጥረቱን ውጤት እንጂ በእድል ወይም ባጋጣሚ አለመሆኑን ይህ ቻምፒዮና ማሳያ መሆን ይችላል። አትሌቶቻችን ያላቸውን ብቃት ተጠቅመው፣ በራሳቸው የአሯሯጥ ዘዴ፣ በሚታወቁበት ብልሃት ውጤታማ መሆናቸው የስራቸው ፍሬ መሆኑን ለማረጋገጥ እንዳለፈው ጊዜ መትጋትና ቅድሚያውን ለሃገራቸው መስጠት ይጠበቅባቸዋል።

ለዚህ ደግሞ ተደራራቢ ውድድሮች፣ ጉዳት፣ ህመም፣ ሃዘን፣ አስቸጋሪ የውድድር ስፍራና የአየር ሁኔታ፣ ፖለቲካዊ ተቃርኖ፣ … ሳይበግራቸው ሀገራቸውን ለማስጠራት ሲሉ ብርቱ ትግል ያደረጉ አንጋፋ አትሌቶችን ማበረታታት ያስፈልጋል። በእርግጥም ጽናታቸው የጥንካሬ ምንጭ ይሆናል። በፍጹም ትህትና፣ የሀገር ፍቅር ስሜት እንዲሁም የእርስ በእርስ መከባበር ሀገራቸውን ለረጅም ጊዜ የወከሉ እንደነ ደራርቱ ቱሉ እና ገዛኸኝ አበራ ባሉ አትሌቶች መመራትም ብርታት ሊሆን ይችላል።

ዓለም እስከዛሬ ካየቻቸው የረጅም ርቀት አትሌቶች መካከል ጀግናው አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ቀዳሚው ነው። ይህ አትሌት ከ800 ሜትር እስከ ማራቶን ባሉት ርቀቶች 61 የሀገር ውስጥ እንዲሁም 27 የዓለም ክብረወሰኖችን መሰባበር ችሏል። በዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና መድረክም 4 የወርቅ፣ 2 የብር እና 1 የነሐስ በጥቅሉ 7 ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብ የድል ተምሳሌት ሊሆን ችሏል።

ኃይሌ ዛሬ ለደረሰበት ክብርና ስኬት ምክንያት የሆነው ታታሪነቱና ሀገሩን የማስጠራት ዓላማን በመሰነቁ ነው። ለዚህም አሸንፎ ሜዳሊያ ካጠለቀ በኋላ የሀገሩ ብሄራዊ መዝሙር ሲሰማ የሚተናነቀው እንባ ማሳያ ነው። በዓለም ላሉ አትሌቶች ሁሉ አርዓያ የሆነው ታላቁ አትሌት፤ ዛሬ ለተጀመረው ውድድር ዝግጅት እየተደረገ ሳለ በልምምድ ሜዳ ተገኝቶ የሰጠውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ጥቅሙ ከፍተኛ ነው።

ይህንን በመሰለ ታላቅ የውድድር መድረክ አገርን ከራስን አስቀድሞ የትኛውንም ዋጋ ከፍሎ ውጤት እንዲመዘገብ ማድረግ ተገቢ ነው። ለዚህም ማሳያ የሚሆኑ በርካታ ምርጥ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አሉ። በዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና መድረክ በጀግንነት አክብሮትን ካገኙ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ አንዱ ነው። በ5ሺ እና 10ሺ ሜትር ውድድሮች የደመቀ ታሪክ ያለው ይህ አትሌት እአአ ከ2003 እስከ 2009 በተካሄዱ ቻምፒዮናዎች 5 የወርቅ እና 1 የነሃስ በጥቅሉ 6 ሜዳሊያዎችን ለሀገሩ ማስቆጠር ችሏል።

በዚህም በመላው ዓለም በርካታ ሜዳሊያዎችን ከሰበሰቡ አትሌቶች መካከል ስድስተኛ ደረጃ ላይ ይቀመጣል። ትውልድ ከሚያከብራቸው አትሌቶች መካከል አንዱ የሆነው ቀነኒሳ እአአ በ2005 ሄልሲንኪ ላይ ቻምፒዮን የሆነው ከደረሰበት ሃዘን በቅጡ ሳያገግም ‹‹ሀገሬን›› ብሎ በተሳተፈበት ውድድር መሆኑ ለአሁኖቹ ጀግኖች ትልቅ ትምህርት ነው።

በቻምፒዮናው 5 የወርቅ እና 1 የብር በድምሩ 6 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ቀዳሚ የሆነችው አትሌት ጥሩነሽ ዲባባም እአአ በ2007 ኦሳካ ላይ ከሆድ ህመሟ ጋር ታግላ አሸናፊ መሆኗም በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ አልፎ ውጤታማ የመሆን ተሞክሮን ለዛሬዎቹ ጀግኖች አስተምራለች።

ኢትዮጵያ ‹‹አረንጓዴው ጎርፍ›› የሚል የክብር ስም የመሸለሟ ምክንያት አትሌቶቿ በቡድን በመሮጥ እንዲሁም አንዱ የሌላውን ድካም በመሸፈን ተከታትለው በድል አድራጊነት ውድድራቸውን በመፈጸማቸው እንደሆነ ይታወቃል። በመሆኑም የኢትዮጵያን ክብር በዚህ ታላቅ መድረክ ከፍ ለማድረግና ነገ ሀገርን ለሚረከቡ እልፍ ታዳጊዎች ምሳሌና አርዓያ ለመሆን መትጋት ያስፈልጋል።

ፈርቀዳጁ ጀግና አትሌት አበበ ቢቂላ፣ እነ ኃይሌ ገብረስላሴን፣ ቀነኒሳ በቀለን በመተካት ዛሬ ቡዳፔስት ላይ ኢትዮጵያን ከሚወክሏት አትሌቶች ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው። ይህ ደግሞ የትውልድ ሰንሰለት ብቻም ሳይሆን የታሪክ አደራም በመሆኑ የአንድነት መሳሪያ ሆኖ ወደ ፊትም ያገለግላል።

የአሁኑን ትውልድ ጀግኖች የሚመለከተው መጪው ትውልድ ሀገርን ስለመውደድ፣ ራስን ሳይሆን ባንዲራን ስለማስቀደም፣ አደራን ስለመወጣት፣ ኢትዮጵያን በበጎ ስለማስጠራት፣ እርስ በእርስ ስለመከባበር፣ ጠንክሮ ስለመስራት እንዲሁም ስለስኬታማነት የሚማረው በዚህ ነው። እነዚህ ጀግኖች መስታወት ሆነው የትውልዱን ነገ ዛሬ ላይ ለማንጸባረቅ በሚያደርጉት ጥረትም ሕዝብ የተለመደ ድጋፉን በመስጠት ሊያበረታታቸው ይገባል።

ድል ለኢትዮጵያውያን አትሌቶች !

 ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 13/2015

Recommended For You